ለምለም መንግሥቱ
ደባርቅ ዩኒቨርስቲ አራተኛ ትውልድ ከሚባሉት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ነው ። ዩኒቨርሲቲው በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሥር ሆኖ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑለት የቆየ ሲሆን፣ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ግን ግንባታዎችን ጨምሮ አንዳንድ ሥራዎችን በራሱ አቅም በማከናወን ላይ ይገኛል ። በመሆኑም የተማሪዎች የቅበላ አቅም ለማሳደግና ለመማር ማስተማሩ የሚያግዘውን የግንባታ ሥራ በበጀት አመቱ ህዳር ወር ላይ መጀመሩን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀጃው ደማሞ ይናገራሉ።
እንደእርሳቸው ገለጻ፤የተጀመረው የግንባታ ሥራ ለተማሪዎች ማደሪያና ለሌሎችም የሚያገለግሉ 12 የሚሆኑ ሕንፃዎች ሲሆኑ፤ለግንባታው የሚውል የሲሚንቶ ግብአት ዩኒቨርስቲው ለማቅረብ ከተቋራጭ ጋር የውል ስምምነት ፈጽሞ ነው ወደ ሥራው የገባው።ተቋራጩም ሥራውን በሶስት መቶ ቀናት እንዲያስረክበው በስምምነቱ ተካቷል ። ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲው ለግንባታው ከተወሰነ ጊዜ በላይ የሲሚንቶ ግብአት ማቅረብ ባለመቻሉ ግንባታው ከ12 በመቶ በላይ ሊዘልቅ አልቻለም ። ምክንያቱ ደግሞ የሲሚንቶ አቅርቦት አለመኖርና የዋጋ ንረት ነው።
ዩኒቨርሲቲው ቅድሚያ የሚያገኝበትን አሰራር ተከትሎ የሲሚንቶ ግብአቱን በፋብሪካ ዋጋ ተረክቦ ሲያቀርብ ቢቆይም ለግንባታው የሚያስፈልገውን ያህል ከፋብሪካ ማግኘት አዳጋች ስለሆነበት ግንባታው በጊዜው እንዳይጠናቀቅ ሆኗል ። ውጭ በሚሸጠው ዋጋ ገዝቶ ለማቅረብ ደግሞ አሰራሩ አይፈቅድለትም ። በያዘው ዕቅድ መሠረት የግንባታ ሥራው ተጠናቅቆ ቢሆን ኖሮ ዩኒቨርሰቲው በቀጣይ አመት የተማሪዎች የቅበላ አቅሙ አሁን ካለበት ሶስት ሺ ወደ ሰባት ሺ እና ከዚያም በላይ ከፍ ይል ነበር።የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት መከሰቱ ዩኒቨርሲቲው ከተቋራጩ ጋር በገባው ውል ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል ። ተቋራጩ ከነገ ዛሬ ግብዓት ቀርቦለት ሥራው ይጠናቀቃል በሚል የሰራተኞች ደመወዝ ሲከፍል በመቆየቱና የውሉ ጊዜ በመራዘሙ የተለያዩ ወጭዎችን አስቦ ተጨማሪ ክፍያና ጊዜ መጠየቁ አይቀሬ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ያስረዳሉ ።
ከመንግሥት ጋር የኮንትራት ውል ገብተው የጤና ተቋም በመገንባት ላይ እንደሆኑ ሌላው በምሬት ሀሳባቸውን የሰጡን የእቴቴ ኮንስትራክሽን ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋ ታደሰ ናቸው ። ግንባታው የሚያስፈልገውን ሲሚንቶ ለማግኘት ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በማሳወቅ ግብዓቱን ቀጥታ ከፋብሪካ ለማግኘት ጥረት ተደርጓል ። ይሁን እንጂ የደብዳቤ ልውውጦች ውጣ ውረድ የበዛባቸውና መፍትሄ የሚያስገኙ ባለመሆናቸው በዚሁ ምክንያት ሥራው ከመጓተትም በላይ ሆኗል ። በደብዳቤ የሚቀርበው ጥያቄ በሚኒስትር ደረጃ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች በፊርማቸው እንዲያረጋግጡ እንደሚፈለግና እነርሱን ለማግኘት ደግሞ ከባድ እንደሆነም ይገልጻሉ ። በእርሳቸው እምነት ከተቋራጩና ከነጋዴው ገንዘብ እየሰበሰቡ ሲሚንቶ እናቀርባለን የሚሉ ኤጀንት ተብለው በሚንቀሳቀሱና በተወሰኑ የልማት ድርጅቶች አማካኝነት እንዲከፋፈል መደረጉ እጥረቱን አባብሶታል ፡፡ በተለይም ኤጀንቶች ፋብሪካዎች ሥራ አቁመዋል የሚልና አንዳንዱም አሳማኝ ያልሆነ ምክንያት በመስጠት ጫና እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ። ድርጅታቸው በኤጀንት በኩል እንዲቀርብለት ገንዘብ ከፍሎ ሳይቀርብለት ከስድስት ወር በላይ ጊዜ መውሰዱንና እስካሁንም አለማግኘቱን ጠቅሰዋል ። አልፎ አልፎም በተሽከርካሪ እጥረት የሚቀርብ ምክንያት መኖሩን የጠቀሱት አቶ ተስፋ፤ድርጅታቸው መኪና አቅርቦ አገልግሎቱ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ተቀባይነት እንዳላገኘ ያስረዳሉ ። የትራንስፖርት እጥረት የሚያነሱት በፈለጉት ዋጋ ለመጫን ሲሉ እንደሆነም ገልጸዋል ። የትራንስፖርት ጭማሪው ለጫኝና አውራጅ ከሚከፈለው ጋር ሲደመር ለዋጋ መናር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አመልክተዋል። እንደሌሎች አገልግሎቶች ሁሉ የትራንስፖርት አገልግሎቱ በመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ታሪፍ ቢወጣለት ግን ችግሩ ይቃለል እንደነበርም ተናግረዋል።
በግንባታ ዘርፍ የረጅም ጊዜ ልምድ እንዳላቸው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግርማ ኃብተማርያም፤በመሀል ላይ ሆነው ዋጋውን በማናር የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጥሩ አካላት መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተናገሩትን ሀሳብ ይስማማሉ ። በሥራው በቆዩበት ረጅም ዓመታት ተሞክሮ የዋጋ ጭማሪ ቢኖርም የአንድ ኩንታል የሰሚንቶ ዋጋ ስምንት መቶ ብር አለመድረሱንና የተባባሰ ችግር እንዳላጋጠማቸው አስታውሰዋል ። አሁን ያሉት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በግማሽ አቅማቸው እየሰሩ እንኳን እስከ 70 በመቶ የማቅረብ አቅም አላቸው ። አቅርቦቱ በቂ ነው ባይባልም አሁን የተፈጠረውን ያህል የዋጋ ንረት መድረስ እንዳልነበረበት ይገልጻሉ ። እርሳቸው እንደሚያስታውሱት በአንድ ወቅት ሲሚንቶ በውድድር ነበር የሚቀርበው ። ፋብሪካዎቹ በራሳቸው መኪና አከፋፋዩ ጋር በማቅረብ ጭምር ምርታቸውን የሚሸጡበት ጊዜ ነበር ። አሁን በአንድ ጊዜ ችግሩ ተባብሶ ትልቅ መነጋገሪያ መሆኑ ለእርሳቸውም ግራ ገብቷቸዋል ። የግንባታ ሥራ እያደገ መምጣቱ ፍላጎት እንዲጨምር ማድረጉን ቢያምኑም መጋነን ግን አልነበረበትም ይላሉ።
ኢንጂነር ግርማ እንደገለጹት፤ውዥንብሩ ብዙ ነበር ። ፋብሪካዎች ማምረት አቁመዋል።ሌላም ሌላም እየተባለ ሲሚንቶ በጥቁር ገበያ እየተሸጠ ነበር ። መንግሥትም ለጉዳዩ ምላሽ ሲሰጥ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ ነው ቢልም ችግሩ ለቀናት ዘልቋል። በተለይም በክልሎች ችግሩ የበረታ ነበር ። አከፋፋዮች ተመድበዋል ቢባልም ሥራ ላይ አልነበሩም። ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሌሎችም ጋር የሥራ ውል ገብተው እንቅስቃሴ ላይ የነበሩ ተቋራጮች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ሥራ አቁመዋል። አንዳንድ ተቋራጮች ሥራው እንዳይስተጓጐልና ሥማቸውንም ለመጠበቅ ሲሉ በጥቁር ገበያም እየገዙ መንቀሳቀስ ቢጀምሩም ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ለማቋረጥ ተገደዋል ። ተቋራጩ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። እንደ ጋራ መኖሪያ ቤት ፣ የትምህርት፣ የጤና ተቋማትና ሌሎችም ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን በገባው ውል መሠረት ሰርቶ አጠናቅቆ ሊያስረክብ አልቻለም። ሌላው ተቋራጩ የግንባታ ውል ሲገባ የትራንስፖርት ወጭን ሳይጨምር ከ233 እስከ 295 ብር ባለው በፋብሪካ የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ነው። ግዥው ከአከፋፋይ ሲፈጸም፣ የማጓጓዣ፣የጫኝና አውራጅ ሲጨመርበት ወጭው ከፍተኛ ነው ። ይህ ሁሉ ጫና የሚያርፈው ተቋራጩ ላይ ነው ። በክልሎች ደግሞ ችግሩ ከፍ ይላል ። ተቋራጩ በግብዓት አቅርቦት ዋጋ መናር ምክንያት የዋጋ ማስተካከያ ተቀባይነት የለውም ። አሰሪው ድርጅት በአብዛኛው የመንግሥት ተቋማት በመሆናቸው ችግሩ በቀላሉ መፍትሄ አያገኝም ። ጫናው ተቋራጮች ላይ ቢያርፍም በተዘዋዋሪ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት በሆነው ላይ ጫና እየተፈጠረ ነው። ችግሩ በአንድ በኩል ብቻ አያበቃም ። ፕሮጀክቶች ሲስተጓጎሉ ሰራተኞች ሥራቸውን ያጣሉ ። ሰራተኛ ደግሞ በሥሩ የሚያስተዳድሯቸው ሰዎች ስለሚኖሩ ችግሩ ተያያዥ ነው ። የሰራተኛ ኃይል በመያዝ ግንባታቸው ያለው ድርሻ ሲቀንስ መንግሥትም ይቸገራል ።
የሲሚንቶ ዋጋ መናር የትምህርት፣የጤና እና ሌሎች ተቋማትን ግንባታ ዕቅድ በማስተጓጎል እራስ ምታት ሆኖ መክረሙ ይታወሳል ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ገለጻ ባደረጉበት ወቅት የዘርፉን ችግሮች አንስተዋል ። በተለይም በመካከል ላይ ሆነው እጥረቱ እንዲፈጠር የሚያደርጉትን ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ ላይ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል ። ተጨማሪ የሲሚንቶ ማምረቻ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ በማስገባትም ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል ። ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም በየጊዜው መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸውን እርምጃዎች ከመውሰድ አልተቆጠበም።
ሲያነጋግር የነበረው የሲሚንቶ እጥረት ጉዳይ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ መልካም ነገር ተሰምቷል። ኩንታሉ እስከ ስምንት መቶ ብር ደርሶ የነበረው የሲሚንቶ ዋጋ በግማሽ ቀንሶ ገበያ ላይ መዋል መጀመሩ በግንባታው ዘርፍ ላይ ለሚገኙ እፎይታን ሰጥቷል።
በዚህ ላይም ኢንጂነር ግርማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ተጨማሪ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ቅድመ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን መግለጻቸው እፎይታን የሚሰጥ ተስፋ እንደሆነ ተናግረዋል ። ከእርሳቸው ንግግር ማግሥት በጎተራ አካባቢ ከአቅራቢዎች የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ በግማሽ ወርዶ ገበያ ላይ መዋሉ አስደስቷቸዋል ። ማህበራቸው ባለሙያዎችን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወደ ተለያዩ የመሸጫ ቦታዎች አሰማርተው የዳንጎቴ ፋብሪካ በ455ብር፣ሀበሻ ደግሞ በ420ብር እየቀረበ መሆኑን አረጋግጠዋል ። እንዲህ ያለው ውጤት መንግሥት ተደጋጋሚ የሆነ እርምጃ በመውሰዱ እንደሆነ አመልክተዋል ። እርምጃው የዘገየ ቢሆንም ለውጥ መምጣቱ እንዳስደሰታቸውና ማህበራቸውም መልካም የሆነ ነገር መመስገን አለበት ብሎ ስለሚያምን በደብዳቤ የምስጋና መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ገልጸዋል።
ኢንጂነር ግርማ የመጣው ለውጥ ጊዜያዊ እንዳይሆንና ወደ ነበረበት እንዳይመለስ ስጋታቸውንም አክለዋል። እርሳቸው እንዳሉት እታች ድረስ ወርዶ ማረጋገጥ ይገባል። በግማሽ ዋጋ ቀንሰው ያቀረቡ ቢኖሩም ሽያጩ በወረፋና በግፊያ ነበር ሲከናወን የነበረው።ይህም የራሱ ተጽእኖ ስላለው ወደ ኋላ እንዲመለስ ምክንያት ይሆናል። ወረፋ መብዛቱ የሥራ ጊዜን ከመሻማቱ በተጨማሪ በወረፋ መብዛት የሚጠቀሙ አካላት እንዳይፈጠሩም ይሰጋሉ። ማከፋፈያዎችን በማብዛት ስርጭቱን ሰፋ ማድረግ ቢቻል ግን ስጋቱን መቀነስ እንደሚቻል ይጠቅሳሉ ። አንድ ድርጅት ወይንም ተቋራጭ ከ20 ኩንታል በላይ እንዳይወሰድ የሚል ተከትሎ በመንግሥት የተላለፈው መልዕክት ላይም ጥያቄ አላቸው ።
‹‹20 ኩንታል ለአንድ መኖሪያ ቤት እንኳን በቂ ግብአት አይደለም ። በአርማታ ደረጃ ከስድስት ሜትር ኩብ በላይ እንደማይሰራ ይገልጻሉ ። በተደጋጋሚ ለግዥ ሰልፍ እየጠበቁ አያዋጣም ›› ይላሉ ። ቅድሚያ የሚሰጣቸው እየተለዩ እንደአስፈላጊነቱ በቅደም ተከተል የሚስተናገዱበት ሁኔታ ቢመቻች፣ እንዲሁም መንግሥት አቅም እስኪፈጠርም ችግሩን ለማቃለል ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ከውጭ ሀገር በማስመጣትም ድጋፍ ቢደረግ የሚል ሀሳብ አላቸው ።
ማህበሩ አማራጮችን ለመንግሥት በማቅረብም ሆነ በሙያ ሥነ ምግባር ጉድለት ችግር የሚፈጥሩትን በማጋለጥ ጭምር ያደረገው አስተዋጽኦ ስለመኖሩ ኢንጂነር ላቀረብኩላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሀሳባቸውን ከማቅረብ አልተቆጠቡም ። ያለውንም ችግር ያሳያሉ ። በሥነ ምግባር በኩልም ሙሉ ለሙሉ ከችግር የጸዱ ይኖራሉ ብለው አይጠብቁም ። እጥረቱ እንዲፈጠር፤አላግባብ ለመጠቀም የሚያከማቹ እንደሚኖሩ ይገምታሉ ። ማህበራቸው በዚህ ውስጥ የሚገኙ አባላቶቻቸውን አይታገሷቸውም ። የማህበሩ አባላት የሥነ ምግባር ስምምነት ከማህበሩ ጋር ውል ስለገቡ በዚያ መሠረት ከተገኙ ማህበሩ ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሮጀክት ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በቅርበት ስለሚሰራ ለተቋማቱ ያሳውቃል።
እስካሁን ግን ጥፋተኛ ሆኖ ያቀረቡት ተቋራጭ የለም ። ግን ደግሞ ኢንጂነር ግርማ የማይስማሙበት ነገር አላቸው ። ጥቂቶች ባጠፉት ብዙኃን በአንድ መፈረጅ እንደሌለባቸውና ለጉዳትም እንዲዳረጉ መደረግ እንደሌለበት ተናግረዋል ። በአንድ ወቅት ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመከታተያ መቆጣጠሪያ በመትከል ችግሩን ለመቅረፍ ሀሳብ አቅርቦ እንደነበር በማስታወስ ይሄን ቢያጠናክር መሳሪያው ከፋብሪካ ቀጥታ ወደ ሚፈለገው ሥፍራ ማጓጓዙን ለመከታተል ቴክኖሎጂው አጋዥ መሆኑን አመልክተዋል።
የዘርፉ ባለሙያዎች በሲሚኒቶ ዋጋ መቀነስ የተሰማቸው ደስታ ከፍተኛ እንደሆነ ቢገልጹም ዘላቂነቱ ላይ ግን እንዲሰራ ጠይቀዋል ። በሥራ ላይ ያሉት ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ፤ተጨማሪ ወደ ሥራ ይገባሉ የተባሉትም ፈጥነው ቢገቡ የሀብት ብክነት ይቀንሳል ። ተቋራጮችም ለአዳዲስ ሥራ ይነቃቃሉ።
አቶ ተስፋ ፤ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደ ሀገር መሪ አላግባብ የዋጋ ንረትን በሚያስከትሉ ላይ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን በመግለጽ የራሳቸውን ድርሻ ተወጥተዋል ። ይሄ በዘርፉ ለምንገኘው ተስፋ ይሰጣል ። በድርጅቴ መንግሥት ጩኸቴን ሰምቶኛል ነው ያልኩት ። ምሥጋናችንን የምናቀርብበት መንገድ ካለም ለማቅረብ ዝግጁ ነን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ተገኝተው ንግግር ባደረጉ ማግሥት የሲሚንቶ ዋጋ አሻቅቦ ከነበረበት በግማሽ ቀንሷል ። ይሄ ለእኔ ትልቅ ውጤት ነው ። ከዚህም በላይ እንዲሻሻል እጠብቃለሁ። ምክንያቱም ከፋብሪካ ሶስት መቶ ብር ባልሞላ ዋጋ እየተሸጠ ገበያ ላይ አራት መቶ ብር መሸጡ አግባብ ነው ብዬ አላምንም ሌሎች ነገሮችም ተፈትሸው መሻሻል ይኖርበታል ። የሲሚንቶ ግብዓትን ጨምሮ በሌሎችም ላይም በተመሳሳይ እርምጃዎች ተወስደው የተጓተቱ የግንባታ ፕሮጀክቶች መፋጠን ይኖርባቸዋል። በተለይም በመንግሥት ለሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተብለው የሚሰሩ ሊታዩ ይገባል ። ግንባታው በተጓተተ ቁጥር ተጎጂው ሕዝብ ነው ። በመሆኑም እርምጃው የአንድ ወቅት ብቻ እንዳይሆን ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ ። በተለይም ቅድሚያ ለማግኘት የሚደረገው የደብዳቤ ልውውጥ አሰራርም እንዲፈተሽ ጠይቀዋል ።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጃጀውም ‹‹የሰሞኑን ተስፋ አድርገን ከሀበሻ ሲሚንቶ ወደ 75ሺ ኩንታል ለመረከብ ውል ገብተናል ። መንግሥት በሰጠው አቅጣጫ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ እስከ ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ድረስ የተሻለ እንቅስቀሴ ይኖረናል›› ብለዋል ።
የዘርፉ ባለሙያዎች በሲሚንቶ ዋጋ ላይ መሻሻል ቢኖርም በቀጣይነቱ ላይ ስጋታቸውን ይገልጻሉ ። ሥራ ላይ ያሉት ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ፤ተጨማሪ ወደ ሥራ ይገባሉ የተባሉትም ፈጥነው ቢገቡ የሀብት ብክነት ይቀንሳል ። ተቋራጮችም ለአዳዲስ ሥራ ይነቃቃሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2013