ራስወርቅ ሙሉጌታ
ኪም ሰይፉ ትባላለች ትውልዷ በእስያዊቷ ሀገር ካምቦዲያ ነው። ገና የሁለት ዓመት ህፃን እያለች ነበር በሀገሪቱ ተከስቶ በነበረው ጦርነት ሰላማዊ አየር መተንፈስ ከናፈቃቸው ቤተሰቦቿ ጋር በመሆን ወደ ኒውዝላንድ ያቀናችው። ሦስት ወንድሞችና ሁለት እህቶች ያሏት ኪም የልጅነት ጊዜዋን በኒውዝላንድ ካሳለፈች በኋላ እ.ኤ.አ በሁለት ሺህ ሰባት ዓ.ም ከኒውዝላንድ ከአንድ ሀቢታት ፎር ሂውማኒቲ (Habitat for Humanity) ከተሰኘ አንድ ክርስቲያናዊ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመሆን መጠለያ የሌላቸውን ለማዳረስ ወደ ኢትዮጵያ ታቀናለች። ኢትዮጵያ ከመጣች በኋላም በጅማ አካባቢ ባሉ ገጠራማ መንደሮች ለሦስት ሳምንት የጭቃ ቤቶችን ስትገነባ ከቆየች በኋላ ቀልቧ ኢትዮጵያ እንድትቆይ የነገራት ቢሆንም የግድ ከቡድኑ ጋር መመለስ ስለነበረባት ወደ ሀገሯ ታቀናለች። ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ከመጣች ጊዜ ጀምሮ በርካታ የሚማርኩ ለእሷ ህይወት የሚመቹ ነገሮችን በማስተዋሏ አንድ ቀን እንደምትመለስ ለራሷ ቃል ገብታ ነበር። በዚህ ሀሳብ ውስጥ ሆና ምክንያት በመፈለግ ለሁለት ዓመት ከቆየች በኋላ የእንግዚዝኛ ቋንቋ መምህርት በመሆን ለማገልገል ለበጎ ፈቃደኝነት ተመዝግባ ዳግም ኢትዮጵያ በመምጣት በአዳማ ከተማ ሦስት ወራትን ታሳልፋለች። ከዛ በኋላ እጮኛዋን ማግኘት ስለነበረባት ተመልሳ ወደ ሀገሯ ኒውዝላንድ ለማቅናት አዲስ አበባ ስትገባ ከዓመታት በኋላ አዲስ የህይወት ምዕራፍ ያስጀመራት አጋጣሚ ይፈጠራል።
ከአዳማ ተነስታ አዲስ አበባ ገብታ የበረራዋ ቀን እስኪደርስ ለማረፍ ሆቴል ስታማትር ቦሌ መንገድ ኬ ዜድ የሚባል ሆቴል ታገኝና ወደዛው ጎራ ትላለች። እናም እዛ ደርሳ በወቅቱ ሻንጣ የሚያንቀሳቅስ ሠራተኛ ከመሰላት ወጣት የሆቴሉ አስተዳደር ጋር ትገናኛለች። አስተዳደሩ ለጊዜው ሠራተኞች ለጥቂት ጊዜ በሥራ ቦታቸው ባለመገኘታቸው ሻንጣዋን ይዞ በሊፍት ወደተያዘላት ማረፊያ ያቀናል። ኪም በሙሉ ሱፍ ተሽቀርቅሮ ሻንጣዋን የያዘላትን ወጣት በአትኩሮት በመመልከት በወስጧ ውበቱን ስታደንቅ ትቆይና ምንም የፍቅር ስሜት ባይሰማትም ለወጣቱ «በጣም ቆንጆ ነህ» ትለዋለች። ወጣቱ ግን ኮስተር ብሎ ምንም ምላሽ ሳይሰጣት አልጋ የያዘችበት ክፍል አድርሷት በቀላሉ አመሰግናለሁ ብሏት ይመለሳል። በነጋታው ግን ሊፍት ላይ ሲገናኙ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ወጣቱ ምን እንዳሰበ ባይገባትም የማታ መኮሳተሩን ቀይሮ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ የኢሜል አድራሻዋን ይጠይቃትና በዛው ይለያያሉ።
ከቀናት በኋላ ኒውዝላንድ እንደገባች ወጣቱ አጭር ግን ብዙ መልዕክቶችን የያዘች የኢሜይል መልዕክት ይልክላታል። እንዲህ ይል ነበር «ኪም በህይወቴ የማልማት አይነት ልጅ ነሽ፤ እወድሻለሁ፤ ጥሩ ጊዜም አሳልፈናል ሁሌም እጠብቀሻለሁ….» ኪም የተላከላትን መልዕክት ስታነብ እጅግ ትደነቃለች መክንያቱም እሷ ባደነቀችው ወቅት ምንም ያላላት ይብስ ብሎ የተኮሳተረባት ወጣት እንዲህ ተለውጦ ያላሰበችውን አስቦ መናገሩ ነበር። ያም ሆኖ የተፈጠረባትን መደነቅ በመደበቅ በጣም አመስግናው ነገር ግን ፍቅረኛ ስላለኝ ጥያቄህን መቀበል ይከብደኛል ስትል ምላሽ ትሰጠዋለች። ከዚህ በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ሳይገናኙ ከቆዩ በኋላ ኒውዝላንድ በመሬት መንቀጥቀት ስትመታ «እንዴት ሆንሽ፤ ቤተሰቦችሽ» የሚል ደብዳቤ ዳግም ከወጣቱ ይደርሳታል። ይህኛውም መልዕክት ለኪም ሁለተኛ ያላሰበችውን ግርምት የፈጠረባት ቢሆንም አሁንም በድጋሜ አመስግናው የመሬት መንቀጥቀጡ ግን እኛ ካለንበት በጣም ሩቅ የሆነና ሌላ ግዛት ውስጥ ነው ብላው ይለያያሉ።
በዚህ ሁኔታ ሁለት ዓመታት ካለፉ በኋላ ኪም በልቧ ሃሳብ መሰረት ሙሉ ለሙሉ ህይወቷን ኢትዮጵያ ለማድረግ አስባ ስለነበር ለሶስተኛ ጊዜ የዙምባ ዳንስ መመህርት በመሆን ወደ ኢትዮጵያ ትመጣለች። በዚህ ጊዜ ነበር ለሁለተኛ ጊዜ በማይታመን አጋጣሚ ከወጣቱ የሆቴል አስተዳዳሪ ጋር በድጋሜ በአካል ለመገናኘት የበቁት። አጋጣሚውም እንዲህ ነበር ጓደኛዋን ለማግኘት ቀጠሮ ይዛ ቦሌ አካባቢ ስትንቀሳቀስ ወጣቱ ያያትና ያናግራታል፤ በጣም ተገርማ ስታወራው ትቆያለች። ሁለተኛው አጋጣሚ ግን እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ አልነበረም። ስልክ ከተለዋወጡ በኋላ በሳምንቱ ተገናኝተው ሻይ ቡና ማለት ይጀምሩና መደበኛው ግንኙነት ወደ ፍቅር እያደገ መምጣት ይጀምራል።
ወጣቱ ዮናስ ታዬ ሰይፉ ይባላል ተወልዶ ያደገው ሰበታ መግቢያ በተለምዶ አረቄ ፋብሪካ ማዞሪያ በሚባለው አካባቢ ነው። አባቱ የኮንጎ ዘማች እንዲሁም በንጉሡ ዘመን የቦክስ ተወዳዳሪና በኋላ ደግሞ ሹፌር የነበሩ ናቸው። የቤት እመቤት የሆኑት እናቱ ዘጠኝ ልጆች የወለዱ ሲሆን አሁን አምስቱ በህይወት ይገኛሉ። ዮናስ በእንደዚህ አይነቱ ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ያደገ በመሆኑ ፍጹም ተግባቢ ተጫዋችና ቀልድ አዋቂም ነው። ዮናስ ጌቴ ሰማኔ በሚባል ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የጀመረ ሲሆን ቆይቶ ትምህርት ቤቱ ለሴቶች ብቻ ሲባል ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ይዛወራል። የተዛወረበት የትምህርት ቤት ግን ትምህርቱ የሚሰጥበት ቋንቋ እሱ አፉን በፈታበት አማርኛ ሳይሆን በኦሮምኛ በመሆኑ ወትሮም ጥሩ ውጤት ላልነበረውና ለትምህርቱ ትኩረት ለማይሰጠው ዮናስ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኖበት ውጤቱ በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆል ይጀምራል። እስከ አስረኛ ክፍል ድረስም በውጤቱ የሚበልጣቸው ልጆች ቢበዛ ሁለት ብቻ ነበሩ።
አስረኛ ክፍል ሲደርስ ግን ታሪኩን የሚቀይር አጋጣሚ ይፈጠራል። ከሌላ አካባቢ ሽጠው የመጡ ልጆች የሰፈር ጓደኛቸው ያደርጉትና ከልጆቹ ጋር መዋል ሲጀምር እነሱ ከቀን ጊዚያቸው የተወሰነውን በጥናት እንደሚያሳልፉ ይመለከታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አብረው ሲጫወቱ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ያላቸውን ህልምና የሚያደርጉትን ዝግጅት ሲመለከት እሱም ወደዛው እየተሳበ ይመጣና በህይወቱ ትልቁ መዳረሻ አድርጎት የነበረውን የሹፍርና ሞያ ወደ ጎን በመተው እሱም እንደ ጓደኞቹ ጎበዝ ተማሪ በመሆን ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ይወስናል። ነገር ግን ምንም የትምህርት መሰረት ያልነበረውና ከክፍል የመጨረሻዎቹን ደረጃዎች ሲያስተናግድ የኖረው ዮናስ ወደ ጉብዝና ለመሸጋገር የጀመረው የጥናት እንቅስቃሴ እንደ ተራራ እየከበደው ይመጣል። ይህም ሆኖ ከራሱ ጋር በመምከር በተለይ ጓደኞቹ «አላማህ መንጃ ፈቃድ ማወጣት ቢሆንም ትምህርቱ ለሁሉም መሰረት ይሆናል» ብለው ስላሳመኑት በትጋት ማጥናቱን ይያያዘዋል። ቤተሰቦቹና የቀድሞ ጓደኞቹ ግን የትም ላትደርስ አትልፋ እያሉ ያሾፉበት ነበር።
እሱ ግን በያዘው መስመር ቀጥሎ ከዓመታት በኋላ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያበቃውን ነጥብ ለማምጣት ይበቃል። እናም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የሆቴል ማኔጅመንት ትምህርቱን ይጀምራል። ነገር ግን አሁንም ነገሮች አልጋ ባልጋ ሊሆኑ ሳይችሉ ይቀራሉ። በተለይ የመጀመሪያውን ዓመት ሁኔታዎች ከአቅሙ በላይ ሆነውበት በጭንቀት ይወጠራል። የጨነቀው ዮናስ ወደ ዩኒቨርሲቲው አመራሮች በማቅናትም የገጠመውን ነገር ሁሉ ይነግራቸዋል። እነሱም ለጊዜው ጭንቀቱ እንዲለቀው የመተኛ ክፍሉን ይቀይሩለትና በርትቶ ከሠራ ተመርቆ መውጣት እንደሚችል ተስፋ አሰንቀው ይልኩታል። ቀስ በቀስ ከተማሪዎቹም ከትምህርቱም እየተግባባ ይመጣና ከዛሬ ነገ ተባሮ ይመጣል የሚለውን የጓደኞቹን እና የቤተሰቡን ሟርት መና ለማስቀረት ጠንክሮ መንቀሳቀስ ይጀምራል። ከሶስት ዓመት በኋላም የማዕረግ ተመራቂ ለመሆን ይበቃል። ወዲያውም አዲስ አበባ በመመለስ ቦሌ አካባቢ ኬ ዜድ በሚባል ሆቴል ለአስተዳደሪነት ሥራ ያገኝና ከአንድ ጓደኛው ጋር ቤት ተከራይቶ አዲስ ህይወት ይጀምራል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለ ነበር በአንዲት የተባረከች ቀን ከዛሬ ባለቤቱና የአንድ ልጁ እናት ኪም ጋር ለመገናኘት የበቃው። ዮናስ የነበረውን አጋጣሚ እንዲህ ያስታወሰዋል።
«በዕለቱ እሷን ተቀብዬ አልጋ የማስያዝ ሥራ የኔ ባይሆንም መሥራት የነበረባቸው ሁለቱም ሰዎች በሚገርም አጋጣሚ ለደቂቃዎች በሥራ ገበታቸው ላይ ሳይገኙ በመቅረታቸው የሁለቱንም ሥራ ሸፍኜ ስድስተኛ ፎቅ ከሚገኘው ክፍሏ ድረስ እየሸኘኋት እያለ ʽቆንጆ አበሻʼ አለችኝ። ወዲያው ደንግጨ ስለነበር ዝም አልኳት፤ ሻንጣዋን ይዤ ክፍሏ ካስገባኋት በኋላ ግን ስለእሷ ማሰብ ጀመርኩ። ቆየት ብላ ደግሞ መጸሐፍ ይዛ መጥታ እንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ ማንበብ ጀመረች። ሰሞኑን አንድ ነገር እንደማደርግ እያሰብኩ ዝም አልኳት። በነጋታው ስመጣ ግን ለቃ ሄዳለች አሉኝ። ለምን እንደሆነ ባላውቅም በጣም ደነገጥኩ ሳጣራ ደግሞ ሀገሯ ሩቅ ነው።
የውስጤን በውስጤ ይዤ ባገኛት እየወደድኩ የርቀቱ ነገር እያስጨነቀኝ በኢሜል ሰላምታ ላኩላት፤ እሷ ግን «የሆቴሉ ባለቤት አንተ ነህ?» ሰትል ጠየቀችኝ። በቃ ይህች ልጅ በትልቁ አስባኛለች ብዬ ተስፋ ቆረጥኩ። ነገር ግን ከቀናት በኋላ አላስችል ስላለኝ ጠንካራ የፍቅር ደብዳቤ ላኩላት፤ እሷ ግን በምላሹ “ሳሞግስህ እንኳን አላመሰገንከኝም ነበር ከዛ በኋላ ስንገናኝም ምንም ያልከኝ ነገር አልነበረም፤ አሁን የምትለው እንዴት ሊፈጠር ይችላል? በዛ ላይ ጓደኛ አለኝ” የሚል ምላሽ ላከችልኝ። ያኔ ተስፋ ቆርጬ ሁሉንም ነገር አቆምኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ከቢቢሲ በኒውዝላንድ የመሬት መንቀጥቀጥ መድረሱን ስሰማ እንዴት ሆናችሁ ብዬ ላኩላት (ከዓመታት በኋላ ሀገሯ ስሄድ አንድ ሀገር መሆኑ እንጂ የመሬት መንቀጥቀጡ የደረሰበት ቦታ እሷ ከምትኖረበት በእጅጉ የራቀ ነበር።»
በዚህ የተዘጋው ጓደኝነት ከሁለት ዓመት በኋላ አዲስ አበባ መጥታ በአንዲት መናፈሻ ውስጥ ይገናኛሉ። ዮናስ ግራ እንደገባው ደፈር ብሎ ታስታውሰው እንደሆነ ይጠይቃታል። ሚስተር ታዬ ትለዋለች በለመደችው ቋንቋ የአባቱን ስም አስቀድማ። አይ አይ ሚስተር ዮናስ ይላታል ባገርኛ የስም አጠራር አውቄሀለው ትለውና መነጋገር ይጀምራሉ። እሱ የቀደመው ታሪክ እንዳይደገም የፈራ ቢሆንም እሷ እያቀረበችው ስትመጣና ውለው ሲያድሩ የቀደመው ፍቅሩ እያገረሸበት ይመጣል። በወቅቱ ግን እሷ ምንም የሚሰማት ነገር አልነበረም፤ ቀናት ቀናትን እየወለዱ ሲመጡና አብረው ሲያሳልፉ ሁኔታው ግራ ሲጋባት አንድ ቀን እፈልግሀለሁ ብላ ትቀጥረውና «ነገርህ ወደ ሌላ እያመራ ይመስለኛል፤ በእኔ በኩል እንደዚህ አይነት የፍቅር ሀሳብ እንደሌለ ማወቅ አለብህ» ብላ በአንዲት ደመናማ ቀን ታረዳዋለች። እንዲህ ብላው ለጊዜው ብትለየውም እሱ ግን ምንም ሊቆርጥለት ስላልቻለ ዙምባ ዳንስ ታስተምርበታለች በየተባለበት እየዞረ ሲመቸው ሰላም እያለ በማናገር ሳይመቸው ደግሞ እያያት መመላለሱን ይቀጥላል።
አንድ ቀን ግን እሷው ትቀጥረውና መገናኛ አካባቢ ቶፕቪው ሆቴል ሲሄዱ መንገድ ላይ ሁለት ህፃናት ወንድማማቾችን ታይና “አብረውን እንዲያመሹ ይዘህልኝ ና” ትለዋለች እናታቸውን አስፈቅዶ ልጆቹን ይዟቸው ይመጣና ከልጆቹ ጋር አብረው አምሽተው ይለያያሉ። ከሳምንት በኋላ ኪም ወደ ጂማ እንደምታቀና ስትነግረውና አብሯት እንዲሄድ ስትጠይቀው መጀመሪያ ለራሱም ባልገባው ምክንያት ፈቃደኛ ሳይሆን ይቀርና በኋላ ነገሩን ሲያስበው መሄድ እንዳለበት የሚሄደውም ሁለቱን ልጆች ከእናታቸው አስፈቅዶ ይዟቸው መሆን እንዳለበት ይወስንና ይነሳል። እናም በእቅዱ መሰረት እሷን ለማስደመም በማሰብ ልጆቹን ከእናታቸው አስፈቅዶ ወደ ጅማ ያቀናል፤ በጉዞውም እያለ አልመጣም ብሏት ስለነበር ለእሷ ደውሎ አንድ ከአሜሪካ የመጣ እንግዳ መኖሩንና ጅማ መሄድ እንደሚፈልግ በመንገር ያለችበትን ሲያጣራ ይቆያል። እናም ሳታስበው ሁለቱን ልጆች ይዞ ካለችበት ይከሰታል። በጣም በመደነቅም በመገረምም ትቀበለውና ለአምስት ቀን አብረው ያሳልፋሉ። የጅማው ቆይታ እሷን ወደ ፍቅር ይመራትና ግንኙነት ይጀምራሉ፤ በዛችው አጋጣሚም ኪም ትፀንሳለች።
ከወራት ቆይታ በኋላ ኪም ክትትል ለማድረግ ወደ ሆስፒታል ስታቀና «ጽንሱ ያለበት ሁኔታ ጥሩ አይደለም» ይወርዳል የሚል ልብ የሚሰብር መርዶ ለእሷም ለዮናስም ይነገራቸዋል። ለማረጋገጥ ብለው ሌላ ሆስፒታል ሲሄዱ ደግሞ ተስፋ አንዳለው ይነግሯቸዋል። ይህን ጊዜ ኪም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህክምና ተስፋ የሚጣልበት ባለመሆኑ ወደ ሀገሯ ሄዳ የእሷንም የልጃንም ጤና መከታተል እንዳለባት ወስና ወደ ኒውዝላንድ ታቀናለች። እንዳሰበችውም ልጁ በሙሉ ጤንነት እዛው ኒውዝላንድ የተወለደ ሲሆን በእርሷው ጥረት ከመወለዷ ሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ ዮናስ ኒውዝላንድ እንዲደርስ ታደርጋለች። ኪምም ልጇን “አንበሳ” ብላ ትሰይመዋለች።
ዮናስ ኒውዝላንድ ሲደርስ ተቀብለውት ማኖር የጀመሩት የኪም ቤተሰቦች ነበሩ። በመጀመሪያ አካባቢ በተመሰረተው ግንኙነት ደስተኛ ያልነበሩ ቢሆንም ውሎ ሲያድር ግን ነገሩን ከመቀበል አልፈው ድጋፉንም እንክብካቤውንም ያጠናክሩለታል። ዮናስ አንድ ካፍቴሪያ ውስጥ የሚሰራ ቢሆንም ከአገሬው ባህል ጋር ለመግባባት ግን ይቸገር ነበር። አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቦቿ በልማዳቸው መሰረት ሳያስበው ተነስተው «እስካሁን ሁሌ የምትበላው እኛ ያዘጋጀነውን ነው፤ በል የዛሬ ምግብ የምታዘጋጀው አንተ ነህ ይሉት ነበር»። ወጣ ሲሉም የተለያዩ ከባባድ ጨዋታዎችን እንዲያካሂድ ይገፋፉታል። ከሶስት ዓመት በኋላ ግን ስራውንም ሀገሩንም ባህሉንም እየለመደው ሲመጣ የራሱን ቤት ተከራይቶ ይወጣና ባለቤቱንና ልጆቹን ይዞ መኖር ይጀምራል።
በአዲሱ ቤት መኖር ከጀመረ ከአራት ዓመት በኋላ ደግሞ ምንም እንኳን እሱም ባለቤቱና ልጁም የኒውዝላንድ ዜግነት ያላቸው ቢሆንም ኪም «እዚህ ሀገር መቆየት አልፈልግም ኢትዮጵያ መሄድ አለብን» የሚል ሀሳብ ታነሳለች። ዮናስ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ለመመለስ በቂ ጥሪት ባለመቋጠሩ፤ በሌላ በኩል በዚህ በኮሮና ወቅት ወደዚህ መጥተህ ምን ልትሆን ነው የሚለው የቤተሰቦቹ ውትወታ ግራ ያጋባው ይጀምራል። ይህም ሆኖ ኪም ከወሰነችው ነገር የማትመለስ በመሆኗ ጓዛቸውን ሸክፈው ወደ ኢትዮጵያ ያቀናሉ። ነገር ግን አዲስ አበባ በገቡበት ወቅት በኮሮና ምክንያት ቤት ለመከራየት እንኳን ስላልቻሉ ዓለም ገና ከሚገኘው ዮናስ እናት ቤት ስድስት ወር ለመቆየት ይገደዳሉ።
ከዚያ በኋላ ነበር ቦሌ አካባቢ ለትርፍ ብቻ ሳይሆን ለማህበራዊ አገልግሎትም በማሰብ አንድ «እንተዋወቅ» የሚል ካፍቴሪያ ከፍተው የራሳቸውን ቤትም ተከራይተው መኖር የጀመሩት። እንተዋወቅ ዋናው አለማ የእነሱ መተዳደሪያ ቢሆንም ኢትዮጵያዊነት እሴት የሚባሉትን መተሳሰብ፤ መዋደድ መረዳዳት ለማሰተማርና ለማስፋፋት ያሰበ ካፍቴሪያ ነው። ዛሬ በስፋት ባይተገብሩትም በእያንዳንዱ ጠረጴዛ የሚቀመጥ እርስ በእርሱ እንዲወያይ መረጃ እንዲለዋወጥ የሚያደርጉ ነገሮችን አዘጋጅተዋል። በአንድ ጥግም ስለ ካፍቴሪያውና የእነሱ ህይወት የሚገልጽ ቦርድ ተቀምጦ ተገልጋይ እንዲያውቃቸው ብሎም የእነሱን ተሞክሮ እንዲማርበት አድርገዋል።
በተጨማሪ ኪም ከስትሮ «የጁስ መጠጫ» ጀምሮ ምንም አይነት ላስቲክ በአገልግሎቷ የማትጠቀም ሲሆን እቃ እንኳን የምትገዛው ሊበሰብሱ የሚችሉ እንደ ዘንቢል ያሉ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም ነው። ይህን የምታደርገው ደግሞ በአካባቢው ጥበቃ ረገድ የአቅሟን ለመሥራት እቅድ ስላላት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ያልተጠቀምንባቸው ነገሮች አሉ የምትለው ኪም፣ ዮናስ እናት ቤት በሰነበተችበት ወቅት የተለማመደችውን አጥሚት ዛሬ በካፍቴሪያዋ አንዱ የቤቱ ስፔሻል አድርጋ እያቀረበችው ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት ጥንዶቹ ቦሌ በሚገኘው ካፍቴሪያቸው አካባቢ ቤት ተከራይተው እየኖሩ ሲሆን ልጃቸው አንበሳም በግሪክ ስኩል ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2013