ዘለዓለም የሣጥን ወርቅ (የእፀ ሣቤቅ አባት)
በሕይወት ስንኖር የመኖርን ትርጉም ከምንረዳባቸው አጋጣሚዎች ውስጥ አንዱ ራዕይ ነው። ፋኖስ ያለ ላንባ፣ ሻማ ያለክር ብርሀን እንደማይሰጡ ሁሉ ሕይወትም ያለ ራዕይ ምንም ናት። ለማሸነፍም ሆነ ለመሸነፍ ወደዚህ ዓለም አልመጣንም ራሳችንን የፈለግነውን አድርገን የምንፈጥረው ራሳችን ነን። የተፈጠርነው ከታላቅ ሀይል ጋር ነው፤ ያን ታላቅ ሀይል ፈልጎ የማግኘት ሀላፊነት ግን አለብን። ሀይላችንን ስናውቅ ብቻ ነው ተዐምር መስራት የምንጀምረው። የተፈጠርነው በምክንያት ነው ስንኖርም በምክንያት መሆን አለበት። ወደዚህ ዓለም ዝም ብለን አልመጣንም፤ ለዓለም ሁሉ የሚበጅ፣ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚጠቅም ታላቅ ሥራ ሠርተን እንድናልፍ ነው። ብዙዎቻችን ግን ይኼን እውነት አናውቀውም። ለምን እንደምንኖር የማናውቅ ብዙዎች ነን። ለምን እንደምንማር፣ ለምን እንደምንሠራ፣ ለምን እንደተፈጠርን የማናውቅ ብዙዎች ነን።
ከዚያኛው ዓለም ወደዚህኛው ዓለም የመምጣታችን ምስጢር አንድ ነው። እርሱን ታላቅ ተግባርን መፈፀም ነው። አብዛኞቻችን ግን ለሌላው የሚበጅ ቀርቶ ለራሣችን የሚሆን ምንም የለንም። ካለራዕይ በደመነፍስ የምንኖር ነን። ሀገር ራዕይ ያላቸው ወጣቶች ትፈልጋለች። በማሠብ የሚኖሩ ትውልድ ያሥፈልጓታል። በየትኛውም ጊዜ የተፈፀሙ መጥፎ አጋጣሚዎች ሁሉ ራዕይ በሌላቸው ሰዎች የተፈፀሙ ናቸው። ዝም ብላችሁ አትኑሩ። በውስጣችሁ ታላቅ ሕልምን ትከሉ። በመከራ የማይዝል በውጣ ውረድ የማይረታ ጽኑ ማንነትን አዳብሩ። በዓለም ላይ ታላላቅ ተዓምራቶች የተሠሩት ራዕይ ባላቸው ጥቂት ግለሠቦች ነው። ራዕይ ሕይወትን ውብ የምናደርግበት ጥበብ ነው። ራዕይ ያለ ትጋት ያለ ጠንክሮ መሥራት ምንም ነው። አብዛኛው ሰው ራዕይ እንዳለው የሚናገር ነው።
በየትኛውም ሁኔታ ላይ ያለን ሰው መጠየቅ ብትችሉ ማከናወን የሚፈልገው ብዙ ነገር እንዳለ ይነግራችኋል። ሕጻን ሆነን ስታድጉ ምንድነው መሆን የምትፈልጉት ስንባል ብዙ ነገር አውርተን እናውቃለን። ግን አንዳችንም ከወሬ ባለፈ ሕልማችንን እውን ለማድረግ ሥንጥር አንታይም። አንዳችንም ለሕልማችን ሥንለፋ፣ ደፋ ቀና ሥንል አንታይም። አብዛኞቻችን ተኝተን የምንመኝ፣ ሳሣንሰራ ትልቅ ነገርን የምንፈልግ ነን። በየሠፈሩ ተቀምጠን እየዋልን፣ እየቃምን እያጨስን ከሱስ መውጣት ተሥኖን ለጠየቀን ሁሉ ግን ራዕይ እንዳለን የምናወራ ነን። በክፋትና በተንኮል ተሞልተን ለሀገርና ለሕዝብ ክብር የቆምኩ ነኝ ሥንል የምንጎርር እንዲህም ነን። ራዕይ ያለው ሰው በምንም ተዓምር ወደ ሱስ፣ ወደ ጥፋት አይገባም። ራዕይ ከመጥፎ ነገር መከልከል ነው። ራዕይ ያለው ማህበረሠብ በምንም ምክንያት ወደ ውድመት ወደጥፋት አይዘምትም።
ራዕይ እኮ ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ ጥሩ ሆኖ መቆም ማለት ነው። ራዕይ ማለት እኮ ለምናልመው ጥሩ ነገር ሥንል ዛሬን መታገስ እንዲህም የሚገለጽ ነው። እኛ ግን እያጠፋን፣ እያፈረስን፣ እየዘረፍንና እየዋሸን ራዕይ አለን የምንል ሕዝቦች ነን። ራዕይ ሥልጣኔ ነው። ሀገር በአንድም በሌላም መልኩ ራዕይ ያላቸው ሕዝቦች ያስፈልጓታል። ራዕይ የሌለው ሕዝብና ትውልድ ከጥፋት ሌላ ልማት የለውም። የእስካሁኑ አበሣችን ከራዕይ መራቃችን የፈጠረው ጥፋት እንደሆነ ነው የማስበው። አሁንም ራሣችሁን እንድታድሱ እመክራችኋለው። ያለሕልምና ራዕይ የኖራችሁባቸው ጊዜያቶች የከሠራችሁባቸው ናቸው። ዳግመኛ ከሥራችሁ እንዳትኖሩ ራሣችሁን ፍጠሩ። ራዕይ ያለ ሥራ ማንገቻ የሌለው ከበሮ ነው። ያለ ሥራ ያለ ትጋት ራዕይ ብቻውን ዋጋ የለውም። ራዕይ እውነት የሚሆነው በሥራና በትጋት ሲታገዝ ብቻ ነው። በፈተና የማይወድቅ፣ በመከራ የማይዝል ብርቱ ክንድ ያሥፈልጋችኋል። ከምንም በላይ ደግሞ ቅን ልብና መልካም ሐሳብ ያስፈልጋችኋል። ከሕዝብ ላይ እየሠረቀና እየቀማ የሚኖር አንድ ሰው ራዕይ አለኝ ብሎ ቢያወራ ትርጉም የለውም።
ራዕይ ለራሥም ለሌሎችም ታማኝ ከመሆን የሚጀመር ነው። የእኛም ብርሀን የሚፈካው ለሌሎች ብርሀን መሆን ሥንችል ነው። እኛም የሚሣካልን ለሌሎች መልካምና ከሕልማቸው እንዲገናኙ ማገዝ ሥንችል ነው። በክፉ ልብ ውስጥ ሥኬት የለም። በውሸተኛና በከሐዲያን ዘንድ ውድቀት እንጂ ደስታ የለም። ስለዚህም በታማኝነት ሕልማችሁን እውን ለማድረግ ኑሩ። ኖረን እንድናልፍ ብቻ አልተፈጠርንም። ታላቅ ነገርን እንድናደርግ እንጂ። ታላቅ ነገር ደግሞ መገኛው ከየትም አይደለም፤ ከእኛ ውስጥ ነው። ራሣችሁን በትጋትና በቁርጠኝነት ለለውጥ ካዘጋጃችሁ እመኑኝ ሥኬታማ ትሆናላችሁ። ሣይሰሩ ከመመኘት፣ ተቀምጦ ከመናፈቅ ውጡ። ከጥላቻ ከምቀኝነተ ተለዩ። ልባችሁን በፍቅር በይቅርታ ሞልታችሁ አሁናችሁን ጀምሩ። ለራሣችሁ እድል ስጡ…ከነበራችሁበት…ከኖራችሁት አስተሳሰብ ውጡና በትጋት የታገዘ አዲስ ማንነትን ልበሱ። ለራሣችሁ ሁሌም የተሻለ ነገር እንዲያይ፣ የተሻለ ነገር እንዲፈጥር እድል ስጡት። የምትፈልጉት ሕይወት የእናንተ ለመሆን እናንተን እየጠበቀ ነው። እስካሁንም በከንቱ ምኞታችሁ ከንቱ ሆናችሁ ኖራችኋል። ከእንግዲህ ግን ለውጥ ያሥፈልጋችኋል ለውጣችሁ ደግሞ አእዕምሯችሁ ውስጥ ነው…ትክክለኛውን እናተን እየጠበቀ።
አሁኑኑ ሥራ ወዳድ የሆነውን፣ በትጋት በልፋት የሚያምነውን፣ በአንድነት የሚደነቀውን እናተን ፍጠሩት። ሁሉም ነገር ያለው አስተሳሰባችን ውስጥ ነው ። ወንድምክን እየጠላክ፣ በብሄርና በሀይማኖት እየተባላክ የምታሣካው ጥሩ ነገር የለም። የተሠራ እያፈረስክ፣ በወገኖችህ ላይ ጨካኝ ሆነህ የምታመጣው ገድል የለም። ሥኬት ከትህትናና ከመታዘዝ የሚጀምር ነው። እኛ ከተለወጥን ሥኬት የትም ቦታ አለ። ታላላቆቹ ሀገራት የአሁኑ ስሥልጣኔ ላይ የደረሱበት ትክክል ያልሆነ ራሳሣቸውን ካፈረሱ በኋላ ነው። ትክክል ባልሆነ አስተሳሰብ ውስጥ ትክክል የሆነ ነገር የለም።
ተፈጥሮ ውስጣችሁ ያስቀመጠውን ታላቅ ሀይል ፈልት። ዝም ብላችሁ ባክናችሁ አትኑሩ…ሀገር የሚለውጥ ሀይል ውስጣችሁ አለ። ወጣትነታችሁን ለለውጥ ተጠቀሙት። ከማይጠቅማችሁ ከማንኛውም ነገር ወጥታችሁ ራሣችሁን በትክክለኛ ቦታ ላይ አግኙት። በምንም ሁኔታ ላይ ብትሆኑ ራሣችሁን ለለውጥ ካዘጋጃችሁ መለወጥ ይቻላችኋል። በአምና አስተሳሰብ ዛሬን አትኑሩ። የትላንት አስተሳሰባችሁ የፈየደላችሁ አንዳች ነገር ከሌለ ከዚያ ውጡና ለውጥ በሚያመጣ አዲስ አስተሳሰብ ቀይሩት። ራሣችሁን ካወቃችሁ፣ ለምን ሰው እንደሆናችሁ ከተገነዘባችሁ እመኑኝ ተዓምር መሥራት ይቻላችኋል። ምንም ሁኑ፣ በየትኛውም ሁኔታ ላይ ቁሙ ታላቅ መሆን ይቻላችኋል። እናንተ ብቻ ጀምሩ… እናተ ብቻ ለለውጥ ተዘጋጁ። ፈላስፋው ዚግዚግለር… ”ለመጀመር ታላቅ መሆን አይጠበቅባችሁም፣ ታላቅ ለመሆን መጀመር ግን ግድ ይላችኋል” ሲል ይነግረናል። እውነት ነው ታላቅነት ያለው በመጀመር ውስጥ ነው አብዛኞቻችን ጀምረን የምናቆም እንጂ የምንጨርስ የለንም።
የዚህ ዓለም ድንቁ ነገር ያለው በመጀመር ውስጥ ነው። ውድቀትን እየፈራን፣ እከስር ይሆን እያልን የምናሣካው ምንም ነገር የለው። ቁርጠኛ ሁኑ..ማመንታትን ከውስጣችሁ አውጡ። በራሳሣችሁ ካመናችሁ መቼም የትም ሥኬታማ መሆን ይቻላችኋል። ራሣችሁን ተመልከቱት…ውስጣችሁን እዩት። ጥንካሬያችሁ የቱ ጋ እንዳለ ድረሱበት። ድክመታችሁ የት እንደሚገኝ እወቁት። ሥኬታችሁ የለው ጥንካሬያችሁ ያለበት ቦታ ጋ ነው። ከሌሎች ላይ ዓይናችሁን አንስታችሁ ራሣችሁን ተመልከቱት። ደሞ ራስን መመልከት ይቻላል እንዴ እንዳትሉኝ? ራስን መመልከት ውስጥን መመልከት ነው። ከራስ ጋር መነጋገር፣ ከራስ ጋር ማውራት..መስማማትም ነው። ማየት ከተግባር ይቀድማል።
በሕይወታችሁ ውጤታማ ትሆኑ ዘንድ አንድን ነገር ከማድረጋችሁና ከመወሰናችሁ በፊት ከራሣችሁ ጋር ተማከሩ። ነገሩን ተረዱት። ስለዚያ ነገር በሚገባ እወቁ። የእስካሁኑ ክሥረታችሁን ካለማየት፣ ካለማገናዘብ በሥሜት የሆነ ነው። ሩጫ ሥናይ አብረን የምንሮጥ፣ ድምጽ በሠማን ቁጥር በለው የምንል ብዙዎች ነን። ሁሌም ለምን ስትሉ ራሣችሁን ጠይቁ። አንድን ነገር ከማድረጋችሁ በፊት፣ ውሣኔ ከማድረጋችሁ በፊት ራሣችሁን ለምን ስትሉ ጠይቁ። የምንፈልጋቸው አብዛኞቹ የሕይወት መልሶች ለምን በሚለው ጥያቄ ውስጥ የተቀመጡ ናቸው። ለምን ብላችሁ ሣትጠይቁ የምትከውኑት ነገር ሁሉ ፍጻሜው ሥህተት ነው። በምክንያት፣ በማገናዘብ ኑሩ ያልኳችሁ ለዚህ ነው። አሁን ላይ ሀገራችን ከምንም በላይ የሚያሥፈልጋት ከድርጊት በፊት ለምን ብሎ የሚጠይቅ ወጣት ነው። ማየት እስከቻላችሁት ድረስ ርቃችሁ እዩ። ርቃችሁ ተመልከቱ። መሄድ እስከቻላችሁ ድረስ ርቃችሁ ሂዱ። ማሰብ እስከቻላችሁ ድረስ ርቃችሁ አስቡ። ሥኬታችሁ ባያችሁት ልክ፣ በሄዳችሁት ልክ፣ ባሰባችሁት ልክ የሚመዘን ነውና።
ሥኬታማ ለመሆን ዓለም አንድ ሚስጢር ብቻ ነው ያላት፤ እርሱም ራዕይና ትጋት የተጣመሩበት ሀይል ነው። ከፍ ሲል እንደነገርኳችሁ መልካም ነገር የልብና የጭንቅላት ውጤት ነው። ካለህሕልምና ራዕይ በመኖራችን መኖር የሚገባንን ጣፋጭ ሕይወት እየኖርን አይደለም። እንደ ሀገር እንደ ሕዝብ እንደ ግለሠብም ብናየው እንኳን የእኛ ሕይወት እጅግ የሚያሣዝን ነው። በዙሪያችን ሁሉ ሞልቶ ምንም እንደሌለን ነን። በተፈጥሮ ታድለን፣ በውሀ ሀብታችን የአፍሪካ የውሀ ገንቦ የሚል ሥም ወጥቶልን ውሀ የሚጠማን ነን። ለም መሬታችን ከእኛ አልፎ ጎረቤት ሀገራትን ሲያጠግብ እኛ ግን ርሀብተኛ ነን። ለምን ይመሥላችኋል? እኔ ግን ራዕይ ስለሌለን ነው እላለው። ሕብረት አንድነት ስለጎደለን ነው እላለው። ሥራ ስለጠላን፣ ለለውጥ የሚሆን የነጠረ ሐሳብ ስለሌለን ነው እላለው። እንደዚያማ ባይሆን በብዙ ነገራቸው ከእኛ ያነሱ ሀገራት ዛሬ ላይ ርዳታ ሲሰጡን ቆመን አናይም ነበር። እንደዛ ባይሆን እማ ብዙዎች ከኋላችን ተነስተው አይቀድሙንም ነበር። በተፈጥሮ ሐብታቸው ከእኛ ያነሱ ሀገራት አይበልጡንም ነበር። አሁንም ጊዜው አልረፈደም አሁን ላለችው ሀገራችን አንድነታችን ዋጋ አለው።
በራዕይ እንኑር። የሚባክን ጊዜ፣ የሚባክን ወጣትነት እንዳይኖረን እንትጋ። ሕልማችሁን ሣታሳኩ መሽቶ የሚነጋ ቀንና ሌት አይኑር። ለራዕያችሁ አትተኙ። በከንቱ ኖራችሁ አትለፉ። ከትላንት እስከዛሬ ብዙዎች ያለ ራዕይ ለራሣቸውም ለሀገራቸውም ሣይጠቅሙ አልፈዋል። ከእነሱ ውስጥ እንዳትደመሩ በማሰብ የሚኖር ምክንያታዊ ሆናችሁ ቁሙ። አሁኑኑ የምትፈልጉትን ሰው ሆናችሁ ከአልጋችሁ ላይ ተነሱ። ብዙ ያልተሣኩ ሕልሞች፣ ብዙ ያላለቁ ምኞቶች፣ ያልተቋጩ ተሥፋዎች መቃብር ውስጥ አሉ። ከማለፋችሁ በፊት ራሣችሁን ጠቃሚ ዜጋ አድርጋችሁ ፍጠሩት። ሕይወት አጭር ናት። በዚህ አጭር ጊዜያችሁ ውስጥ ወደሚጠቅማችሁ ብቻ ሩጡ። ለሐሜት ለትችት ለአልባሌ ነገር ከዕድሜያችሁ ላይ አንዳች ቀን አታዋጡ። አሸናፊ ስትሆኑ በማሸነፍ ሐሳብ ላይ ነው የምትጠመዱት። ከንቱ ስትሆኑ ደግሞ ሐሳባችሁ ሁሉ ስለከንቱ ነገር ይሆናል። ራሣችሁን ግዙት።
ትላንትን ገላችሁ ወደዛሬ ኑ…ዛሬ ለእናተ የሚሆን ብዙ በረከቶች አሉት። ብዙዎቻችን ከትላንት ስላልተላቀቅን ዛሬያችንን እንደ ትላንት እየኖርን ከነበርንበት ሣንቀሳቀስ እንኖራለን። ለምንም ነገር ዓላማ ይኑራችሁ። ተኝታችሁ ስትነሱ፣ መሽቶም ወደማደሪያችሁ ስትሄዱ ለራሣችሁ የምትነገሩት አዎንታዊ መልዕክት ይኑር። እየበራችሁ ኑሩ…ጎዳና ላይ ከምታዩዋቸው ሰዎች ተለዩ። ብሩህ ነገን የምታዩበትን ፍላጎት በውስጣችሁ አቀጣጥሉ። ሐይላችሁን በትንሽ ነገር አትጡት። ራሣችሁን ከሁኔታዎች በላይ አጠንክሩ። ሕይወት እሽቅድምድም ናት። ያሰብነው ነገር ሁልጊዜ ላይሆን ይችላል። መቻልን፣ ተሥፋ ማድረግን እንደገና ሞክሩ፣ ወድቆ መነሳትን መለማመድ ግድ ይላችኋል። ወድቀው የቀሩ ብዙዎች አሉ። ሞክረው አልሣካ ሲላቸው በዚያው ወደ ጨለማ የገቡ ጥቂቶች አይደሉም። ጥንቃሬያችሁ የሚለካው በወደቃችሁ ቁጥር መነሣት ስትችሉና ሕልማችሁን እውን ስታደርጉ ብቻ ነው። እኔም እናተም ሁላችንም ባለን አቅም ለሀገርና ለሕህዝባችን ጥቂት ነገር ማድረግ ብንችል ኢትዮጵያ የማታድግበት ሕዝባችን ከድህነት የማይወጣበት ምንም ምክንያት የለም እያልኩ ላብቃ። ቸር ሠንብቱ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2013