ፍሬህይወት አወቀ
ወጣት ማለት አዳዲስ ነገሮችን ለመተግበር የሚናፍቅ፤ ብርታትና ጥንካሬ የተሞላ፤ ትኩስ ሀይል ብቻ ሳይሆን የማይቻል የሚመስለውን ሁሉ የሚችል ጉልበታም ነው።በከተሞች ሲርመሰመሱ የሚታዩትና ባህር ተሻግረው የሚጓዙት ሥራ ፈላጊ ወጣቶችም ኑሯቸውን ከማሻሻል ባለፈ ሀገርን መለወጥ የሚችል አቅም የሰነቁ ናቸው።ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የወጣት ሥራ አጥ ቁጥር በየዓመቱ እያሻቀበ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ሳይቻል ቀርቷል።
የመንግስት ከባድ ፈተና የሆነውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍ በተለያየ ጊዜ የተወሰዱ እርምጃዎች እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ።ይሁንና ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል ይበልጥ ሥራ ፈላጊው ቁጥር በእጥፍ እያደገ በመምጣቱ ሥራ አጥነት በሀገሪቷ ስር መስደድ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።በመሆኑም ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዕድሜያቸው ለስራ የደረሱና ስራ የሚፈልጉ ወጣቶች ወደ ስራ ገበያው ይመጣሉ፤ ሀገሪቱ የምትፈጥረው የስራ ዕድል ደግሞ አንድ ሚሊዮን ያክል ብቻ መሆኑን የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መረጃ ይጠቁማል።
እኛም ይሄን መነሻ በማድረግ አሁን በሀገሪቱ ለመጣው ለውጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ወጣቶች ከመሆናቸው አንጻር ሰፊ ቁጥር ላለው ሥራ አጥ ወጣት ባለፉት ሶስት የለውጥ አመታት የሥራ አጥ ቁጥሩን ለመቀነስ ምን ጥረት ተደረገ፤ ስኬቶቹ ምንድን ናቸው ቀሪ ሥራዎችስ፤ በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምን ታስቧል፣ በሚሉ እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ የፌዴራል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አማካሪ ወይዘሮ ሙሉእመቤት አሸብር ያደረሱንን መረጃ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
በርካታ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ሥራ አጥነት በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣና በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ትልቅ ጫና እያደረሰ ያለ ፈታኝ የሀገሪቷ መሰናክል ነው።ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሱ ወጣቶች በየጊዜው ወደ ገበያው የሚቀላቀሉ ቢሆንም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ደግሞ ምላሽ የመስጠት አቅሙ እጅግ ያነሰ በመሆኑ ችግሩ ሥር እየሰደደ የመጣ ሆኗል።
ችግሩ ከሀገሪቷ ኢኮኖሚ አቅም በላይ ከመሆኑ ባሻገር ሥራ መፍጠር ያለበት መንግስት ነው የሚል አስተሳሰብ በማህበረሰቡ ውስጥ መኖሩና የግሉ ዘርፉ ሚናውን በአግባቡ ባለመወጣቱ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል።ነገር ግን በተጨባጭ ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር የሚችለው ከመንግስት ይልቅ የግሉ ዘርፍ ነው።በመሆኑም የግሉ ዘርፍ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ባለመቻሉ የስራ አጥ ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል።በተለይም ወጣቶችና ሴቶች ሥራ ሳይኖራቸው እንዲኖሩና በኢኮኖሚው ውስጥ የራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።
ለጥፋትም ሆነ ለልማት ቅርብ የሆነው ወጣት በራሱ ሥራ ፈጥሮ ጤናማ መንገድ እንዲከተል የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን በተመለከተም፤ ወጣትም ይሁኑ ሴቶች እንዲሁም በየትኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሰው ሁሉ መሰረታዊ ፍላጎቶች አሉት።ሁሉም ሰው በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ሕይወቱ የሚያስፈልጉት መሰረታዊ ፍላጎቶች ካልተሟሉለት ሁልጊዜም ለሀገር ችግር መሆኑ አይቀርም።በተለይም ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ገቢ ማግኘት ካልቻሉ ትልቅ የሀገር ሸክም ይሆናሉ።ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ላይ ጫና ያሳድራል።
የሥራ አጥ ቁጥር መበራከት በዋናነት የመንግስት ጥያቄ እንደመሆኑ መንግስት በርካታ የረጅም እና የአጭር ጊዜ ዕቅዶችን አቅዶ እየሰራ ሲሆን፤ ባለፉት 20 ዓመታትም በጥቃቅንና አነስተኛ ስትራቴጂ ተነድፎ በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን በማደራጀት የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎች ሲሰጡና የተለያዩ ሥራ ዕድሎችን በመፍጠር በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። ነገር ግን በሚፈለገው መጠን ችግሮችን እየቀረፈ አልሄደም።ምክንያቱም መንግስት የፈጠረው ዘዴ እየመጣ ካለው ሥራ ፈላጊ ወጣት ጋር ሊጣጣም ያልቻለ በመሆኑ ነው።
ይሁንና ይህ ሥር የሰደደውን የሥራ አጥነት ችግር ለማቃለል ካለፉት ሶስት የለውጥ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ አዳዲስ አማራጮችን በመጠቀም እየተሰራ ነው።በተለይም ችግሩ በመንግስት አቅም ብቻ መፈታት የሚችል ባለመሆኑ የግሉን ዘርፍ የማነቃቃትና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ለዘርፉ እንቅፋት የሆኑ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማሻሻል ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲቻል ኮሚሽኑ የግሉን ዘርፍ እያበረታታ የሚገኝ ሲሆን አጋር አካላትንም አሳታፊ በማድረግ ይሰራል።
ቀደም ሲል የሥራ ዕድል ፈጠራ እንደ ሀገር ፍኖተ ካርታ አልነበረውም።ይሄን በመገንዘብም በቀጣይ እንደ ሀገር ሊያሰራ የሚችል የአስር ዓመት ስትራቴጂክ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ ነው።በመሆኑም በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በሀገሪቱ 20 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ ነው።ይህ ዕቅድ ደግሞ የኮሚሽኑ ብቻ አይደለም። መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ከዕቅዳቸው ጋር እንዲዋሀድ በማድረግ እየሰሩ ይገኛሉ።
በዚህ ረገድ ባሳለፍነው በ2012 ዓ.ም ለሶስት ሚሊዮን ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዜጎች ሥራ መፍጠር ተችሏል።በተያዘው ዓመትም ለሶስት ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።የሥራ ዕድል አንድ ዘርፍ ላይ ተጀምሮ የሚያልቅ ስራ ባለመሆኑና ሁሉንም ዘርፎች የሚነካካ እንደመሆኑ በዘርፉ ያሉትን እንቅፋቶች ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ የትብብር መድረኮችን በማዘጋጀት እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም ከፌዴራል እስከ ወረዳ ባሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት እየተገናኙ በዘርፉ ያሉትን እንቅፋቶች መለየትና እንቅፋቶቹን ለመፍታት ከመንግስትና ከግሉ ዘርፍ ምን ይጠበቃል በሚል በየሁለት ወሩ የሥራ ዕድል ፈጠራው የሚገኝበት ደረጃ ይገመገማል።
ከዚህ በተጨማሪም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የሥራ ዕድል ፈጠራ ብሔራዊ ምክር ቤት በየ ሩብ ዓመቱ እየተገናኘ አፈጻጸሙን እየገመገመና ላጋጠሙ ችግሮችም መፍትሄ እየሰጠ የሚሄድ ሲሆን፤ ክልሎችን ጨምሮ በተዋረድ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ያሉ የስራ ዕድል ፈጠራውን የሚገመግሙ ምክር ቤቶች አሉ።እነዚህን ምክር ቤቶች በማጠናከር የዘርፉን ችግር ማቃለል የሚቻል ሲሆን፤ በተለይም የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ፋይናንስ የሚፈልግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በፋይናስ አቅርቦቱም የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየፈቱ ለመሄድ የሚያስችል ሁኔታ ይፈጥራል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከስራ እድል ፈጠራ ስራዎች አኳያ ሂደቱን ከለውጡ በፊትና ከለውጡ በኋላ በሚል መመልከት የሚቻል ቢሆንም፤ ትናንት የነበረው ወጣት ዛሬም ያለው ወጣት መሆኑንና ፍላጎቱም የቀጠለ ነው። ነገር ግን ከለውጡ በፊት በነበረው አንድ አይነት አቅጣጫን ይዞ መጓዝ አዋጭ አልሆነም።በተለይም የግሉ ዘርፍ ማነቆዎች ያልተፈቱለት የነበረ በመሆኑ ዘርፉ ውጤታማ መሆን አልቻለም።ለአብነትም በኢትዮጵያ የንግድ ልማት ሂደትን ለማፋጠን የሚያስችል አሰራር በአሁን ወቅት እየተሰራ ይገኛል።
በመሆኑም ባለፉት ሶስት የለውጥ ዓመታት የግል ባለሀብቱ ወደ ተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ገብቶ ትላልቅ ስራዎችን በመስራት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲችል ትኩረት ተሰጥቶት ተሰርቷል።በተያያዘም ወጣቶች በራሳቸው ሥራ ፈጣሪ በመሆን የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ሰርተው ቀጣሪ እንዲሆኑ የሚያስችልና የማበረታታት ሥራ እየተሰራ ይገኛል።ነገር ግን የሥራ ዕድልን በቋሚነት መፍጠርና ችግሩን ለዘለቄታው መፍታት የሚቻለው መንግስት የግል ዘርፉን አጠንክሮ መጠቀም ሲችል ነው።
ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት የነበረው ሁኔታ መንግስት እራሱ ሥራ ፈጣሪ እራሱ ቀጣሪ እየሆነ ማህበረሰቡ መንግስትን ብቻ እየጠበቀ የነበረበት ሂደት ነበር።ነገር ግን ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት እየተሰራ ያለው ሥራ ማህበረሰቡ ዓይኑ ከመንግስት ላይ ማንሳት የሚያስችለው ነው።በመሆኑም መንግስት በርካታ የሰው ሀይልን መያዝ የሚችለውን የግሉን ዘርፍ ለማጠናከርና ለመደገፍ እንቅፋቶችን የማንሳትና የፖሊሲ ጉዳዮችን የማስተካከል ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።በዚህም መሰረት የሚመጣውን ሥራ ፈላጊ ወጣት አቅም በፈቀደ መጠን ወደ ሥራ እንዲገባና የራሱን ገቢ በመፍጠር በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት እየተሰራ ነው።
በተለይም የግሉ ዘርፍ ሥርዓትና ሕጉን ተከትለው በቀላሉ ወደ ሥራ በመግባት ለራሳቸውም ተጠቅመው ማህበረሰቡንም ማገልገል እንዲችሉ የማድረግ ሥራዎች ተጀማምረዋል።በተጨማሪም የማነቃቂያ ፕሮግራሞችን በመዘርጋት ነገሮች ቀላል እንዲሆኑና ለግል ዘርፉ በቂ የሆነ ድጋፍ በመስጠት የተሻለ ሥራ ለመስራት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
ኮሚሽኑ ከገጠር ወደ ከተማ ፈልሰው የሚመጡ፣ ተመርቀው ሥራ አጥ የሆኑ፣ አካል ጉዳት ያለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ ወጣቶች፣ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቷ እየተለመደ ለመጣው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በስትራቴጂው አካትቶ ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን፤ የሥራ ገበያውም እነዚህን ሁሉ ያካተተ እንዲሆን እየተሰራ ነው።
ምክንያቱም ዜጎች የሥራ ዕድል ካልተፈጠረላቸው ለሀገር አደጋና ሥጋት ይሆናሉ።ወጣቱ ሥራ ከተፈጠረለት ግን ከጥፋት ይልቅ አጀንዳው ልማት ይሆናል።ነገን ተስፋ በማድረግ ቤተሰብ ስለመመስረት፣ የትምህርት ደረጃውን ስለማሻሻል፣ ቤተሰቡን ስለመርዳትና ለሀገር ልማት ያስባል።ሥራ ከሌለው ግን የጥፋት ሰለባ በመሆን ለሀገር ሥጋት ሆኖ ከቤተሰቡ ጀምሮ ሀገርን ይበጠብጣል።ስለዚህ የሥራ ዕድል የመፍጠር ጉዳይ የመንግስት ጉዳይ ብቻ አይደለም።ፖለቲካም አይደለም፤ ይልቁንም የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ነው።
በተለይም የሥራ ባህላችን እንደ ሀገር የተሳሳተ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች አሉ።በህብረተሰቡ ውስጥም ሥራ ማለት ተቀጥሮ ቢሮ ውስጥ መስራት ብቻ እንደሆነ ይታሰባል።ትምህርት ማለት በከፍተኛ ተቋም ገብቶ መማር ብቻ እንደሆነም ይታሰባል።ነገር ግን አጫጭር ስልጠናዎችን በመውሰድ በተለያዩ የሥራ መስኮች መሳተፍ የሚቻል በመሆኑ ከዚህ በፊት የተጓዝንባቸውን መንገዶች በመቀየር ፈጣንና ተለዋዋጭ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመን በሀገራችን ተንሰራፍቶ ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ማቃለል ይቻላል።
በዚህ መልኩ ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ደግሞ በዋናነት አመለካከትን መቀየርና ማስተካከል አስፈላጊ እንደመሆኑ በተለይም ሚዲያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በሰፊው መስራት ይኖርባቸዋል። በቀጣይ አስር ዓመት ሀገራዊ በሆነው መሪ ዕቅድ ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋትና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ምሰሶዎች ተቀምጠዋል።ከእነዚህም መካከል የትኞቹ ዘርፎች ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር ይችላሉ፤ የሥራ ገበያው ምን ይፈልጋል፤ ሀገሪቷ ያላት እምቅ ሀብት ምንድን ነው ችግሮቹስ የሚሉ ጥያቄዎችን በዝርዝር የለየ ሰፊ ዕቅድ እንደመሆኑ ችግሩን መቅረፍ ያስችላል።
ለዚህም የመንግስት ቁርጠኝነት ወሳኝ በመሆኑ የሥራ አጥነትን አጀንዳ አጥብቆ በያዘው ልክ ውጤታማ መሆን ይቻላል።የኢትዮጵያ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንም በሁሉም የሥራ ዘርፎች የሥራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳን የማስተዳደር፣ የማቀናጀት እና የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው እንደመሆኑ፤ በመላው አገሪቱ የሚፈጠሩ ስራዎች ዘለቄታ ያላቸው እንዲሆኑ እ.ኤ.አ በ2020 ዓ.ም ሶስት ሚሊዮን፣ በ2025 14 ሚሊዮን፣ በ2030 ደግሞ 20 ሚሊዮን የስራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ የማመቻቸትና ድጋፍ የማድረግ ሥራ እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013