ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
ትናንት ዛሬና ነገ በእያንዳንዳችን ነፍስና ሥጋ ላይ የታተሙ የህልውና ማህተሞች ናቸው። መኖር ማለት በእነዚህ የጊዜ ሂደቶች ውስጥ ሳይንገዳገዱ ማለፍ ወይም እየተንገዳገዱ ሳይወድቁ መሄድ አሊያም ደግሞ በወደቁ ቁጥር እየተነሱ የሚደረግ ዘላለማዊ ጉዞ ነው።
አንዱ አንዱን ይወልደዋል፤ አንዱ አንዱን ይፈጥረዋል፤ የእነዚህ የቀናት ፈረቃ በልደት ተጀምሮ በሞት የሚጠናቀቅ ነው። ዛሬ በትናንት ተፈጥሯል፤ ነገ ደግሞ በተራው በዛሬ ይፈጠራል። ሰው ስንሆን በዚህ ውስጥ ማለፍ ግድ ይለናል።
ሁሉም ቀናት ለሁላችንም እኩል ናቸው። ለአንዱ መጥፎ ለአንዱ ጥሩ የሆነ ቀን የለም። ሁሉም ነገር በአስተሳሰባችን በኩል የሚሆን ነው። በህይወታችን እስካሁን ድረስ የማይመለሱ በርካታ ትናንቶችን ኖረናል..ወይም በከንቱ አባክነናል። ይህ ማለት በማይደገም ህላዊ ውስጥ ነን ማለት ነው። ይህ ማለት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰው ሆነናል ማለት ነው።
አሁን ላይ ብዙዎቻችን ትናንት ባበላሸነው ግፍ ዛሬ የምንሰቃይ ነን። ደስታ ርቆን፣ የመኖር ትርጉሙ ጠፍቶን በታፈነ ድምጽ እየዬ የምንል ብዙዎች ነን። ከተፈቀደልን ተፈጥሮአዊ እርከን ወጥተን ባልተገባ ቦታ ላይ በመቆም በቁጭት፣ በፀፀት የምንባክን እልፍ ነን። እንደዚሁም ለራሳችን ህይወት ሃላፊነት መውሰድ አቅቶን የምንዳክር ሞልተናል።
በተሰጡን ትናንት ዛሬና ነገ ላይ መልካም ነገር የምንጽፈው እኛ ነን። ብዙዎቻችን ሥራ ስናጣ መንግሥትን የምናማርር፣ ከትምህርታችን ስንወድቅ በመምህሮቻችን ላይ ጣታችንን የምንቀስር፣ የሆነ ነገር ሞክረን አልሳካ ሲለን የሆነ ነገር የምንፈጥር ሰበበኞች ነን። ለብዙ ነገር ቤተሰቦቻችንን ጓደኞቻችንን ምክንያት የምናደርግ እንደዚህም ነን። ለምንም ነገር ሃላፊነት ስንወስድ አንታይም።
ኑሯችንን፣ ህይወታችንን ባጠቃላይ ሰውነታችንን ለሌሎች አሳልፈን የሰጠን ነን፤ በዚህ እውነት ውስጥ ውድቀት እንጂ ልዕልና የለም። መሸነፍ እንጂ ማሸነፍ የለም። ከተሳሳትንም ልክ ከሆንም ተመስጋኝም ተወቃሽም ራሳችን መሆን አለብን። በዙሪያችን ያሉ ጥሩ ሰዎች ከእኛ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱ መሆን አለባቸው።
ሁሉ ነገራችሁን ለሌሎች ሰጥታችሁ እንዴት ነው የራሳችሁ የሆነ ነገር የሚኖራችሁ? መጀመሪያ የራሳችሁ ሁኑ፣ ከዛ ወደዚህ ምድር የመጣችሁበትን ትልቅ አላማ ፈልጉ። ከዛም የሚያስፈራችሁን ድፈሩ፣ ከዛም ተአምር ለመሥራት ተዘጋጁ።
ራሳችሁን እየሸሻችሁ፣ ከእውነት እየራቃችሁ የምታሳኩት ታላቅ ነገር የለም። መልካም ነገሮች ሁሉ ራስን ከመሆንና ራስን ከማወቅ የሚመነጩ ናቸው። ሌሎችን ከማወቃችሁ በፊት ራሳችሁን እወቁ። ሌሎችን ከመረዳታችሁ በፊት መጀመሪያ ራሳችሁን ተረዱ። ለሌሎች የምንተርፈው መጀመሪያ ለራሳችን በቂ ስንሆን ብቻ ነው።
በተሸራረፈ እውነት የምትገነቡት የስኬት ግንብ የለም። መጀመሪያ ከእስራታችሁ ውጡ። መጀመሪያ ከኖራችሁትና ወደ ህይወታችሁ ዳግመኛ ከማይመጣው ትናንት ተላቀቁና ዛሬን ኑሩ። መጀመሪያ እኔ ማነኝ ስትሉ ራሳችሁን ጠይቁ..ጠይቃችሁም መልሱን መልሱ። ኒልሰን ማዴላ እንዳለው የራሳችሁ የህይወት መሪና ካፒቴን ራሳችሁ ናችሁ። በቃ ይሄ ነው።
ጎዳናው ሁሉ ግራ በገባው ሰው የተሞላ ነው። ብዙዎቻችን ዛሬን የጠላን፣ አሁናችንን የምንፀየፍ ነን። ግና ዛሬን መኖር ጥበብ ነው..አለማት ላይ ካሉ ጥበቦች ሁሉ የሚልቅ። ቅሉ ግን ማናችንም ዛሬን ኖረን አለማወቃችን ነው። አብዛኞቻችን በትናንት የምንብሰለሰል፣ ባለፈ የምንሰቃይ ነን።
የቅርብ ጊዜ ጥናት ይፋ እንዳደረገው አብዛኛው ሰው የቀኑን ሰማኒያ በመቶ የሚያሳልፈው ትናንትን በማሰብ ነው ። ዛሬ የምርጦች ቀን ናት..ምርጦች ዛሬን ትተው ወደ ትናንት አይሄዱም። በአዕምሯችሁ ስትልቁ ትናትን ገላችሁ ትቀብሩታላችሁ።
ማሰብ ስትጀምሩ፣ የመኖር ዋጋው ሲገባችሁ ነገን ዛሬ ላይ መሥራት ትጀምራላችሁ። ነገን ዛሬ ላይ መሥራት ማለት ዛሬን ገሎ ስለ ነገ መጨነቅ ማለት አይደለም፤ ዛሬን በአግባቡ እየኖሩ ለነገ የሚሆን መልካም ስንቅ መሰነቅ ማለት ነው። መልካም ስንቅ ጥሩ ከማሰብ፣ ጥሩ ከመመኘት፣ ጥሩ ከማለም የሚጀምር ነው። ጀንበራችሁን ለማንም አትስጡ፤ የነጋችሁ ብርሃን የሚበራው ዛሬ ባበራችሁት ብርሃናችሁ ልክ ነው። ዛሬአችሁ ጨልሞ ከሆነ ደግሞ ትናንት ላይ ጥሩ ብርሃን አላበራችሁም ማለት ነው።
ዛሬን በመኖር፣ ለራሳችሁም ለሌሎችም መልካም በማሰብ ነጋችሁን ብሩህ ማድረግ ይቻላችኋል። አንዳንዶች የትናንት ብርሃን ከዛሬአቸው የተሻለ መስሏቸው ዛሬአቸውን ያጨልማሉ። ጥቂት ልባሞች ደግሞ በዛሬ ብርሃናቸው የነገ አለማቸውን አሻቅበው ያያሉ።
ሁላችንም ነገን አናውቀውም..ነገ የሚሰምረውም ሆነ የሚበላሸው ዛሬ በምንሆነው ነገር ነው። ዛሬ ላይ ለሀገር ወገን የማንበጅ ሆነን እየኖርን ከሆነ፣ ራሳችንን በእውቀት በመልካም አስተሳሰብ እየገነባን ከሆነ፣ በተንኮል በራስ ወዳድነት እየኖርን ከሆነ ብሩህ ነገ አይኖረንም ። ብሩህ ነገ የሚፈጠረው ብሩህ ዛሬ ባላቸው ሰዎች ነው። ስለዚህም ነጋችሁ ያማረ ይሆን ዘንድ ዛሬአችሁ ያማረ መሆን ግድ ይለዋል።
ትናንት ላይ ሆነን ነገ የምንለው ዛሬን ነው..፤ ትናንት ላይ ሆነን ነገ ባልናት ዛሬ ላይ ከትናንቱ የተሻለ ህይወት መኖር ካቻልን ድርብ ተሳስተናል ማለት ነው። ባዲሷ ዛሬ ላይ ቆመን ሌላ ነገ ከተመኘን ደግሞ የቀናት ጥገኛ እንጂ ለውጥ ናፋቂዎች አይደለንም ማለት ነው።
የሰው ልጅ በቃኝን የማያውቅ ራስ ወዳድ እንስሳ ነው። ምኞቱ እውን ይሆንለት ዘንድ ትናንትም ዛሬም ነገም ያስፈልጉታል፤ ግን የትኛውም ቀን ከዛሬው አይበልጥም..የሁሉም ጽንሰትና ውልደት በዛሬ እትብት ውስጥ የተቋጠረ ነው። ደግሜ እላችኋለሁ፤ ያለ መልካም ዛሬ መልካም ነገ የለንም። ዛሬ የነገ ስንቅ ናት..ነገን ማያ መስተዋትም። ዛሬ የዘላለማት ጅማሬ ነው።
በእድሜአችሁ ላይ የምትጽፉት መልካም ቀን ሁሉ ከዛሬ አስተሳሰባችሁ የሚነሳ ነው። ዛሬን እያማረራችሁ የምትገነቡት አዲስ ሰማይና ምድር የለም። እንድትኖሩበት ከተሰጧችሁ ቀናት ሁሉ የዛሬዋ ቀን ልዩ ናት። ይቺ ቀናችሁ ናት ተስፋ ያደረጋችሁትን ነገ የምትሰጣችሁ። ይቺ ቀናችሁ ናት በእናንተ እና በዘላለማት መካከል የተሰመረችው። በመጨረሻም እንዲህ አልኩ..ትናንትም ነገም ዘለዓለምም ከዛሬ አይበልጡም የሁላችንም ምርጡ ቀን ዛሬ ነው…ከዛም አዲስ ነገ..ከዛም አዲስ ህይወት በቃ እንደዚህ ነው። አበቃሁ። ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2013