ኢትዮጵያ 4ኛውን ሀገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከመጋቢት 29 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ ታካሂዳለች፡፡ ቆጠራው መንግሥት የአገሪቱን ህዝብ ቁጥር በአግባቡ ተገንዝቦ ለሚያዘጋጀው እቅድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ምሁራን ይገልጻሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ ቆጠራ ለአንድ አገር ልማት እና እድገት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይጠቅሳሉ፡፡ የመንግሥትን አገልግሎት ወደህዝቡ ለማድረስ ብሎም በህብረተሰቡ ዘንድ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ በጀት ለመመደብና ልማትን ለማምጣት ሀገሪቱ ያላትን የህዝብ ቁጥር ማወቅ ሊዘለል የማይችል ተግባር ነው። መንግሥት የህዝቡን ቁጥር ካላወቀ ከየት ተነስቶ ወደየት እንደሚደርስ፣ ለየትኛው ህብረተሰብ ምን አይነት አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ለማወቅ እንደሚቸገርም ያብራራሉ፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ጣሰው ማብራሪያ፤ አገሪቱ እ.አ.አ በ2025 ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ መሰለፍን እንዲሁም ድህነትን ለመቀነስና የትምህርት ተደራሽነቱን ለማስፋት የያዘቻቸውን ራእዮች ለማሳካት እየሠራች ትገኛለች፡፡ በልማት ወደኋላ የቀሩ ክልሎችም ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ እየሠራችም ነው፡፡
እነዚህን እቅዶች ለማሳካትና ሥራው በምን አይነት ሁኔታ እየሄደ ነው የሚለውን ለመከታተል የግድ የህዝቡን ቁጥር ማወቅ ያስፈልጋል ሲሉ ፕሮፌሰር ጣሰው ያመለክታሉ፡፡ ቆጠራው ከተካሄደ ከአስር ዓመት በላይ እንደሆነው፣ እስካሁንም እየተሠራ ያለው በግምት መሆኑንና ግምት ደግሞ ስህተቶች ውስጥ ሊከት እንደሚችል ያስገነዝባሉ፡፡ ቆጠራው የመንግሥት እቅዶችን ለመገምገምና የት እንደደረሱ ለማወቅም በጣም እንደሚጠቅም በመጠቆም፡፡
«ተደራሽነትን ለመለካት የህዝብ ብዛት መጠን በትክክል መታወቅ ይኖርበታል›› የሚሉት ፕሮፌሰር ጣሰው፣ ‹‹አሁን ግን የህዝቡን ቁጥር ካለማወቅ የተነሳ አንዳንድ የስታትስቲክስ መረጃዎች እየተፋለሱ ይገኛሉ፡፡ የህዝብ ቁጥር በትክክል ባለመታወቁ ነጠላ የትምህርት፣ የውሃ፣ የጤና ተደራሽነትና የመሳሰሉት ስታትስቲክሶች እየተበላሹ መጥተዋል ሲሉም አክለው ያስረዳሉ፡፡ የትምህርት ቅበላን ለአብነት በመውሰድም፣ ቅበላው ከመቶ በመቶ በላይ ሄዷል እየተባለ እንደሚገለጽ ይናገራሉ፡፡ ይህም የህዝብ ቁጥሩ በትክክል አለመለካቱን እንደሚያሳይ ነው የሚያስረዱት፡፡
እንደ እርሳቸው አነጋገር፤ የመንግሥትን አፈጻጸም ለመለካት እንዲሁም እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት ለማወቅ መስተካከል ያለበትንም ለማስተካከል የህዝቡ ቁጥር መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ልማት ወደ ድሃውም ሆነ ሀብታም መዝለቅ እንደሚኖርበት፣ ለሴት፣ ለወንድ፣ ለወጣት፣ ለህፃናት እንዲሁም ለአዛውንት ማድረግ የሚገባውን ለማከናወን የህዝብ ብዛቱን በአግባቡ ማወቅ ለመንግሥት ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ቆጠራው በአግባቡ ከተካሄደ በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎችም ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት አቅምና እቅድ ይኖረዋል፡፡
የህዝቡን ቁጥር በትክክል አለማወቅ በርካታ ቅሬታዎች እንዲነሱ እንደሚያደርግ አመልክተው፣ ለጭቅጭቅና ለስህተት እንደሚዳርግ በመጥቀስ፣ የተጣጣመ ሥራ ለመሥራት የህዝቡ ቁጥር በትክክል ሊታወቅ ይገባል ይላሉ፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት የምርምርና አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዶክተር ኤባ ሚገና፤ አገር እንደ አገር ለመቀጠል እንዲሁም ለዕቅድ ቆጠራ ወሳኝ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ መንግሥት የህዝብ ብዛትን ካላወቀ ለአገሪቱ የሚያስፈልገው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ሌሎች ልማታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማካሄድ እንደሚ ቸገርም ያስረዳሉ፡፡
የአንድ አገርን ህዝብ ይቅርና በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ያሉትን ሠራተኞች ቁጥር ማወቅ አስፈላጊውን መገልገያ ለማቅረብም ሆነ ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን የግድ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
መንግሥት እቅዱን ከማውረዱ በፊት ምን ያህል ህዝብ በየትኛው የእድሜ ክልልና የት አካባቢ ይገኛል የሚለውን መረዳት አለበት ያሉት አቶ ኤባ፣ ቆጠራው ፖሊሲና ስትራቴጂም ለማውጣት ወሳኝ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ አገሪቱ ምን አይነት ማህበራዊ መዋቅር ቢኖራት ነው መለወጥ የምትችለው? የሚለውን ለመመለስም የቆጠራ ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
የአርሲ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር እንዳለው ፉፋ የህዝብን ቁጥር ለማወቅ መነሳት ማለት ህዝብን በተገቢው መንገድ ለማገልገል ማሰብ ነው ይላሉ፡፡ በተለይ ማህበራዊ ጉዳይ የሆኑትን እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ መንገድና መሰል አገልግሎትን ለማቅረብ እንዲሁም መሰረተ ልማቱን ለማሟላት እንደሚጠቅም ይገልጻሉ፡፡
‹‹ቆጠራው የሚካሄደው የእገሌ ብሄር ህዝብ ብዛት ከእገሌ ብሄር ይበልጣል፤ አሊያም ያንሳል ለማለት ሳይሆን፣ መንግሥት ግልጽነትን በተላበሰ መልኩ ህዝብን በእቅድ እንዲያገለግል ነው›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡
እንደ ዓለም አቀፍ ማሰብና እንደ አገር ደግሞ መሥራት ዋናው ጉዳይ መሆኑንም በመጥቀስ፣ አገሪቱ እንደ ህዝቧ ብዛት አገልግሎት መስጠት ያስችላት ዘንድ የህዝብ ቁጥሩን ማወቅ ያሻታል ይላሉ፡፡ ቆጠራው ሊፈታቸው የሚችሉ ችግሮች እንዳሉ ማሰብ እንደሚገባም ይገልጻሉ፡፡
ፕሮፌሰር ጣሰው፤ ቆጠራው በቴክኖሎጂ መደገፉ ብዙ ጊዜ የሚፈጀውን አሰራር በአጭር ጊዜ ለማከናወን እንደሚያስችል ጠቅሰው፣ ከወረቀት ወደ ኮምፒውተር መሸጋገሩም የሚፈጠረውን ስህተት ለማስቀረት ይረዳል ይላሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ መረጃ ሰብሳቢው መረጃ በሚሰበስብበት ወቅት የሚያስገባው ቁጥር ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስም፣ ትክከለኛ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን እንደሚጠ በቅም ያስገነዝባሉ፡፡
ዶክተር ኤባ ቆጠራው በቴክኖሎጂ መደገፉ ተዓማኒነትና ፍጥነት እንዲኖረው እንደሚያግዝ በመግለጽ የፕሮፌሰር ጣሰውን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ እርሳቸውም መረጃውን በመስክ ሆነው የሚሰበስቡ ሰዎች እውቀትም ወሳኝ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ መረጃ መሰብሰብ ትዕግስት እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ መረጃ ሰብሳቢዎቹ ግድየለሽ መሆን እንደሌለባቸው እና ቁርጠኛ ሆነው መሰብሰብ እንደሚኖርባቸው ያሳስባሉ፡፡
ዶከተር ኤባ አክለውም መረጃ ሰጪዎችም ትክክለኛውን መረጃ ለመስጠት ይችሉ ዘንድ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ እድሜንም ሆነ የቤተሰብ ቁጥርን ጨምሮም ሆነ ቀንሶ መናገሩ ለመረጃው ተዓማኒነት አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳደር መሆኑም ከግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ የሁለት ዓመት ልጅን የአምስት ወር ህጻን ነው ብለው ቢያስመዘግቡ ጉዳቱ የሀገር ነው በማለትም ምሳሌ ጠቅሰው ያብራራሉ፡፡ ምክንያቱም በየትኛው የእድሜ እርከን ላይ ምን ያህል ሰው አለ የሚለውን ለመረዳትና በዛ የእድሜ ክልል የሚያስፈልገውን በማቅረብ እንዲሁም በማቀድ ስራ ላይ እንቅፋት እንደሚሆን በመግለጽ፡፡
በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 103 ንኡስ አንቀጽ5 ላይ የህዝብና ቤት ቆጠራ በየአስር ዓመቱ እንደሚካሄድ ተደንግጓል፡፡ በዚሁ መሰረት በህዳር ወር 2010 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ቆጠራ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት ሳቢያ ከአንዴም ሁለቴ መራዘሙ ይታወሳል፡፡
የህዝብና ቤቶች ቆጠራው ወቅታዊ እና ሊከናወን የሚገባው ነው፡፡ መንግሥት ቆጠራውን በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ ለማካሄድ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ቆጠራውን ለሚያካሂዱ ባለሙያዎችም ሥልጠናዎች እየተሰጡ ናቸው፡፡ ሥልጠናውም ባለሙያዎችን ጨምሮ ለኅብረተሰቡ ጭምር በስፋት መሰጠት ይኖርበታል፡፡ በመረጃዎቹ አስፈላጊነትና በቴክኖሎጂው ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ሊሸሸጉ የሚችሉ መረጃዎች እንዳይኖሩ እንዲሁም የተጋነኑ መረጃዎችን ማስወገድ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011
በአስቴር ኤልያስ