የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሊቅ

በተሰማሩበት የሙያ መስክ የላቀ አበርክቶ በማኖር የሀገራቸውን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስጠሩና ታሪካቸውን በደማቅ ቀለም ማፃፍ የቻሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል አይደለም። ከእነዚህ እንቁ ግለሰቦች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሊቅ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ አንዱ ናቸው።

ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ከአባታቸው ግራዝማች ከበደ አድነውና ከእናታቸው ወይዘሮ ፋንታዬ ነከሬ ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ። የሙዚቃ ፍቅርን ገና በልጅነታቸው ያሳደሩባቸው እናታቸው ቢሆኑም ታዳጊው አሸናፊ ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳሉ ወላጅ እናታቸውን በሞት አጥተዋል።

ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ መሠረታዊ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (አሁን ኮከበ ጽባሕ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚባለው) ካጠናቀቁ በኋላ ከሐረር የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ተመርቀዋል። ከዚያም ወደ አሜሪካ በማቅናት ኒውዮርክ ከተማ ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሮቸስተር፣ ኢስትማን የሙዚቃ ትምህርት ቤት (University of Rochester’s Eastman School of Music) በ1954 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለሰ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን መሥርተዋል።

የትምህርት ቤቱም የመጀመሪያው ዳይሬክተር ከመሆናቸውም ባሻገር ሙዚቃን በማስተማር አገልግለዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ.ወ.ክ.ማ.)፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት መርሓ-ዕውራን ትምህርት ቤት እና በመሳሰሉ የወጣቶች ማኅበራት እየተገኙ የሙዚቃ ትምህርት ይሰጡ ነበር።

የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው ከ 1955ዓ.ም እስከ 1960 ዓ.ም ድረስ ባገለገሉበት ወቅት በንጉሠ ነገሥቱ “ብሔራዊ የሙዚቃ አቀናባሪ” ተብለው ከመሠያማቸውም ሌላ ለባሕላዊ ጉዳዮች ላደረጉት የላቀ ተዋጽኦ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ተሸላሚ ሆነዋል። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የልደት በዓል በተከበረበት በዚሁ ወቅት በሀንጋሪያ መንግሥት ተጋብዘው ወደ ቡዳፔስት በመጓዝ ታዋቂውን «እረኛው ባለዋሽንት» እና «የኢትዮጵያ ሲንፎኒያ” የተባሉትን ሁለት ድርሰቶቻቸውን በአቀናባሪነትና በኦርኬስትራ መሪነት አቅርበው፤ በሸክላ አሳትመዋል። መታሰቢያነቱንም ለጃንሆይ የልደት በዓል አበርክተዋል። ከሸክላው የሚገኘውን ገቢ በወቅቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሥር ይተዳደር ለነበረው የመርሐ-ዕውራን ትምህርት ቤት ለግሠዋል።

ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ‘ጥቁሩ ኮዳሊ’ የሚለውን ማቆላመጫም ያገኙት የረቂቅ ሙዚቃ ድርሰታቸውን በሀንጋሪ ውስጥ ከ’ፊልሃርሞኒክ ኦርኬስትራ ጋር በእርሳቸው ሙዚቃ መሪነት ባቀረቡበት ጊዜ ነበር። ታሪኩ እንዲህ ነው፦ እ.ኤ.አ 1967 ዓ.ም. በቡዳፔስት ሃንጋሪ ታላላቅ አውሮፖውያን የሙዚቃ አቀናባሪዎች የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ባቀረቡበት አዳራሽ ውስጥ አንድ አዲስ ክስተት ታየ፡፡ ይኸውም በዚያ የነበረውን የአውሮፓ የሙዚቃ ኦርኬስትራ ለመምራት ቆሞ የነበረው ከአህጉረ አፍሪካ የ26 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ወጣት አሸናፊ ከበደ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ወጣት የሙዚቃ አቀናባሪ በሚያስደንቅ ሁኔታ ቅንብሩን ከመምራቱ የተነሣ በጊዜውና በቦታው የነበሩት ነጭ ተመልካቾች፦ «አንድ ጥቁር አፍሪካዊ በሙዚቃ ትምህርት የሠለጠኑትን የነጮች ኦርኬስትራ እንዴት ሊመራ ቻለ?» በማለት አድንቀው ነበር፡፡

የመጀመሪያውንና ታላቅ የሆነውን እረኛው ባለዋሽንት” የሚለውን ቅንብሩን በይፋ ካቀረበ በኋላ የፕሮፌሰር አሸናፊ ዝና በመላው ሃንጋሪ ናኘ፤ ሃንጋሪያውያን በሀገራቸው ታዋቂ ከነበረውና እ.አ.አ ከ 1882 –1967 ዓ.ም. ከኖረው ዞልታን ኮዳሊ ከተባለው የሙዚቃ አቀናባሪ ጋር በማመሳሰል «ጥቁሩ ኮዳሊ» የሚል ስም ሰጡት። ፕሮፌሰር አሸናፊ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የዓለም አቀፍ የሙዚቃ ትእይንቶች ላይ ተገኝተዋል በተለይም በ1960ዎቹ አካባቢ በርካታ ሙዚቃዎችን አቀናብረዋል፤ ኦርኬስትራዎችንም መርተዋል።

በተጨማሪም ስለ ሦስተኛው ዓለም ሀገሮች፣ ስለ ዐረብ፣ ስለ ጃፖንና ስለ አውሮፖ ሙዚቃ ከነበረው ጥልቅ ዕውቀት የተነሣ በሙዚቃ ጥበብ ሚዩዚኮሎጂ/ ታላቅ ሰው ለመባል በቅተዋል፤ በዚህም ምክንያት ታላላቅ የሙዚቃ ሰዎችንና ሥራዎቻቸውን ይዘው በሚወጡ ጽሑፎች ላይ ስማቸው ተጽፏል፡፡ በ(International Who is Who In Music 1.0.9 ) ከአፍሪካውያንና አፍሪካ አሜሪካውያን ታዋቂ ሙዚቀኞች ተርታ ሳይቀር አንዱ ሆነው ተቆጥረዋል።

ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ በተመለሱ ጊዜ የሙዚቃ ጥናታቸውን አጠናቀው፣ በሁለተኛ ዲግሪ በ1960 ዓ.ም፤ በዶክትሬት ደግሞ በ1963 ዓ.ም ከ ʿዌስሊያን ዩኒቨርሲቲ’ ተመረቁ። ከ 1962 ዓ.ም እስከ 1968 ዓ.ም ድረስ በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ፣ ‘ክዊንስ ኮሌጅ’ እና በማሳቹሴትስ ብራንዲስ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ለአሥራ ዘጠኝ ዓመታት በፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ፤ መጀመሪያ በፕሮፌሰርነት በኋላም የዩኒቨርሲቲው “የጥቁር አሜሪካውያን የባህል ማዕከል” ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በተጨማሪም በዶክተር መላኩ በያን የተመሠረተውን “የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር ድርጅት” ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።

ፕሮፌሰር አሸናፊ ከሙዚቃ አቀናባሪነታቸውና ከኤትኖሚ ዚኮሎጂስትነት ባሻገር የፈጠራ ፀሐፊም ናቸው፡፡ ለምሳሌ፦ ከሥራዎቻቸው መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስለትና በ1964 ዓ.ም. የታተመው “Confes­sion” የተባለው ድርሰት ሀያስያንን በመማረክ የአፍሪካ ደራስያን፣ አራቱ የአፍሪካ ሥነ ጽሑፎች (Hour fri­can Literature) በሚሏቸው ኅትመቶች ውስጥ ተካቶ ሊጻፍ በቅቷል፡፡

ከዚህም ባሻገር የተለያዩ ሥራዎቹን ማለትም ከሙዚቃ ጋር የተያያዙ መጣጥፎችን፣ በዓለም ሙዚቃ ላይ የጻፋቸውን መጽሐፎቹን ጨምሮ ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ ሙዚቃ ነክ ከሆኑት ሥራዎቹ መካከል እ.ኤ.አ በ1966 ዓ.ም የሙዚቃ ሰዋሰው፣ የአምባራስ የአዝማሪ ሙዚቃ በ1969 ዓ. ም. ፣ የአፍሪካ ሙዚቃ በምዕራቡ ዓለም በ1972 ዓ. ም. “The Bon-Lyre of North East Africa. Kirar. The Devil’s instru­ment” በ 1977 ዓ.ም ሙዚቃ በጥቁር አይሁዶችና በክርስቲያን ማኅበረሰብ፣ በ 1980 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ዘመናዊና ባህላዊ ሙዚቃ ሂደት፣ በ1976 ዓ. ም. የጥቁሮች ሙዚቃ ሥረ መሠረት፣ የአፍሪካውያንና የጥቁር አሜሪካውያን የሙዚቃ መሣሪያ ዓይነቶችንና ውዝዋዜዎችን የዳሰሰባቸው የጽሑፍ ሥራዎችና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመናዊ አባባሎችና ግጥሞችን ለሕትመት አብቅተዋል፡፡ ከ 8 የሚበልጡ ዋና ዋና የሙዚቃ ሥራዎችንም አቀነባብረው አበርክተዋል።

ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ / Febri Sbolar/ የሚል የምሁርነት ስያሜ የተሰጣቸው ሲሆን የተለያዩ ሽልማቶችንም አሸንፈዋል። ለምሳሌ፦ UNESCO Florida Finc – Mrs Couns, Na fional Endow­ment for the Humanist, Canada National Mu­sic Counsel, American Learned Society Coun­sel 0-9 UNESCO Research Grant ሽልማቶችን ተቀብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር አሸናፊ ከሙዚቃ ድርሰቶቻቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትና ተወዳጅነትን ያተረፈው ‘እረኛው ባለዋሽንት’ ብቻ ሳይሆን ከሌሎቹም አንዳንዱን ለመጥቀስ፦ ‘ሰላም ለኢትዮጵያ’፤ ‘የሀገራችን ሕይወት’፤ ‘የተማሪ ፍቅር’፤ ‘እሳት እራት’፤ ‘ኮቱሬዥያ’ እና ‘ኒርቫኒክ ፋንታሲ’ የሚባሉት ድርሰቶች የሚጠቀሱ ናቸው። በሥነ-ጽሑፍ ረገድ ደግሞ በተማሪነታቸው ዘመን በ1956 ዓ.ም የደረሱት እና ያሳተሙት “ንስሐ” ወይም Confessions የተባለው መጽሐፍ እና “የሙዚቃ ሰዋሰው” እንዲሁም በርካታ የጥናትና ምርምር ድርሰቶች ይጠቀሳሉ።

የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ዋና ጥረት የነበረው በተለያዩ ባህሎች ውስጥ ያሉ አስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን የወከለ አንድ ዓይነት የሆነ የሰው ልጆችን ማንነት የሚገልጽ የሙዚቃ ቅንብርን አግኝቶ በእርሱ አማካኝነት ኪነ ጥበብን መግለጽ ነበር፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ በዓለም ውስጥ ለሚታየው የዘር ግጭትና መድሎ እንዲሁም ማኅበራዊ ኢ-ፍትሓዊነት መፍትሔ የሚሆንን ነገር በሙዚቃው ውስጥ ይፈላልግ ነበር።

ፕሮፌሰር አሸናፊ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሙዚቃ አቀናባሪነታቸው ይልቅ በምሁርነታቸው በመምህርነታቸው የበለጠ ይታወቃሉ። በሙዚቃው ቅንብር ከዓለም አቀፍ መርሆች ይልቅ በራሳቸው ፈጠራ ላይ ያተኩራሉ። ከዚህ የተነሣም ምዕራባውያን ባስቀመጡት የሙዚቃ ምድብ ሊፈረጁና ደረጃቸው ሊታወቅ አልቻለም፡፡

በተጨማሪም ፕሮፌሰር አሸናፊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በአውሮፖ የሙዚቃ መሣሪያዎች እንዲዳብርም አድርገዋል። በጣም የሚወዷቸውን የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ ለምሣሌ፦ ዋሽንትን፣ ክላርኔትንና ቫዬሊንን በመጠቀምና የኢትዮጵያን ዜማ በማስገባት አስደናቂ ኢትዮጵያዊ ዜማዎችን ለመፍጠር ችለዋል። ለምሣሌ «እረኛው ባለዋሽንት» እና አራቱ ዋና ዋና ሥራዎቹን ጨምሮ ኮቶ ዚተር በሚባል ባለ13 ክር መሳሪያ ክላርኔት ወይም ፍሉትና ቫዬሊን በመጠቀም የተጫወቷቸው ናቸው።

ይህ የኢትዮጵያን ዜማ ከምሥራቅና ከምዕራብ የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር በመቀላቀል በሙዚቃ ዓለም አቀፋዊነትን የፈጠረ ሲሆን፣ በዚህ ሥራቸውም ሁለቱንም የዓለም ሥራ ማለትም ምሥራቁንና ምዕራቡን ሊያስደንቅ ችሏል። በዚሁ ሙያ በቆዩበት ዘመን ሁሉ ለትውልድ ሀገራቸው ለኢትዮጵያና እንዲሁም ለጃፖን፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ ፤ ለህንድ ፣ ለምሥራቅ አውሮፖ፣ በተለይም ለሀንጋሪና ለአሜሪካ ሙዚቃ የተለየ ትኩረት ነበራቸው።

የፕሮፌሰር አሸናፊ የሙዚቃ ቅንብሮች ውስጣዊ ስሜትን የሚፈጥሩትን ያህል በውጫዊ ነገሮችም ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ፡፡ ለምሣሌ አንዳንድ ቅንብሮቹ በማኅበረሰብ፣ በፖለቲካና በመንግሥት ላይ ያተኮሩ ሲሆነ ከፊሎቹ ደግሞ በቀጥታ ከሙዚቃና የሙዚቃን ቅንብር ከመተወን ጋር ይያያዛሉ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ናቸው።

እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ እና በ1970ዎቹ በነበሩት የኢትዮጵያ መንግሥታት ጫና የተነሣ የግጥምና የዜማ ይዘቶች ፖለቲካውንና ርእዮተ ዓለሙን በሚደግፉበት መልኩ እንዲደርሱ ይደረግ ነበር፡፡ ከነበረው ጫና የተነሣ የፕሮፌሰር አሸናፊ የግጥምና የዜማ ድርሰቶች ውጫዊ ይዘታቸው ባለሥልጣናቱ እንደሚፈልጉት ቢመስሉም በውስጣቸው ግን ድብቅ ምስጢርን ያዘሉ እንዲሆኑ ስለማድረጋቸው ይነገራል።

ፕሮፌሰር አሸናፊ ፍሎሪዳ ውስጥ በሚገኘው የታለሀሴ ዩኒቨርስቲ በአፍሪካ አሜሪካ የባህል ማዕከል በዳይሬክተርነት በቆዩበት ጊዜ፣ የአፍሪካንና የአፍሪካ አሜሪካንን ዳንስ፣ ሙዚቃ እና ድራማ በፍሎሪዳ ከተማ እንዲታይ ያደርጉ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር አሽናፊ ከታላቅ የሙዚቃ አቀናባሪነታቸውም በላይ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው አስተማሪ ነበሩ።

እርሳቸው በነበሩበት ኮሌጅ ውስጥ የሙዚቃ አስተማሪ የነበረች አንዲት ሴት ስለ ፕሮፌሰር አሸናፊ በተማሪነቷ ጊዜ ስለነበራት ትውስታ ስትናገር፣ «እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ ውስጥ ሙዚቃ በሚያስተምረን ወቅት ምርምር ያሠራን ነበር። ከክፍል በፊትና በኋላ የአፍሪካ ሙዚቃ እንሰማለን። ከተዛባ አመለካከታችን የተነሣ ቀድሞ እንጠላው የነበረውን የአፍሪካ ሙዚቃ መውደድ ጀመርን። ከዚህም የተነሣ የጥቁር አፍሪካ፣ የእስያንና የዐረቡ ዓለም ሙዚቃዎች በኮሌጁ የኮርስ ዝርዝር ውስጥ ተካተቱ፡» የሚል ምስክርነት ሰጥታለች።

ፕሮፌሰር አሽናፊ ግንቦት 1 ቀን 1990 ዓ.ም በ 60 ዓመታቸው በታለሃሴ ፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ በማገልገል ላይ እያሉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ፕሮፌሰር አሸናፊ ከመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ባለቤታቸው (ወይዘሮ እሌኒ ገብረመስቀል) እና ከሁለተኛ አሜሪካዊት ባለቤታቸው አራት ልጆችን (ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ) ልጆችን አፍርተዋል። ፕሮፌሰር አሸናፊ ጥንታዊውን ኢትዮጵያዊ ባለቅኔና የሙዚቃ አቀናባሪ የነበረውን ቅዱስ ያሬድን የሚያደንቁ የሚወዱ ከመሆኑ የተነሣ ከአሜሪካዊት ሁለተኛዋ ባለቤታቸው ከዶክተር ሜትኮዊክስ የወለዱትን ልጃቸውን ስም ያሬድ ብለው ሰይመውታል።

እኛም እኚህን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለውለታና በዘርፉ ሀገራቸውን በከፍተኛ ክብር ማስጠራት የቻሉትን ሰው ነፍስ ይማር እንላለን።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም

Recommended For You