አብርሃም ተወልደ
ታዋቂው የፍልስፍና ሰው ኮንፊሽየስ “በየትኛውም ሁኔታ ጊዜ የለኝም፤ እረፍት የሚባል አላውቅም ብለህ የምታስብ ቢሆን እንኳ ለራስህ እና ለማንበብ የግድ ጊዜ መስጠት አለብህ። ይህን አላደረክም ማለት ግን በገዛ ፍላጎትህ ራስህን አላዋቂ እና የማይፈልግ ሰው እያደረክ ነው ማለት ነው።” ሲል ተናግሯል። እርግጥ ነው ፤ ሳይታለም የተፈታ ሀቅ። ያሳለፍከውን የህይወት ጊዜ ለመገምገምም ሆነ ለአካልም እረፍት ለመስጠት እና ለቀጣይ ግዳጅ ራስንም ለማዘጋጀት ጊዜ መውሰድ እና ማንበብ ይደር የማይባል የህይወት አካል ሊሆን ይገባዋል።
እኛም ለዛሬ በዝነኞች የእረፍት ውሎ የራሳቸው የእረፍት ጊዜ የማሳለፊያ መንገድ ከአላቸው ዝነኞች መካከል አንዱን አርቲስት ይዘን ቀርበናል። አርቲስቱ በጥበብ እድሜው ሁለት አልበሞችን፣በርካታ ነጠላ ዜማዎችን ሰርቷል። በስራዎቹ አንቱታን ተጎናጽፏል።
ከአራት ያላነሱ የጥበቡ ቤተሰቦችን ሽልማቶች አግኝቷል። ብዛት ያላቸው ሰርተፍኬቶችን ለሰራቸው ስራ መታሰቢያ ተብለው ተሰጥተውታል።
አርቲስቱ ከጥበቡም ባሻገር የምህድስና ሙያ ባለቤትም ነው። የምህድስና ትምህርቱንም የተከታተለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣በሙያውም የተለያዩ ቦታዎች ከመቀጠር እስከ አማካሪነት ድረስ ሰርቷል፤ እየሰራም ይገኛል።
በማህበራዊ ህይወቱ የቀና እና የተሳካለት እንደሆነ ባልንጀሮቹ እና የሙያ አጋሮቹ ይመሰክሩለታል። የተቸገረ ሰው ሲያይ በተቻለው አቅም የሚረዳ ሌሎችም ይህንኑ እንዲያደርጉ የሚመክርና የሚያስተባብር ነው። የዛሬ የዝነኞች ውሎ እንግዳችን ፍልቅልቁ፣ ተጫዋቹ ሳሙኤል ብርሃኑ ወይም ሳሚ ዳን ።
የእረፍት ጊዜውን እንዴት እያሳለፈ ነው ?
አርቲስት ሳሙኤል ብርሃኑ (ሳሚ ዳን) የእረፍት ጊዜ ስለማሳለፍ የራሱ የሆነ መርህ እንዳለው ይገልጻል። ማድረግ የሚፈልገውን ብቻ እንደሚያደርግ እና ማድረግ የማይፈልገውን በምንም አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንደማያደርግ ይናገራል።
አርቲስት ሳሙኤል እንደሚለው፤ በመጀመሪያ ማንኛውም ሰው ጊዜውን እና በዚያ ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባው ሊያውቅ ይገባል ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ጊዜን የራስ ማድረግ ያስፈልጋል። ጊዜን የራስ ለማድረግ በመጀመሪያ የገንዘብ ነጻነትን ማግኘት የግድ ነው፤ ምክንያቱም አንድ ሰው የወደደውን ወይም በልቡ ያለውን ለመከወን ያ! የጊዜ ነጻነት መሰረታዊ ነው።
በመጀመሪያ የጊዜ አለቃ ለመሆን የተለያዩ ቦታዎች ተቀጥሮ በመስራት ማለትም እኔ የምፈልገውን ዓይነት ጊዜ ሳይሆን የተቀጠርኩበት የሚፈልገውን አይነት ጊዜ አሳልፌያለሁ ይላል። ከብዙ ልፋት እና ድካም በኋላ የደረስኩበት ግኝት ግን ሰው የሚያዝበት ጊዜ ሊኖረው እንደሚገባ ነው ሲል ያብራራል።
አሁን ባለሁበት ሁኔታ የማዝበት የጊዜ ባለቤት ነኝ። ስለዚህ ጠዋት ተነስቼ አንዱን ቀን እረፍቴ ማድረግ እችላለሁ ያለው አርቲስቱ፣ በዚያ ጊዜ የተሰማውን እንደሚያደርግ ይገልጻል። ጠዋት ተነስቶ መጽሐፍ ማንበብ ከሆነ የፈለገው እንደዛው እንደተሰማው መጽሀፍ ያነባል።
አርቲስቱ የራሱ የሆነ የመጽሐፍ ምርጫ እንዳለው የገለጸ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ልቦለድ ላይ ያተኩር እንደ ነበር ያስታውሳል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ግለ ታሪኮችን ምርጫው እንዳደረገ ይናገራል። ልክ እንደ መጽሐፉ በሌላኛው የእረፍት ቀኑ ላይ የተሰማው ፊልም ማየት ከሆነ ፊልም ያያል። የእረፍት ጊዜውን ሌሎች ሰዎች ወይም ሁኔታና አሰራሮች እንደማይሰጡት ያውቃል፤ ራሱ አርቲስቱ በፈለገው ጊዜ ግን እረፍት እንደሚያደርግ ይናገራል። በእነዚህ ጊዜያት ላይ የሚወስነው ደግሞ አርቲስቱ ጠዋት የተነሳበት ሁናቴ ነው።
በእረፍት ጊዜ ላይ ዋና እና የማልደራደርበት ነገር አለ ሲል ይገልጻል። ማህበራዊ ህይወት ዋና እና መሰረታዊ ጉዳይ ነው። የታመመ መጠየቅ፣ለቅሶ መድረስ እና መሰል ጉዳዮች ለአፍታም ቢሆን ቸል የማልላቸው ናቸው ይላል። አርቲስቱ ሌሎቹን ሁሉ የሚያደርገው ከማህበራዊ ህይወት መልስ መሆኑን ያብራራል።
የእረፍት ጊዜን ሌሎች እንዴት ያሳልፉ
አርቲስት ሳሙኤል ብርሃኑ (ሳሚ ዳን ) ጊዜ ከሀብቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሶ ፣ የትኛውም ሰው በተቻለው መጠን የሚያዝበት ጊዜ ሊኖረው እንደሚገባ ያስገነዝባል።
እንደ አርቲስቱ ገለጻ፤ የፈለጉትን የጊዜ ነጻነት ደግሞ ለማግኘት አስቀድሞ የሚያስፈልጉትን ነገሮች መስራት ያስፈልጋል። ለዚህ የጊዜ ነጻነት ለማግኘት አንዱ እና ዋናው ጉዳይ የገንዘብ ነጻነት ማግኘት ነው። አንድ ሰው እንደሚሰማው ለመኖር ለምሳሌ መተኛት ሲያስፈልገው መተኛት ፣መስራት ሲያስፈልገው እንዲሁ ለመስራት የገንዘብ ነጻነት ቀድሞ ማግኘት ለማግኘትም መስራት ይኖርበታል።
ሰው ከጓደኞቹ እና ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር መጋጨት እንደሌለበት ጠቅሶ፣ አንድ ነገር እናድርግ ሲባል ግለሰቦች የራሳቸውን አቋም በግልጽ ሊያስቀምጡ ይገባል ሲል ያስገነዝባል።
ማንኛውም ግለሰብ ምን ማድረግ እንዳለበት ራሱ መወሰን አለበት የሚለው አርቲስቱ፣ ሌሎች ሰዎች የግለሰቡን አዋዋል እና የውሎ ሁኔታ ሊወስኑለት አይገባም ነው የሚለው። ይህን ምክር የሚሰማ ማንኛውም ግለሰብ ከይሉኝታ ተላቆ በራሱ ለራሱ ውሎ ሊወስን ይገባል ይላል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም