በጋዜጣው ሪፖርተር
ወተትን የማያውቅ ሰው የለም፡፡ ሁላችንም ጡት መጥባት ከጀመርንበት ቀን ጀምሮ ስለወተት እናውቃለን። መላው የአጥቢ እንስሳት ዘር ከአይጥ እስከ ትልቁ ዝሆን ድረስ ሁሉም እናቶች ለልጆቻቸው ዕድገት እንዲጠቅም በተፈጥሮ የተሰጠን ጸጋ ነው፡፡
ወተት ለሕፃናት ዕድገትና ጤንነት የሚበጅ ምርጥና የተመጣጠነ የምግብ ይዘት አለው፡፡ በአጭሩ ለዕድገት መሠረታዊ የሆኑ አሚኖአሲዶችን የያዘ 3.5 በመቶ ፕሮቲን አለው፡፡ ለኃይል ተፈላጊ የሆኑ ቅቤ 4 በመቶ እና ላክቶስ የሚባል ስኳር 4.8 በመቶ ሲኖረው ለአጠቃላይ ጤና ተፈላጊ ንጥረ ነገሮች (ሚኒራሎች) እና ቫይታሚኖች ወተት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ወተትን በግብዓት በመጠቀም ቅቤ፣ አይብ እርጎና የመሳሰሉ ጠቃሚ የወተት ተዋጽዖ ዓይነቶች በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ ተመርተው ለሰው ልጅ ጥቅም ይውላሉ፡፡
የአገራችን የወተት ሀብት በአመዛኙ የሚመረተው በግለሰብ ገበሬዎች ነው፡፡ የሚበዛው ወተትም ለአምራች ቤተሰብ ጥቅም የሚውል ሲሆን የሚተርፈው ብቻ ወደ ገበያ ይወጣል፡፡ ስለዚህም ከቤተሰብ ፍላጎት በላይ ሆኖ የሚሸጠው ወተትና የወተት ተዋጽዖ መጠን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡
ወተት ለአገር ከፍተኛ የኢኮኖሚ አስተዋጽዖ ሊያደርግ የሚችል የግብርና ዘርፍ መሆኑን ተገንዝበን ተገቢውን ትኩረት መስጠት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ አንዱ መንገድ ነው፡፡ የወተት ሀብታችን በዘመናዊና አጥጋቢ መልክ እንዲጓዝ መሠረታዊ ለውጥ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ አስተማማኝና ዘላቂ በሆነ መንገድ ዘርፉን ማሻሻል አገራዊ ጥቅሙ የጎላና የሚገኘው ጥቅምም ግዙፍ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ ይሁን እንጂ ዘርፉ የተወሳሰቡ ችግሮች እንዳሉበት ይታመናል፡፡ ስለሆነም መጀመሪያ የዘርፉን ዋና ዋና ችግሮች ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች አጥንቶ የመፍትሄ ጎዳናውን በጋራ ከመቀየስ ሌላ አማራጭ የለም፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የቀንድ ከብት ሀብት አላት፡፡ በአፍሪካ በአንደኛ ደረጃ ትገኛለች፡፡ ይሁን እንጂ የሚመረተው የወተት መጠን ከላሞች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ላሞች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ይገመታል፡፡ ታዲያ በአገራችን አንድ ላም (በመጀመሪያው ስድስት ወራት) የምትታለበው ወተት መጠን በአማካይ በቀን 1.54 ሊትር ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም በአገሪቱ በጠቅላላ የሚመረተው የወተት መጠን በዓመት 3.2 ቢሊዮን ሊትር ነው፡፡ ይህ ዝቀተኛ የወተት ምርታማነት ከተጠቃሚው ኅብረተሰብ ፍላጎት ጋር ሲታይ ብዙ ሥራ መስራትን ይጠይቃል፡፡
ወተት በሚፈለገው መጠንና በጥራት እንዲመረትና ለተጠቃሚው እንዲቀርብ ማድረግ ለኢኮኖሚ ዕድገትና የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያውያን የምንጠጣው የወተት መጠን ከሌሎች አገሮች ጋር ሲወዳደር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ የተሻለ የወተት ምርት የሚገኘውም የግጦሽ ሣር እንደልብ በሚሆንበት በክረምት ወራት ነው፡፡ በአጠቃላይ የወተት ተጠቃሚነታችን በማንኛውም መመዘኛ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ አንድ ታዳጊ ወጣት በቀን እስከ አንድ ሊትር ወተት ሊጠጣ እንደሚገባው በመስኩ ያሉ የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ፡፡ ሆኖም ግን 50 በመቶ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ሕፃናት የቀነጨሩ መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ አንዱ ምክንያትም ሕፃናት በፈጣን ዕድገት ዘመናቸው በቂ ወተት አለማግኘታቸው ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ የወተት አቅርቦት በአብዛኛው በገጠር ገበሬዎች የሚመረት ሲሆን በዘመናዊ ዘዴ የሚመረተው በጣም ትንሽ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ የሚፈለገው የወተት መጠንና አቅርቦት አይመጣጠንም፡፡ ስለዚህም በወተት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ የአገራችን አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር በተለይም በከተማ ነዋሪው ሕዝብ በፍጥነት እየጨመረ በመሄዱ የወተት ምርትና አቅርቦት ከባህላዊው መንገድ ወደ ዘመናዊነት እንዲጓዝ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በየሱፐር ማርኬቱ ተደርድሮ የሚታየው የዱቄት ወተት መጠን በየጊዜው በመጨመር ላይ ነው፡፡ ይህ በውጭ ምንዛሬ ተገዝቶ የሚገባ ምርት የሕዝቦችን የወተት ፍላጎት ለማሟላት አለመቻላችንን ይጠቁማል፡፡
የወተት ምርትን ስናሳድግ ከጥራትና ለጤና ተስማሚነት ጋር አብሮ ማየት ይገባል፡፡ ከጤነኛ ላም የሚታለብ ወተት በጥራቱ አስተማማኝና ከችግር ፈጣሪ ጥቃቅን ህዋሳት ነፃ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ወተት በሚታለብበት ጊዜ፤ በማለቢያና በማቆያ (ማስቀመጫ) ዕቃዎች ጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ በወተት አመራረትና ለገበያ በማቅረብ ዙሪያ በሚከሰቱ የጽዳት ጉድለቶች ምክንያት በተጠቃሚው ኅብረተሰብ ላይ የሚያስከትለው የጤና ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህም በመነሳት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምግብ ትምህርት ማዕከል ‹‹ኢንሹር›› የሚባል ፕሮጀክት በወተት ጥራት ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በቢል ጌትስ የገንዘብ ድጋፍ፤ ሙያና ልምድ ባላቸው ተመራማሪዎችና ድህረ ምረቃ ተማሪዎች ተሳትፎ በመካሄድ ላይ ሲሆን የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ወተት ከታለበ (ከተመረተ) ጀምሮ ለተጠቃሚዎች እስከሚደርስ ድረስ ስለሚከሰቱ የጥራት ችግሮች በተለይም የጤና ቀውስ ሊያመጡ ስለሚችሉ ጥቃቅን ሕዋሳትና ኬሚካሎች በዝርዝር ማጥናት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የጥናቱን ውጤቶች መሠረት በማድረግ ከወተት ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በመፍጠር ጥራቱን የጠበቀ ወተት ለተጠቃሚው ይደረስ ዘንድ ለሚደረገው የጋራ ጉዞ መሠረት መጣልን ዓላማው ያደረገ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢንሹር ፕሮጀክት ዶክተር ዳዊት አባተ ነግረውናል፡፡
ዶክተር ዳዊት እንዳሉት፤ የፕሮጀክቱ ተግባራት በመላው ሀገሪቱ ገበሬዎች፤ ከወተት ሻጭና ከዘመናዊ የወተት አምራቾች ጋር በቅርብ የመስክ ጥናት በማካሄድ ተፈላጊ የመስክ መረጃ ያሰባስባል፡፡ የወተትና የወተት ተዋጽኦ ናሙናዎች ከየክልሉ በማሰባሰብ በዘመናዊ መንገድ በተደራጀ ላቦራቶሪ ከጤና ጠንቅ ህዋሳት ዓይነት ብዛትና ስርጭት ለማወቅ ይሰራል፡፡ የተገኙትን ዋና ዋና ውጤቶች ለሚመለከተው ሁሉ በየመድረኩ በማቅረብና በማሳተም ያሳውቃል፡፡ ከዚህም በላይ ከጎጂ ህዋሳትና ኬሚካሎች ነፃ የሆነ የወተት ምርት ለተጠቃሚው እንዲደርስ ለማገዝ የሚረዱ ሥልጠናዎች በመስጠት ላይ ነው፡፡
ወተት አምራቾች ወተትን ከማለብ ጀምሮ ለተጠቃሚው እስኪደርስ ያሉትን የጥንቃቄ እና ተገቢውን የንጽህና እርምጃ በተግባር ማዋል ለወተት ጥራት ወሳኝ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ዳዊት፤ የጤና ጠንቅ የሆኑ ሕዋሳትን ለመከላከልና የወተት ጥራትን ለማሻሻል የሚረዱ ሥልጠናዎች በተለይም ለሴት ገበሬዎች ይሰጣል። የወተት ጥራት መጓደል ከንጽህና ጉደለት ብቻ ሳይሆን ከመኖ ጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ጥራቱን ያልጠበቀ መኖ የሚመገቡ ላሞች ለጤና ጎጂ የሆኑ እንደ አፍላቶክሲንና የጸረ-ተባይ ኬሚካሎች ሊበከል ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ ወተት አምራቾች/ሻጮች ሆን ብለው የሚጨምሯቸው አላስፈላጊ የሆኑ ጎጂ ነገሮች አልፎ አልፎ በወተት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከእንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ሁሉም እንዲቆጠብ ማስቻል ለወተት ጥራት የጎላ አስተዋጽዖ ይኖረዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ፕሮጄክቱ ከጥናትና ምርምር ውጤቱ በመነሳት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀራረብ ምክክር መድረክ በማዘጋጀት እንቅስቃሴ ጀምሯል። ዋናው ጉዳይ የወተት ጥራት ደረጃ መሥራትና መቆጣጠር የሚቻልበትን መንገድ በመመካከርና ለመወሰን የሚቻልበትን መንገድ መሻት ነው፡፡ ወተት የማምረትና የመሸጥ ገበያ ሰንሰለት ለጥራት ቁጥጥርና ክትትል አዳጋች እንደሚያደርገው ግልጽ ቢሆንም ደረጃ በደረጃ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡
የወተትን ጥራት ለማሻሻልና ዘላቂ ለማድረግ አሁን ካለበት አመራረትና አቅርቦት በመለወጥ ዘርፉን ማዘመን ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ዳዊት፤ ይሁን እንጂ ከወተት አምራች እስከ ተጠቃሚ ያለው ሰንሰለት ግልጽና አንድ ዓይነት ባለመሆኑ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በዚህ ላይ የወተት ዋጋ በየጊዜው በማሻቀቡ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ገንዘብ አቅምን የሚፈታተን ሆኗል፡፡ ስለዚህም የወተት ምርታማነትን ማሻሻል ጥቅሙ ዘርፈብዙ ነው፡፡ የወተትን አመራረትና ስርጭት ወደ ዘመናዊ መንገድ ለመለወጥ የግል ባለሀብቶችን ጠንካራ ተሳትፎ ስለሚጠይቅ መንግሥት ሁኔታዎችን ሊያመቻች እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡
የወተት ላሞችን በብዛትና በጥራት ለማራባት በቂና ተስማሚ ቦታ ያስፈልጋል፡፡ የወተት ሀብት ልማት ዞን (ቦታ) በመለየት ለላሞች ማራቢያ፤ ለመኖ ማምረቻ እንዲሁም የወተት ማምረቻ (ፋብሪካ) የሚያጠቃልል ተስማሚ ቦታ ማመቻቸት ይጠይቃል፡፡ የተሻሻሉ (የተዳቀሉ) ምርጥ የወተት ላሞችና ጥራቱን የጠበቀ የእንስሳት መኖ ዝግጅትና አቅርቦት ሊዳበር ይገባል፡፡ የወተት ላሞችን ጤንነት ለመጠበቅ የመድኃኒትና የክትባት መርሀ ግብሮች ተጠናክረው መገኘት አለባቸው፡፡ ይህ ሁሉ ሲፈጸም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የአመራረት መንገድ ስለሚመቻች ጥራቱን የጠበቀ ወተትና የወተት ተዋጽዖ በብቃት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ዶክተር ዳዊት እንዳሉት፤ ይህ ጉዳይ በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በወተት ሀብት ባለሙያዎችና በመስኩ የተሰማሩ ባለሀብቶችና የባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡ ስለወተት ጉዳይ ያገባኛል ይመለከተኛል የሚል ግለሰብ፤ ድርጅትና የመንግሥት መሥሪያ ቤት፤ ወተት አምራቾች ፤ ወተት አቅራቢ ማህበራት መላው የወተት ተጠቃሚ ኅብረተሰብ ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡
ስለዚህም ለውጥ ለማምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካላትን ፍላጎት ማሟላት የለውጥ ሂደቱን ስኬታማ ያደርገዋል፡፡ ለዚህም አንዱ ባለድርሻ አካል የሌላውን ችግርና ፍላጎት ጠንቅቆ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚህም በመነሳት ለሁሉም የሚበጅና የሚመች መመሪያ ወይም ፖሊሲ ለመቅረጽ መሠረት ይጥላል፡፡ አማራጭ የፖሊሲ ሀሳቦችን በመመርመር የወተት ጥራት ደረጃ በማውጣት ማስፈጸም ያስችላል፡፡
ፖሊሲዎች በጥናት በተገኙ ሣይንሳዊ ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ሲወጡ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ግልጽ ይሆናል፡፡ ከዚህም በላይ የሚወጡ መመሪያዎች በማስፈጸም ሂደት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በቅድሚያ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን ለወተት ሀብት ዘርፍ ድጋፍ ሰጪ በተለይም የጥራት ደረጃን የሚያረጋግጡ ተቋማት እንዲጠናከሩ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን አለበት ሲሉ የመፍትሄ ሀሳብ ይጠቁማሉ፡፡
የኢትዮጵያን የወተት ምርት፤ ጥራትና አቅርቦት ዘመናዊ ለማድረግ ዘርፉ ትክክለኛና አስተማማኝ መንገድ ሊይዝ ይገባል፡፡ ለዚህም ዓላማ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጠንካራ ተሳትፎና የመንግሥትን ልዩ ትኩረት ይሻል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2013