(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
ብርሃን ይሁን፤
የብርሃን ተቀዳሚ ሥራ ጨለማን መግፈፍና የኃይል ምንጭ መሆን ነው። ሌሎች በርካታ አገልግሎቶቹ ምናልባትም ለቅንጦት የሚፈለጉ ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ። ሀገሬ ታላቁን የህዳሴ ግድቧን በልጆቿ ብርቱ ውሳኔና ጥረት እየገነባች ያለችው ራሷን ከጥልቅ የድህነት ጨለማ ለማውጣትና ዜጎቿን ለመታደግ እንጂ ለመቀናጣት ፈልጋ አይደለም።
ጉዳዩ ቢያሳፍርም የድሃ ድሃ እና ድሃ እያሉ ለድህነታቸው ደረጃ ከመደቡ ሀገራት ተርታ ቀዳሚውን ሠልፍ የያዘችው ይህቺው ሀገሬ ሳትሆን እንደማትቀር እጠረጥራለሁ። ከአሁን ቀደም በዚሁ ጉዳይ ላይ ተደጋጋሚ ጽሑፎችን ስላስነበብኩ ደግሜ ብዕሬን አላደክመውም። ይህ ጉዳይ አሳፋሪ ከሚባሉት የሀገሬ የታሪክ ገመናዎች መካከል ዋናውና ተቀዳሚው ስለሆነ ደጋግሞ መተረኩ እርባና የለውም። በህዳሴ ግድቡ ላይ የሀገሬ ዜጎች ትንሹም ይሁን ትልቁ ዓይኑንና ቀልቡን በአትኩሮት ጥሎ ፕሮጀክቱን ከፍጻሜ ለማድረስ የሚረባረበው ይህንን ክፉና የተጣባንን ድህነት ይሉት አዚም ለመመከት እና የልማቱን ጎዳና ለማቅናት እንጂ ሌላ ምንም የተለየ ምክንያት ኖሮን አይደለም።
ድህነትን እያንቆለጳጰስን “ድህነታችን” ስንል መኖራችን እንዴት አሳፋሪ እንደሆነም በቅርቡ “በሕግ አምላክ” የማለት ያህል ብዕሬ እሪታውን ቢያሰማም ጩኸቱ ከጆሯቸው ያልደረሰ ሹመኞችና አወቅን ባዮች ዛሬም በየሚዲያው ደግመው ደጋግመው ቃሉን ሲጠቀሙበት እያስተዋልን ነው። ለመሆኑ የድሃና የድሃ ድሃ መለያ መስመሩ ምን እንደሆነ ልዩነቱን ለምን ደፈር ብለው አያሳዩንም። ድሃ ማነው? የድሃ ድሃ የሚለካውስ በምን መስፈርት ነው? መልሱን እነሆ የሚለን ባናገኝም ጠይቀን ማለፉ ግን ለታሪካችንም ሆነ ለኅሊናችን ሳይበጅ የሚቀር አይመስለኝም። ይህን መሰሉ “የራስ ግራ መጋባት” ከምናፍርበት ሀገራዊ ገመናችን መካከል አንዱ ነው ብንል በራሳችን ጉዳይ ተቆጭ ሊኖረን አይገባም።
የቅዱስ መጽሐፉ የዘፍጥረት ታሪክ እንደሚተርክልን ፈጣሪ ቅርጽና መልክ ያልነበራትን ምድር ማበጃጀትና ማስዋብ የጀመረው በከበባት ጥልቅ ጨለማ ላይ “ብርሃን ይሁን!” የሚል መለኮታዊ አዋጅ በማወጅ ነበር። የበረታው ድቅድቅ ጨለማም በፈጣሪ ብርቱ ድምጽ ሲገፈፍ ኢትዮጵያን የከበባትና ገነትን የሚያጠጣው የግዮን ወንዝ ግርማ ሞገሱን እንደተላበሰ በወገግታ ታጅቦ መገለጡንም ይሄው የቅዱስ መጽሑፉ ታሪክ ይተርክልናል። ይህ ጉዳይ የአፈ ታሪክ ወግ አይደለም፤ እውነትም እምነትም እንጂ።
ሳናጣ ለደኸየንበት፣ ሳንቸገር ለተቆራመድንበት ሀገራዊ ጥልቅ ድህነት እንደ አንድ መመከቻና መቅረፊያ ተስፋችንን የጣልነው ከመሸ በኋላም እንኳን ቢሆን በህዳሴ ግድባችን ላይ ነው። በግድባችን ላይ ዜጎች እያተሙ ያለው አሻራ ሲነበብ የሚሰጠው ትርጉም አገልግሎቱን ብቻ የተመለከተ ሳይሆን በዝርዝር ባይተነተንም ለታላቋ ዓለማችን፣ ለጎረቤት ሀገራትና ለተፋሰሱ አባላት ትርጉሙ ቀላል አይሆንም። በተለይም እኛን ለሚያጣቅሱ ጉዳዮች የብርሃኑ ትሩፋት በቀላሉ የሚታይ ስላልሆነ ብንጓጓላትና ብንሳሳለት ተገቢም አግባብም በልበ ሙሉነት እናረጋግጣለን።
«አፈ ወሪሳዎቹ» ሁለቱ የናይል ቤተሰቦች፤
“አፈ ወሪሳነት” እንዳመጣለት የሚናገር፣ የሚለፈልፍ፣ ለከት የለሽ ይሉት ዓይነት ሰብዕና መገለጫ ነው። “አፈ ወሪሳ” ግለሰብ የሚናገረው አስቦ ሳይሆን የስሜት ሙቀቱ ሲያንተከትከው የሚያወጣው ትንፋሹ ያማረለት እየመሰለው ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን በታላቁ የአባይ ወንዛችን ላይ የህዳሴ ግድባችንን ጨክነን ለመገንባት የተነሳነው ከጥልቅ የጨለማ ግዞት አርነት ለመውጣት እንጂ የትኞቹንም የተፋሰስ ሀገራት ለመጉዳት በማሰብ እንዳይደለ ቀደም ሲል በዝርዝር ገልጫለሁ።
ይህ የሀገራችንና የመንግሥታችን ጽኑ አቋም በተለያዩ መልኮችና መድረኮች ሲገለጽ መኖሩ ለናይል ቤተሰብ ሀገራት አይጠፋቸውም። ማረጋገጫውም በተለያዩ ጊዜያትና ወቅቶች ደርሷቸዋል። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባልነቱ ከልዑካን ቡድኑ ጋር ሕዝብንና ሀገርን በመወከል በተወሰኑ የተፋሰሱ ሀገራት በተደረገው ጉዞ ለየሀገራቱ መሪዎችና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ለመግለጽ የተሞከረውም ይሄው ያልተሸፋፈነ እውነታ ነው።
ሀገሬ እየገነባችው ያለው ግድብ አንዱንም የተፋሰሱን ሀገር እንደማይጎዳ ይህ ጽሑፍ አቅራቢ ከኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የልዑካን ቡድን አባላት ጋር በመሆን በግብጽ ታላቁ ቤተ መንግሥት በመገኘት ለፕሬዚዳንት አል ሲሲ ማረጋገጫውን ሰጥቷል። ፕሬዚዳንቱም የልዑካን ቡድኑን መልዕክት ካደመጡ በኋላ “እውነት ነው ሀገራችሁ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር እንዳለባት እንረዳለን። ሕዝባችሁም በድህነት ውስጥ መኖሩ አልጠፋንም ነገር ግን የግድቡ ፕሮጀክት በጥንቃቄና ያለምንም ጉዳት እንዲጠናቀቅ ለመሪዎቻችሁ መልእክት አድርሱልን” በማለት በጥሩ የመግባባት መንፈስ ተልእኮው እንደተጠናቀቀ ብዕሬም ብቻ ሳይሆን ኅሊናዬም እውነቱን ይመሰክራል።
ከፕሬዚዳንቱም በተጨማሪ ከሀገሪቱ የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ፣ ከእስልምና መሪው ከታላቁ ሙፍቲ፣ በየደረጃው ከሚገኙት ከፍተኛ የሀገሪቱ የሥራ መሪዎች፣ ምሁራንና የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋርም የልዑካን ቡድኑ ተመሳሳይ መልእክቶችን ለማድረስ ሞክሯል።
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ወደ ሱዳንና ዩጋንዳ በማቅናትም ለየሀገራቱ መሪዎችና ለሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ግድቡ በየትኛውም የተፋሰሱ ሀገር ላይ ጎጂ ተጽእኖ እንደማያስከትል ሕዝብን በመወከል ከተንቀሳቀሰው ቡድን ማረጋገጫው ተሰጥቷቸዋል። ጥሬ ሐቁ ይህ ሆኖ እያለ ሰሞኑን በግብጽና በሱዳን ሀገራት በኩል እየተጎሰመ ያለው የጦርነት ነጋሪት አዋጅ ምን ይሉት እብደት እንደሆነ ለመረዳት ያዳግታል።
“አፈ ወሪሳዎቹ” የየሀገራቱ መሪዎች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ምሁራንና የጦር አበጋዞች የህዳሴ ግድባችን እውነታ ጠፍቷቸው ሳይሆን ኅሊናቸውን በማሳወር ያለማቋረጥ እያስተላለፏቸው ያሉት የእብሪት መልእክቶችና ፉከራዎች እንኳን ለሰሚዎች ቀርቶ በራሳቸው ሕዝብ ፊትም ለትዝብት ሳይዳርጋቸው አይቀርም።
“የራሴ ምድር ከሚያመነጨው መቶ ፐርሰንት ወንዝ ተጠቅሜ ድህነቴን ልክላ፤ የእናንተን ድርሻ በፍጹም አላጓድልም” እየተባለ ደግሞ ደጋግሞ ማረጋገጫ ሲሰጣቸው ለምን ከእውነታው ጋር ትንቅንቅ ለመያዝ እንደመረጡ ለእነርሱም ሆነ ለእኛ ግልጽ አይደለም። የሱዳናዊው ጄኔራል ፉከራ፣ የፕሬዚዳንት አል ሲሲ ቀረርቶ፣ የትንኮሳና የጠብ አጫሪነት ያዙኝ ልቀቁኝ ምን ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ታሪካቸውን ቢመረምሩት እውነቱ በቀላሉ ሊገባቸው ይችል ነበር።
ግብጽ የአስዋንን፣ ሱዳን የመረዌን ግድቦች በየፊናቸው ሲገነቡ ማንንም አላስፈቀዱም፤ እከሌ ከሚባል ሀገርም ተቃውሞና ዛቻ የሰነዘረባቸው አልነበረም። ጥረታቸውን አሳክተውም ሕዝባቸውን በኤሌክትሪክ ብርሃን ሲያጥለቀልቁ መንፈሱን አጥቁሮ ያኮረፋቸውም ሆነ ያስፈራራቸው አንድም ሀገር ስለመኖሩ ታሪካቸው አይነግረንም።
ኢትዮጵያ ላይ ሲሆን ግን ያውም አንዳችም የባእዳን አስተዋጽኦ በሌለበት ሁኔታ የራሴን የተፈጥሮ ፀጋ በራሴ ሕዝብ ገንዘብ ገንብቼ ተጠቃሚ ልሁን ብላ ስትፍጨረጨር ለምን ምላሳቸውንና ጣታቸውን እያስረዘሙ ደም በለበሰ ዓይናቸው ደም እንደሚያሸቱ ግራ ያጋባል። “ጠብ ያለሽ በዳቦ” ትንኮሳቸውም ፍጻሜው በምን ሊደመደም እንደሚችል ጠፍቷቸው ሳይሆን ራሳቸውን እየሸነግሉ ማቅራራታቸው “አፈ ወሪሳነት” ባህሪያቸው ግድ ቢላቸው ነው።
«ውሃ ስንቁ» የፈርኦን ልጆች፤
የሀገራችን ቀደምት ታሪክ በብዙ አስደናቂ ክስተቶች የወዛ ነው። ለምሳሌ፤ አንዱን የታሪካችን አንጓ እናስታውስ እንኳን ብንል “የውሃ ስንቁ” ጉዳይ የሚዘነጋ አይደለም። የታሪኩ አሻራ ዛሬም ድረስ ስለሚታወስ ጭርሱኑ ደብዝዟል ማለት አይቻልም። ከፊውዳል ሥርዓተ ወጎች መካከል አንዱ የደጅ ጠኝነት ባህል ይጠቀሳል። ምክንያት ይኑረውም አይኑረው ሥልጣኔ አነሰ ወይንም የሀብቴ መጠን ክብሬን አይመጥንም ስለዚህ ባለው ላይ ይጨመርልኝ የሚል የየአካባቢው ሹም በንጉሥ ደጅ እየተገኘ ለወራትና ለዓመታት ደጅ መጥናት የተለመደ ባህል ነበር። ተገፋሁ፣ ተበደልኩ ወዘተ. የሚሉት ውሃ የሚቋጥሩት አቤቱታዎች ሳይዘነጉ በተለየ ሁኔታ ግን ለተሻለ ወንበርና ሀብት ደጅ መጥናት በነገሥታቱ ዘመን የተለመደ ነበር።
ይህን መሰሉ ስንቅን ሸክፎ ለተሻለ የስልጣንና የተጠቃሚነት ወንበር አቤቱታ የሚቀርብበት ደጅ ጥናት ስንቅም እንኳን ቢያልቅ ውሃም እየጠጣሁ ቢሆን ሙግቴን አልተውም እየተባለ እልህ የሚጋቡበት ባህል ነው። የሆነው ሆኖ ግን በቂ ምክንያት ይኑረውም አይኑረው ደጅ ጠኚው የቋጠረው የስንቁ ጭብጦ ወይንም በፍትፍት የተጠቀጠቀው አገልግሉ አለያም መጠባበቂያ ገንዘቡ ሲሟጠጥ፣ የዕለት እንጀራውም መንጠፍ ይጀምራል። የመተማመኛ ስንቁ በሙሉ መሟሟቱ ሲረጋገጥም “ውሃን በስንቅነት” ተስፋ ማድረግ ግዴታ ስለሆነ ስያሜው የተገኘው ከዚሁ ታሪካዊ ዳራ ነው።
ይህንን አባባል ተውሰን ለፈርኦን ልጆች ብንሰጣቸው ጥሩ ገላጭ ሊሆን ይችላል። የግብጽ ሹማምንት ነጋ ጠባ በዓለም መንግሥታት ጽ/ቤቶች ደጃፍ ላይና በየሸንጎዎቻቸው በምክንያት የለሽ አቤቱታና ደጅ ጥናት ሲንጨረጨሩ እያስተዋልን ነው። “በአባይ ወላጅ” ሀገሬ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ማዕቀብ እንዲጣል፣ ወይንም አይዟችሁ አለንላችሁ እንዲባሉ በመሸ በነጋ በደጅ ጥናት መትጋታቸው በእጅጉ የሚያስገርም ክስተት ነው።
ሀገሬ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የወሰደችው አቋም የጋራ ተጠቃሚነትን የማይሸረሽር ብቻም ሳይሆን ፍትሐዊና ሞራላዊም ድጋፍ ያለው ነው። ማንንም ሳትጎዳ ተፈጥሮ የለገሳትን ፀጋ እንዳሻት ትጠቀማለች። በዓለም አደባባይ ኡኡታ የሚያሰሙት ምክንያት የለሾቹ የፈርኦን ልጆችም “ስንቅና መከራ እያደር መቅለሉ ስለማይቀር” እውነቱ ሲገለጽ ትዝብት ላይ መውደቃቸው አይቀሬ ነው።
የፈጠራ ትርክታቸው ገሃድ ተገልጦ መራቆት ሲጀምርም ያኔ በራሳቸው ድርጊት አፍረው በፀፀት መቀጣታቸው አይቀርም። የውሃ ስንቁነት የመጨረሻ ውጤቱም አተርፍ ባይ አጉዳይነት መሆኑ ይገለጥላቸዋል። የሀገሬ አቋም ግን ዛሬም ሆነ ነገ አይለወጥም፣ አይበረዝም፣ አይሻርም። አባይ ወንዛችንን የለገሰን በብቸኝነት ፈጣሪ ራሱ ነው። ምንጩም የራሳችን ምድር ነው። የብርሃን ኃይል ለማመንጨት ሌት ተቀን የምንተጋውም የጉልበታችንን አቅም ለተፋሰሱ ሀገራት ለማሳየት ሳይሆን የተጫነብንን የድህነት ጠላት አንበርክከን ሕዝባችንን ከጉስቁልና ግዞት ነፃ ለማውጣት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ አታካራና ሙግት ስለማያስፈልግ ምላሻችን ከራሳቸው ባህል የመነጨው ብሂል ሊሆን ይገባል፤ “ግመሎቹ ይሄዳሉ፤ ውሾችም ይጮኻሉ!” – ይሄው ነው። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013