ጥበብ በሰዎች የሚፈጠር ሰዎችን የሚያንጽ ልዩ ሚስጥር ነው፡፡ የሰዎች ስልጣኔ፣ አኗኗርና ዘርፈ ብዙ የህይወት ልምድ ማሳያ መሳሪያም መሆኑ ይነገራል፡፡ ሀገር በቀል ጥበብ ሳይቀየጥ ለማህበረሰባዊ ጥቅም ሲውል ጥበቡ ያፈራው ማህበረሰብ ደርሶበት የነበረውን ስልጣኔ ያመላክታል፡፡ ጥበብ ከዘመን ጋር ሳይለወጥ በጊዜ ርዝመት ተበግሮ ሳይቀየጥ የቀደመን ጊዜ ሲያመላክት የጥበቡ ረቂቅነት ያስደምማል፡፡
በኢትዮጵያ ደቡብ ክልል ደራሼ ወረዳ የሚገኙ አራት ብሄረሰቦች በጋራ ያጣመረ የብዙ ሀገረሰባዊ ጥበቦችና ባህሎች ቢኖሩም፤ ‹‹ፊላ›› ደራሼዎችን በአንድነት የሚያሰልፍ ልዩ የሙዚቃ ጥበባቸው መለያቸው ነው፡፡ ‹‹ፊላ›› በክዋኔ ታጅቦ ያማረ ህብር ዜማ የሚከወንበት በዋሽንት መሰል በትንፋሽ የሚሰራ የሙዚቃ መሳሪያ የሚታጀብ ጥበብ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ ቀለም ያለው ኢትዮ ጃዝ የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ ስልት በአለም አቀፍ መድረክ ያስተዋወቀው ዶክተር አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ በደራሼዎቹ ሙዚቃ ተማርኮ ጥናትና ምርምር ማድረጉ አልቀረም፡፡ እንደ ዶክተር አርቲስት ሙላቱ ‹‹ፊላ›› የጃዝ ሙዚቃ መነሻ የሆነና ልዩ የረቀቀ የሙዚቃ ጥበብ ነው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ የረቀቀ ሳይንሳዊ ሙዚቃ መሆኑን በመግለጽ፤ የደራሼዎች ፊላ ባለ ሰባት ኖታ መሆኑን በጥናቱ አረጋግጧል፡፡
እያንዳንዳቸው የተለያየ ድምጽ የሚያወጡ 24 የሚደርሱ የራሳቸው ርዝምት፣መጠንና ቅርጽ ያላቸው ከቀርከሀ የሚሰሩት ዋሽንት መሰል የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያዎች ጥምረት ነው ‹‹ፊላ››ን የሚፈጥረው፡፡ በአንድ ሰው መሪነት ምቱ ሳይዛባ ያለንዳች መዛነፍ በእግርና አካል እንቅስቃሴ ይታጀባል፡፡ ‹‹ፊላ›› በክዋኔ የታጀበ የሙዚቃ መሳሪያው ተጫዋቾችና የክዋኔ ተግባር አጠቃሎ የያዘ ሲሆን፤ እነዚህ በማህበረሰቡ በልዩ ኪናዊ ጥበብ የተሰሩ ሙዚቃ መሳሪያዎች በአንድ ላይ ሲደመጡ አካባቢውን የሙዚቃ ድግስ ማዕድ ያለበት ያስመስሉታል፡፡
ክብ ሰርተውና ከሁለቱም ጾታ ተውጣጥተው በትንፋሽ ጥሩ የሆነ ሰው ተመርጦ የሚከውነው ይህ ህብራዊ ዜማ የራሱ የሆነ ልዩ ጣዕም አለው፡፡ ተሰምቶ የማይሰለች ተደምጦ የማይጠገብ ከዋኞቹም እየተጫወቱ በሄዱ ቁጥር መሳሪያው ጉልበት ይሰጣቸው ይመስል ቅላጼውና ድምጸቱ ይበልጥ እያመረ ለረጅም ሰዓታት ሲጫወቱ ለተመለከተ አንዳች የአግራሞት ስሜት በውስጡ ማጫሩ አይቀርም፡፡
ወጣት ሰለሞን ገብረ ዮሀንስ የሙዚቃ መምህርና የባህል ጥናት ተመራማሪ ነው፡፡ ሰፊ ጥናት በሚፈልገው በፊላ ሙዚቃና ክዋኔ ላይ ምርምሮችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ሰለሞን ፊላ ሳይንሳዊ ሙዚቃ የሙዚቃው ከዋኞችን ደግሞ የሙዚቃው ሳይንቲስት ይላቸዋል፡፡ ወጣት ሰለሞን ሙዚቃን ቀርቦ የመመርመሩና የማጥናቱ ስራ የሰርክ ተግባሩ ነውና ፊላን በተለየ መነጽር ይመለከተዋል፡፡ ፊላ የኢትዮጵያውያን ጥበበኞች የተጠበቡበት ከዘመናዊ ሙዚቃ ቀድሞ የተገኘ ሀገር በቀል ልዕቀት ማሳያ መሆኑን የሚናገረውም በምክንያት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቅኝት በተለምዶ አራት ከሚባለው የዘለለ ለመሆኑ በተለያዩ የሀገራችን ክፍል የሚገኙ ሀገር በቀል የሙዚቃ ቅኝቶችን ለማሳያነት በመጥቀስ የሙዚቃ ባለሙያና ተመራማሪው ሰለሞን ያስረዳል፡፡ ፊላ ደግሞ የራሱ የሆኑ ልዩ ቀለም የተመጠነ ምት የተሟላ ኪናዊ ውበት የተላበሰ የረቀቀ ሙዚቃ መሆኑና አንድ የተለየ ቅኝት እንዳለው ያነሳል፡፡ ከዋኞቹ ተናበው መስራት፤ 24 የሚደረሱ የሙዚቃ መሳሪያዎቹ በአንድ ሰው መሪነት ተሰናስሎ በውህደት የማይሰለች ዜማ መፍጠር መቻላቸው የሚደንቀው ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድ ሰው መሪነት ሙዚቃን መምራት ከአውሮፓውያን ቀዳሚ የሚያደርጋቸው ማሳያ መሆኑን ይገልጻል፡፡
ፊላ የማህበረሰቡ ታሪክ መንገሪያና ማሳወቂያም ጭምር ነው፡፡ በፊላ የሙዚቃ ትርኢት ላይ ከዋኙ የማህበረሰቡ ባህላዊ መገልገያ እቃዎችና ልዩ ልዩ የሰብል ምርቶችም ጭምር የሚቀርቡበት ሂደት በራሱ የተለየ ድባብ ይፈጥራል፡፡ በፊላ ላይ የሚታየው ዳንስና ክዋኔ በዋናነት የማህበረሰቡ የአኗኗር ዘዴ ማሳያም ጭምር መሆኑን ተመራማሪው ይገልጻል፡፡ ፊላ ዘርፈ ብዙነቱ ያልተነገረ ነገር ግን የረቀቀ የሙዚቃ ጥበብ ነው፡፡
የሙዚቃ መሳሪያውን በመጠንና በሚያወጡት ድምጽ ፍሰት በሶስት ይከፍሉታል የሙዚቃ መሳሪያ ፈጣሪዎቹ፡፡ ከቀርከሀ የሚሰሩት ፊላዎች እያንዳንዳቸው መጠሪያ ስምና የቅርጽ (መጠን) ልዩነት አላቸው፡፡ ከ50 እስከ 70 ሴንቲ ሜትር የሚደርሱ በሸንበቆ የተሰሩ ዋሽንት መሰል ዘንጎች ‹‹ቶንቶሊያ›› (ካሳንያ) ፣መካከለኛ ከ20 እስከ 45 ሴንቲ ሜትር የሚደርሱ ዘንጎችን ፣‹‹ኦታንትያ›› ከ10 እስከ19 ሴንቲ ሜትር የሚደርሱትን ደግሞ ‹‹ፍትንፍታያ›› በማለት ሰይሟቸዋል፡፡ ከነዚህ የተለያየ ርዝመት ያላቸው የሙዚቃ መሳሪያዎች የሚወጡ ድምጾች አንዱ ካንዱ ጋር የተለያዩ ናቸው፡፡
መምህር ምስራቅ ገዛኸኝ በአርባ ምንጭ መምህራን ኮሌጅ የሙዚቃ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡ ፊላ በተሰኘው የሙዚቃ መሳሪያና ክዋኔ ላይ የተወሰኑ ጥናት ያደረጉ ሲሆን፤ ሙዚቃ በመማር እና በልዩ ክህሎት የሚፈጠረው ሙዚቃ (ዜማ) የመፍጠር ጥበብ፤ ደራሼ ላይ በህብረተሰቡ በቀላሉ ባማረ ክዋኔ ታጅቦ በሚከወን ፊላ ላይ መመልከት መቻሉን ይገልጻሉ፡፡ የደራሼዎች የረቀቀ ሙዚቃዊ ጥበብ 24 የሚደርሱ የራሳቸው ርዝመት መጠንና ቅርጽ ያላቸው ከሸንበቆ የሚሰሩት ዋሽንት መሰል የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያዎች በጥምረት የሚከወነው በህብር የሚፈጠረው ድምጽ ማህበረሰቡ በራሱ ክህሎት የፈጠረው የረቀቀ ጥበብ ለመሆኑ መስካሪ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ቅኝቶች በተለምዶ ከተቀመጡት ከፍ ያለ ቁጥር እንዳለው የሚናገሩት መምህር ምስራቅ፤ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በተለይ በደቡብ ክልል ገና ያልተነኩና የራሳቸው ልዩ ቀለም ያላቸው እስካሁን በጥናት ከተለዩ የኢትጵዮያ ሙዚቃ ቅኝቶች ለየት ያሉ የሙዚቃ ድምጽና ክዋኔዎች መኖራቸውን ያነሳሉ፡፡ የእነዚህ የሀገረሰብ የጥበብ ውጤት የሆኑት ሙዚቃዎች ተጠንተው ቢሰራባቸው እንደ ሀገር የዳበረ የሙዚቃ ሀብት ባለቤት እንድንሆን ያደርገናል፡፡
ሙዚቃ ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር ገና ትኩረት ያልተሰጠው መስክ መሆኑን የሚናገሩት መምህር ምስራቅ፤ የሙዚቃ ሀብታችን ተጠንቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች ቢስፋፉ በጎ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ በክልል ደረጃም ቢሆን ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ትልቅ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
የደራሼ አካባቢ ማህበረሰብ በሰርክ ተግባሩ በተለያየ መንገድ የሚጠቀምበት ፊላ ዋንኛ መከወኛ ጊዜና ሁኔታዎች በጥንት ዘመን የማህበረሰቡ ንጉስ ከህዝቡ ጋር ውይይት ለማድረግ በሚቀርብበት ጊዜ ለንጉሱ መቀበያነት፣ ለህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳ፣በሰርግ ስርዓት፣በአዝመራ ስብሰባ ወቅትና በሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ወቅት ባማረ ክዋኔ በራስ በረቀቀ ጥበብ የተሰራውን የሙዚቃ መሳሪያ ፊላ ማህበራዊ ገጠመኙን ይከሽኑበታል፡፡
ወጣት ታደሰ ካይዛ የአካበባቢው ተወላጅ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ፊላን እየተጫወተ እንዳደገና ለሙዚቃ መሳሪያውና ለክዋኔው ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ይናገራል፡፡ ታደሰ ከጓደኞቹ ጋር የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት ወደ መስክ ሲሄዱና ሲመለሱ ፊላ ከመጫወት ባሻገር ስራ ሰርተው ሲደክማቸው መሀል ላይ የድካም ስሜት ለማጥፋትና የስራ ስሜት ለማነቃቃት ፊላ መሳሪያቸው ነው፡፡ ለታደሰ በአንድ ቅኝት በህብረት የሚወጣው ድምጽ ልዩ ሀሴት የሚፈጥርለት የማህበረሰቡ ጥበባዊ ሀብት ነው፡፡
ከመሀል አንዱ መሳሪያ ጎሎ ድምጹ ሲሰማ ልዩነትን የሚፈጥረው በሁሉም የፊላ መሳሪያዎች ደግሞ የተንሰላሰለ ጥዑም ሙዚቃ መንቆርቆር የአንድነትና የህብረት ሚስጥር አስተማሪም ጭምር ነው፡፡ በአብሮነት የሚደምቀው የፊላ ሙዚቃዊ ክዋኔ የማህበረሰቡ ጥምረትና መተሳሰር ሌላኛው ማሳያ ነው፡፡ ፊላ በጋራ የሚከወን በመተባበር የሚፈጠር የህብረት ድምጽ ነውና ማህበረሰቡ በጋራ መቆም አብሮ ማበር የተለየ ውብ ቀለም ፈጥሮ ከፍ ያለ ውጤት ላይ መድረስ ያስተምረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2011
ተገኝ ብሩ