የድምፅ አልባዋ ልጅ አያት

ሰሜን ሸዋ ሰላ ድንጋይ የተባለች ቦታ ነው የተወለዱት። የስልሳ ሰባት ዓመት አዛውንት የሆኑትን ወይዘሮ ወርቅነሽ አሰፋን ያገኘናቸው በትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማህበር የልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕፃናት ማዕከል ውስጥ ለፋሲካ በዓል የተዘጋጀ የስጦታ መርሃ ግብር ላይ ነበር።

አጠገባቸው ተቀምጬ ማውራት ስንጀምር ነበር ሳግ በተቀላቀለው ድምፅ ጨዋታቸውን የጀመሩት። መከፋት ሞልቶ ሊፈስ ያለበት ሰዓት ላይ ደርሼ ማባበል እስኪከብደኝ ድረስ ብሶታቸውን አንድ በአንድ ዘረዘሩልኝ። መከፋት ቀንድ አውጥቶ ነፍስ ዘርቶ ፊቴ ሲቆም ተመልከተኩት። ተነግሮ የማያልቅ ሀዘን ውስጣቸው ሞልቶ አንደበታቸው ከሚናገረው በላይ መሆኑን መላ አካላቸውን የሚንጠው በእንባ የታጀበ ድምፅ ከቃል በላይ መከራ መሸከማቸውን ያሳያል።

አንድ ቀን ልጅን ሲያተኩሰው መያዣ መጨበጫ ለሚጠፋት እናት ይህ ስሜት ምን ማለት እንደሆነ አይጠፋትም። ለአስራ ሶስት ዓመታት ከዛሬ ነገ ለውጥ ይመጣል በማይባልበት ሁኔታ ልጅ ሳትናገር፤ ሳትራመድ፤ እንደ ልቧ ሳትመገብ፤ እንደ ልጅ ቦርቃ ሳታድግ ከመመልከት የላቀ ውስጥን የሚሰብር ሀዘን ከወዴት ይገኛል።

በተለይ አያቶች ለልጅ ልጆቻቸው ካላቸው ፍቅር አንፃር ሲታይ ህመሙ ገዝፎ ይታያል። ለዚህም ማሳያ ወይዘሮ ወርቅነሽ ናቸው። ወይዘሮዋ ከበዛው መከፋት ከእንባው መለስ ያወጉኝን ታሪካቸውን እነሆ ብያለሁ መልካም ቆይታ።

እኚህ እናት ከተወለዱባት ሰላ ድንጋይ ከወላጆቻቸው ጋር መጥተው አዲስ አበባ ነበር ያደጉት። አዲስ አበባ የወጣትነታቸው ጊዜ ሳያበቃ በወግ ተድረው ተኩለው እንደነበር ያስታውሳሉ። አግብተው ከትዳራቸው ሁለት ሴቶችና ሁለት ወንዶች ልጆችን አግኝተው በፍቅር በደስታ ይኖሩ ነበር። ደስታውና ፍቅሩም ባለቤታቸው በሞት እስከተለዯቸው ጊዜ ድረስ ቀጥሎ እንደነበር ያስታውሳሉ።

መልካም ሚስትና እናት ሆነው ባላቸው የሚያመጡትን ገንዘብ በጎተራ አካባቢ አርባ ሰባት የሚባል ሰፈር በምትገኘው አነስተኛ የቀበሌ ቤት እያብቃቁ ደስታና ፍቅር ይሞሉበት ነበር። ያገኙትን በሙሉ ልጆቻቸውን ለማሳደግ አንድም ነገር ሳይጎል ለማኖር ሲሉ ያወጡ ስለነበር ምንም ተቀማጭ ገቢ አልነበራቸውም።

ዛሬ የገዙት አስቤዛ ካለቀ ስለነገው ብዙም የማይገዳቸው እለት እለቱን የሚኖሩት እነ ወይዘሮ ወርቅነሽ የሚቀጥለውን ወር ቀለብ ለመግዛት የሚያስችል ሰባራ ሳንቲም እንኳን ሳይኖራቸው ነበር የትዳር አጋራቸው የልጆቻቸው አባት በሁለት በሶስት ቀን ህመም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። የለቅሶው ሥርዓት አልቆ ሁሉም ሰው በየቤቱ ሲከተት ለልጆቻቸው የሚያቀምሱት ነገር ከእጃቸው ማጣት ጀመሩ።

የልጆቻቸው አባት ከሞቱ በኋላ ዓመት እንኳን ሳይቆይ ችግር ጓዙን ጠቅልሎ ቤታቸው ገባ። በዚህ ሲሉት በዚያ ሲቀደድ፤ ይሄንን ሲደፍኑት ያኛው ሲያፈስ፤ በሰቀቀን ሲንገዳገዱ ቆይተው ለልጆቻቸው መሆን እንደማይችሉ ሲያወቁት ቢያንስ ትንንሾቹ በረሃብ ከማለቃችን በፊት ለዘር ይትረፉ በማለት ወንድ ልጆቻቸውን በጉዲፈቻ አሜሪካን ሀገር ለሚኖሩ ነጮች ይሰጣሉ።

“ልጆቼ ዓይኔ እያየ እንዳይሞቱብኝ ስል ትልልቆቹን አጠገቤ አስቀርቼ የአምስትና የሰባት ዓመት እድሜ ያላቸውን ልጆቼን ለፈረንጆቹ ሰጠሁ። ያኔ በልጆቹ ናፍቆት የተሰቃየሁትን ሰቃይ መቼም አልረሳውም” የሚሉት ወይዘሮ ወርቅነሽ ችግር የአብራካቸውን ክፋዮች አሳልፈው እንዲሰጡ ካደረጋቸው በኋላ ጤና ማጣታቸውን ይናገራሉ።

ወንዶቹን ለጉዲፈቻ ከሰጡ በኋላ ሁለቱን ሴት ልጆች በትግል ሊያሳድጉ ቢሞክሩም እንዲህ በቀላሉ የሚገፋ አልሆነም፤ ልጆቹም ደጅ ማየት ለመዱ።

አሁን ላይ ውጭ ካሉት ልጆቻቸው ጋር በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ቢገናኙም በቋንቋ ምክንያት የልባቸውን ተነጋገርው ስላልተግባቡ ውስጥ ውስጣቸውን ይበላቸዋል። ልጆቻቸው በሕይወት እንዳሉ ማወቃቸው ግን እፎይታ እንደሰጣቸው ይናገራሉ።

ከሴቶቹ ልጆቻቸው አንዷ አረብ ሀገር በስደት የምትኖር ሲሆን ብዙም ሊሳካላት አልቻለም። የሌላዋ ልጅ ታሪክ ደግሞ እንደሚከተለው ነው። ይህቺ ልጅ እኔና ወይዘሮ ወርቅነሽ እንድንገናኝ ምክንያት የሆነችና በትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማህበር የልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕፃናት ማዕከል ውስጥ በመረዳት ላይ ያለች ልጅ ናት።

ከአራቱ ልጆቻቸው መካከል አንዷ ታማሚ የሆነች በወጣችበት ውላ የምታድር ትሆናለች። በዚህ መካከል አንዲት ሴት ልጅ የወለደችው የወይዘሮ ወርቅነሽ ልጅ ሕፃኗን ለማሳደግ ምንም ፍላጎት ሳይኖራት እሳቸው ላይ ትታ ሄደች። “ለነገሩ ለሳድጋት ብትልም ህመሙ እያሰቃያት ልጅቷ ከገጠማት ጉዳት በላይ ታከብድባት ነበር” የሚሉት ወይዘሮ ወርቅነሽ ይህችን ስጦታዬ የሚሏትን ልጅ ተቀብለው ማሳደግ ጀመሩ።

ልጅቱ ተደራራቢ የጤና እክል ያለባት በመሆኗ እንደ ልጅ ሳትሮጥ አልጋ ላይ ቀረች። ልዩ ፍላጎት ያላት ከመሆኗም በላይ ቀኑን ሙሉ አንድ ወንበር ላይ ተቀምጣ የምትውልም መገላበጥ የሚቸግራት ልጅ ሆነች።

ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕፃናት ከሌሎች ልጆች የበለጠ ፍቅር እንደሚፈለጉ ሁሉ የወይዘሮ ወርቅነሽም ልጅ አንዳንድ ቃላት በማውጣትና በማቀፍ ፍቅሯን የምትገልፅ አሳዛኝ ልጅ መሆኗን አያትዋ ይናገራሉ።

እንደ ወይዘሮ ወርቅነሽ ገለፃ ሕፃናቱን የያዙ ወላጆች ላይ ማህበረሰቡ ውስጥ ያለው አመለካከት አሉታዊ ነው። ሰው ልጆቹ በእርግማን ነው የተገኙት የሚለውን አስተሳሰብ በመቀየር ለእነዚህ ድርብርብ የጤና ችግር ላለቸው ሕፃናት ፍቅር መስጠት ይገባል ይላሉ።

የወይዘሮ ወርቅነሽ የልጅ ልጅ ባላት ልዩ ፍላጎት ችግር ምክንያት ያልተለመዱ ባህሪያት ቢኖራትም እንደ ልቧ አለመንቀሳቀሷ ግን ከሁሉ በላይ የሚያስከፋቸው መሆኑን ይናገራሉ። የቤቴ ድምቀት ናት የሚሏትን የልጃቸውን ልጅ የምታያሳየው ሰውን የመውደድና የፍቅር ስሜት ለመዋደድ ምንም ዓይነት የጤና ችግር እንደማይገድብ ጥሩ ማሳያ ናት ይላሉ።

የወይዘሮ ወርቅነሽ የልጅ ልጅ የተሻለ ሁኔታ ላይ እንድትሆን ሕክምና እንደሚያስፈልጋት የሚናገሩት አያቷ “ የተሻለ ሕክምና አግኝታ መንቀሳቀስ ብትችል በእድሜ ማምሻ ላይ ያገኘኋትን በረከቴን ሳልሞት እራሷን ችላ ብመለክት ምኞቴ ነው። ልጅቷ የተሻለ እንክብካቤ ብታገኝ በሕክምና ብትረዳ ለውጥ ታመጣለች ብዬ አምናለሁ” የሚሉት እኚህ ሴት ልጅቷን የሚያሳክምላቸው ሰው እንደሚፈልጉ በእንባ ተማፅነዋል።

ወይዘሮ ወርቅነሽ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ሁሉም ወረዳዎች ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ድርጅት ውስጥ የተወሰነ ድጋፍ እያገኙ እንደሆነ ይናገራሉ። ማህበሩ እኔና እሳቸው በተገናኘንበት የፋሲካን በዓልን አስመልክቶ በተዘጋጀው ዝግጅትም ለወይዘሮ ወርቄና ተደራራቢ የጤና ችግር ላለባቸው ከሁለት መቶ ሀምሳ እናቶችና ውስጥ መቶ ሰባ አምስት ለሚሆኑ ሕፃናት እናቶቻቸው የዱቄት እና የዘይት ዶሮና እንቁላል 1ሺ500 የኪስ ገንዘብ ስጦታን አበርክቷል።

ትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማህበር መስራችና ዳይሬክተር ወይዘሮ አሳየች ይርጋ እንደተናገሩት ለስጦታው የሚሆን ገቢ የተገኘው ከተለያዩ ለጋሾች በቀረበ ጥያቄ ሲሆን ፤ በተጨማሪም የኦቲዝም ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀ የማስ ስፖርት ላይ ነው። በዚህ ስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ማህበሩ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን በማግኘቱ በርካታ ሰዎች በራሳቸው ዶሮ እንቁላልና ገንዘብ አበርክተዋል። ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በየዓመቱ ለአዲስ ዓመትና ለፋሲካ በዓላት ድጋፍ ስለሚያደርግ ለእናቶቹ የሚሰጠው ስጦታ ዓይነቱ በዛ እንዲል ሆኗል።

በዚህኛው በዓል ለመቶ ሰባ አምስት እናቶችና ልጆቻቸው ድጋፍ የሚደረግበት ምክንያት ከወር በፊት በነበረው የሙስሊም ማህበረሰብ በዓል ላይም ተመሳሳይ ድጋፍ በመደረጉ የተነሳ መሆኑን ሲስተር አሳየች ትናገራለች።

በአኬዥያ መንደር ውስጥ ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባቸው 18 ሕጻናት የሚገኙ ሲሆን ለእነዚህ ሕፃናት በጤና፣ በምግብ፣ በመጠለያ፣ በትምህርት እና የሥነ-ልቦና አገልግሎት እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን ለጋሾች የሚሰጡት የዓመት በዓል መዋያም ለተረጂዎቹ እንደሚሰጥ ተናግራለች።

ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባቸውን ልጆች እጅግ አስቸጋሪዎች በመሆናቸው እነሱን ይዘው ያለ ምንም ገቢ የሚኖሩት እናቶች መደገፍ የሁሉም ማህበረስብ ግዴታ ሊሆን ይገባል የምትለው ወ/ሮ አሳየች ሕፃናቱ በማህበረሰቡ ውስጥ ሲገለሉ የኖሩ ሲሆን የሚገባቸውን ድጋፍ እና እንክብካቤ ማግኘት ሳይችሉ ኖረዋል። በዚህም ምክንያት ለተለያዩ የጤና፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም የሥነ ልቦና ቀውስ ተጋላጭ ሆነዋል። ይህንን ለመቅረፍ ደግሞ ሁሉም ማህበረሰብ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ትላለች።

ትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማህበር ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባቸውን ሕፃናት ማቆያ፣ ትምህርት ቤት ፣ ሆስፒታል እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ኦሮሚያ ክልል፣ ሸገር ከተማ፣ ፉሪ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 1 ልዩ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን ላለፉት 17 ዓመታት አዲስ አበባን ጨምሮ በአራት ማዕከላት በማህበረሰብ ውስጥ ወላጆቻቸውን ላጡና ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች ድጋፍና እንክብካቤ እንዲሁም የኤች አይ ቪ ስርጭት ለመቀነስ ወደ 12 ሺህ ገደማ የህብረተሰብ አካላትን ተጠቃሚ እያደረገ መቆየቱን ለቀጣይ ታብራራለች።

ጠጋ ብሎ ስለችግራቸው ለጠየቃቸውም ሀዘናቸው ተጋብቶበት ልብ የሚንጥ አሳዛኝ ስሜት ውስጥ ይገባል። በጥቂት ደጋጎች ድጋፍ እነዚህ አሳዛኝ ሕፃናት ድጋፍ እያገኙ ቢሆንም ድጋፉ ግን በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ዜጋ የተቻለውን ሊያበረክት ይገባል። ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሀምሳ ሰው ጌጡ ነውና ይህንን የማህበረስብ ችግር በመረዳት ሁሉም ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል።

በየቤቱም ልክ እንደ ወይዘሮ ወርቅነሽ ዓይነት በልጆቻቸው ምክንያት ቤት ተዘግቶባቸው በሀዘንና በችግር የሚደቆሱትን እናቶች መመልከት የማህበረሰቡ ኃላፊነት ነው። ልጆቹ የምድር ስጦታዎች እንደመሆናቸው ሁሉም ሰው የየራሱን ጠጠር በመጣል የችግሩን ስፋት ሊቀንስ ይገባል በማለት የዛሬውን ጽሑፍ ቋጭተናል። ቸር ይግጠመን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2016 ዓ.ም

Recommended For You