ሕፃናትን በቀላሉ ማስተማር የሚያስችለው ባለድምጽ የአማርኛ ፊደል ገበታ ፈጠራ ባለሙያዎች

ወጣት ዘርባቤል መስፍን እና ቤተሰቦቹ የማሜ መጫወቻና ፐዝሎች መስራቾች ናቸው። ‹‹የአማርኛ ባለድምጽ ፊደል ገበታ›› የተሰኘ ሕፃናትን በቀላሉ ማስተማር የሚያስችል ለየት ያለ ፈጠራ መሥራት ችለዋል። ባለድምጽ የፊደል ገበታው ሥራ ላይ ካሉት ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎች ይለያል፤ የፊደል ገበታው ካለምንም እገዛ በራሱ ድምጽ አውጥቶ ማስተማር ወይም ማስረዳት ይችላል።

ወጣት ዘርባቤል እንደሚለው፤ ወላጆች ልጆቻቸውን የተሻለ ትምህርት ቤት በማስገባት እንዲማሩ በተለይ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ይታወቃል። ይሁንና ሕፃናቱ እንግሊዝኛ ቋንቋን የበለጠ እያወቁ ቀስ በቀስ አማርኛ ቋንቋን እየረሱ ወይም ችላ እያሉ ይገኛሉ። ወላጆች በራሳቸው ጥረት ልጆቻቸውን ለማስተማር ቢፈልጉም፣ ከሥራ ጋር ተያይዞ ጊዜ ማግኘት እየተቸገሩ በመሆናቸው የአማርኛ ፊደላት ለማስተማር ሲቸገሩ ይስተዋላሉ።

ይህ አዲስ ፈጠራ ግን ሕፃናትን (ልጆችን) ልክ እንደ መምህር እያስተማረና ጥያቄም እያቀረበ የራሱን ሥራ መሥራት ይችላል። በፊደል ማስተማሪያው በሶፍት ዌር አማካኝነት ፊደላት ድምጽ እንዲኖራቸው ተደርጎ ተዘጋጅተዋል፤ ሁኔታው ልጆች በስልክ ወይም በስክሪን ላይ የሚያጠፋትን ጊዜ በማስቀረት ፊደላትን በመማር በቀላሉ እንዲማሩና ቁምነገሮች እንዲያውቁ ያስችላል።

የእነ ዘርባቤል የፈጠራ ሥራ የሆነው ይህ የፊደል ገበታ፣ የኢትዮጵያን ባህል እና ቴክኖሎጂ በአንድ አጣምሮ ይዟል። በቤት ውስጥ የሚሰቀል ስለሆነ ሕፃናት ፊደሉን በሚጫኑበት ጊዜ ድምጽ እያወጣ ያስተምራል። ድምጽ እያወጣ ካስተማረ በኋላ ልክ እንደ መምህር ልጆቹ ምን ያህል ተረድተዋል ወይም አውቀዋል የሚለውን ለመረዳትም ጥያቄ ያቀርብላቸዋል። ጥያቄውን በትክክል የማይመልሱ ከሆነ ወደ ቀጣይ ጥያቄ አይሸጋገርም፤ ይልቁንም ደግመው እንዲማሩ እድሉን ይሰጣል። ጥያቄውን በትክክል ከመለሱ በኋላ ጥያቄው በትክክል መመለሱን ገልጾ ወደ ቀጣይ ጥያቄዎች ይሸጋገራል።

ፊደላትን ከማስተማር ባሻገርም ቁጥሮችም ያሉት ሲሆን፤ ልጆች ቁጥሮችንም በእጃቸው ሲጫኑ ቁጥሮችን በመቁጠር በድምጽ እየጠራ እንዲማሩ ያደርጋቸዋል። ቁጥሮቹንም የተመለከቱ ጥያቄዎችንም ያቀርብላቸዋል።

ሕፃናት በመጀመሪያ ጊዜ ፊደላትን ለመማርና ለማወቅ በጣም እንደሚጓጉ ይታወቃል፤ ጠዋትም ሆነ ማታ በተመሳሳይ መንገድ በተደጋጋሚ ሲማሩ ደግሞ ቶሎ የመሰላቸት ባህሪም ይታይባቸዋል የሚለው ወጣት ዘርባቤል፤ የባለድምጽ የፊደል ገበታ ማስተማሪያው ግን ይህን ሁሉ በማስቀረት ሕፃናቱ ወደውት በፍቅር እንዲማሩ እንደሚያደርግ ይገልጻል። ይህን ፈጠራ እንዲወዱት ከሚያደርጉት መካከል አንደኛ ድምጽ አውጥቶ ማስተማሩ ነው። ሁለተኛ ጥያቄ ማቅረቡ ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ እየተዝናኑ የሀገራቸውን ባሕል እንዲያውቁ የሚረዳ መሆኑ ነው ሲል ያብራራል፡፡

ወጣት ዘርባቤል እንደሚለው፤ ባለድምጽ የፊደል ገበታ ማስተማሪያው ሙዚቃ ማዳመጥም ያስችላል። ሕፃናት ሙዚቃ ማዳመጥ ሲፈልጉ የሙዚቃውን ቦርድ በእጃቸው በመጫን ከፈተው ማዳመጥ ይችላሉ። መዚቃውም በውስጡ የኢትዮጵያን ባሕላዊ እሴቶች፣ ወግ እና ትውፊቶች የሚያንጸባሩቁ መዝሙሮች፣ ተረቶች፣ ምሳሌዊ አነጋገሮች፣ ግጥሞች ፣ አባባሎች ፣ የአባቶች ምክር እና ሌሎች ከ20 በላይ ትራኮች የተካተቱበት ነው። ለአብነት የሙዚቃ መጫወቻውን ሲጫኑ በመጀመሪያ ላይ የሚያዳምጡት የኢትዮጵያን ሕዝብ መዝሙር ነው። ሕፃናቱም መዝሙሩን ያለሰው እገዛ ተምረው በቃላቸው ይዘው ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ያስችላል፡፡

‹‹በዚህ የባለድምጽ ፊደል ገበታ ማስተማሪያ አማካኝነት ሕፃናት ሦስቱን ማለትም አማርኛ የማዳመጥ፣ የማንበብ እና የመናገር ክህሎቶቻቸውን ማሳደግ ይችላሉ›› የሚለው ዘርባቤል፤ የተቀረውን አራተኛውን የመጻፍ ክህሎት ደግሞ በቤታቸው ሆነው እዚያው በፊደል ገበታው ላይ ባለው በነጭ ሰሌዳ (ኃይት ቦርድ) ላይ ጽፈው በመለማመድ እያንዳንዱን ፊደል ለማወቅ ያስችላቸዋል ሲል ያብራራል። የፊደል ገበታው የተሰራበት ቁስ ፕላስቲክ መሆኑን ጠቅሶ፣ በቀላሉ በእጃቸው ወይም በሶፍት ካልሆነም በዳስተር መጥፋት እንደሚችሉ አስረድቷል።

እነ ዘርባቤል፤ ይህን የፈጠራ ሥራ ለመሥራት መነሻ የሆኗቸው በአሁኑ ወቅት በአቅራቢያቸው የሚመለከቷቸው በስልክ ስክሪን ላይ የተጠመዱ ሕፃናት መሆናቸውን ተናግሯል። ሕፃናት ስልክ ላይ ካላቸው ጥገኝነት ተላቅቀው ፊደላትን በቀላሉ መማር የሚችሉበትን መንገድ ለመፍጠር እንዲሁም ወላጆች ልጆቻቸውን ፊደል ለማስቆጠር ያለባቸውን ጫና ለመቀነስ በማሰብ ይህን መፍትሔ ማግኘታቸውን ይገልጻል። ‹‹ከምንም በላይ ግን ችላ ያልናቸውን የሀገራችንን የአማርኛ ፊደላት በቀላሉ መንገድ እንዲያወቁት ተብሎ የተዘጋጀ የፈጠራ ሃሳብ ነው ›› ይላል።

የባለድምጽ ፊደል ገበታ ማስተማሪያው ሶፍትዌር፣ ሚሞሪእና ቺትስን አካቶ የያዘ ነው። ከእያንዳንዱ ፊደል ጋር የተያዙ ቦርዶች ስላሉ ቦርዱ ከሚሞሪው ጋር ተገናኝቶ ድምጽ ይፈጥራል። ለዚሁ ተብሎ ከተዘጋጀው ፕሮግራም ጋር እንዲገናኝ ተደርጎ ድምጹ ወጥቶ እንዲሰማ ይደረጋል።

‹‹ የፈጠራ ሃሳብ እንደመጣልን ጥናት አድርገናል፤ የጥናቱ ውጤት የአማርኛ ፊደላት በሕፃናት ዘንድ እየተረሱ መምጣታቸውን አመላክቶናል›› የሚለው ዘርባቤል፤ ይህ ችግር ደግሞ ለትምህርት ቤቶች እና ለወላጆች ብቻ የሚተው እንዳልሆነ ገልጾ ሕፃናቱ በቀላሉ ከስልክ የሚላቀቁበትን እና የወላጆች ጫናም የሚቀነስበትን መንገድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አመንን ሲል ያብራራል። ለዚህም ሕፃናት እየተጫወቱ በቀላሉ ፊደል የሚማሩበትን ባለድምጽ የፊደል ገበታ እውን ማድረጋቸውን አስታውቋል።

የፊደል ገበታው አሁን መሠረታዊ የአማርኛ ፊደላትን ድምጽ ብቻ እያወጣ እንዲጠራ ሆኖ የተሰራበት ሁኔታ የሥራው ክፍል አንድ መሆኑን አብራርቶ፣ በቀጣይ በክፍል ሁለት ደግሞ ይህን በማስፋት ሞክሼ ፊደላትን፣ የፊደላትን ቀመርና ሌሎችንም እንዲያካትት በማድረግ እንደሚሰራ ዘርባቤል አመላክቷል። ሌሎች በጣም ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት ማቀዳቸውንም ይናገራል።

ይህን ማስተማሪያ ከአንድ ዓመት እስከ 6 ዓመት ያሉ ልጆች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አመልክቶ፤ አንድ ሕፃናን ማስተማሪያውን ለመጠቀም ሲፈልግ እንዴት መጠቀም እንደሚችል የሚያሳዩ ቪዲዮዎች መዘጋጀታቸውንም አስታውቋል። ባለድምጽ ፊደላት ማስተማሪያው በፓኬጅ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግሮ፤ ፓኬጁ ሲከፍት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳይ መመሪያ ውስጡ እንዳለውና በመመሪያ መሠረት በቀላሉ ለመጠቀም እንደሚቻል አስገንዝቧል፡፡

እነዘርባቤል ማስተማሪያውን መሸጥ ከጀመሩ አንድ ዓመት ሞልቶቸዋል። እስካሁን 600 ቅጂዎችን ሸጠዋል። ማስተማሪያውን መጠቀም በጀመሩ ወላጆች በኩል ምንም ዓይነት ቅሬታ ገጥሞቸው እንደሚያውቅ ይናገራል። እንዲያውም ወላጆች በጣም እንደተደሰቱበት ሕፃናትም ወደውት እየተማሩበት እንዲሆነ በሰበሰቡት አስተያየት ማወቃቸውን ይገልጻሉ፡፡

ይህ ማስተማሪያ በአዲስ አበባ ከተማና በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች እየተሰራጨ መሆኑንም ዘርባበል ያመላክታል። ማስተማሪያውን ለሚፈልጉ ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነ እንዲያገኙት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሶ፤ በአቅራቢያቸው ለሚገኙት ደግሞ ባሉበት በማድረስ፣ ርቀው ላሉት ደግሞ በፖስታ ቤት በኩል እንዲደርሳቸው እያደረጉ እንደሆነ አስታወቋል፡፡

ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ እንዳብራራው፤ ይህ ማስተማሪያ የሚመረተው በቻይና ነው፤ በዚያ ሲመረት የማምረቻ ዋጋው ቅናሽ ያለው ቢሆንም፣ ሀገር ውስጥ እስኪገባ ድረስ ያለው ወጪ ዋጋውን ከፍተኛ አድርጎታል። ለዚህም አንዱ ምክንያት ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ሶስት እጥፍ ቀረጥ የሚከፈልበት መሆኑ ነው። ስለዚህ የአንዱ የፊደል ገበታ ዋጋ 2ሺ ብር ነው።

አሁን ለጀማሪ የፈጠራ ባለሙያዎች(ስታርትአፖች) ትኩረት እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሶ፣ በሕጉ ላይ ማሻሻያ የሚደረግ ከሆነ አሁን ካለው ዋጋ በጣም ይቀንሳል፤ ያንን ተከትሎም ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ይቻላል ሲል አብራርቷል፡፡

የባለድምጽ የአማርኛ የፊደል ገበታን ለመሥራት የሚያስፈልጉት ነገሮች ዲዛይን፣ ሶፍትዌር፣ በውስጡ የሚገቡት ድምጾቹ ሲሆኑ፤ እነዚህ ሁሉም እዚሁ ተሰርተው ለፕላስቲኩ ሲባል ብቻ ወደ ቻይና እንደሚላክ የሚገልጸው ዘርባቤል፤ ቻይና በሚመረትበት ጥራት በሀገር ውስጥ ፕላስቲኩን የሚያመርት አምራች ቢኖር ሁሉንም በቀላሉ ሀገር ውስጥ መጨረስ ይቻል እንደነበር አስረድቷል፡፡

አሁን ላይ ሀገር ውስጥ ፕላስቲክ የሚያመርቱ እንዳሉ ጠቅሶ፣ እነሱ ግን ለዚህ ማስተማሪያ መሥሪያ የሚውል ጥራቱን የጠበቀ ፕላስቲክ ግን ለማግኘት እንዳልቻሉ አመላክቷል። የሀገር ውስጦቹ ፕላስቲኮች በፍጥነት የሚቀደዱና የሚበላሹ መሆናቸውን ገልጾ፣ ማስተማሪያውን የሚጠቀሙት ሕፃናት እንደመሆናቸው መጠን ፕላስቲኩ ረጅም ጊዜ ሊያገለግል የሚችል አለበት፤ ወላጆችም የሚፈልጉት እንዲህ ዓይነቱን ነው፤ የቆይታው ጊዜ ያስጨንቃቸዋል ሲል ያብራራል፡፡

‹‹እኛም እንደወላጆች የሚያስጨንቀን ጥራቱን የጠበቀ መሆኑና የቆይታ ጊዜው ነው። የሚፈለገውን ጥራት ባሟላ መልኩ ሀገር ውስጥ የሚያመርት አምራች ካለ አብረን ለመሥራት ፈቃደኞች ነን ›› ሲሉም አስታውቋል፡፡

እሱ እንዳብራራው፤ ከቻይና የሚመጣው ማስተማሪያ በጣም ረጅም ጊዜ ይቆያል። ባትሪው ቢያንስ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ያህል ሊያገለግል ይችላል። ፈጽሞ አይጨማደድም፤ ውሃ ቢገባበት እንኳን መከላከያ የተገጠመለት በመሆኑ አይበላሽም። በቤት ውስጥ የሚሰቀል በመሆኑ በጣም ረጅም ጊዜ ይቆያል፡፡

‹‹ማስተማሪያው ሕፃናት ራሳቸው በቀላሉ ሊማሩበት ይችላሉ። ከወላጆች የሚጠበቀው ማስተማሪያው የሚጠቀምበትን ሦስት የሪሞት ባትሪ ማስገባት ብቻ ነው። ከዚያ ሕፃናት በባህሪያቸው መነካካትና መሞከር ስለሚወዱ ሲነካኩትና ሲሞክሩ በራሳቸው ሊያውቁት የሚችሉ ነው›› ይላል፡፡

‹‹ባለፈው ዓመት ሥራው ከጀመርን አንስቶ ለስድስት ወራት ያህል አብዛኛውን ሥራ የሠራነው ሳይንስ ሙዚየም ውስጥ ነው፤ ከሙዚየሙ ትልቅ ድጋፍ አግኝተናል። የማስተዋወቅ ሥራ ሰርተናል፤ አብዛኛዎቹን ምርቶችም እዚያው መሸጥ ተችሏል›› የሚለው ዘርባቤል፤ አሁንም ከወር በፊት በጀመሯቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች እና ቲክቶክ ላይ እያስተዋወቁ እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡

በዚህ የፈጠራ ሥራ በአዲስ አበባ በተካሄደ የስታርትአፖች ውድድር ላይ አሸናፊ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ የፈጠራ ባለቤትነት መብትን ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ማግኘት ተመዝግበው እየጠበቁ መሆኑን ተናግሯል።

እነዘርባቤል ትኩረታቸውን ሕፃናት ላይ ስላደረጉ ከዚህ ፈጠራ በተጨማሪ ሕፃናት ፐዝሎችን በመገጣጠም የሀገራቸውን ታሪክ በቀላሉ እያወቁ እንዲያድጉ የሚያደርጉ ፐዝሎችን ለየት ባለመልኩ አዘጋጅተዋል። ፐዝሎቹን ዲዛይን፣ ምስልና ግጥም በማዘጋጀት አሳትመው ሕፃናት በቀላሉ የሀገራቸውን ታሪክ እንዲያውቁ እያደረጉ ነው።

ለአብነትም አትሌት አበበ ቢቂላን በተመለከተ ፐዝል አዘጋጅተዋል። ሕፃናት የአበበ ቢቂላን ማንነት ለማወቅ ሲፈልጉ ምስሉን የሚያሳይና ምንድነው የሰራው የሚለውን እንዲያወቁ የሚያስችል ነው። ፓዝሉም በአማርኛና በእንግሊዘኛ ግጥም የተዘጋጀ ነው። ፐዝሉን መገጣጠም የሕፃናት አእምሮ የበለጠ እንዲሰፋ ይጠቅማል፤ ገጥመው ከጨረሱም በኋላ ይሄ ምንድነው ብለው የሀገራቸውን ታሪክ እንዲያወቁ ለማድረግ ይረዳል ሲል ዘርባቤል ያብራራል። የሀገራችንን ታሪካዊ ቦታዎች የተመለከቱ ፐዝሎች በሀገሪቱ እንዳሉ ጠቅሶ፣ እነርሱ ይህን አሻሽለው በተለየ መልኩ ማዘጋጀታቸውን ያመላክታል።

እሱ እንዳብራራው፤ ይህ የፊደል ገበታው የመጀመሪያ ሥራ ነው፤ እነ ዘሩባቤል ወደፊትም ከዚህ በተሻለ መልኩ የአማርኛን ፊደሎች ማስተማር የሚቻልበትን ዘዴ ለመፍጠር ይሰራሉ። በተለይ ሕፃናትን ከስልክ በማራቅ ባሕሉን መሠረት ባደረገ መልኩ ቴክኖሎጂን ጨምሮ የሀገራቸውን ባህልና ሥርዓት በእጃቸው ሳይቀር ዳስሰው እንዲውቁ፣ እንዲማሩበትና እንዲለምዱ ለማድረግ ብዙ ሥራዎችን ይሰራሉ። በተጨማሪ ሌሎች ለሕፃናት የሚሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት እየተዘጋጁ ናቸው፡፡

ወጣት ዘርባቤል ፤ በተለይ አሁን ላይ ሥራ ለሚጀምሩ ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎች (ስታርትአፖች) ከዚህ በላይ ጥሩ እድል የሚያገኙ አይመስለኝም ፤ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ሥራ ፈጣሪዎች ሀሳቡ እያላቸው የተቀመጠውን መስፈርት ለማሟላት ባለመቻላቸው ሲቸገሩ ቆይተዋል። በመሆኑም አሁን ላይ አብዛኛዎቹ ችግሮች በሚባል ደረጃ እንዲቀረፉ የሚያደርጉ የሕግ ማሻሻያዎች እየወጡ ናቸው፤ ሃሳብ ያላቸው የፈጠራ ባለሙያዎች ያላቸው ሃሳብ ይዘው ሥራቸውን መጀመር ይችላሉ ሲል ምክረ ሃሳቡን ሰጥቷል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2016 ዓ.ም

Recommended For You