ልጆችና የትንሳኤ በዓል

የክርስትና እምነት ተከታይ ለሆናችሁ እና ለቤተሰቦቻችሁ ‹‹እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል (ፋሲካ) በሠላም አደረሳችሁ›› ማለት እንወዳለን። እናንተም ‹‹እንኳን አብሮ አደረሰን!›› እንዳላችሁን አንዳችም ጥርጥር የለንም። ታዲያ ልጆችዬ በዓሉን እንዴት እያሳለፋችሁት ነው? የትንሳኤ በዓልስ ለምን እንደሚከበር ታውቃላችሁ?

ልጆችዬ! የሃይማኖት አባቶች ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ የሰው ልጆች የሠሩትን ሀጥያት ይቅር ለማለት በዕለት አርብ ተሰቀሎ፤ በራሱ ስልጣን ከሙታን መካከል ተለይቶ እሁድ ዕለት በሦስተኛው ቀን መነሳቱን ምክንያት በማድረግ የትንሳኤ በዓል በደማቁ እንደሚከበር ያስረዳሉ። ይህንን በማሰብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሃይማኖት አባቶች እና ምዕመናን ነጭ ለብሰው ሌሊቱን በቅዳሴ እና በተለያዩ መንፈሳዊ መርሃ ግብሮች ያከብሩታል። በሌሎች የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድም በዓሉን ‹‹ስለ እኛ የተከፈለ መስዋዕትነት እና ቤዛነት ነው።›› በማለት በዝማሬ እና በአምልኮ በደመቀ ሁኔታ ያከብሩታል።

በትንሳኤ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሠው ልጆች ቤዛ የሆነበት፣ ፍቅሩን እስከ ሞት ድረስ የገለጸበት እንደሆነ በሊቃውንቱ ይገለፃል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል እርሱ ሞቶ ሕይወትን የሰጠበት፣ ፍቅሩን የገለጸበት በመሆኑ፤ የክርስትና እምነት ተከታዮች ችግረኞችን በመርዳት ፣ በመዋዳድ፣ በፍቅር፣ በሠላም እና በአንድነት በመሆን በዓሉን ማክበር እንዳለባቸው ያሳስባሉ።

ልጆችዬ! ምንም እንኳን ይህ በዓል መሠረቱ ኃይማኖታዊ ቢሆንም በሀገራችንም ሆነ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ዕለቱን ከመንፈሳዊ ክዋኔዎች ባሻገር በተለያዩ መንገዶች ያከብሩታል። በሀገራችንም እንደየአካባቢው ሁኔታ የተለያዩ ምግብና መጠጦች ይዘጋጃሉ። ድፎ ዳቦ በመጋገር፣ ዶሮ ወጥ እና ሌሎች ምግቦች በማዘጋጀት ፣ ቤታቸውን አስውበው ቄጤማ ጎዝጉዘውና እና አሳምረው ከዘመድ አዝማድ ጋር በመሆን በተለየ ደስታ ያከብሩታል። ልጆችዬ! የእናንተም የበዓል አከባበር ከላይ እንደጠቀስነው አይነት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

በዚህ በዓል ታዲያ ወላጆች (አሳዳጊዎች) ለልጆቻቸው አዳዲስ ልብሶችን በመግዛት አቅማቸው ካልፈቀደ ወይም ዕቅዳቸው ካልሆነ ደግሞ ያላቸውን ልብስ እና ጫማ አጥበው እንዲሁም አሳምረው በማልበስ በዓሉን በደስታ ደምቀው እንዲያከብሩ ያደርጋሉ። ወላጆችም በተመሳሳይ መንገድ ራሳቸውን አስውበው እና አስጊጠው በዓሉን በቤታቸው ሰብሰብ ብለው፣ ወላጆቻቸውን ለመጠየቅ ከቅርብ ቦታ ራቅ እስካለ ቦታ በመሄድ፣ ዘመድ አዝማድን ‹‹እንኳን አደረሳችሁ?›› በማለት በታላቅ ድምቀት እንደሚያከብሩት ተመልክታችኋል ብለን እናምናለን። እናንተም በቤታችሁ ሰብሰብ ብላችሁ አልያም ወደ ወላጆቻችሁ ቤተሰቦች ጋር በመሄድ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ብላችሁ እና ተብላችሁ፣ ተመርቃችሁ እና ደስ ብሏችሁ በዓሉን በደስታ እንደምታሳልፉ ተስፋ አደርጋለሁ።

ልጆችዬ የትንሳኤን በዓል ጨምሮ በሌሎች በዓላት ላይ የተለያዩ ምግቦች፣ ኬኮች፣ ከረሜላዎች፣ ለስላሳ እና ሌሎች መጠጦች ይዘጋጃሉ። ታዲያ እናንተም ስትመገቡም ሆነ ስትጠጡ በመጠኑ እና በጥንቃቄ መሆን ይኖርበታል። ምናልባትም ‹‹ይህን ባናደርግ ምን እንሆናለን?›› የሚል ጥያቄ ታነሱ ይሆናል። ለምን መሠላችሁ ልጆችዬ? አብዝቶ መመገብ ከመጠን ላለፈ ጥጋብ ወይም ለምቾት ማጣት ይዳርጋችኋል። እንዲሁም ቅባታማ ምግቦች እና ሌሎች ምግቦች የሆድ ህመም ሊያመጣባችሁ ይችላል። ይህንን ካደረጋችሁ ግን በዓሉን በደስታ ከማሳለፍ ይልቅ በጭንቀት እና በህመም እንድትውሉ ትገደደላችሁ ማለት ነው። ስለዚህም በመጠን እና በጥንቃቄ መመገብ ይኖርባችኋል። ደግሞም ልጆችዬ በበዓላት ቀን ብቻ ሳይሆን ሁሌም ይህን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባችኋል።

ሌላው ልጆችዬ ከቦታ ቦታ በምትንቀሳቀሱበት ጊዜ የመኪና አደጋም ሆነ ሌላ ችግር እንዳያጋጥማችሁ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጉ። ወላጆቻችሁ ወይም ቤተሰቦቻችሁ የሚሏችሁንም ስሙ እሺ! ልጆች። ‹‹እሺ›› አላችሁ አይደል? በጣም ጎበዞች።

ዛሬ በዓል ስለሆነ አጠር እናድርገው አይደል? መልካም። ልጆችዬ! የሃይማኖት አባቶች ሁሌም እንደሚሉት በዓሉን በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመደገፍ እና በመንከባከብ ማሳለፍ ይገባል አይደል? ‹‹እንዴ! በሚገባ እንጂ! ›› የሚል ምላሽ እንደምትሰጡኝ ተስፋ አለኝ። እናም የተቻላችሁን መደገፍ ይኖርባችኋል። የቻላችሁትን ለመርዳት ግን ከወላጆቻችሁ ጋር መመካከር እና መነጋገር ይኖርባችኋል። ልጆችዬ በድጋሚ መልካም የትንሳኤ በዓል ይሁንላችሁ።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You