ፍሬህይወት አወቀ
ለሰው ልጅ አዕምሯዊና አካላዊ ዕድገት ወሳኝ ከሆኑት የምግብ አይነቶች መካከል አንዱ ፕሮቲን ነው፡፡ ፕሮቲን በተለይም በህፃናት ዕድገት ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የህፃናት መቀንጨር የሚስተዋል ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ መቀንጨር ማለት አካላዊ መክሳትና መቀጨጭ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ ዕድገትን በመቀነስ ትምህርት የመቀበል አቅምን ጭምር የሚጎዳ ነው፡፡
መቀንጨርን ለመከላከል ህጻናት በፕሮቲን የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ ፡፡ ይሁንና በፕሮቲን ከበለጸጉ ምግቦች መካካል በጣም ርካሽ ዋጋ አለው የሚባለው ዕንቁላልን በሀገሪቱ ምን ያህል ህጻናቶች ያገኛሉ፤ አሁን ያለው የዶሮና የዕንቁላል ዋጋስ ወዴት እየሄደ ነው፤ በቀጣይስ ዘርፉ ምን ተስፋና ስጋት አለው? የሚሉ ጥያቄዎችን ይዘን በዶሮ እርባታ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎች ማህበር ፕሬዚዳንትና የሀዋሳ ዶሮ እርባታ ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገነነ ተስፋዬን አነጋግረናቸዋል፡፡
አቶ ገነነ ይኖሩበት ከነበረበት ባህር ማዶ ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ በውጭው ዓለም በተለያየ መልኩ በየጊዜው ለምግብነት የሚቀርበው ዶሮ በሀገራቸው ማግኘት አልቻሉም፡፡ ይህን ክፍተት በመረዳት ወደ ኢንቨስትመንቱ ገብተው ላለፉት ሰባት ዓመታት የመንግስት የነበረውን የሀዋሳ ዶሮ እርባታ ማዕከልን አስፋፍተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ከእንስሳት ሀብት የዶሮ እርባታ ብቻውን ከማንኛውም ዘርፍ በበለጠ የስራ ዕድል መፍጠር የሚችል መሆኑን ይናገራሉ። ሰንሰለቱ የረዘመ እና ሰፊ የሰው ሀይል ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን በልኩ አልተሰራበትም፡፡ ኢንቨስትመንቱ ትኩረት የተነፈገው በመሆኑ ውጤታማ መሆን አልተቻለም፡፡ ለዚህም ነው ዶሮ ብርቅ ሆኖ የሚታየው፡፡ ዶሮ ብርቅ በሆነበት ሀገር ላይ ደግሞ እንቁላል ማግኘት የማይታሰብ መሆኑን ይጠቅሳሉ ፡፡
በሀገሪቱ ባለፉት ስድስት ዓመታት 22 የሚደርሱ የዶሮ ማባዣ ማዕከላት የነበሩ መሆኑን ያነሱት አቶ ገነነ፤ እነዚህ ማዕከላትም ከውጭ ሀገር የተሻሻሉ ወይም ምርጥ ዘር የሚባለውን የዶሮ ጫጩት በማምጣት እነዛን ጫጩት አባዝተው ለአርሶአደሩና ለወጣቶች ያስረክባሉ፡፡ አርሶ አደሩና ወጣቱም ለ45 ቀን አቆይቶ ስጋና እንቁላል ለሚያመርቱ ያቀብላሉ፡፡ እነዚህ የማባዣ ማዕከላት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ማነቆዎች ምክንያት እያደጉ መሄድ ሲገባቸው ቁልቁል በመውረድ አሁን ላይ ስድስት ብቻ ቀርተዋል፡፡ ፍላጎት እየጨመረ ባለበት በዚህ ጊዜ የማባዣ ማእከላቱ ቁጥር ማነስ በዘርፉ አሁን እየታየ ያለውን የዶሮና የእንቁላል እጥረት ከማስከተሉም በላይ በቀጣይ ችግሩ የከፋ እንዳይሆን ያላቸውን ስጋት አመላክተዋል፡፡
ዘርፉ በራሱ ማደግ የሚችልና በጣም ውስን ድጋፎችን የሚፈልግ እንደመሆኑ መንግስት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሰፊ የስራ አጥነት ችግር ባለበት ሀገር በርካታ ወጣቶችን መያዝና የስራ ዕድል መፍጠር የሚችል ዘርፍ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ዶሮ በምግብ ዋስትና ጠቀሜታው የጎላ ድርሻ አለው፡፡ ነገር ግን የሚጠይቀውን ጥቂት የውጭ ምንዛሪ፣ የተወሰነ የመሬትና የብድር አቅርቦት ማግኘት አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ማባዣ ማእከላት እየተዘጉ መሆኑነ ይናገራሉ ፡፡
የዶሮ እርባታ በጥቂት ወጪ ብዙ ማትረፍ የሚቻልበት ዘርፍ ነው፤ ሆኖም ግን አልተሰራበትም የሚሉት አቶ ገነነ፤ በጥቂት የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ጫጩቶች አስመጥቶ ማባዛት ካልተቻለ እንቁላል በውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት አስገዳጅ እንደሚሆን ይናገራሉ። ነገር ግን እንቁላልና የዶሮ ስጋ ከውጭ ለማስገባት ከሚጠይቀው የውጭ ምንዛሪ ባነሰ ወጪ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ጥቂት ጫጩቶች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ማግኘት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
አንደኛ የዶሮ ስጋ ወደ ሀገር ውስጥ ከማምጣት ይልቅ ጥቂት ጫጩቶችን በማስገባት ወጪ መቀነስ ፤ ሁለተኛ ቴክኖሎጂውን በማምጣት ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር ይቻላል፡፡ እንዲሁም በሀገር ውስጥ አባዝቶ ለገበያ ማቅረብ ምርቱን በትኩሱ ለመጠቀም የሚረዳ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከውጭ ሀገር እየገባ ለገበያ የሚቀርበው የዶሮ ስጋ ምን ያህል ጥራቱ የተጠበቀ ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የሌለን እንደሆነም አቶ ገነነ አንስተዋል፡፡
ይሁንና ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ መንገድ የእንቁላል ዋጋ የመወደዱ ምክንያት ዓለም አቀፍ የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ታድያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት መንገድና ሆቴሎችን በመዝጋቱ ትዕዛዝ የነበራቸው በመሰረዛቸው ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ጫጩቶችና ሶስት ሺህ ኪሎግራም የዶሮ ሥጋ ለማስወገድ ተገደድን፤ በዚህም ከፍተኛ ኪሳራ ደረሰ፡፡ ይህ የሆነው ረዘም ላለ ጊዜ አቀዝቅዞ ማቆየት የሚያስችል በቂ ቦታ ባለመኖሩ ሲሆን በዚህም 123 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ማጋጠሙን አስታውሰዋል።
በዚህ ችግር ምክንያት እንቁላል የምትጥል ዶሮ በመጥፋቷ ዛሬ ላይ እንቁላል በሰባት ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ይሁንና ዘርፉ ይህን ችግር ተቋቁሞ በአዲስ መልክ ወደ ስራ ለመግባት እየተደረገ ያለው ጥረትም ሌላ መሰናክል ገጥሞታል የሚሉት አቶ ገነነ፤ ዘርፉ ማንሰራራት በጀመረበት በአሁን ወቅት የመኖ ዋጋ መቶ በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡ የዶሮ መኖ ከውጭ ከሚገባው በተጨማሪ ፋጉሎ፣ አኩሪ አተር፣ በቆሎና ሌሎችንም ከሀገር ውስጥ ይጠቀማሉ፡፡ ይሁንና 1800 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል የኑግ ፋጉሎ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 3400 ብር ገብቷል፡፡
‹‹በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ከውጭ በሚገባው መኖ ላይ ከዚህ ቀደም ያልነበረ ቫት እንዲጣልና መኖ መሆን የሚችሉ የአኩሪ አተር ተረፈ ምርትና የኑግ ፋጉሎ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ መንግስት መፍቀዱ ችግሩን አባብሶታል፡፡ ዘርፉ በእነዚህ ተደራራቢ ችግር ውስጥ ሆኖ በአሁን ወቅት አንድ እንቁላል ሰባት ብር ቢሸጥ እንቁላል አምራች ወጣቶች እየከሰሩ እንደሆነና በቀጣይ በዚህ ዋጋ ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡
ችግሩ በዚሁ ከቀጠለና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ነገሩን በጥልቀት ተረድተው ችግሩን መፍታት ካልቻለ እርሳቸውን ጨምሮ የቀሩት ስድስት የዶሮ ማባዣ ማዕከላትም ሊዘጉ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።
ለዶሮዎች መኖ ዋናውና መሰረታዊ ጥያቄ እንደመሆኑ በቂ ምርት ማምረት ሳንችል ወደ ውጭ ይላካል ብለው ላነሱት ጥያቄ ግብርና ሚኒስቴርና ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፍላጎታቸው የተለያየ በመሆኑ መልሳቸውም የተለያየ ነው ያሉት አቶ ገነነ፤ ነገር ግን አሁን ላይ የተፈጠረውን የመኖ አቅርቦት ችግር ለመፍታት እነዚህ አካላት ዘይት አምራቹን፣ ጥሬ ዕቃው የሚሸጥበትን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እና የዶሮ ማባዣ ማዕከላትን በጋራ ጠርቶ በማነጋገር ጉዳዩን በቅንነት መረዳት ከተቻለ ችግሩን መፍታት የሚቻል ነው ይላሉ፡፡
መንግስት በየትኛውም ዘርፍ ያለውን የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ ያለበት ስለመሆኑ ያነሱት አቶ ገነነ፤ የመንግስት ሥራ ፖሊሲና ስትራቴጂ ማውጣት በመሆኑ ሥራውን ለፈፃሚው አካል በመተው በነፃነት ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ከንግዱ ዘርፍ ወጥቶ ፋብሪካዎቹን ለግሉ ዘርፍ እየሰጠ ባለበት በዚህ ወቅት የግሉን ዘርፍ አሳታፊ ያላደረጉ በርካታ አሰራሮች አሉ፡፡ መንግስት ፈፃሚውን አካል ሳያማክር የሚተገብራቸው ሥራዎች በሙሉ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የሚያመዝን እንደሆነ ጠቁመው፤ አሁን ላይ የተፈጠረውን የመኖ እጥረት ለማቃለል ፈፃሚውን አካል ማማከር ተገቢ እንደሆነ ያስቀምጣሉ፡፡ ለአብነትም በቀጣዩ አስር ዓመት ሀገራዊ መሪ ዕቅድ ሲወጣ ባለድርሻ አካለቱን ሳያማክሩ ነው፡፡ ስዘሊህ በቀጣዩ ጊዜ የዶሮ እርባታ ዘርፍ ምን እንደሚጠበቅበት የሚታወቅ ነገር እንደሌለም አብራርተዋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ አዲስ አስተሳሰብ የመጣ ቢሆንም ያልተለወጡ አስፈፃሚዎችም አሉ፡፡ ይሁንና በግብርና ሚኒስቴር ያሉ ሰዎች ከዚህ ቀደም ከነበሩት አመራሮች የተሻሉ፣ ለመስራት ፍላጎት ያላቸውና በዘርፉ ዕውቀት ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ታች ያሉት አካላት ዛሬም ያልተለወጡና የግሉን ዘርፍ እንደ አጋር ከማየት ይልቅ እንደ ባላንጣ የሚቆጥሩ በመሆናቸው ዛሬም ድረስ ችግሮችን ለመሸከም መገደዳቸውን ይገልፃሉ።
ሌላው በኢንቨስትመንቱ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ኢትዮጵያ ውስጥ የአመጋገብ ባህላችን ያልዘመነ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዘርፉ አላደገም፡፡ ዛሬም ዶሮን በሽንኩርት ብቻ የምንመገብ ከመሆኑም በላይ ዶሮ የበዓል ምግብ ሆኖ ቀርቷል፡፡ የዶሮ አረባብ ዘዴውም ባህላዊ ነው፡፡ በመንግስት በኩል ደግሞ ከምግብ መደርደሪያ መጥፋት የሌለበት ዕንቁላል ላይ ተጨማሪ እሴት ታክሰ (ቫት) ጥሏል፡፡ ማህበረሰቡ ካለው ባህላዊ አስተሳሰብ በተጨማሪ መንግስት ዕንቁላል ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉ በራሱ አንድ ችግር ነው፡፡ ሌላው ዓለም ላይ እንቁላል መሰረታዊ የምግብ አይነት በመሆኑ የተጨማሪ እሴት ታክስ የለውም፡፡ እንዲያውም መንግስት ዶሮ አርቢውን የሚደጉምበት ሁኔታ መኖሩን ለአብነት ያነሱት አቶ ገነነ፤ እንደ ኢትዮጵያ የመቀንጨር ችግር ላለበት ሀገር ደግሞ አምራቾችን መደገፍ ቢቀር ተጨማሪ እሴት ታክስ ማንሳት ቢችል የተሻለ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
የዶሮ እርባታ ዘርፍ ከገባበት ቅርቃር ውስጥ መውጣት የሚችለው መንግስት ችግሩን ማድመጥና መረዳት ሲችል በመሆኑ፤ በቅድሚያ አሁን ስድስት የቀሩትን የዶሮ አርቢ ማዕከላት ከሥራ እንዳይወጡ በቂ ክትትልና ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡ ይህም ሲባል ዘርፉ የሚጠይቀው የውጭ ምንዛሪ ጥቂት ስለሆነ ከሌሎች ጋር ወረፋ ባይጠብቁ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ ላይ ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ከሚጠይቀው አካል ጋር ወረፋ ለመጠበቅ ይገደዳሉ፡፡
ዶሮ አርቢዎች በአማካኝ በዓመት ከሶስት እስከ አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ፤ ይህም ዶላር በአንድ ጊዜ የሚፈለግ ሳይሆን በተለያየ ጊዜ የሚወሰደው ነው፡፡ ይህ ዶላር በወቅቱ ተፈቅዶ ባለመወሰዱ የሚከሰቱ እጥረቶች አሉ፡፡ አንድ አርቢ በአንድ ወር ቢዘገይ ከማዕከሉ ተቀብሎ የሚያሳድገው ወጣትም በአንድ ወር ይዘገይበታል። ማዕከላቱ አንድና ሁለት ወራት ሊታገሱ ይችሉ ይሆናል ነገር ግን ተቀብለው የሚያረቡት ወጣቶች የቤት ኪራይና ለብድር ተቋማት ከፍለው መታገስ አይችሉምና ከዘርፉ የሚወጡበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት የዋጋ መናር ይከሰታል፡፡
አበዳሪ ተቋማትን በተመለከተም ከግልና ከንግድ ባንኮች ልማት ባንክ የተሻለ ነው፡፡ ይሁንና ልማት ባንክም የራሱ ችግር ያለው ሲሆን ለሁሉም ብድር አንድ አይነት ፖሊሲ አለው፡፡ ስለዚህ ለሁሉም አመቺ በሆነ መንገድ ቢዘጋጅ የተሻለ እንደሚሆን አቶ ገነነ አንስተው አሁን አሁን ግብርና ሚኒስቴር ለብሔራዊ ባንክ የድጋፍ ደብዳቤ በመጻፍ ችግሩን ለማቃለል ሞክሯል፡፡ ነገር ግን ደብዳቤ በመጻፍ ጊዜያዊ መፍትሔ ከመፍጠር እንደየዘርፉ ባህሪ ሁሉም በቅደም ተከተል የሚስተናገድበት መፍትሔ ማምጣቱ በኢንቨስትመንቱን ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ለንግድ የሚሆን ዶሮ ባለመኖሩ ችግሩን አግዝፎታል፡፡ የሀገር ውስጥ ዝርያ ዶሮ ለንግድ አይሆንም፤ ምክንያቱም በጣም ጥሩ የተባለች ኢትዮጵዊ ዶሮ ቢበዛ 60 እንቁላል የምትጥል ሲሆን፤ ከውጭ የሚመጡት ደግሞ ከ300 በላይ እንቁላል መጣል የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከውጭ የተሻሻለ ዝርያ በማምጣት ከሀገር ውስጥ ዝርያ ጋር አዳቅሎ ዘርፉን ማሻሻልና ዘለቄታዊ መፍትሔ መስጠት የሚቻል መሆኑን ይጠቅሳሉ። ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት በጋራ በመስራት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አመልክተው ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2013