የሲዳማ ክልልን አትሌቲክስ የማጠናከር ጥረት

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ታሪካዊ ድሎችን በማስመዝገብ ግንባር ቀደምና የውድድር አድማቂ ከሆኑ ሀገራት ተርታ ትመደባለች:: ለአትሌቲክስ የሚያመች የአየር ንብረትና መልከዓ ምድራዊ አቀማመጧ ደግሞ ለዚህ ተጨማሪ አቅምን ፈጥሮላታል:: ለስፖርቱ አመቺ ተፈጥሮን በመታደላቸው እምቅ አቅም ካላቸው ክልሎች መካከል በቅርቡ የተቋቋመው ሲዳማ ክልል ይጠቀሳል::

በርካታ የሩጫ እና የሜዳ ተግባራት ላይ ተሳታፊ በመሆን ሀገርን ያስጠሩ አትሌቶችንም ይኸው ክልል አፍርቷል:: አትሌት ቱርቦ ቱሞ እና በላይነህ ዴንሳሞን የመሳሰሉ አንጋፋዎችንም መጥቀስ ይቻላል:: ይሁንና ካለው አመቺ የአየር ንብረትና የመልክዓ ምድር አቀማመጥ አንጻር እምቅ አቅሙን አውጥቶ በመጠቀም ላይ ነው ተብሎ አይታመንም:: በመሆኑም ክልሉ አቅሙን አውጥቶ በሀገር አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ ተሳትፎን ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው የክልሉ ፌዴሬሽን አስታውቋል:: በክልሉ ሁለት ትልልቅ ክለቦች (ሲዳማ ቡና እና ሲዳማ ፖሊስ) እንዲሁም ክለቦቹን ሊመግቡ የሚችሉ በብሄራዊው ፌዴሬሽን እና በክልሉ ስፖርት ኮሚሽን የሚደገፉ የስፖርት ማዕከላትና ፕሮጀክቶችም ይገኛሉ::

ለስፖርቱ ውጤታማነት ትልቁን ድርሻ የሚወስደውን የፕሮጀክቶች ስልጠና ለማጠናከር እንዲሁም ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን በማደራጀት ከትምህርት ቤቶች ጋር የማቆራኘት ስራዎችም ተጀምረዋል:: በስራቸው 500 የሚሆኑ ታዳጊዎችን አቅፈው የሚገኙ 18 ፕሮጀክቶች ሲኖሩ፤ በክረምት መርሃ ግብር የተደራጁ 12 ተጨማሪ ፕሮጀክቶችም ይገኛሉ:: ከነዚህም በተጨማሪ በቀጣይ እንደ አዲስ የሚደራጁ ፕሮጀክቶች ከስፖርት ምክር ቤቱ ጋር እንዲተሳሰሩ የማድረግ ስራዎችም እየተከናወኑ ነው::

ስፖርቱ በዘላቂነት ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖረው የማዘውተርያ ስፍራ ያለው ሚና ትልቅ ሲሆን፣ ክልሉም ከትምህርት ቤቶች፣ ከወረዳዎች እና ከዞኖች ጋር አስተሳስሮ ስፖርቱ የሚፈልገውን ምቹ አካባቢ ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ችሏል:: በቀጣይ እነዚህን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ውጤታማ ተሳትፎን ለማድረግ ለአሰልጣኞች ስልጠና የመስጠት፣ ደረጃቸውን ማሻሻል እና የአቅም ግንባታን ለማድረግም ታቅዷል:: ፌዴሬሽኑ በዚህ ዓመት ለ85 ዳኞችና አሰልጣኞች የአቅም ግንባታና የሙያ ማሻሻያ ስልጠና መስጠት ችሏል::

በተለያዩ የእድሜ እርከኖች በክልል እና ሀገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ ውድድሮች ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው ክልሉ የተሻለ ውጤት ቢያስመዘግብም የሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አስራት አሰፋ ይናገራሉ:: በሀገር አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ ተሳትፎን የሚያደርግ እንዲሁም ጠንካራ ስፖርተኞችን ለሀገር ማፍራት የሚችል የክልል ፌዴሬሽን ለመፍጠር በእቅድና በተግባር በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል:: ክልሉ ሶስት ዓይነት የአየር ንብረቶች ያሉት በመሆኑ ለሁሉም የስፖርት ዓይነቶች የተመቸ ቢሆንም፤ ለአትሌቲክስ ስፖርት ደግሞ ይበልጥ ተመራጭ ነው:: ይህንኑ ጸጋውን በመጠቀምም የክልሉን አትሌቲክስ ስፖርት ተሳትፎ ውጤታማ ለማድረግ መስራት አስፈላጊ ነው::

ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ዓመታት ለስፖርቱ ተሳትፎና ውጤታማነት ምን መስራት እንደሚኖርበት ለይቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል የስፖርቱን እንቅስቃሴ በውጤታማነት ለመምራት የሚያስችሉ አደረጃጀቶችን ማጠናከርና ማስፋት አንዱ ነው:: ከአበረታች ቅመሞችና ከዕድሜ ማጭበርበር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ለስፖርት ቤተሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥና የአቅም ግንባታ ስራዎችን አጠናክሮ መስጠት፣ የውስጥ ውድድሮችን በማብዛትና በማጎልበት የፕሮጀክቶችን አቅም አሳድጎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረግም የእቅዱ አካል ናቸው:: ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር፣ ስፖርቱን ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝና ተጨማሪ ክለቦችን ለማቋቋምም በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆኑም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል::

በክልሉ የሚካሄዱ ሀገር አቀፍ ውድድሮች የክልሉን የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ ከማሳደግ አኳያ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል:: ለውድድር የሚመጡት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ትልቅ ልምድን ለመለዋወጥ ስለሚጠቅሙ ተጨማሪ አቅም መሆን ስለሚችሉ ጥቅሙ የጎላ ነው:: በክልሉ ያሉትን ምቹ የማዘውተርያ ስፍራዎች በመጠቀም በቀጣይ ትልልቅ ውድድሮችን በማካሄድ ተጨማሪ ተሞክሮዎችን ለመውሰድ እና ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖር ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል::

ዓለማየሁ ግዛው

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም

Recommended For You