ያንሠራሩት የድሬዳዋ ነጋዴዎች

የድሬዳዋ ነጋዴዎች ለማትረፍ ተሻምተው የሸመቱትን ጨርቃጨርቅ እና ጫማዎች እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶችን አንዳንዶች ሱቃቸው ውስጥ ሌሎች ደግሞ መጋዘን አከማችተዋል። ጊዜው የሰኔ መጨረሻ በመሆኑ ሐምሌ 19 ቁልቢ ገብርኤልን ለማንገስ ከኢትዮጵያ የተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ የታቦት አክባሪዎች፤ እግረ መንገዳቸውን ድሬዳዋ ጎራ ብለው መሸመታቸው እንደማይቀር ነጋዴዎቹ እርግጠኛ ሆነዋል።

በታቦት አንጋሾች እንደሚጎበኙ የገመቱት ነጋዴዎች በሰፊው ለማትረፍ ሱቃቸው እና መጋዘናቸው ሞልቶ እስኪትረፈረፍ በገፍ ለገበያ የሚያቀርቡትን አዘጋጅተዋል። ይሁንና ከሰማይ እንደሚወርድ በረዶ ያልተጠበቀ መዓት ወርዶ የድሬዳዋ ከተማን እና አጠቃላይ ነጋዴውን ተስፋ አጨለመ። ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ለድሬዳዋ ከተማ ከባድ የሃዘን ቀን ሆነ። ሊነጋጋ ሲል የተነሳው የእሳት አደጋ እየተንቀለቀለ የተጠቀጠቀውን ጨርቃጨርቅ እና ጫማዎች እየተንበለበለ መብላት ጀመረ። ለማጥፋት ያልሞከረ አልነበረም።

እሳቱ ላይ አሸዋ እየደፉ እሳቱ አልጠፋ ሲል፤ ገሚሱ ጭንቅላቱን ይዞ ሲጮህ፤ ገሚሱ እንባውን እያፈሰሰ ፈጣሪውን ይማጸን ነበር። በመጨረሻም ከተማዋን ይበላታል የሚል ስጋት እስከ መፍጠር የደረሰው እሳት፤ 458 ሱቆችን እና መጋዘኖችን አንድዶ በቁጥጥር ስር ዋለ። ይህን ያህል ሱቅ ሲቃጠል ያስከተለው ጉዳት ከባድ ቢሆንም፤ እሳቱ ቢቀጥል ደግሞ ጉዳቱ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል በመገመት የድሬዳዋ ነጋዴዎች ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ።

ቀን ቀንን እየተካ የነበረው አደጋ እየተረሳ አሁን እንደታሪክ ቢነሳም፤ ዛሬም ድረስ ሁኔታውን ከእንባ ጋር የሚያስታውሱ ብዙ ናቸው። እያስታወሱ የመከፋታቸው ምክንያት፤ በድሬዳዋ ከተማ በትልቅነት የሚታወቀው የአሸዋ ገበያ መጋዘን እና ሱቆች በእሳት አደጋ መጋየታቸው ብቻ ሳይሆን፤ ከተማዋ በእሳት ልትጠፋ ነው ብለው ሰግተው ስለነበረ ጭምር ነው።

ሱቃቸው ከተቃጠለባቸው መካከል አቶ መሃመድ አረጋ አንዱ ናቸው። አቶ መሃመድ ዳንሆዳግ የገበያ ማዕከል አክሲዮን ማህበር ሰብሳቢ ናቸው። ማህበሩ የተመሠረተው ሱቆቹ ከመቃጠላቸው በፊት ቢሆንም፤ ሱቆቹ ከተቃጠሉ በኋላ የተቃጠለባቸውን 458 ባለሱቅ ነጋዴዎችን ወክለው ከከተማው አስተዳደር ጋር አብረው በመሥራት ላይ መሆናቸውን አቶ መሃመድ ይናገራሉ፡፡

ነጋዴው ለመገናኘት እና ነጋዴው የሚያንሰራራበት ሁኔታ ለማመቻቸት የማህበሩ መኖር ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ያስረዳሉ። እንደአቶ መሃመድ ገለፃ፤ በአዳጋው የሠው ህይወት አልጠፋም። ይሁንና የደረሰው የንብረት ጉዳት ከነጋዴዎቹ አልፎ ከተማዋን እና አገሪቷን የጎዳ ነበር። ከ458 ሱቅ በተጨማሪ ሌሎች በአቅራቢያው የሚሠሩ ነጋዴ ግለሰቦችም በተቃጠለው ቦታ መጋዘን ውስጥ የሚሸጧቸውን ዕቃዎች በማስቀመጣቸው ንብረታቸው ወድሟል።

በጊዜው የጠፋው ንብረት ምዝገባ የተደረገ መሆኑን አስታውሰው፤ 7ሺህ ካሬ ላይ የነበረው ሃብት አስታውሶ ለመናገር ከባድ ነው። በጥናት ሳይረጋገጥ ይህን ያህል ነው ለማለት እንደሚቸገሩ ያስረዳሉ። ቃጠሎ እጅግ ከባድ ጉዳት በማስከተሉ ከመንግሥት በተጨማሪ ባለሃብቶች እና ብዙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም እርዳታ ለመስጠት ቢረባረቡም፤ በሌላ በኩል ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት የሰው ሕይወት ማጥፋቱ ተደራራቢ እርዳታ የሚፈልግ አካል በመፈጠሩ ምክንያት እርዳታ ተስተጓጎለ ይላሉ።

‹‹ የእኛ ንብረት ቢጠፋም የእነሱ ደግሞ ሕይወት ጠፋ። ስለዚህ እርዳታው ወደ እዛ ዞረ። የክልሉ መንግሥት ሊያሰባስብ የፈለገውን ያህል ማሰባሰብ አልተቻለም›› የሚሉት አቶ መሃመድ፤ ሆኖም የተወሰነ ገንዘብ ቢሰበሰብም ለእያንዳንዱ ለማከፋፈል መታሰቡን ያስረዳሉ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሱቁ እንደተቃጠለ ወዲያው ሱቅ የተቃጠለባቸው ነጋዴዎች ከተቃጠሉት ሱቆች አቅራቢያ መንገዱን በማጠር ዋናው ጉዳይ ተለዋጭ ቦታ መሠጠቱ ነው። ቦታ ከተሠጣቸው በኋላ በራሳቸው ሱቁን ሠርተው ከጨረሱ በኋላ ወደ ሥራ መግባታቸው ትልቅ እፎይታን ሠጥቷቸዋል።

የመንግሥት ድጋፍ ንግዳቸውን እንዲቀጥሉ እንደረዳቸው ይጠቁማሉ። ከንቲባው እና ምክትል ከንቲባው አጠቃላይ የከተማ አስተዳደሩ ተረባርቦ በመስራት በሁለት ወር ውስጥ መሬት በመስጠት ሱቃቸው የተቃጠለባቸው ነጋዴዎች ወደ ንግዳቸው እንዲመለሱ መደረጉ ከምንም በላይ ነጋዴው እንዲያንሠራራ አግዟል ሲሉ አቶ መሃመድ የከተማ አስተዳደሩ የሠራላቸውን ይናገራሉ።

የከተማ አስተዳደሩ ዜጎች በመሆናቸው መልሰው መቋቋም አለባቸው ብሎ ቦታዎች ማመቻቸቱ የሚያስመሰግነው መሆኑን አመልክተው፤ ‹‹ቦታው ባይገኝ እስከ አሁን ምን እንሆን ነበር?›› ሲሉ ይጠይቃሉ። አቶ መሃመድ ለሁለት ወር ነጋዴው ሥራ ፈቶ ምን ያህል ቤተሰብ እንደማቀቀ ሁሉም ያውቃል ሲሉ ተናግረው፤ ሁኔታው በዛ መልክ ቢቀጥል የሚሆነውን ማሰብ እንደሚያስፈራ ያብራራሉ።

እንደእሳቸው ገለፃ፤ ሱቆቹ ሲቃጠሉ አካባቢውን ትቶ የጠፋ ነበር። አንዳንዶች የሚሠሩበት ቦታ የተሠጣቸው በስልክ ተፈልገው ተጠርተው ነው። ምንም እንኳ በአንድ አጋጣሚ ሙሉ ለሙሉ ንብረታቸውን ቢያጡም፤ አሁን ላይ አንሠራርተው ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን ለመርዳት ደርሰዋል። ሁሉም ሰው በየመደብሩ ገብቷል፤ መልሶ ተቋቁሟል። ነጋዴው የተቃጠለበትን ያህል ንብረት ባያፈራም፤ ራሱን እና ቤተሰቡን ከማኖር አልፎ ለሀገሩ ግብር መክፈል የሚችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል።

ማህበሩ ቀደም ሲልም እንደነበር አስታውሰው፤ ካርታ ወስደው፤ ዲዛይን አሠርተው ግንባታ ፈቃድ ወስደው ሊገነቡ እንደነበር በመጥቀስ፤ የቀደመው ካርታ እና ዲዛይን አሥር ዓመት ያለፈው መሆኑ እንዲሁም የከተማው ፕላን በመቀየሩ እንደገና ከከተማዋ ፕላን ጋር የተናበበ ሌላ ዲዛይን አስወጥተው ሊሠሩ ሲዘጋጁ ቃጠሎ እንደቀደማቸው ይናገራሉ።

አሁን በተቃጠለው ቦታ ላይ ከሃምሌ ጀምሮ የህንፃ ግንባታ ይጀመራል ያሉት አቶ መሃመድ፤ ቃጠሎ የተከሰተበትን ቀን ምክንያት በማድረግ በአንድ አመቱ ሰኔ 25 የመሠረተ ድንጋይ ሊጣል መሆኑን አመላክተዋል።

‹‹የከተማ አስተዳደሩ በአግባቡ እየረዳን ነው። ሰዎች ተመድበውልን በእያንዳንዱ ነገር ላይ ድጋፍ እየተደረገልን ይገኛል። ከተቋራጮች ጋር ከማገናኘት በተጨማሪ የገንዘብ ችግር እንዳያጋጥመን በዝቅተኛ ወለድ ከሚያበድሩ ባንኮች ጋርም አገናኝተውናል፡፡›› የሚሉት አቶ መሃመድ፤ ከተቋራጮችም ሆነ ከባንኮች ጋር በንግግር ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል። እየተቀራረቡ እያነጋገሩት ያለው ተቋራጭ በስምንት ወር ውስጥ አጠናቅቆ አስረክባለሁ እያላቸው መሆኑን አስታውቀው፤ ከግሎባል ባንክ ጋር ተቀናጅተው ለመሥራት እየተወያዩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

እሳቸው እንደሚያስረዱት፤ የሚገነቡት ሁለት ሕንፃዎች ናቸው። ወጪው 450 ሚሊዮን ብር ይሆናል የሚል ግምት ተይዟል። ይህንን ብር ማህበሩ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የተቋቋመ በመሆኑ ነጋዴዎቹ እያዋጡ የነበረውን ገንዘብ እና የተለያዩ የብድር አማራጮችን በመጠቀም ግንባታው ይከናወናል።

ሐምሌ ቁልቢ ገብርኤል ካለፈ በኋላ ሥራው ይጀመራል የሚል ዕቅድ መያዙን አስታውሰው፤ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ እናቶች እና ሌሎችም ደካሞች በመኖራቸው የመንግሥት ድጋፍ ሊቀጥል ይገባል ይላሉ።

ሌላኛው አቶ ሁሴን ከድር ይባላሉ። ለ30 ዓመታት የሠሩበት ሱቅ የተቃጠለባቸው እና የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ አባል የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ናቸው። አቶ ሁሴን ከድር እንደሚናገሩት፤ ‹‹ቃጠሎ እጅግ የሚያስከፋ እና አንገት የሚያስደፋ ነበር። በትንሹ የ1ሺህ 333 ሰዎች ንብረት የወደመ ሲሆን፤ ከ458 ሱቅ በተጨማሪ ተለጥፈው የሚሠሩ ሳህን ተራ እና መሃል አሸዋ ያሉ በመጋዘን ዕቃ ያስቀምጡ ነጋዴዎችም ከፍተኛ ጉዳት ገጥሟቸው ነበር። ይሁንና ከዛ ሁሉ ውድመት በኋላ መንግሥት እና ሕብረተሰቡ እያበረታታን እየኖርን ነው።›› ይላሉ፡፡

‹‹ሁለት አካላት ተጎድተዋል። ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ መሬቱም ተጎድቷል። መሬቱ ያለ ልማት ተቀምጧል።›› ያሉት አቶ ሁሴን፤ ቦታውን ለኮሪደር ልማት በሚያመች መልኩ ተስተካክሎ በመሠጠቱ ለማልማት መዘጋጀታቸውን ይናገራሉ። በቀጣይ በደንብ ለምቶ ነጋዴው እንዲጠቀም እና መንግስትም ተገቢውን ግብር እንዲያገኝ ለማልማት ቆርጠው መነሳታቸውን ተናግረዋል።

አቶ መሃመድ እንደተናገሩት ሁሉ፤ አቶ ሁሴን ቀድሞም ቢሆን ህጋዊ ማህበር በመመስረት ካርታ አውጥተው ሕንፃ ለመገንባት እየተዘጋጁ እንደነበር አስታውስ፤ ይሁንና እሳቱ እንደቀደማቸው ያብራራሉ። ካለፈ በኋላ ደግሞ መንግስት ጊዜያዊ ምትክ ቦታ የሠጣቸው መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ፎቅ ለመስራት ሁኔታዎችን እያመቻቹ መሆኑን ይናገራሉ። በእርዳታ በኩል መንግስት የተቻለውን እያደረገ መሆኑን አመልክተው፤ ከዛ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን መንግሥት ከጎናቸው ባይቆም ነጋዴው ራሱን የሚችልበት ሁኔታ እጅግ ከባድ ይሆን እንደነበር ተናግረዋል።

የተቃጠለበት ነጋዴ ከአቅሙ በላይ ሆኖበት ለተወሰነ ጊዜ ወደ ልመና ልቡ ከጅሏል። ጊዜው ክፉ በመሆኑ ያቺን ሰዓት ከአስር ብር ጀምሮ የረዳ ወገን የሚመሰገን ነው ሲሉ የተናገሩት አቶ ሁሴን፤ ሕዝቡ የሚያውቀው ሥራ ነው። ልመና አይወድም፤ አሁን ለልጆቹ የሚያበላውን አላጣም ብለዋል።

‹‹ይሁንና የምንፈልገው ሠርተን ሰው ሆነን ለሠላምም ሆነ ለማንኛውም ነገር ከመንግሥት ጎን መቆም ነው። ነገር ግን ህንፃውን ለመገንባት ካሳለፍነው ጉዳት ባለማገገማችን አሁንም መንግሥት እንዳይረሳን እንሻለን፤ እገዛ እንፈልጋለን። ›› ብለዋል።

በማህበሩ ነጋዴዎች ከአስር ዓመት በላይ የቆጠቡ መሆኑን አስታውሰው፤ በቀጣይም ቁጠባው ይቀጥላል። ሆኖም ብድር የሚያስፈልግ በመሆኑ ከባንክ ጋር በመገናኘት ቦታውን በነጋዴው ብቻ ሳይሆን በብድር ለምቶ በረዥም ጊዜ የሚከፈልበት ሁኔታ እንዲመቻች እና በአጭር ጊዜ ወደ ሕንፃው መግባት እንዲቻል እየሠሩ መሆኑን እና ለዚህም የመንግሥት ዕገዛ እንዳይለይ ጠይቀዋል። ጨምረውም ሕብረተሰብ የተጎዳ በመሆኑ እርዳታ እና ድጋፍ የሚያደርግ በጎ አድራጊ ከተገኘ የድሬዳዋ ነጋዴ ራሱን ችሎ ለሌላው ለመትረፍ ጊዜ እንደማይፈጅበት አስገንዝበዋል።

በምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You