ዲሞክራሲ መሬት ወረደ፤ የህዝቦች የመምረጥና መመረጥ መብቶች ተከበሩ፤ የብሄር ብሄረሰቦች መብቶች እውቅና አገኙ ከተባለበት ድህረ 1983ዓ.ም ጀምሮ የዘንድሮው አገር አቀፍ ምርጫ 6ኛችን ነው።
በቁጥር 6ኛችን ይሁን እንጂ በአንዱም የህዝብም ሆነ የራሳቸውን የፖርቲዎቹን እርካታና ምስጋና እንኳን አላገኘም፤ ይህ ነው የሚባልና ዲሞክራሲያዊ ስርአትን እውን ለማድረግ የሚያስችል ውጤት አልተመዘገበበትም። ማለትም ሁሉም ያለ እንከን የተካሄዱና ዳር የደረሱ፤ የጋራ ስምምነት በተደረሰበት መልኩ የተጠናቀቁ አልነበሩምና ነው። በሁሉም ውዝግብ ነበር፤ በሁሉም ግጭት ነበር፤ በሁሉም ደም ፈሷል፤ በሁሉም መጭበርበርና ማጭበርበር ተከናውኗል፤ በሁሉም ኮሮጆ ተገልብጧል።
ከሁሉም ከሁሉም የዲሞክራሲው በር ተከፍቷል፤ እንከን የለሽ ምርጫ ለማድረግ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ወዘተ በተባለበት ታሪካዊው ምርጫ 1997 የተጠበቀው ቀርቶ ያልተጠበቀው እውን ሆኖ ዘመኑና ምርጫው የራሳቸውን ታሪካዊ ጠባሳ ትተው አልፈዋል። ይህ ሁሉ በታሪክ ድርሳናት ላይ ተገቢውን ስፍራ በመያዝ ስለእኛ ሲናገር እንደሚኖረው ሁሉ ተዋንያኑንም ለትዝብት እንደሚያበቃ የታወቀ ነው። ከ97ቱም ሆነ ከሌሎቹ የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው ምን አይነት ምርጫ ተካሂዶ፤ በምን መልኩ ተጠናቆ ለታሪክ ምስክርነት ይበቃ ይሆን የሚለው ዜጎችን ከወዲሁ እያስጨነቀ ያለ በመሆኑ ነው።
ጉዳዩን ከህዝብ ስሜትና አስተያየት አኳያ ከተመለከትነው የመራጩንም ሆነ ተመራጩን ወገን ፍላጎት ከወዲሁ ካጤንነው ምርጫው ካለፉት ስህተቶች የፀዳ፣ እንከን የለሽ፤ እስር፣ አፈና፣ እንግልት፣ ወዘተ የሌለበት፤ ማጭበርበርም ሆነ መጭበርበር የሌለበት፤ ኮሮጆ የማይገለበጥበት፤ ድምፅ ሰረቃ፣ ጦር ሰበቃ – – – የማይኖርበትና ያሸነፈ ወገን የመንግስት ስልጣንን ተረክቦ አገሪቱን የሚመራበት ሰላማዊ ሽግግር እንዲሆን ነው፤ ቢያንስ በሀሳብ ደረጃ። ጥያቄው “ይሄ ይሆናል እንዴ?” የሚለው ሲሆን አያይዘን ካየነው ጉዳዩ በጥያቄ ምልክት ስር ከመውደቅ አይድንም፤ በተለይ ሂደቱን ሆን ብሎ ለማወክ በሚመስል መልኩ በአዲስ ጉልበት ወደ ውድድሩ ሜዳ መግባታቸውን ልብ ላልን ይህ እውነት አይሆንም ብሎ መናገር አይቻልም። ገና ከወዲሁ እሰጥ አገባው፣ ማፈንገጡ፣ ውንብድናው፣ ወዘተ እየተጧጧፈና ለምርጫ ሳይሆን ለፍጥጫ፣ ጡጫና እርግጫ ዝግጅት እየተደረገ ይመስላል። እየታየ ያለው እልህ እንጂ እውቀት መር ቅስቀሳ አይደለም። ሩጫው ለመወዳደቅ እንጂ ተፎካክሮ ለማሸነፍ (ለመሸናነፍ) አይመስልም። ከአማራጭ ፖሊሲ ይልቅ የቃላት ፍላፃው፣ የነገር አሽሙሩ፣ ብሽሽቁ … ነው ግዘፍ ነስቶ የሚታየው።
እንደ አለመታደል ሆኖ እስካሁን እየተደረጉ ባሉ የማሟሟቂያም እንበላቸው ወይም የመግቢያ ቅስቀሳዎች ላይ ሙስናን አጠፋለሁ፤ ስራ አጥነትን እቀንሳለሁ (አጠፋለሁ እንኳን ባይሉ)፤ ሰላምና መረጋጋትን አሰፍናለሁ፤ ኢኮኖሚውን አሳድጋለሁ፤ በህዝቦች መካከል በሰላም አብሮ የመኖር፣ የመረዳዳት፣ መደጋገፍ፣ መተሳሰብ ወዘተ እሴቶችን አስጠብቃለሁ፤ በዜጎች መካከል ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር አደርጋለሁ፤ በመላ አገሪቱ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ የዲሞክራሲው ምህዳር እንዲሰፋ፣ የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ አበክሬ እሰራለሁ ወዘተ የሚሉ፤ ለአገርና ለወገን የሚበጁ ድምፆችን ሳይሆን እየሰማን ያለነው የግል ህይወት ተኮር፣ ራስን ብቻ ማእከል ያደረገና ህዝብን ወደ የማያባራ ብጥብጥ የሚመሩ መርዘኛ ቅስቀሳዎችን ነው። ይህ ደግሞ አሁኑኑ ካልታረመ ትርፉ አበሳ ሲሆን እዳውም ገብስ አይደለምና ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል።
ህዝብ እየጠበቀ ያለው ለአንድነትና ለፍቅር፣ ለሰላምና ደህንነት፣ ለእድገትና ብልፅግና፣ ለአብሮነትና ወንድማማችነት እተጋለሁ የሚል ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ ሳለ፤ እየሰማንና እያየ ያለው እውነታ ግን ተስፋ አስቆራጭ ነው ባይባልም ተስፋ ሰጪ ነው ማለት ግን አይቻልም። ሁኔታዎች በሙሉ እያመለከቱን ያሉት ከህዝብ ፍላጎት በተቃራኒውና የመንደር ጎረምሶች ስብስብ አይነት ነገሮችን እንጂ ምራቅ የዋጠ የፖለቲካ ተሳትፎን አይደለም።
ህዝቡ የአርሶ አደሩን ችግሮች ከስራቸው መንግዬ እጥላለሁ፤ የከተሞችን የተወሳሰቡ ችግሮች ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ (የውሸትም ቢሆን) እፈታለሁ፤ ባልተፈለጉ ቢሮክራሲያዊ አሰራሮች የተተበተቡ የህዝብ አገልግሎት እንቅፋቶችን በመፍታት አሰራሮችን አሻሽላለሁ፤ ህዝብን እያማረረ ያለውን የህገ-ወጥ ንግድና የኑሮ ውድነት ስርአት አስይዛለሁ፤ በዜጎች መካከል ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን አሰፍናለሁ የሚሉ የመወዳደሪያ አማራጭ ሀሳቦችን መስማት እየናፈቀ ሳለ ጆሮው እየተቃጠለ ያለው ግን ለአገርና ህዝብ ስጋት የሆኑ ቃላትን በመስማት ነው።
ከመረጣችሁኝ በአገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበር፤ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፤ የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲጨምር፤ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲስፋፉ፤ የሴቶች፣ ህፃናትና እናቶች ሁለንተናዊ መብቶች እንዲከበሩ በርትቼ እሰራለሁ የሚል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ እስካሁን አልተሰማም። ስለመኖሩም በእርግጠኝነት አፍን ሞልቶ መናገር አስቸጋሪ የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው።
ባጠቃላይ የህዝብ ፍላጎትም ሆነ የምርጫ ተፈጥሯዊ ባህርይ የሚፈልጉት አቢይ ጉዳይ ቢኖር ከላይ የዘረዘርናቸውን አይነት ተግባራት እንጂ ለግል ዝና፣ እውቅናና ሀብት ለማፍራት የሚደረግ አይደለምና በዘንድሮው ምርጫ የሚሳተፉ አካላት በሙሉ ከወዲሁ ሊያስቡበት ይገባል እንላለን።አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2013