እፀገነት አክሊሉ
የዛሬ 10 ዓመት የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ አገር ከዳር እስከ ዳር ነበር በደስታ የዘለለው፤ ምክንያቱ ደግሞ ለዘመናት አይደፈርም ተብሎ የኖረውን ይህንን ስራ ማስጀመር መቻል ከስኬትም በላይ ስኬት ስለነበር ነው። በወቅቱ ህዝቡ ደስታውን በከፍተኛ ሁኔታ ከመግለጽ ጎን ለጎን ለግድቡ ግንባታ አስፈላጊ የሆነውን የገንዘብ መዋጮ ቦንድ በመግዛትና በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ቆይቷል። ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ ይህንን ያህል ቀና ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበረው አመራር ግን ከስራው ጥፋቱ ከፍጥነቱ መጓተቱ በዝቶ እነሆ ዛሬ በአምስት ዓመቱ ይጠናቀቃል የተባለው ግድብ 10 ዓመቱን ደፍኗል።
ነገር ግን የዛሬ ሦስት ዓመት ወደሥልጣን የመጣው የለውጥ አመራሩ ሂደቱን በጥሞና በማየት ያስፈልጋል ያለውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ እንደገና ከዜሮ መጀመር በሚባል ሁኔታ ስራውን አስጀምሮ ዛሬ ላይ 79 በመቶ ለመድረስ ተችሏል ።
እኛም የህዳሴውን ግድብ የመሠረት ድንጋይ መቀመጥ 10ኛ ዓመትን አስመልክተን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ከዶክተር አረጋዊ በርሄ ጋር ቃለ ምልልስን አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸው ዋና ዋና ሥራዎች ምን ነበሩ? ምንስ ውጤት ተገኘ?
ዶክተር አረጋዊ፦ የግድቡ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበትን አሥረኛ ዓመት ለማክበር በዝግጅት ላይ ነን፤ ምንም እንኳን የግድቡ ግንባታ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ ሙስናና ምዝበራ አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ህብረተሰቡን በማስተባበር የተለያዩ የድጋፍና ንቅናቄ ስራዎችን በመስራት የሚጠበቅበትን ያህል ባይሆንም የተቻለውን ነገር ግን ሲያደርግ ቆይቷል። ከለውጡ በኋላም ቢሆን ጽህፈት ቤቱ የግድቡን ጠቃሚነት፣ አሻጋሪነት፣ በመገንዘብና በማስገንዘብ ሥራ ላይ ይገኛል። ጽህፈት ቤቱ እንዲሁም መንግሥት የግድቡን አስፈላጊነት ለህዝቡ የማስረዳት የማነቃቃት ሥራ በመስራታቸውም አሁን ላይ ስራው ከቆመበት እንዲቀጥል ሆኗል፤ ውጤቶችም እየታዩ ይገኛሉ።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ የተሰራው የህዝብ ተሳትፎን የመመለስም ሆነ የግድቡን ግንባታ የማፋጠን ሥራ እጅግ ትልቅና አስደሳች ውጤት የታየበት ከመሆኑም በላይ በአሁኑ ወቅት የግድብ ግንባታ 79 በመቶ ላይ ማድረስ አስችሏል።
ይህ አይነት ውጤት ቢመዘገብም ቀሪው 20 እና 21 በመቶ ሥራ ቀላል ካለመሆኑም በላይ በርካታ ሥራን ገንዘብን የሚፈልግም ነው። ከህዝቡም ሆነ ከመንግሥት ትልቅ ሥራን የሚጠይቅ ነው። በመሰረቱ አሁን ላይ ህዝቡ ግድቡን ለመደገፍ እጅግ ተነሳስቷል። በአገር ቤት ያሉ ብቻ ሳይሆኑ ውጪ አገር ያሉትም በታላቅ ወኔና ቁርጠኝነት የግድቡን ሥራ ዳር ለማድረስ ከፍተኛ የሆነ ጥረትን እያደረጉ በመሆኑና ሁሉም አሻራቸውን እያሳረፉ ስለሆነ ውጤትም እየታየ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በዚህ አሥር ዓመት ውስጥ ግድቡ የደረሰበት ደረጃ በእርስዎ እይታ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አረጋዊ፦ ግድቡ የአገርን ገጽታ የሚያሳይ የአንድነታችን ተምሳሌትም ነው። ከዚህም ባሻገር ደግሞ ብዙ ሰው ተስፋ የጣለበትም ነው። ምክንያቱም ግድብ ከ6ሺ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ነው የሚያመነጨው። ይህ የኤሌክትሪክ ሃይል ደግሞ በአፍሪካ አንደኛ ነው።
በአንፃሩ አሁን ያለንበት ሁኔታ 65 በመቶ የሚሆነው የአገራችን ህዝብ የኤሌክትሪክ ብርሃን የማያገኝ ጨለማ ውስጥ የሚኖር ከመሆኑ አንጻር ይህንን ሁሉ የሚለውጥ ተብሎም ተስፋ የተጣለበት ነው። ከዚህ የተነሳም ነው ህዝቡ እየተሳተፈ ያለው፤ በመሆኑም በዚህ አካሄዳችን ከቀጠልን ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሥራውን አጠቃለን እንጨርሳለን። ግድቡም የሚፈለግበትን ኃይል በአስተማማኝ ሁኔታ ይሰጣል የሚል አስተያየት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፦ በአሥሩ ዓመት ውስጥ ሀዝብን ለማስተባበር የተሰሩ ስራዎች እንዴት ይገለጻሉ?
ዶክተር አረጋዊ፦ ህዝቡ የዓድዋ ድልን ለመድገም ነው የሚያስበው፤ የህዝቡ ወኔ አንድነትና ሌላም ሌላም በሚገርም ሁኔታ ነው እየታየ ያለው፤ ይህ የህዳሴ ግድብ አንድነትን፣ ፍትሃዊነትን፣ አሻጋሪነትንና ሉዓላዊነትን ጨምሮ የሚያሳይ በመሆኑ ህዝቡ በንቃት ነው የሚሳተፈው፤ ተሳትፎው ደግሞ በሚያስገርም ሁኔታ የዓድዋን ድል እንደመድገም አድርጎ ነው እየወሰደው ያለው።
በነገራችን ላይ የዓድዋ ድል እኮ እንዲሁ ከሜዳ ተነስቶ የመጣ አልያም እኛ ጣሊያኖቹን በልጠናቸው የመጣ አይደለም፤ ይልቁንም ለድል ያበቃን ነገር አንድነታችንና በአንድነት መቆማችን ነው። ስለዚህ ህዝቡ አሁን ላይ ለግድቡ ያለው ወኔ በዚህ ደረጃ ነው።
ስለዚህ መነሳሳቱ ትልቅ ነው ከዚህም በላይ ከህጻን እስከ አዛውንት ያሉ ሁሉ ተሳትፏቸውን በተለያየ ደረጃና መጠን እያደረጉ ነው። ለምሳሌ ሰሞኑን አምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሮግራም አዘጋጅቶ እዛ ነበረንና ህጻናት በግድቡ ዙሪያ ያቀረቡት የስዕል ትርኢት፣ ወጣቶቹ ያቀረቡት ቲያትር፣ በዚህ ውስጥ ደግሞ የከበቡንን ጠላቶች እንዴት ማሸነፍና ግድቡን ማጠናቀቅ እንደምንችል የገለጹበት መንገድ ህዝቡን ያስለቀሰ ነበር። ይህ የሚያሳየው የህዳሴው ግድብ በሁሉም ልብና ደም ውስጥ የሚዘዋወር መሆኑን ነው።
በመሆኑም ህዝቡ የግድቡ ሥራ የማሻገር የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ብሎም የአገር ሉአላዊነት ጉዳይ መሆኑን ተረድቶ ከእሱ የሚፈለገውን ሁሉ አድርጎ ስራውን ለማጠናቀቅ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦አሁን የግድቡን አሥረኛ ዓመት አንድ አካል የሆነው የቦንድ ሽያጭ ሳምንትም እየተካሄደ ነውና እንደው በዚህስ ላይ ያለው የህዝብ ተሳትፎ ምን ይመስላል?
ዶክተር አረጋዊ፦ በቦንድ ሽያጭ ሳምንቱ ላይ ኅብረተሰቡ እየተሳተፈ ነው፤ ነገር ግን ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እየተንቀሳቀሰበት ነው ማለት ደግሞ አይደለም። እስከ አሁንም የተወሰኑ ኢንዱስትሪዎች ባንኮች ኩባንያዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ። ምናልባት ጽህፈት ቤቱ ካለበት የሰው ኃይል እንዲሁም የቁሳቁስ እጥረት አንጻር በቅስቀሳው ብዙ ስላልተሰራ ይሆናል። በመሆኑም በቀጣይ ቀናት ህዝቡ ቦንዱን ባለው አቅም እንዲገዛ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ ለመስራትም እየተንቀሳቀስን ነው።
በእስከ አሁኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልማት ባንክና ብሔራዊ ባንክ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ለሌሎች መነሳሳትን ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ። የቦንድ ሳምንቱ ዘመቻ እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ የሚቆይ ቢሆንም ህዝቡ ግን ዓመቱን ሙሉ በሚያገኘው አጋጣሚ በሙሉ ቦንዱን እየገዛ አስተዋጽኦ ማድረግም አለበት።
አዲስ ዘመን፦ የግድቡ መሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ 10 ዓመት ሞልቶታል፤ የግንባታው ሂደት ከለውጡ በፊትና በኋላ እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር አረጋዊ፦ እውነት ለመናገር ከለውጡ በፊት የነበረው አሠራር ብልሹ ነው። በርካታ የሙስና ስራዎች ይሰሩበትም ነበር። እንደሰማነው እኮ ሙስናው ወይም ብልሹ አሠራሩ የጀመረው ከምንጣሮው ነው። ከዛ በኋላም በሚገጠሙ ማሽኖች ለግንባታ ስራው በሚውሉ ብረቶች አሸዋ ሲሚንቶና ሌሎችም ላይ በርካታ የሙስና ስራዎች ሲሰሩ ነበር። በዚህም ምክንያት ደግሞ የግንባታ ሂደቱ ከተያዘለት ጊዜና ገንዘብ በላይ ብዙ ሀብትና ንብረትን ሊጠይቅ ችሏል።
ከለውጡ በኋላ ያለው የግንባታው ሂደት ትልቅ እንደምታ የታየበት ነው፤ በወቅቱ የተበላሸውን የኢንጂነሪንግ ሥራ ከመከለስ ጀምሮ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የገቡትን ግን ደግሞ ለግድቡ ግንባታ የማይሆኑትን ማሽኖች በመቀየር በኩል በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል ፤ በዚህም በሁለት ዓመት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ልናይ በቅተናል።
በጠቅላላው ግን ያለፈው ግዜ የሙስና የተበላሸ አሠራር የሌቦች መናኸሪያ ሆኖ ነበር የቆየው አሁን ግን ያ ሁሉ ቀርቶ ትልቅ ቁጥጥር እየተደረገ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ በመሆኑም በዚህ ሁለት ዓመት 79 በመቶ አፈጻጸም ላይ ለመድረስ ተችሏል ።
አዲስ ዘመን፦ መንግሥት በግድቡ ግንባታ ላይ አጋጥመው የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የሄደበትን መንገድ በስኬትም በጉድለትም እንዴት ያዩታል?
ዶክተር አረጋዊ ፦ ከለውጡ ወዲህ በእውቀትም በተዓማኒነትም በተቆርቋሪነትና በአፈጻፀም ትልቅ ስኬት የታየበት ነው፤ ለእኔ የሚታየኝ እሱ ነው። በፊት ይታይ የነበረው በስራው ላይ የነበሩ ኢንጂነሮች፣ ዲዛይነሮችና ኮንትራክተሮች በሙሉ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር እንዲሁም ለስራው ቁርጠኝነት ስላልነበር ብዙ ብልሽት ደርሷል። የለውጡ አመራርም ከዛ በመማር ችግሮቹ እንዲታረሙ ከማድረግ በላይ አንዳንድ ስራዎች እንደውም እንደ አዲስ እንዲጀመሩ ሁሉ እስከማድረግ የደረሰም ሥራ ተሰርቷል። ይህ ባይሆን ኖሮ አሁን የደረስንበት ውጤት ላይ መድረስ አይቻልም ነበር። በመሆኑም ይህ አካሄድ ወደኋላ የማይመለስበትና የማይቀዛቀዝበትን አካሄድ መጠቀም ደግሞ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ የአገሪቱ ለውጥና የህዳሴው ግድብ መሠረት የተጣለበት ቀን መገጣጠም ለእርስዎ ምን ስሜት ይፈጥርቦታል?
ዶክተር አረጋዊ፦ ጥሩ ስሜት ነው የሚፈጥርብኝ፤ በቀደሙት ጊዜያት በገዛ ውሃችን ለማኞች የሆንበት ሁኔታ ነው የነበረው፤ ግብጽ አንድ ጠብታ ውሃ አስተዋጽዖ የማታደርግ ዓባይ የእኔ ነው ህገ መንግሥቴ ላይ አስቀምጨዋለሁ እያለች ፍትሃዊ ያልሆነ ምናልባትም የቅኝ ገዢዎች አስተሳሰብ ይዘው እንደራሳቸው በማድረግ የሚያደርጉት ነገር ነበር። ስራውን ለማደናቀፍም በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል፤ ይህ ደግሞ የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንዳይመስልሽ፤ ከጥንት ጀምሮ የሚያደርጉት ነገር ነው። ነገር ግን በጦርነት ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት አልሳካ ሲላቸው በዲፕሎማሲው መጥተዋል። እንግዲህ የሚሆነውን እናያለን። ግን ደግሞ “የውሃው ባለቤቶች ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ አይጠቀሙ፤ እነሱ ዘላለማቸውን ጎስቋላ ኑሮን ይኑሩ፤ እኛን ይመቸን” ማለት ስግብግብነት ነው። በመሆኑም ተባብረን ይህንን ስህተታቸውን እንዲያዩ ማስቻል አለብን።
የውስጥ ችግሮቻችንን ወደኋላ አቆይተን ተባብረን በዲፕሎማሲውና በፖለቲካው ዘርፍ እየፈጠሩብን ያለውን ጫና መቋቋም መቻል አለብን። ይህንን ደግሞ ልናደርገው እንችላለን። እዚህ ላይ የሚያስፈልገው የአገር ጥቅምንና የቡድን ጥቅምን ለያይቶና ሰፋ አድርጎ ማየት ብቻ ነው።
የአገር ጥቅም የሁላችንም ከመሆኑም በላይ የግድቡ መጠናቀቅ ደግሞ ለሁላችንም ብርሃን የሚያስገኝ ነው። ስለዚህ ይህንን አይተን ተባብረን ከተንቀሳቀስን በዲፕሎማሲውም ይሁን በፖለቲካው መስክ የሚቃጣብንን ሁሉ መቋቋም እንችላለን።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ ለረጅም ዓመታት በስደት ኖረው በለውጡ ምክንያት ወደአገር ቤት ገብተዋል፤ አሁን ደግሞ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ነዎት፤ ግን እንደው ይህ ሁኔታ ይመጣል ብለው አስበው ነበር?
ዶክተር አረጋዊ፦ መምጣቴ በጣም ነው ደስ የሚለኝ። እነዛን ሁሉ ዓመታትም ስታገል የነበረው አገሬ ለመግባት ነበር፤ በዚህም ተሳክቶልኛል። ነገር ግን የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር እሆናለሁ ብዬ በፍጹም አላሰብኩም።
ያኔ አገሬ መግባት አለብኝ ብዬ ሳስብ የነበረው ምናልባትም የከፍተኛ ትምህርት ተቋምን በመምህርነት አገለግላለሁ፤ አልያም ያሉኝን የህይወት የፖለቲካ እንዲሁም በውጭ አገር የተማርኳቸውንና ያገኘኋቸውን እውቀቶች አቀናብሬ መጽሃፎች እጽፋለሁ፤ ይህም ካልሆነ ደግሞ ጋዜጦች ላይ በመጻፍ ሀሳቤን አካፍላለሁ ብዬ ነበር ያሰብኩት። አጋጣሚ ሆኖ ግን የለውጡ መንግሥት ህዝብን በታላቁ ግድባችን ዙሪያ የማስተባበር ኃላፊነትን ሰጠኝ። ይህ ደግሞ አስደሳች ነገር በመሆኑ ኃላፊነቱን ተቀብዬ በደስታ ነው እየሰራሁ ያለሁት።
አዲስ ዘመን ፦ የለውጡ አመራር ወደሥልጣን ከመጣ ወዲህ የተመዘገቡ ድሎች ያሉ ቢሆንም ጉድለቶችም አይጠፋምና እንደው እነዚህን እንዴት ይገልጿቸዋል?
ዶክተር አረጋዊ ፦ ጥያቄው በዚህ የለውጥ ሂደት ጉድለት አለወይ ? የሚለው ነው፤ በእርግጥ ሁሉ ሙሉና ዝግጁ የሆነ ነገር የትም ዓለም ላይ አይገኝም። ሁልጊዜ ሥራ ሲሰራ ነገሮች ተለዋዋጭ ስለሆኑ ከለውጡ ጋር መራመድ ቀላል አይደለም።
የእኛን ለውጥ ደግሞ ከባድ የሚያደርገው ነገር ላለፉት ጊዜያት የነበሩት ስርዓቶች በጣም ወደኋላ የቀሩ አፋኞች ነበሩ፤ በጠቅላላው ህዝብ የሚቆጣጠረው ስርዓትም አልነበረም ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት ወደኋላ ቀርተናል። ለዚህ ሁኔታ መፈጠር ደግሞ ትልቁ ጥፋት ያለው እኛ ጋር ነው።
ይህም ማለት እኛ እንደ ህዝብ የሚጠቅመንን ስርዓት መገንባት አለመቻላችን ነው። ህዝቡ ተደራጅቶ ሲቪክ ማህበር ፈጥሮ የሚፈልገውን ነገር በአግባቡ በህገ መንግስቱ መሰረት ማስኬድ ቢችል ኖሮ መንግሥትን መቆጣጠር ብሎም መቋቋምም ይችል ነበር። ያ ህብረት አንድነት እንዲሁም ተራማጅ ስርዓት የመፍጠር ሁኔታ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ጥቂት ሰዎች ይመጣሉ፤ ስልጣኑን ይይዛሉ፤ ህዝቡንም ይነዱታል፤ ሁሉም ይኖሩ የነበረውም ለቡድን ጥቅማቸው ስለነበር ያ ሁሉ ነገር ተፈጥሯል።
አሁን ደግሞ ሁኔታዎች እየተለወጡ ነው፤ ዛሬ ላይ ህዝብ በሲቪክ ማህበራት በፖለቲካ ድርጅት መደራጀትና ጥቅሙን ለማስከበር የሚያስችለው በር ተከፍቷል ፤ በተከፈተው ደግሞ አልገባም የሚል አለ። ግን ደግሞ የተደራጀው ህዝብ ስለሚቋቋመው የትም አይደርስም። በአጠቃላይ ሳየው ለውጡ ግን ወደ አብዮታዊነት የተጠጋ ይመስለኛል። ቀላል መሻሻል አይደለም፤ አሁን እኮ ህዝብ ሥልጣን እንዲጨብጥ በር ተከፍቷል። ይህም ቢሆን ግን ልዩነቶች ይንጸባረቃሉ። ልዩነቶቹን እየተጠቀሙ መካከል የሚገቡ ለግል ጥቅማቸው ማራመጃ ለማድረግ የሚሞክሩ ወደነበርንበት ሊመልሱን የሚሞክሩ ብዙ ናቸው።
ከነዚህ ውስጥ አንዱ የጁንታው ቡድን ነው። እርሱ ቢሳካለት ወደነበርንበት የጨለማ ኑሮ ሊመልሰን ይፈልጋል። ይህ ደግሞ ሊሆን የማይችል መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። በመሆኑም የለውጡን ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንደዚህ አድርገን መመዘን እንችላለን።
አዲስ ዘመን ፦ ሲፈለግ የነበረው ለውጥ መጥቷል ግን አሁን ላይ ለለውጡ መምጣት ምክንያት የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎች ለምሳሌ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የመሳሰሉት ላይ መልስ ለመስጠት የተሄደበት ርቀት በእርስዎ እይታ እንዴት ይገለጻሉ?
ዶክተር አረጋዊ፦ ለመመለስ የተቻለው ሁሉ ጥረት እየተደረገ ነው። ሙሉ ለሙሉ አልተመለሱም። እነዚህ ጥያቄዎች እንዳይመለሱ የሚያደርጉ ደግሞ በርካታ ተግዳሮቶች አሉ። ከነዚህም ውስጥ አንዱና ትልቁ ችግር ህዝቡ አለመደራጀቱ ነው፤ ተደራጅቶ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ግዴታውን ለመወጣት አልቻለም። የተደራጀ ህዝብ መንግሥትን የሚረዳ በመሆኑ ለስራው ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ግን ደግሞ ይህ አሁን ላይ እየተሞከረ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ አልሆነም።
ሌላው ተግዳሮት ደግሞ ለውጡን ከማይደግፉ ኃይሎች የሚመነጭ ሲሆን በየክልሉም የህወሓት ጁንታ ተላላኪዎች አሉ፤ እነዚህንም መቆጣጠር ያስፈልጋል። ግን ደግሞ እነዚህንም ማስወገድ የሚቻለው በመሣሪያ ብቻ ሳይሆን ህዝቡን አደራጅቶ አንፈልጋችሁም እንዲል ማስቻልም ሲቻል ነው።
በመሆኑም አሁንም ከችግሮቹ ወጥተን ለውጡን ለማየትና መንግሥትም በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲወጣቸው ለማስቻል መስራትና መቀዛቀዝን ማስወገደም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ የለውጡን ቀጣይ ተስፋ በተለይም ከምርጫ ጋር አያይዘው ቢገልጹልኝ?
ዶክተር አረጋዊ፦ ምርጫ ትንሽ አስቸጋሪ ሆኖ ይታየኛል። ምርጫ ማካሄድ የህዝቡን ድምጽ ለመስማት ያስችላል። መደረግም አለበት። ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን የሰላም የመረጋጋትና ሌሎች ሁኔታዎችም ጎን ለጎን በፈጠነ ሁኔታ መካሄድ አለባቸው ነው የምለው። ለምሳሌ አሁን ትግራይ ላይ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። ጁንታውም ምርጫውን ለመረበሽ ተበታትኖ እየሰራ ነው። በተመሳሳይ በሌሎች አካባቢዎችም ይህ ዓይነት ችግር ሊኖር ስለሚችል ህዝቡ ተረጋግቶና ተደራጅቶ የሚፈልገውን ፕሮግራም ወይም ድርጅት ጠይቆና መርምሮ ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ አይታየኝም። ስለዚህ እነዚህ እንቅፋቶች በቶሎ መወገድ ስላለባቸው። መንግሥት በዚህ በኩል የቤት ስራውን መስራት ይገባዋል።
የትግራይ ምርጫ ተላልፏል። ነገር ግን በሌሎች አካባቢዎች ላይ ምርጫው በታቀደው ጊዜ እንዲካሄድ ምርጫ ቦርድም እየተሯሯጠ ነው፤ በመሆኑም ከላይ ያሉትን ችግሮች መመርመርና የተረጋጋ ምርጫ እንዲኖር ለማድረግ መስራቱ አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የትግራይ ህዝብ የለውጡ ተጠቃሚ እንዳይሆን የነበሩት ችግሮች ምን ነበሩ? አሁንስ ምን ምቹ ሁኔታ አለ?
ዶክተር አረጋዊ ፦ የህወሓት ጁንታ ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት ተመችቶት ተዝናንቶ እንደፈለገው ህዝቡን ረግጦ ሲገዛ ነበር። በዚህ ምክንያት ደግሞ ህዝቡ የድህነት ማቅ ለብሶ ነው የኖረው፤ የልመና እህል ነበር የሚበላው። እነሱ ደግሞ አዲስ አበባ ተቀምጠው ህዝቡን ያስተዳድሩ የነበረው በተላላኪዎቻቸው ነው እንጂ ፍጹም ረስተውት ነበር።
አሁን ላይ ደግሞ እነዚህ ተላላኪዎች ግማሾቹ በጫካ፤ ገሚሶቹ ውጪ አገር ሆነው ለመመለስ ሲለፈልፉ ነው የሚውሉት፤ ነገር ግን አሁን ህዝቡ ጥቅምና ጉዳቱን በደንብ ተረድቷል። እነሱን መመለስ አይደለም ማሰብም አይፈልግም። በነበረው ችግር ላይ ተጨማሪ ችግር ውስጥ እንደከተቱትም ያውቃል፤ በመሆኑም መንግሥት አቅሙን አጠናክሮ ፈጣን እርምጃዎችን በመውሰድ ህዝቡን የለውጡ ተጠቃሚ ሊያደርግ ይገባል። የትግራይ ህዝብም አንድነቱን አጠናክሮ ከሌሎች እህት ወንድሞቹ ጋር በመሆን ለውጡን ማሳካትም ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፦ የትግራይ ህዝብ ለታላቁ የህዳሴ ግደብ ሲያደርግ የነበረው ድጋፍና አጠቃላይ አስተዋጽኦን እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር አረጋዊ፦ የሚገርም ነገር ነው። የህዳሴ ግድቡን ለመጀመር ነገሥታቱም በኋላም በደርግ ዘመን ሀሳብ የነበረ ቢሆንም በቁርጠኝነት ወደ ስራው የተገባው ግን በኢህአዴግ ዘመን በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአስተዳደር ጊዜ ነው፤ በወቅቱ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ጨዋታ የነበረው ቢሆንም ግን ስራው ተጀምሯል። በጣም የሚገርመው ግን ኋላ ላይ የህወሓት አመራሮች ህዝብ እንዳይሳተፍ ግድቡ ተሽጧል እስከማለት ደርሰውም ነበር። ይህ የሚያሳየው ደግሞ አስተሳሰባቸው ኋላ የቀረ መሆኑን ነው። እንደውም ተመስጋኝነቱን ወይም ሽልማቱን ለማግኘት እኛ የጀመርነው ነው፤ መፈጸምም አለበት ብለው ማለት ነበረባቸው። ግን የዘቀጡና መጥፋታቸውም የማይቀር ሃቅ እየሆነ ሲመጣ የጀመሩት ግድብ ላይ ሴራ መጠንሰስ ጀምረው ነበር፤ ያው እንግዲህ አልተሳካላቸውም።
ነገር ግን ህዝቡ የእነሱን አልባሌ ወሬ ወደጎን በመተው ለግድቡ ግንባታ እንደማንኛውም ዜጋ የራሱን አስተዋጽዖ ሲያደርግም ነበር። የጁንታው ኃይል ከአዲስ አበባ ሸሽቶ መቀሌ ሲመሽግ ግን ድጋፉ እንዳይቀጥል አድርገውታል። በቀጣይ በክልል ሰላምና መረጋጋት ሲፈጠርና ህዝቡ ወደመደበኛ ኑሮው ሲመለስ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነኝ፤ ምክንያቱም የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ የሚያመነጨው ብርሃን የሚያስገኘው ሀብት ሁሉም ለእሱ የሚደርሰውና ካለበት ጎስቋላ ህይወትም እንደሚያላቅቀው ያውቃል።
አዲስ ዘመን፦ በቀጣይ የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ፍጻሜው እንዲታይ የህዝቡ ተሳትፎ ምን መምሰል ይኖርበታል ይላሉ?
ዶክተር አረጋዊ፦ ግድቡ የፍትሃዊነት ጥያቄ ነው። ምክንያቱም ውሃችን አፈራችን ለዘመናት ማንም ሲጠቀምበት እኛ የበይ ተመልካች ሆነን ኖረናል። በመሠረቱ ይህ እንዲሆን የእኛም ጥፋት አለበት። ለምን ያልሽ እንደሆነ ተባብረን ውሃችንንና አፈራችንን ገድበን ለጥቅም አለማዋላችን እንዝላልነታችን ነው። ይህንን ተገንዝበን በቀጣይም ትብብራችንን አጠናክረን በዲፕሎማሲውም በፖለቲካውም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ሆነን ከሠራን ጥቅም ላይ እናውለዋለን።
በመሆኑም በአገር ቤትም እንዲሁም በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተደራጅተው ተጽዕኖ ለመፍጠር ለፍትሃዊነትና ለሉዓላዊነታችን ጠንክረን መስራት ፍትሃዊ ጥያቄያችንን ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሠ ግናለሁ።
ዶክተር አረጋዊ፦ እኔም አመሠግናለሁ
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013