ለ10 ዓመት ኮማ ውስጥ የቆየ ባሏን የተንከባከበች ባለቤቱ የጥንካሬ ተምሌት ተብላለች

በቻይና ለ10 ዓመታት ኮማ ውስጥ የነበረውን ግለሰብ ስትንከባከብ በመቆየቷ ሲነቃ ከተመለከተች በኋላ ባለቤቱ የጥንካሬ ተምሳሌት ተብላ በቻይና እየተወደሰች ይገኛል።

በምሥራቃዊ ቻይና አንሁይ በተባለችው ግዛት ነዋሪ የሆነችው ሰን ሆንግሻይ ባሏ እ.አ.አ. በ2014 በገጠመው ድንገተኛ የልብ ድካም ኮማ ውስጥ ይገባል። በአጭር ጊዜ ከኮማ ይወጣል፤ የቤተሰቡም ስጋት ይወገዳል ተብሎ ቢጠበቅም ምን እየተካሄደ እንደሆነ በውል መረዳትና መግለጽ የማይችለው ባል 10 ዓመታት ኮማ ውስጥ ይቆያል።

ከሰሞኑ ግን ሰን ለድፍን10 ዓመታት በተስፋ የጠበቀችው፤ በብዙ የደከመችለት ጉዳይ ፍሬ አፍርቶ የምትወደውና የሁለት ልጆቿ አባት ነቅቷል። ያለፉትን ዓመታት እንዴት እንዳሳለፈች በእንባ ታጅባ ስትነግረው የሚያሳይ ምስልም ተለቋል።

“ምንም እንኳን በጣም ቢደክመኝም ቤተሰባችን ወደቀድሞው ደስታው እንዲመለስ የተከፈለ መስዋዕትነት አድርጌ እወስደዋለሁ” ስትልም ዳዋን ለተሰኘው የቻይና መገናኛ ብዙኃንተናግራለች።

የሰን ባል ረጅም ዓመት ኮማ ውስጥ መቆየቱን ተከትሎ የሚስቱ ድጋፍ እጅግ ወሳኝ ነበር። የሰውነት አካሉን ማዘዝ ስለማይችል አይንቀሳቀስም፤ ይህም ካለሚስቱ ድጋፍ መጸዳዳት እንኳን እንዳይችል አድርጎታል።

ዓይኑ በሂደት በከፊል መገለጥ መጀመሩ ተስፋዬን እያለመለመው ሄደ የምትለው ሰን፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሕመሙ እየበረታ ፈተናዋን ቢያበዛባትም እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ አብራው ለመቆየት ቃል ለገባችለት ባሏ ሙሉ ጊዜዋን ሰጥታ ያለመሰልቸት ተንከባክባዋለች።

የ84 ዓመቱ የታማሚው አባትም የዚህ ምስክር ናቸው። “ሰን የልጄ ሚስት ብትሆንም ከሴት ልጄ የተሻለች ልዩ ሰው ናት፤ ከእርሷ ጋር ማንም አይወዳደርም” ሲሉ ለልጃቸው ያሳየችውን ወደር የለሽ ፍቅር እና እንክብካቤ አድንቀዋል ብሏል ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት በዘገባው።

ከኮማ ከወጣ ባሏ ጋር የተነሳችው ምስልም በቻይና ማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት እየተዘዋወረ ነው።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም

Recommended For You