በደቡብ አፍሪካ አንድ ሕንፃ ተደርምሶ በርካቶች መውጫ አጥተዋል

በደቡብ አፍሪካ በግንባታ ላይ ያለ አንድ ሕንፃ ተደርምሶ አራት ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ በርካቶች መውጫ ማጣታቸው ተነገረ።

በሕንፃው ውስጥ መውጫ ያጡ 51 ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ የነፍስ አድን ርብርብ መጀመሩም ተገልጿል።

በዌስተርን ኬፕ ግዛት በምትገኘው ጆርጅ ከተማ በደረሰው የሕንፃ መደርመስ አደጋ 24 ግለሰቦችን ከፍርስራሹ በማውጣት ወደ ሆስፒታል መውሰድ ተችሏል።

ሕንፃው ሰኞ እለት በተደረመሰበት ወቅት 75 ሠራተኞች ነበሩ። በባህርዳርቻዋ ከተማ የደረሰውን ክስተት መንስኤ ለማጣራት ምርመራ ተጀምሯል ተብሏል።

ሕንፃው በሀገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ገደማ እንደተደረመሰ የዌስተርን ኬፕ አስተዳዳሪ አላን ዊንዴ ገልጸዋል።

ከኬፕታውን በስተምሥራቅ 450 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ከተማ ውስጥ ከደረሰው የመደርመስ አደጋ ሰዎችን በሕይወት ለመታደግ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ወደ ስፍራው ሲጣደፉ ታይተዋል።

ከፍራስራሾቹ ውስጥ ከነበሩት 22 ሰዎች መካከል ሁለቱ ወዲያውኑ ሕይወታቸው አልፏል። በኋላም ሌሎች ሁለት በደረሰባቸው ጉዳቶች ምክንያት ሕይወታቸው እንዳለፈ ተዘግቧል።

“በዚህ አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች መጽናናትን እየተመኘን እየተጠባበቁ ላሉ ቤተሰቦች በሃሳብ ከናንተ ጋር ነን” ሲሉ የከተማዋ ከንቲባ አንድ ቫን ዋይክ ተናግረዋል።

ከ100 የሚበልጡ የነፍስ አድን ሠራተኞች ከአነፍናፊ ውሾች ጋር ተሠማርተው ከሕንፃው ፍርስራሽ ሰዎችን ለማውጣት ሌሊቱን ሙሉ ሲሠሩ ነበር ተብሏል።

ይህንን ሥራ ለማገዝ ዘመናዊ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ተነግሯል። በፍርስራሹ ውስጥ ተቀብረው ከሚገኙ ሰዎች ውስጥ ከተወሰኑት ጋር ንግግር ማድረግ እንደተቻለ ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

ሕንፃው ሙሉ በሙሉ ተደርምሶ ፍርስራሾች ብቻ የሚታዩበት ፎቶዎች ወጥተዋል።

“አንድ ግለሰብ በሕንፃው ላይ ሲሠራ አየሁ። ከዚያም ሕንፃው ሙሉ በሙሉ ሲደረመስ አየሁ። በጣም ደንግጫለሁ። በጣም ያሳዝናል ”ሲሉ ቴሬሳ ጄይ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለሮይተርስ መናገራቸው ተዘግቧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም

Recommended For You