አንገብጋቢው የተማሪዎች ማንበብና መፃፍ ያለመቻል ጉዳይ

ዘመኑ ብዙ ነገሮች የታመሙበት ብቻ ሳይሆን ፈውሳቸውም የቸገረበት ነው። ሁሉም በየ ቤቱ ∙ ∙ ∙ እንዲሉ፣ በየዘርፉ ያልተቸገረ የሙያ ዘርፍ፤ ያልታመመ ማህበራዊ ሴክተር፤ ያልተጎሳቆለ መልክአ ምድር ወዘተ የለም። በእንዝህላሎች “ጠብ ያለሽ በዳቦ″ ያልተቀጠፈ የንፁሀን ነፍስ የለም። ሁሉም ጋ፤ በሁሉም ዘርፍ ችግሮች ሞልተው ተትረፍርፈዋል። ችግሩ፣ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ወደ ትምህርቱ ዘርፍ ጎራ የማለታቸውና ችግርና ህመማቸው ዘመን ተሻጋሪ የመሆኑ ጉዳይ ነው። አዎ፣ ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርም ∙ ∙ ∙ እንደሚባለው፣ በትምህርት በኩል የሚመጣ ችግር አንድን ማህበረሰብ ሳያደቅ እና ሳያሽመደምድ፤ ለሌሎች በርካታ ችግሮችም አሳልፎ ሳይሰጥ አያልፍም። አሁን እያወራን ያለነው ከዛ በመለስ፣ ያ ከመሆኑ በፊት ∙ ∙ ∙ ነውና ወደ ጉዳያችን እንሂድ።

ከሰሞኑ አሳዛኝ ትምህርት ነክ ዜናዎች አንዱ የሆነው የተማሪዎች ክህሎት ጉዳይ ሲሆን እሱም “ማንበብ″ እና “መጻፍ″ን የተመለከተው፤ በቀጥታ ከመጪው ትውልድ ጋር የተያያዘው መሰረታዊ ጉዳይ ነው።

“ማንበብ″ እና “መጻፍ″ ክሂሎች ናቸው። ከክሂሎትም ዋና ዋናዎቹ ስለ መሆናቸው የቋንቋ ትምህርትን ሀሁ ∙ ∙ ∙ የቆጠረ ሁሉ ያውቀዋል። ባይቆጥርም እንኳን የቋንቋ መማሪያ መጻሕፍትን መግቢያ ገልበጥ ገልበጥ ያደረገ ማንም ሰው አሳምሮ የሚገነዘበው ጉዳይ ነው። በመሆኑም የ“ማንበብ″ እና “መጻፍ″ ጉዳይ መሰረታዊ የሕይወት ጉዳይ፣ የመለወጥ ጉዳይ፣ የማወቅና አለማወቅ ጉዳይ፤ ባጭሩ፣ በትምህርት ዐለም ቋንቋ ሰው የመሆን እና ሰው ያለመሆን ጉዳይ ነው። በመሆኑም፣ ያስጨንቃል፤ የትምህርት ሕመም የሁሉም ሰው ሕመም ነውና ሁሉንም ያሳምማል። “ልጄ የት ይደርስልኝ ይሆን?″ በማለት ጥሪቱን ሁሉ አሟ’ጦ “ልጅህ ማንበብና መጻፍ አይችልም″ የተባለን ወላጅ በሕሊና በማሰብ የችግሩን ጣሪያ ማወቅ ይቻላል።

ችግሩ ዓለም አቀፍ ነው። እንደ ማንኛውም ችግር የትም አለ። በተለይ ወደ አፍሪካ ምድር ስንመጣ፣ ችግሩ የእለት ተእለት ዜና እና በየተሄደበት የሚያጋጥም ማኅበራዊ ችግር ነው። በመሆኑም፣ መፍትሄውም ማኅበራዊ ነው ማለት ነው። ስለዚህ በማኅበር መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። “ለምን?″ ከተባለ መልሱ እየተነጋገርንበት ካለው ማኅበራዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ለአደባባይ የበቃው ዜና-ዘገባ መሆኑን ገልፆ በቀጥታ ወደ ጉዳዩ መሸጋገር ይቻላል።

እንደ ምን ጊዜውም፣ ሰሞኑን ለአደባባይ የበቃውና በማኅበራዊውም ሆነ መደበኛ ሚዲያው ሲሽከረከር የከረመውን ጉዳይ ብዙዎቻችን በሚገባ የምናውቀው ነው። ምናልባት “የተለመደ″ በማለት ያላለፍነው ካልሆነ በስተቀር ወይ አይተነዋል፤ ወይ ሰምተነዋል፤ ካልሆነም አንብበነዋል።

ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱት በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩት ተፈታኝ ተማሪዎች መካከል 3∙2 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት ማለፍ የቻሉት የሚለው ምን ያህል መነጋገሪያ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቻችንን ረብሾ እንደ ነበር የሚዘነጋ አይደለም። ዘንድሮ ደግሞ የተማሩ፣ ግን ደግሞ የማያነቡ ተማሪዎች አሉ የሚል ጥናት ከፈረሱ አፍ እየሰማን እንገኛለን።

የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ንባብን መሠረት አድርጎ ባካሄደው ጥናት እንደ ደረሰበትና ሰሞኑን ይፋ እንዳደረገው፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የ2ኛ እና የ3ኛ ክፍል ተማሪች 56 በመቶዎቹ ምንም ዓይነት ቃል ማንበብ አይችሉም።

በዚህ ንባብን መሠረት ባደረገ ጥናት ከ9 ክልሎች የተወጣጡ ከ16ሺህ በላይ ተማሪዎች በዘፈቀደ (Ran­dom sampling) ተመልምለው የተሳተፉ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ከ401 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተመረጡ መሆናቸው ተመልክቷል።

በጥናቱ የተሳተፉት ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተጻፉ 50 ቃላት ቀርበውላቸው ቃላቱን ያነበቡ እንደሆነ ተጠይቀው የነበረ ሲሆን፤ በጥናቱ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በአፋርኛ፣ በሶማሊኛ፣ በሀዲይኛ፣ በወላይትኛ፣ በሲዳምኛ እና ቤኒሻንጉል ውስጥ በሚነገረው በርታ ቋንቋ የሚማሩ ተማሪዎች መሳተፋቸው ታውቋል።

የተማሪዎችን ፊደል የመለየት፣ ቃላት ወይም አጭር አንቀጽ የማንበብ፣ የማድመጥ እና የመረዳት ችሎታቸውን መመዘንን ትኩረቱ ያደረገው ይህ ጥናት እንዳመለከተው፣ ከ2ኛ እና 3ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 56 በመቶ የሚሆኑት አንድም ቃል ማንበብ አይችሉም።

የፈተናዎች ድርጅት ይፋ እንዳደረገው ከሆነ፣ በጥናቱ ከተሳተፉ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ቢያንስ አንድ ቃል ማንበብ የሚችሉት 37 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ሲሆኑ፤ የተቀሩት 63 በመቶዎቹ አንድም ቃል ማንብብ የማይችሉ (Zero renderers) ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ በደቂቃ ቢያንስ 60 ቃላትን ያነብ ዘንድ ቢጠበቅም ይህንን እዚህ ማግኘት እንዳልተቻለ ከዚሁ ጥናት ተረጋግጧል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉ፤ በተለምዶ ታዳጊ የሚባሉ ክልሎች ላይ ትኩረት እንዲደረግ ምክረ ኃሳብ ከሚለግሰው ከዚህ ጥናት መረዳት እንደተቻለው፣ እንደ ዓለም አቀፍ መለኪያ በደቂቃ 90 ቃላትን ያነባሉ ተብለው ከሚጠበቁት የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች 55 በመቶ የሚሆኑት ከየትኛውም ፊደል ጋር ትውውቅ የላቸውም፤ ፊደላቱን አያውቋቸውም።

በድርጅቱ ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚማሩት የ2ኛ ክፍል ተማሪዎች ቢያንስ በደቂቃ 43፤ እንዲሁም የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች በደቂቃ 53 ቃላትን ያነባሉ ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ውጤቱ ከላይ የተመለከተውን ሆኖ ተገኝቷል።

ቀደም ሲል ጠቆም ለማድረግ እንደ ሞከርነው፣ በእርግጥ ይህ ችግር የኢትዮጵያ ብቻ ላይሆን ይችላል። በሌሎች የአፍሪካ አገራትም ችግሩ ይኖራል። ለምሳሌ በቅርቡ ጥናት የተካሄደባት ደቡብ አፍሪካ ተመሳሳይ ችግር ታይቶባታል።

በባለፈው ዓመት (22 ማይ 2023) የወጣ ጥናት እንዳመለከተው፣ በደቡብ አፍሪካ 81 በመቶ የሚሆኑት የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች በአገሪቱ በሚገኙ በማናቸውም ኦፊሴል ቋንቋዎች ማንበብ አይችሉም። ይህም አገሪቷን ከንባብ ውጤት ምዘና አኳያ -31 ነጥብ እንድታገኝ ምክንያት ሆኗል። ይህም በ2016 78% ከመሆኑ አንፃር ችግሩ (reading crisis ይለዋል ጥናቱ) እየከፋ መምጣቱን የሚያሳይ ሲሆን፤ ችግሩን ለመፍታት የመንግሥት ጥረት አናሳ መሆኑን ያሳያል ይላል ጥናቱ።

ባልተማሩ ወገኖች ቁጥር ዓለምን እየመሩ ያሉትን፣ በአጠቃላይ ከ1.137 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላቸውን፤ አማካይ የእድሜ ጣሪያ 60 ዓመት የሆነባቸውን የሰሀራ በታች አገራት ከተመለከትን ከሶስት ልጆች አንዱ ማንበብ አይችልም። 182 ሚሊዮን ወጣቶች ማንበብም ሆነ መጻፍ አይችሉም። እድሜያቸው ከ15 እስከ 24 የሆኑ 48 ሚሊዮን ወጣቶች መሀይማን ናቸው። 22% (30 ሚሊዮን) የሚሆኑና ትምህርት ቤት መዋል የሚገባቸው የመማር እድሉን አላገኙም። ዝርዝሩ ብዙ ሲሆን ጥናቱን ካከናወነው African Library Project ድረ-ገጽ ማየት ይቻላል።

ምን ይደረግ?

“What Do Teachers Know and Do? Does it Matter? Evidence from Primary Schools in Af­rica″ በሚል ርእስ ሪፖርቱን እንዳቀረበው፣ እንደ ዓለም ባንክ ጥናትና ምክረ ሀሳብ ከሆነ ችግሩ የፖሊሲ ውድቀት (policy failure) ሲሆን፤ መፍትሄውም መንግስታት ዳግም የትምህርት ፖሊሲያቸውን መመርመርና የተሻለ ልምድ ካላቸው አገራት ትምህርት በመቅሰም እንደ ገና መቅረፅ ይገባቸዋል።

እንደዚሁ ሪፖርት ከሆነ፣ መምህራንን ለቁጥር ያህል ብቻ ከማሰማራት ብቃት ያላቸው መምህራንን በዘርፉ ማሰማራትና ተማሪዎቻቸውን እንዲያበቁ ጥረት መደረግ አለበት። በተለይ ራሳቸው መምህራኑ ማንበብ እና መፃፍ የማይችሉ የሆኑበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።

ከሰሃራ በታች ልጆች በቀን ውስጥ ትምህርት ቤት የሚውሉትና ትምህርት ይሰጣቸዋል ተብሎ የተመደበላቸው ጊዜ በአማካይ 2 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ሲሆን፣ ይህ ተማሪዎች በቂ እውቅትና የሚጠበቅባቸውን ክሂሎት ይዘው እንዲወጡ የማያደርግ በመሆኑ ሊሻሻል ይገባዋል።

ይህ ጥናት ከመምህራን አኳያ ጠለቅ ብሎ የሄደ ሲሆን፣ ችግሩንም የአብዛኛዎቹ መምህራን የተማሪዎቹን መማሪያ መፃህፍት ይዘት እንኳን እንደማያውቁ፤ መሰረታዊ የሥነማስተማር ሥነዘዴ እውቀታቸው ዝቅተኛ መሆኑን፣ እንዲሁም በቂ የማስተማር ልምድ ያላቸው መምህራን አናሳ እንደ ሆነ “large shares of teach­ers do not master the curricula of the students they are teaching; basic pedagogical knowledge is low; and the use of good teaching practices is rare″ በማለት ትዝብቱን ያስቀመጠ ሲሆን፤ ከዚህ አኳያ መንግስታት ከባድ የቤት ስራ ያለባቸው መሆኑንም ያስረዳል።

ለዚህ ርእሰ ጉዳይ የተሻለ ግንዛቤ ሲባል የተደረጉ በርካታ ፍተሻዎች እንደሚያረጋግጡት የተማሩ ተማሪዎች ማንበብም ሆነ መፃፍ ያለመቻላቸው መሰረታዊ ችግር በአብዛኛው የተማሪዎች ሳይሆን ከእነሱ ውጪ በሆነ መሰናክል ምክንያት ነው።

እንደ ተፈተሹት ሰነዶች ከሆነ ጥናቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የመምህርነት ሙያ ብዙም የሚያዋጣ አይደለም። ክፍያው ድክም ያለ ሲሆን፣ ያም ሆኖ ጠንካራና ስነምግባር ያላቸውን መምህራን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሳይሆን በጅምላ ክፍያ ላይ የተመሰረተና ሰነፎችን የሚያበረታታ ነው።

እንደ አንድ ጠንከር ያለ ጥናት (Zinah Issa፣ 2024) ልክ እንደ ተማሪዎቹ ሁሉ የማያነቡ ወይም የማይፅፉ መምህራንም አሉ፤ ከዚህም አጠቃላይ ስርአቱ ብልሹ ስለ መሆኑ መረዳት ይቻላል (most teachers too cannot read or write and you realize the whole system is corrupted and defective)።

ባጠቃላይ፣ ሰሞኑን በየኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ድርጅት አማካኝነት ይፋ የተደረገው ጥናትና ውጤቱ ልክ እንደ 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ውጤት ሁሉ እጅግ አስደንጋጭ ነው። በተለይ ለጋ ሕፃናት፣ ለወደፊት ሕይወታቸው መሰረት የሚጥሉበትን፤ ይህንን እድሜና የክፍል ደረጃ እንዲህ ሆኖ ማየት እጅጉን ይከብዳል። ድሮ የአራተኛ ክፍል ተማሪ በእንግሊዝኛ ድርሰት ጽፎ ዓለም አቀፍ አሸናፊ በመሆን የከበረ ሽልማትን ይቀበልባት የነበረች አገር ዛሬ “በጥናቱ ከተሳተፉት የ2ኛ እና 3ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 56 በመቶ የሚሆኑት አንድም ቃል ማንበብ አይችሉም።

ከሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ቢያንስ አንድ ቃል ማንበብ የሚችሉት 37 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። የተቀሩት 63 በመቶዎቹ አንድም ቃል ማንብብ የማይችሉ (Zero renderers) ናቸው።″ ወዘተ የሚል ነገር መስማት ለሰሚው ግራ ነው። በመሆኑም፣ የሚመለከተው ሁሉ ይህንን አስፈሪና አሳሳቢ ችግር (አጥኚዎች፣ genera­tional catastrophe ይሉታል) ለመቅረፍ ተኝቶ ሊያድር አይገባም። የትምህርት ሕመም የሁላችንም ሕመም፤ የአገር መታመም ነውና ፋታ ሊሰጠው አይገባም እንላለን።

ግርማ መንግሥቴ

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You