ዳንኤል ዘነበ
በማኅበረሰብ የንቃተ ህሊና መለኪያ (Social Pyramid) ከፍ ያለ ቦታ ከሚሰጣቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በቀደምትነት የምናገኘው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወይም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ነው። ዩኒቨርሲቲ የሚለው ቃል “ዩኒቨርሳል” ከሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተወሰደ ሲሆን፤ በአማርኛ ትልቁ ዓለም የሚለውን ፍቺ ይሰጣል። የሰው ልጅ በትምህርት አለም ውስጥ በሚኖረው ጉዞ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሲገኝ በእውቀት ደረጃው ይጎለብታል፤ የአስተሳሰብ አድማሱ ይልቃል፤ ለነገሮች የሚኖረው አተያይ ይሰፋል ተብሎ ይታሰባል።
ይህም ዩኒቨርሲቲዎች የሚቋቋሙበት መሠረት ዓለም አቀፍ አስተሳሰቦችን ማንሸራሸር እንዲችሉ መሆን እንደሚገባ አመላካች ነው። የሀገራችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁመና ለዚህ የቀረበ ስለመሆኑ ያጠራጥራል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች፣ የጎጠኝነትና የቡድን ፀብ መናኸሪያ እየሆኑ መምጣታቸው በዋነኝነት ይጠቀሳል። ተማሪዎች በፖለቲካ እና በዘር ቆጠራ ተጽዕኖ ወድቀው ምክንያት አልባ ፀቦችን ከማስተናገድ ተሻግረው የሞት መናኸሪያ እስከመሆን ደርሰዋል።
ከትልቁ ዓለም ወደ መንደር የወረዱት ተቋማት
የ2011 የትምህርት ዘመንን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። በዚህ ዓመት በሀገሪቱ ከሚገኙት 50 የሕዝብ ዩኒቨርሲቲዎች በአንድ ሶስተኛው የተለያየ መጠንና አይነት ያላቸው የተማሪዎች ሁከትና ብጥብጦች አጋጥመው እንደነበር ይታወሳል። ለዚህ ደግሞ ተቋማቱ ከፖለቲካ ነፃ አለመሆናቸው፣ የአመራሮች ቁመና እና ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች በምክንያትነት ይቀርባሉ። ተቋማቱ ከፖለቲካ ነፃ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ ሰፊ ችግር የተፈጠረ መሆኑን ከሚገልፁ በርካታ ምሁራን መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ይጠቀሳሉ።
ዶ/ር ዳኛቸው እንዳሉት «በኢትዮጵያ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሪዎች እና ባለሙያዎች ከፖለቲካ ነፃ ባለመሆናቸው ምክንያት የግጭትና የጦርነት ቀጣና ሆነው ዘመናትን እንዲጓዙ አስገድዷቸዋል። በወታደራዊው መንግስት የደርግ ዘመን በርካታ የዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎችና መምህራን ወደ ፖለቲካው ሲገቡ ‹ወዶ ገቦች› የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው ነበር። አሁንም ያለው እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም» የሚል ነበር።
ከዶክተር ዳኛቸው ንግግር ዩኒቨርሲቲዎች ከፖለቲካ ተፅእኖ ጋር የሚያደርጉት ጉዞ ትናንት እስከ ዛሬ መጓዙን እንገነዘባለን። በየዩኒቨርሲቲዎቹ ለሚታየው የሠላም መናጋት አንዱ መነሾ መሆኑን እንረዳለን። የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ “የዩኒቨርሲቲዎቻችን አሁናዊ ተግዳሮቶች” በሚል ርዕስ የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሐዲስ አለማየሁ ጉባኤ አዳራሽ ባስመረቁት መጽሀፋቸው በተመሳሳይ ይኼንኑ ያመላክታሉ።
የአካዳሚክ ነጻነት አልባዎቹ ተቋማት
ዶክተር ተፈራ መላኩ «የአመራሩ ቁመና» የሚል ንኡስ ርዕስ በመስጠት፤ የዩኒቨርሲቲዎቻችን ከፖለቲካ የፀዱ ካለመሆን ጋር ተያይዞ በተቋማት ትናንትም ሆነ ዛሬ በአመራሩ ዙሪያ ብዙ የሚዝረከረኩ ችግሮች ስለመኖራቸው ይተርካሉ። «ትናንት ከባለስልጣናት ደኀንነት ጋር ውስኪ እየተራጩ በተቋሙ ዕድገት ዙሪያ ትችት የሚያቀርቡትን በአንድም ይሁን በሌላ እያስፈራሩ ፀጥ ረጭ አድርጎ ለመምራት የሞከሩ አልጠፉም። ዛሬም ቢሆን ልማድ ሆኖብን በትንሹም ቢሆን የሚዳዳ አመራሮች ያለን ይመስለኛል» ይላሉ።
የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዛሬም እንደ ትናንቱ ከእነዚህ የፖለቲካ ባሪያ አመራሮች አርነት አለመውጣታቸውን በመጽሀፋቸው ይገልጻሉ። አንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች መሆናቸውን የዘነጉ ፖለቲከኞች ከማዕከላዊ መንግስቱ ሲሸፍቱ አብረው ለመሸፈት የሚያምራቸው፤ ከፖለቲከኞች ተፅእኖ መላቀቅ ዛሬም የተቸገሩ፣ ድፍረቱን ያጡ አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች መኖራቸውን በመግለጽ የተቋማቱ በፖለቲካ ተጽእኖ ስር የመውደቃቸውን ደረጃ፣ ስር መሥደድን ጨምረው አስመልክተውናል።
«የፖለቲከኞችን የአክቲቪስቶቻችን ዐይንና ቅንድብ እያነበብን ውሳኔ ለመስጠት የምንሞክር ያለን ይመስለኛል። በራሳችን ፈቃድ አካዳሚክ ነጻነታችንን አሳልፈን የምንሰጥና በተቋሙ የኃላፊነት አሠጣጥ ሳይቀር ፖለቲከኞች እጃቸውን እንዲያስገቡ ለመፍቀድ የሚፈልጉ አመራሮች ያለን ይመስለኛል» በማለት ዩኒቨርሲቲዎቻን የአካዳሚክ ነጻነታቸውን በሸጡ የፖለቲካ ባርያ በሆኑ አመራሮች የመወረራቸውን እውነታ በመጽሀፋቸው ይነግሩናል።
ችግሩ በአንዳንድ ክልሎች በጣም ከፍ ብሎ የሚሠማ መሆኑን አስፍረዋል። በአክቲቪስቶች ተጠልፈው እግር ተወርች ታስረው የተቋሙን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ግለሰቦችን እንኳን ለማረም አቅም አንሷቸው እስከመቸገር መድረሳቸውን ያስመለከቱን ዶክተር ተፈራ፤ በዩኒቨርሲቲዎች ዘንድ የሚታዩ የአመራር ብልሽት በተቋማቱ አጥር ተከልሎ የሚቆም አይደለም።
በአመራሩ የተንሻፈፈ አመለካከት እየተኮተኮቱ ያደጉ ምሩቃን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል መመደባቸው አይቀሬ ነው። በየትኛውም መልኩ በመንግሥትም ሆነ በግላቸው ቢቀጠሩ የታነፁበት መንገድ በሥራው ዓለም ለሀገር የሚኖራቸው አበርክቶ ይወስነዋል። በዘረኝነትና በመንደርተኝነት ደዌ የተጠቃ የዩኒቨርሲቲ አመራር ወደድንም ጠላንም ከሰብዓዊነት ጋር መፋታቱ ግድ ነው። ስብዕናው ጎዶሎ የሆነ መሪ በየትኛውም ሁኔታ መልካም ተከታዮችና ዜጎችን ሊያፈራ አይችልም። ጭንጫ መሬት ላይ የተዘራ ዘር መልካም ፍሬ አያፈራምና።
ዩኒቨርሲቲዎቹን አርነት የማውጫው መንገዱ
ዶክተር ተፈራ በዚሁ መጽሀፋቸው ላይ መፍትሄ ያሏቸውን ነጥቦች አስቀምጠዋል። የዩኒቨርሲቲዎቻችን አመራር ከዘረኝነትና ከመንደርተኝነት ነፃ ካልሆነ፣ የተቋማቱን ዕድገት ከማቀጨጩም በላይ የሀገሪቱን ችግር በማወሳሰቡም ግንባር ቀደም መሆኑ አይቀርም። የአመራር ስምሪቱን ከዚህ አንጻር በየጊዜው በመፈተሽ፤ የዚህ ችግር ሰለባ የሆኑ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችን ያላንዳች ማቅማማት ከሲስተሙ ቆርጦ መጣል ተቋማቱን ብቻ ሳይሆን ሀገርንም መታደግ እንደሆነም ያመላክታል። ስለዚህ የዩኒቨርሲቲ አመራር ከየትኛውም ፖለቲካ ነፃ እንዲሆን የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ከችግሩ መውጫ ቀዳዳውን ያሳየናል። “ምክንያቱም የማኀበረሰባችን የአስተሳሰብ ዕድገት እስካልተቀየረ ድረስ የዩኒቨርሲቲ አመራሩ የፖለቲካ አባል ከሆነ የጥገኝነት መንፈስ መጠናወቱ ግድ ነው። የተቋማቱን ዕድገት በማረጋገጥ ቅቡልነቱን ለመጨመር ከመጣር ይልቅ፤ ለፖለቲከኞች ታማኝና ታዛዥ መሆኑ በእጅጉ ይቀለዋልና” ሲል አመራሩ ከፖለቲካ ነፃ መሆኑ የግድ እንደሚል ይሞግታል።
የፖለቲካ ባህላችን ካለመሰልጠኑ ጋር ተያይዞ የሀገራችን ፖለቲከኞች እርስ በእርሳቸው መራገጥ ሲፈልጉ የእርግጫ ሜዳውን የሚያደርጉት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው። ተማሪዎችን ደግሞ ቀጥተኛ ተዋናዮች ማድረግ ይሻሉ።
ዩኒቨርሲቲ ግን ከየትኛውም ፖለቲካና ከሀይማኖት ነፃ ሊሆን ይገባል። ተቋማቱ የፖለቲካ እንዳይሆኑ መጠበቅና የተማሪዎችን ደህንነትንም ማረጋገጥ የቅድሚያ፣ ቅድሚያ ተግባር ሊያደርጉት ይገባል። የአመራሩ ቁመናም ዥዋዥዌ ከመጫወት ወጥቶ አካዳሚክ ነፃነትን በሚያረጋግጥ መልኩ በገለልተኝነት መምራትና ማገልገል ያስፈልጋል።
የተቋማቱን ደህንነት ለማረጋገጥ ተጠያቂነትን ማስፈን ግድ ይላል። ሠላማዊ መማር-ማስተማርን እያወኩና ንጽህን የድሃ ልጆች እየቀጠቀጡና እየገደሉ ከሕግ ማምለጥ እንደማይቻል በተግባርም ማሣየት ያስፈልጋል። የተቋሙ ማህበረሰብም በተለይም ተማሪዎች ለሕግና ለመርህ ተገዥ እንዲሆኑ ተከታታይነት ያለው ሥራ መሥራት በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ዶክተር ተፈራ አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2013