ልክ የዛሬ አስር ዓመት በዛሬዋ ቀን መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያለመለመ፣ የዘመናት ቁጭታቸውን የተወጡበት፤ ለአፍሪካውያን ተምሳሌት የሆነ ፕሮጀክት ተበሰረ! የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጅማሬ! የዚህ ግድብ እውን መሆን በአባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት የዘለቀ ኢ-ፍትሐዊነት ተቀባይነት እንደሌለው ያረጋገጠ፣ የኢትዮጵያን በሀብቷ የመጠቀም ሉዓላዊ መብት በተግባር ያስመሰከረ፣ በደጁ የዓባይ ውሃ እያለፈ እሱ ግን በብርሃን እጦት ሲሰቃይ ለኖረው ዜጋችን ትልቅ የብርሃን ተስፋን ያጫረ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲቆጩበት የኖሩትን ዓባይ ትርጉም ባለው መልኩ ለኢትዮጵያ ጥቅም እንዲሰጥ የተገራበት ልዩ ሁነት ነበር።
የዚህን ሁነት ዕውን መሆን የሰሙ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ ያለምንም የቋንቋ፣ የባህል፣ የእምነት የኢኮኖሚ አቅም ልዩነት አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን እንዲገልጹ አስገድዷቸዋል ። በዚህም ብቻ ሳይቆጠቡ በማህፀን ካሉ ህፃናትና በመቃብር ካሉ ሰዎች ውጭ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በቦንድ ግዥ፣ በ8100 የገቢ ማስገኛ፣ በቶምቦላ ሎተሪና ወዘተ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የሃብት እጦት ኢትዮጵያውያንን በሃብታቸው ከመጠቀም እንደማያግዳቸው ለዓለም አስመስክረዋል።
መላ ኢትዮጵያውያን እንደ ዓይን ብሌናቸው የሚያዩትና ለደህንነቱ በጋራ ዘብ የቆሙለት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከውጭም ከውስጥም ብዙ ፈተናዎች ቢገጥሙትም መሠረቱ እውነትና ፍትሐዊነት ስለነበር ማንም ሳያስቆመው እነሆ 10ኛ ዓመቱን ዛሬ ደፍኗል ። ከግድቡ ሥራ ጋር በተያያዘ ቀድሞ በአመራር ድክመት ተከስተው የነበሩ ችግሮች በሃገሪቱ ሕዝቦች ትግል ለሥልጣን በበቃው የለውጥ አመራር አፋጣኝ መፍትሔ ተበጅቶለት ዛሬ ላይ በትክክለኛ መስመር እየተጓዘ በፍጻሜው ዋዜማ ላይ እንገኛለን ። ክብር ለለውጡ አመራርና ለመላ ኢትዮጵያውያን ይሁንና በዚህ ዓመት የግድቡ የመጀመሪያ ፍሬ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይልን ኢትዮጵያውያን ይቋደሳሉ ። ዓባይ ለኢትዮጵያ ህዳሴ ሁነኛ መሰረት መሆኑም ይረጋገጣል ።
የመጋቢት ወር ከታላቁ የህዳሴ ግድብ በተጨማሪ ለኢትዮጵያውያን ያበረከተው ሌላኛው ትልቅ በረከትም የለውጥ አመራሩ ወደ ሥልጣን መምጣት ነው። ለሁላችንም ግልጽ እንደሆነው ቅድመ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በነበረው የኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን በነበሩ ዝርፊያዎች፣ ኢ-ፍትሐዊነትና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ዜጎች ተማረው ባነሷቸው የመብት ጥያቄዎችና መብትን ለማፈን በተወሰደ የኃይል እርምጃ አገራችንና ሕዝቦቿ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ቆይተዋል።
የነበረው በመዋቅር የተደገፈ ዝርፊያ፣ በክልሎች ይደረግ የነበረ ጣልቃ ገብነት እንዲሁም እጅግ አረመኔያዊ የኢ- ሰብዓዊነት ተግባር ያንገፈገፈው ሕዝብ ሥርዓቱን አምርሮ ከመታገሉም በላይ እጅግ ውድ የሕይወትና የአካል መስዋዕነት ከፍሏል ። የነበረው ሥርዓት ሕዝቦችን በመከፋፈል፣ በአፈናና በግድያ ትግሉን ለማፈን ቢሞክርም የትግሉ መሰረት እውነት ነበርና ትግሉ ይበልጥ ተፋፍሞ በአገራችን አዲስ የለውጥ አመራር ዕውን ሆኗል ። ለዚህ ለውጥ ፍሬያማነት መላ ኢትዮጵያውያን ካደረጉት አኩሪ ትግል ጎን ለጎን በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ የለውጥ ኃይሎች ያካሄዱት የውስጠ ድርጅት ትግልም ትልቅ ጽናትን የጠየቀና ብዙም ዋጋ የተከፈለበት በመሆኑ በታሪክ ትልቅ ሥፍራን የሚይዝ ነው።
መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ስብሰባ የዶ/ር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት መጽደቅን ተከትሎ ወደ ተግባር የገባው የለውጥ አመራር በጊዜ የለኝም መርህ የሕዝባችንን የዘመናት ጥያቄ ወደ መመለስ የገባው ወዲያውኑ ነበር።
በዚህም በመላ አገሪቱ በገፍ ታስረው የነበሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ከእስር እንዲፈቱ ተደርገዋል። አስከሬናቸው ካልሆነ እነሱማ በሕይወት ይህችን አገር አይረግጧትም የተባሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ድርጅቶች በሰላማዊ መንገድ አገራቸው ገብተው እንዲታገሉ እድል ተሰጥቷቸው ወደ አገር ቤት ገብተዋል ። በርካታ መገናኛ ብዙኃን ከአፈና ተላቀው በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ነፃነትን ከመጎናፀፋቸውም በላይ የበርካታ ብሎገሮችን እገዳ በማንሳት ነፃነታቸውን እንዲጎናጸፉ ተደርጓል።
በዝርፊያና በተሳሳተ አመራር በከፍተኛ የብድር ጫና አደጋ ውስጥ የነበረውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ትክክለኛ መስመር ለመመለስ ሪፎርም ተደርጓል ። በዚህም አደጋ ውስጥ ገብተው የነበሩ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶችን መታደግና ወደ ትክክለኛ መስመር መመለስ ተችሏል ። በከፍተኛ ደረጃ ኢ-ፍትሃዊነት የታየበትን የአገሪቱን መከላከያ ኃይል በሪፎርም ትግበራ ኢትዮጵያን የሚመስል ተቋምም ማድረግ ተችሏል ። በሴራና በተንኮል ተዳክሞ የነበረውን አገራዊ አንድነት በማጠናከርም ረገድ በለውጡ ዘመን ረጅም ርቀት መጓዝ ተችሏል ።
በለውጡ ዘመን እነዚህን መሰል ተስፋ ሰጪና አገርን ከአደጋ የታደጉ ለውጦች ቢመዘገቡም በተለይም በህወሓት ጁንታና በሌሎች የውጭና የውስጥ የጥፋት ኃይሎች ትስስር የተከሰቱ ተግዳሮቶችም እጅግ ብዙ ናቸው። እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በለኮሱት እሳት ሰላማዊ ኢትዮጵያውያን ያለምንም ጥፋታቸው ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ተገድለዋል፤ ቆስለዋል ሃብትና ንብረታቸውም ወድሟል።
ከጅምሩ ለውጡ በብዙ ተግዳሮቶች እንደሚፈተን በመታመኑ ተግዳሮቶችን እያለፉና መፍትሔ እየሰጡ መጓዝን ግድ ብሏል ። ይሁንና በመጋቢት ፍሬዎች እየተጠናከረ የመጣው ኢትዮጵያዊ አንድነት፤ በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ልማትና ዕድገት እያበረከቱ ካለው አበረታች ድጋፍ እንዲሁም የተከፈለው ዋጋ ተከፍሎ የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን ይሆናል ከሚለው የለውጥ አመራር ጽናት የተነሳ ተግዳሮቶች ታልፈው የመጋቢት ፍሬዎች ተስፋና ራዕይ እውን እንደሚሆን አይጠራጠርም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013