የጥቂቶች ጥፋት ለብዙዎች ክስረት

‹‹የክፉን ጎረቤት መብረቅ ይመታዋል›› የሚባል ሀገርኛ አባባል አለ:: ይህንኑ የሚያጠናክር ‹‹ለኃጥአን የወረደ ለጻድቃን ይተርፋል›› የሚባል ሌላም አባባል አለ:: የሁለቱም መልዕክት በአንድ መጥፎ ሰው ምክንያት የሚመጣ ጦስ ለበጎ ሰዎች ሁሉ ይተርፋል ለማለት ነው:: በተለይም ለጥፋተኛው የሚቀርቡ ሰዎች የጉዳቱ ሰለባ ይሆናሉ ማለት ነው:: ‹‹ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል›› የሚል ሦስተኛ አባባል መጨመርም ይቻላል::

ይህን ሁሉ ያስታወሰኝ አንድ ቀላል ገጠመኝ ነው:: አንድ ጓደኛዬ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ባመቻቸው ‹‹ኦንላይን›› ግብይት ዕቃ ገዛ:: ክፍያውን ከፈጸመ በኋላ ሌላ ተጨማሪ ዕቃ እንዲገዛ የሚያስገድድ ዘዴ ዘይደው አስገዙት:: ይህን ያደረጉት ጽሑፉን እንደገና አስተካክለው ነው:: የተስተካከለ (edited) ይላል:: የመጀመሪያውን ዕቃ ስለወደደው ሌላ ተጨማሪ ሊገዛ ከፈለ:: ችግሩ ግን ይህ ብቻ አልነበረም:: በሁለት ሰዓት ውስጥ ይደርሳል ያሉት ዕቃ በሁለት ሳምንትም ሳይደርስ መቅረቱ ነው::

ለጊዜው ቁርጡ ባይታወቅም የማጭበርበር አዝማሚያ ይመስላል:: ይህን የነገርኳቸው ሌሎች ጓደኞቼ እንደነገሩኝ ግን ቅድመ ክፍያ ከፍለው የተከዱ እንዳሉ ነገሩኝ:: በሌላ በኩል ደግሞ ታሽጎ የሚመጣው ዕቃ በኦንላይን የታየው እንዳልሆነ ያጋጠማቸው ነገሩኝ:: ኦንላይን ላይ የሚያሳዩት ሌላ፣ አምጥተው የሚያስረክቡት ሌላ (ጥራቱ የወረደ) ይሆናል:: እንዲህ አይነቶቹ አጭበርባሪዎች የሚጠቅሱት የአድራሻ ቦታ የውሸት ነው:: ከተጠቀሰው ቦታ ሲኬድ ምናልባትም እነርሱ ከሚሸጡት ጋር በፍጹም የማይገናኝ ሌላ ነገር ይሆናል::

እነዚህን ገጠመኞች ስሰማ አስቀድሜ ያዘንኩት በታማኝነት ለሚያገለግሉት የኦንላይን ነጋዴዎች ነው:: ምክንያቱም በእነዚህ አጭበርባሪዎች ምክንያት በአጠቃላይ የዘርፉ ስም ይጠፋል፤ የኦንላይን ግብይት ታማኝነት እንዲያጣ ያደርጋል:: የተጭበረበሩ ሰዎች እና ስለተጭበረበሩ ሰዎች የሚሰሙ ሰዎች ‹‹ኧረ ከኦንላይን አትግዛ›› ነው እንጂ የሚሉት ለይተው ከዚያ ካጭበረበረው ሰው ብቻ አይሉም:: ‹‹የክፉን ጎረቤት መብረቅ ይመታዋል›› ሆነ ማለት ነው:: ምክንያቱም በተመሳሳይ መስመር ላይ ያሉ ሰዎች እንደ ጎረቤት ነው የሚታዩት:: እንዲህ አይነት ማጭበርበሮች በዚያ ዘርፍ ላይ እምነት እንዳይኖር ያደርጋሉ::

ከሦስት ይሁን አራት ዓመታት በፊት በድላላ ሥራ ላይ በተሰማሩ አጭበርባሪዎች ላይ አንድ ትዝብት አጋርተን ነበር:: እነዚህ ደላሎች በየመብራት እንጨቱ ላይ ማስታወቂያ ይለጥፋሉ:: ከማስታወቂያው ግርጌ አድራሻ ይለጥፋሉ:: የሆነ ቦታ ቢሮ ተከራይተው ለትንሽ ጊዜ ከዚያ ቢሮ ሆነው ሥራ ፈላጊዎችን ይመዘግባሉ:: ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ቢሮውን ይለቁታል:: ገንዘብ የሚያስከፍሉት በቅድሚያ ነው:: የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በእነዚህ አጭበርባሪዎች ላይ የሰራውን ዘገባ አስታውሳለሁ::

ጋዜጠኛው ሥራ ፈላጊ መስሎ ሲደውልላቸው ትክክለኛውን ነገር አይናገሩም፤ ሁሉም ነገር የሚሆነው ቢሮ መጥተህ ነው የሚል መልስ ይሰጣሉ:: እኔም ከአንድ ጓደኛዬ ጋር አራት ኪሎ ከጠቆሙት አንድ ቢሯቸው ውስጥ ገብተን አረጋግጠናል:: በር ላይ ሆኖ ይህን የሚከላከልና የሚቆጣጠር ሰው አለ:: አፋጠን ስንጠይቀው ሲጨናነቅ ነበር:: እንግዲህ በእነዚህ አጭበርባሪዎች ምክንያት በደፈናው ‹‹ደላላ›› በሚል የብዙ ታማኝ ደላሎች ስም አብሮ ይጠፋል ማለት ነው:: ድለላ የሚለው ስም ከማጭበርበር ጋር የተያያዘ ትርጉም ይይዛል ማለት ነው::

የኦንላይን ግብይት ቴክኖሎጂ የወለደው ሥራን ያቀለለ የሥልጣኔ መገለጫ ነው:: አንድ ሰው ጊዜ ሳያባክን የሥራ ቦታው ላይ የሚፈልገው ነገር ይመጣለታል:: ይህን የመሰለ ሥልጣኔ ግን ጥቂቶች ጭቃ ሊቀቡት ነው ማለት ነው:: ሰዎች አምነው ላይገዙ ነው ማለት ነው:: በእርግጥ የግድ ሁሉም ክፍያ ቅድሚያ አይሆንም:: ዕቃውን ከተቀበሉ በኋላ መክፈል ይቻላል:: ይህ ሲሆን ግን ሻጮችም እዚያ ድረስ ለፍተን ‹‹አልገዛም›› ቢለን የሚል ስጋት ያድርባቸዋል:: እንዲህ የሚል (አልከፍልም የሚል) አይኖርም ማለትም አይቻልም:: ምክንያቱም መተማመን የጠፋው ከሁሉም ወገን ነው::

እጅግ አደገኛው የኋላቀርነት መገለጫ ስርቆት፣ ማታለልና ማጭበርበር ነው:: ይህን የሚቆጣጠር የሰለጠነ የተዘረጋ ሥርዓት እንኳን ባይኖረን ‹‹ኩሩ ኢትዮጵያዊነት›› እያልን የምንፎክርበት ሞራላችን ግን ሊኖር ይገባ ነበር:: ምክንያቱም ከየትኛውም ዘመናዊ የረቀቀ ቴክኖሎጂ በላይ ሞራል ይበልጣል:: የሰለጠኑት ሀገራት ግን ሁለቱንም አላቸው::

ጋዜጠኛና ደራሲ በረከት በላይነህ ሰሞኑን በአንድ የፖድካስት ሚዲያ ላይ ሲናገር የሰማሁት ገጠመኝ ብዙ እንድገረም ያደረገኝ ነው:: ጓደኛው ያጋጠመው ነው:: ነገሩ እንዲህ ነው::

አንድ ጓደኛው ወደ ሀገረ ቻይና ተጉዞ ነበር:: ያረፈበት ቤት ውስጥ ዕቃ (ስልክ መሰለኝ) ረስቶ ይሄዳል:: የተሰረቀ መስሎት የሄደበት አካባቢ ለሚገኝ የፀጥታ አካል አመለከተ:: እዚያው ቆሞ እያለ የሚያዩትን አይተው (በአሰራራቸው ሥርዓት) ዕቃው ቻይና ምድር ላይ እንዳልጠፋ፣ ይልቁንም ያረፈበት ክፍል ውስጥ እንዳለ ነገሩት:: ‹‹እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል? እንዳልጨቃጨቃቸው ሊገላገሉኝ ፈልገው ነው እንጂ!›› እያለ ወጣ:: ወደ ክፍሉ ሲገባ ግን የጠፋበት የመሰለው ዕቃ እንዳስቀመጠው ነው:: መቼም በዘረጉት ሥርዓት እንጂ በአስማት ሊሆን አይችልም ብሎ እየተገረመ ወደ ሀገሩ መጣ::

ችግራችን ድህነት ነው እንዳይባል የማጭበርበርና የማታለል ድርጊቶች የሚፈጸሙት የተሻለ የገቢ ደረጃ ባላቸው ነጋዴዎች ነው:: በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ሰዎች ሀቀኞች ናቸው:: የጽዳት ሠራተኞች ‹‹ወድቆ ያገኙትን ይህን ያህል ሺህ ብር አስረከቡ›› ሲባል በተደጋጋሚ እንሰማለን:: የሚጠየቁበት የህግ አግባብ ባይኖር እንኳን ለፈጣሪያቸው ግን ታማኝ ናቸው:: የእነርሱ ዳኛ ህሊናቸው ነውና ማንም ስላላየኝ የራሴ ላድርገው አይሉም:: የተሻለ ገቢ አለው የሚባለው አካል ግን ሊያስጠይቀው የሚችል ማስረጃና መረጃ እያለ ሁሉ ልማድ ሆኖበት ያጭበረብራል:: ነጮች ጥቁሮችን የሚጠሉበት አንዱ ምክንያት እንዲህ አይነት ኋላቀርነት ነው:: እንዲህ አይነቱን የኋላቀርነት ልማድ ሳያስወግዱ ‹‹ኩሩ ጥቁር ነኝ! ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ ኩሩ አፍሪካዊ ነኝ…›› ማለት ከንቱ ውዳሴ ነው:: ምንም እንኳን ድርጊቱ የጥቂቶች ቢሆንም ሲደጋገም ግን እንደ ሀገር ብዙ ችግር እንዳለብን ያሳያል::

ሞራል ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ግልጽ ነው:: ያም ሆኖ ግን ከስንዴ ውስጥ እንክርዳድ አይጠፋምና በጥቂቶች ገጽታ እንዳይበላሽ ህጋዊ ቁጥጥር መደረግ አለበት፣ ግለሰቦች አጭበርባሪ ሲያጋጥማቸው ሊያጋልጡ ይገባል:: ‹‹ብናጋልጥ ምን ዋጋ አለው!›› የሚል ተስፋ መቁረጥ እንዳይኖር የፀጥታ አካላትም ጥቆማ ሲሰጣቸው ተገቢውን ትኩረትና ክትትል ሊያደርጉ ይገባል:: ምክንያቱም የእንዲህ አይነት ጥቃቅን ነገሮች ድምር የሀገርን ገጽታ ያበላሻል!

ዋለልኝ አየለ

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም

Recommended For You