
ሀገር፣ ሕዝብ፣ ጥበብ…አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ዓርማ፤ ኢትዮጵያን ይዘው የቆሙ፣ የኢትዮጵያዊነት ፀዳል ነፀብራቆች ናቸው። እነኚህም ባማሩ የጥበብ ቃላት ተከሽነው በግጥም እንዘምራቸዋለን፣ እንደ ዳዊት እንደግማቸዋለን፣ እንደ በረሃው ዮሐንስ ዘ ነጎድጓድ ጮኸን እንሰብካቸዋለን።
ቀለማት ከምድር ከፍ፣ ከሰማይ ዝቅ ብለው ቀስተ ደመናው ስር ይውለበለባሉ። በሰማይና ምድር መካከል የቆሙ የኢትዮጵያ ካስማዎች ናቸውና። የውበቷ ሰንደቅ፣ የሕዝቦቿ ሰንደቅ፣ የማንነቷ ሰንደቅ፣ የከፍታዋ ሰንደቅ፣ የሉዓላዊነቷ ሰንደቅ፣ የጀግንነት አይበገሬነቷ ሰንደቅ፣ የፍቅር፣ የክብር፣ የአንድነት፣ የእኩልነት፣ የነፃነት ሰንደቅ…የሁሉም መጀመሪያ የጥበብ ሰንደቅ ነው። ይሄው ሰንደቅ እየተዘመረለት ይወጣል፤ እየተዘመረለትም ይወርዳል። ከስንቶቻችን የልብ ትርታ ጋር ወጥቶ እንደሚወርድ፣ በስንቶቻችን ልቡና አንደበት እንደምንዘምረው ግን ራሳችን እንወቀው።
በግጥም በዜማ “የዜግነት ክብር” እስካልንበት ድረስ፣ ከመጀመሪያው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ተነስተን በጥበብ ቅኝቱ ስር ጥቂት ሾረን እንቃኛቸው። የሥርዓተ ጥበቡ አንኳር መገለጫ “ሰንደቅ ዓላማ” የሚለው ነውና ቅድሚያ ትርጓሜውስ? እንበል። ሁለት ቃላት ለአንዲት ሀገር ክብር ታጥቀው መሳ ለመሳ ቆመዋልና ‹ሰንደቅ› የሚለው ቃል ካስማነትን የሚያሳይ ‹ምሰሶ› ማለት ነው። ከድካም የሚያበረታ፣ ከውድቀት የሚታደግ ‹ምርኩዝ› እንደማለትም ነው።
ሁለተኛው “ዓላማ” የሚለው ቃል ነው። የዓላማ የመጀመሪያው ነገር ‹ምልክት› ነው። የሀገርን መልክና ወዘና፣ የሕዝቦቿን ማንነትና ደምግባት የሚያመለክት አመልካች ጣት ነው። ምልክቱን የተከተሉ ኢትዮጵያን ያገኛሉ፣ ምልክቱን ያዩ ኢትዮጵያን ያያሉ። ቆራጥነት፣ ሀገር ወዳድነት፣ ለሀገር ተጋዳይነት…ከዚህም ሌላ ዓላማ በራስ ኃይል የመቆም ‹ሉዓላዊነት› እና በየትኛውም ቦታና ጊዜ ‹ነፃነት› የሚል ኃያል ጽኑ ትርጓሜን የያዘ ነው። ሁለቱ ቃላት በአንድ ላይ ተጣምረው ከውስጥ “የሀገር መታወቂያ” የሚለውን ትርጉም ይሰጡናል።
ኢትዮጵያ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሰንደቅ ዓላማ ቢኖራትም ብሔራዊ መዝሙር የተጀመረው ግን በ20ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ሰንደቅ ዓላማና ሀገር ድርና ማግ ሆነው የተቆራኙትም በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት፣ ከ1890 ጀምሮ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በመዝሙር የታጀበው ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከ1919ዓ.ም ጀምሮ ነበር። ከዚህ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሀገራችን ሦስት ብሔራዊ መዝሙሮችን አስተናግዳለች። ዓመተ ምሕረቱን ይዘን ወዲህ ስንመጣ፣ በሀገሪቱ ውስጥ የተደረጉ አስተዳደራዊ የፖለቲካ ለውጦችም በዋናነት በሦስት የሚመደቡ ሆኖ እናገኛቸዋለን። አሃዳዊ፣ ኅብረተሰባዊ እና ፌደራላዊ ሥርዓቶችን የሚያራምዱ ሦስት ሕገ-መንግሥታዊ ድልድዮች ተዘርግተዋል። በዚህ ድልድይ ተሻግረው የመጡ ብሔራዊ መዝሙሮቻችንም ከለውጦቹ ጋር እየተለወጡ መምጣታቸው ለማናችንም ግልጽ ነው። ነገር ግን የአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ብሔራዊ መዝሙር የፖለቲካው አካል መሆን አለበት ወይ? የሚለውን ጥያቄ ሁላችንም ልናስብበትና ልንመልሰው የሚገባ ቁልፍ ነገር ነው። ሀሳቡን ወደኋላ እናሸራተውና በቅድሚያ ግን ሦስቱንም መዝሙሮች አንድ በአንድ እንመልከታቸው።
“ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ
በአምላክሽ ኃይል በንጉሥሽ
ተባብረዋልና አርበኞችሽ
አይነካም ከቶ ነፃነትሽ
ብርቱ ናቸውና ተራሮችሽ
.
.
እያለ የሚቀጥል ነበር የበኩር ዝማሬው።
“ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ” ለሰንደቅ ዓላማችን የተዘመረላት የመጀመሪያው መዝሙር ነበር። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፣ ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ቀደም ብሎ የተዘጋጀ ነው። የዚህ መዝሙር የግጥም ደራሲ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ነው። የዜማውን ሙዚቃዊ ልኬት የሠራው ደግሞ አርመናዊው ኪቮርክ ናልባንዲያን ነው። መዝሙሩን አጥንተው ለመጀመሪያ ጊዜ በኅብረ ዝማሬ ያስደመጡት የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነበሩ። አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን የንግሥና ዘውዳቸውን ደፍተው ስማቸው ወደ ‹ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ› በተቀየረበት በበዓለ ሲመታቸው ዕለት፣ የዝግጅቱ ትልቁ ድምቀት የነበረውም ይሄው መዝሙር ነበር። እስከ 1966ቱ አብዮት ድረስ በሀገራችን ለሀገራችን፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሕዝባዊ ክብረ በዓላትና ዝግጅቶች፣ በውጭ ለባንዲራችን ከጀግኖቹ ክብር ጋር ሲዘመር የቆየው ይሄው መዝሙር ነበር።
ዘመን በዘመን፣ ሥርዓትም በሥርዓት፣ ግጥም በግጥም፣ ዜማም በዜማ፤ መዝሙርም በሌላ መዝሙር ተተካ። ከዘውዳዊነት ወደ ኅብረተሰባዊነት የሥርዓት ለውጥ ያመጣው ወታደራዊው የደርግ መንግሥት፣ የቀደመውን መዝሙር ለመዘመር ከአብዮታችን ድምፅ ጋር አብሮ የማይሄድ ነው በሚል እሳቤ፣ አብዮቱን የሚገልጠውን ሌላኛው መዝሙር እንዲዘጋጅ አደረገ። መዝሙሩ የተዘጋጀው በ1968ዓ.ም ሲሆን ግጥሙን የደረሰው አሰፋ ገ/ማርያም፣ ዜማውን የሠራው ደግሞ ዳንኤል ዮሐንስ ነበር።
“ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ-ኢትዮጵያ ቅደሚ
በኅብረተሰባዊነት-አብቢ ለምልሚ!
ቃል ኪዳን ገብተዋል-ጀግኖች ልጆችሽ
ወንዞች ተራሮችሽ-ድንግል መሬትሽ
ለኢትዮጵያ አንድነት-ለነፃነትሽ
መስዋዕት ሊሆኑ-ለክብር ለዝናሽ!
ተራመጂ ወደፊት-በጥበብ ጎዳና
ታጠቂ ለሥራ-ለሀገር ብልፅግና!
የጀግኖች እናት ነሽ-በልጆችሽ ኩሪ
ጠላቶችሽ ይጥፉ-ለዘላለም ኑሪ።”
ከአብዮት ወደ ግንቦት…ግንቦት 20 1983ዓ.ም ሌላ ሥርዓት፣ ሌላ መዝሙር ተከተለ። ዛሬም ድረስ የምንዘምረው “የዜግነት ክብር” የሚለው መዝሙራችን ደርግን ገርስሶ በተተካው በኢሕአዴግ መንግሥት አማካይነት የተዘጋጀ ነው። የዚህ መዝሙር የግጥም ደራሲ ደረጀ መላኩ መንገሻ ሲሆን፣ የዜማው ደራሲ ደግሞ ሰለሞን ሉሉ ምትኩ ነው።
“የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ
ታየ ሕዝባዊነት ዳር እስከ ዳር በርቶ
ለሰላም ለፍትሕ ለሕዝቦች ነፃነት
በእኩልነት በፍቅር ቆመናል ባንድነት
መሠረተ ጽኑ ስብዕናን ያልሻርን
ሕዝቦች ነን ለሥራ በሥራ የኖርን
ድንቅ የባህል መድረክ
ያኩሪ ቅርስ ባለቤት
የተፈጥሮ ፀጋ የጀግና ሕዝብ እናት
እንጠብቅሻለን አለብን አደራ
ኢትዮጵያችን ኑሪ እኛም ባንቺ እንኩራ።”
እያልን አሁን ድረስ አለን፤ ግን ይህን መዝሙር በትክክል የምናውቅ ስንቶቻችን እንደሆንን ቢፈተሽ ‹ጉድ በይ ሀገር!› የሚያሰኝ ነው።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በቅጡ የሚገናኝበትና የሚተዋወቅበት አንደኛውና ዋነኛው ስፍራ ትምህርት ቤቶች ናቸው። ቀደም ባሉት ጊዜያት ትምህርት ቤቶች ለሰንደቅ ዓላማ ያላቸው ቦታና ክብር ልዩ ነበር። ይሁንና የሰንደቅ ዓላማ፣ በዋናነትም የብሔራዊ መዝሙር ሕልውና ትምህርት ቤቶች ውስጥ ብቻ መጣሉ አሳዛኝ ስህተት ነው። እውነቱን ለመናገር ትምህርት ቤቶች ውስጥም አሁን አሁን ወግና መልኩን፣ ክብርና ሥርዓቱን እያጣ መምጣቱ በአንዲት እይታ የምናስተውለው ነው። በአሁኑና በቀደመው ትውልድ፣ በድሮና በዘንድሮ ተማሪ መካከል ለሰንደቅ ዓላማ ያለው ቦታና አመለካከት ለየቅል መሆኑ በእርግጥ ‹ያሳዝናል› ከማለትም በላይ ነው። ድሮ ድሮ ‹እኔ ካልሰቀልኩ እኔ ካላወርድኩ› ብሎ በባንዲራ የሚዋደቅ ተማሪ፣ አሁን አሁን በስላቦ አይገኝም። ‹እኔ ላዘምር› እያለ እጁን ሰማይ ሰቀል የሚያርገበግብ ተማሪ፣ አሁን ዝም ጭጭ ተለጉሞ አብሮ ለመዘመር እንኳን ልቡ ዝቅ ይልበታል። ይህ ሁሉ የምንሰማው ብቻ ሳይሆን ማየት ከፈለግን የምናየው ሐቅ ነው።
በአንድ አጋጣሚ በጥቂት ወጣቶች ተከበው ሲጨዋወቱ የነበሩ አንድ ጠና ያሉ ሰውዬ፤ ጨዋታው መሐል እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው “…ይህ ትውልድ እንኳን ባንዲራን ከጨርቅ ለይቶ የሚያይ አይመስለኝም። በእኛ ጊዜ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የምንመለከታት ኢትዮጵያ ነበረች። ተማሪ ሆነን በሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት ዶፍ ቢዘንብ፣ ሐሩር ቢወርድ ሳንዘምርና ባንዲራ ሳንሰቅል ሳናወርድ ውልፍት አንልም ነበር። እንዲህ የምናደርገው የመምህራኖቻችንን ቁጣና ቁጥጥር ፈርተን አልነበረም፤ ሁላችንም ከልባችን በሆነ ስሜት ለባንዲራና መዝሙሩ ከነበረን ፍቅርና አክብሮት ነበር።”
የሰንደቅ ዓላማ ሥርዓት ማለት ጠዋት መስቀል፣ አመሻሽ ማውረድ አይደለም። ብሔራዊ መዝሙር ማለትም ባንዲራው ሲሰቀልና ሲወረድ በዝምታ ከሚሆን ተብሎ እንዲሁ የመጣ ማጀቢያ ሳውንድ ትራክ አይደለም። ጠዋት ድምፅ የሚሞርዱበት ቮካል፣ ለጠዋት ተማሪው ማነቃቂያና የዕለቱ ትምህርት ማስጀመሪያም አይደለም። የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት ጥልቅ የሆነ ሀገራዊ ምስጢርና ትርጉም ያለው ነው። ትምህርት ቤቶች ማለት ትውልድን ለሀገር የሚቀርጹበት ትልቁና ወሳኙ ግንባር ነው። ሀገሩን እዚህ ያላወቀ ትውልድ ሌላ የትም ሊያውቅ አይችልም። እዚህ ስለሀገሩ ክብር ግድ ሊለው ካልቻለ የትም ሄዶ ምንም ቢሠራ ክብሯን ሊያስጠብቅና ሊጠብቅ አይችልም።
ባለፍንባቸው በየትኛውም ጊዜና ሁኔታዎች ውስጥ በሰንደቅ ዓላማና በብሔራዊ መዝሙር ወደኋላ የሚል ትውልድም ሆነ አስተሳሰብ እንዳልነበረ፣ በታሪክ ሲነገርም የምንሰማው ነው። ድሮ ድሮ ሲዘመር በወግ በማዕረግ፣ እውነተኛ ከሆነ ስሜትና ፍላጎት ጋር ነበር። ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንኳንስ ለባንዲራና ለመዝሙሩ ይቅርና ቅድመ ሥርዓት በሆነው ‹አሳርፍ…ተጠንቀቅ…ከንዳና አውርድ› ቀልድ አልነበረም። አሁን ግን ምን እየተመለከትን ነው ያለነው? ከወዲህ ባልራቀው በአንደኛው ጊዜ ላይ፤ ለአንዳንድ ተማሪዎች ሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት የቂልነት፣ ሰልፍ ላይ ቆሞ መዘመርም ‹ፋርነት› ሆኖ ታየ። ከዚህ ቂልነትና ፋርነት ለማምለጥ ግቢ ገብቶ በክፍሎች ወይም እስኪያልቅ ከደጅ በጥጋጥጉ የሚወሸቀውን ተማሪ ምን ያህሉ እንደሆነ፣ ከማናችንም በላይ መምህራኑና ራሱ ተማሪው ያውቀዋል። ይህንን ሳንገራና ሳናቀና ዓይኖቻችንን ወደ መጽሐፍትና ሠሌዳ የምንመልስ ከሆነ ማስተማሩም ከንቱ ነው። ‹ሰንደቅ ዓላማን አላከበሩም ማለት ሀገርን አላከበሩም ማለት አይደለም› ልንል እንችል ይሆናል ግን “ዝናብ በሌለበት ደመና አይታይም” የሚል አባባልም አለ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በትምህርት ቤቶችም ሆኑ በአንዳንድ አጋጣሚዎች የምንመለከተው ነገር አለ፤ ብሔራዊ መዝሙርን እየዘመሩ ከመድከም በግዙፍ ቴፕ መልቀቅ። የፈለገውን ያህል ብንዘምን፣ የቱንም ዓይነት ቆንጆ ስፒከር ብንገዛ፤ ብሔራዊ መዝሙርን ከአፍ አውጥቶ መዘመር የሚያደክምና ኋላቀር የሚያደርግ ነው? በትምህርት ቤቶች ውስጥ ለዚህ ሁለት ምክንያቶችን እንሰማለን፤ መዘመርና ማዘመር አሰልቺ ተግባር እየሆነ፣ ሌላኛው ደግሞ ተማሪው እሺ ብሎ ስለማይዘምር ነው። መደረግ የሌለበት ነገር እንደሆነ እያወቁ ዘማሪ በማጣት ስፒከር የሚከፍቱና ከነጭራሹም ስለጉዳዩ ሳያስቡበት ቴፑን ስላገኙ ብቻ የሚለቁም አሉ።
ከሁሉ የከፋው ደግሞ ልሳን አልባውን የክላሲካል ቅንብር ከፍተው የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት የሚያካሂዱም መኖራቸው ነው። ጀግኖቻችን አሸንፈው ወይም በሌላ አጋጣሚ በውጭ ሀገራት መድረኮች ላይ ክላሲካሉ ብቻ የሚከፈትበት የራሱ የሆነ ምክንያት ስላለው ነው። እዚሁ ሀገር ውስጥ ያውም በትምህርት ቤቶች፤ የነገው ሀገር ተረካቢ እንዲህ ባለ መንገድ አሳፋሪ ነው። አብዛኛዎቻችንም ‹ይሄ ምን ችግር አለው፤ እንዲያውም ሞቅ ባለ የስፒከር ድምፅ ያማረ ይሆናል እንጂ› እንደምንል እርግጥ ነው። ነገር ግን፤ ጠለቅ ብለን ወደ ውስጥ ለማየት ከሞከርን ጉዳዩ ስለ ስፒከሩ ወይም ስለ ሥነ ሥርዓቱ መድመቅና አለመድመቅ አይደለም። ትምህርት ቤቶቻችን እንዳመጣው በዘፈቀደ ከመስቀልና ከማውረድ እንዲሁም ከመዘመር በፊት የሰንደቅ ዓላማን ምንነትና የሥነ ሥርዓቱ ዓላማ ምን እንደሆን በቅጡ ሊያውቁና ከትምህርቶች ሁሉ የመጀመሪያው የማስተማሪያ ይዘታቸው ይህ ጉዳይ ሊሆን ይገባል። ከባዮሎጂና ፊዚክስ፣ ከእንግሊዘኛ፣ ከሒሳብና ጂኦግራፊው በፊት የሀገር ክብር የሆነውን ሰንደቅ ማሰንደቅ ይቀድማል። ‹አካባቢ ሳይንስ› ካሉም ትክክለኛው የአካባቢ ሳይንስ መጀመሪያም የሀገርና ክብር ነው። ከቤት ሥራዎች ሁሉ የመጀመሪያው የቤት ሥራ መሆን ያለበትም፤ ብሔራዊ መዝሙሩን አጥንተው እንዲመጡ ማድረግ ነው።
ሰንደቅ ዓላማ ከሚውለበለብባቸው ስፍራዎች ሌላኛው መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ነው። ቀድሞ ቢያንስ በመሥሪያ ቤቱ የጥበቃ አባላት በጊዜና በወጉ ይሰቀልና ይወርድ ነበር። አሁን ግን በአንዳንዱ ቦታ አንድ ጊዜ ተሰቅሎ የሚወርደውም አንድ ጊዜ ነው፤ በዝናብ፣ በፀሐይ፣ በንፋሱ ተቦጫጭቆ ሲያልቅ ነው። አንዳንዱ ቦታ ላይ ቆንጆ ሰንደቅ መስቀያ ብረቶች ሰማይ ጠቀስ ተገትረዋል፤ ቀና ሲሉ ግን ባንዲራው የለም። እንደ ክት ልብስ የሚወጡት ለስብሰባና ክብረ በዓላት፣ ለሆኑ ዓይነት ዝግጅቶች ነው። ትንሽ ሻል ይላል ካሉ ትዝ ባለው ሰዓት ሰቅሎ ትዝ ባለው ሰዓት ያወርዳል። እንኳንስ እንዲህ ሊደረግ፤ ከአሰቃቀልና ከአወራረዱ፣ ከአስተጣጠፍና ከአቀማመጡ ጀምሮ የራሱ የሆነ ሥርዓት ያለው ክቡር ነገር ነው።
ቅሉ ከታች ብቻ ሳይሆን፤ አሁን አሁን ከላይም በሽታ እየሆነ መጥቷል። በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚስፋፋ፣ ሀገርና ሕዝብን ከፖለቲካ እየደባለቀ መላቅጥ ያሳጣን በግልጽ ያልገባን ወረርሺኝ ስለመኖሩ እሙን ነው። ለዚህ በሽታ እንደመንስኤ ልንቆጥረው የምንችለው አንደኛው መንስኤም፤ መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር ሁሉ የብሔራዊ መዝሙርና የእንብርት ዓርማ የመቀየር አባዜያችን ነው። በዚህ ምክንያትም፤ ሰንደቅ ዓላማ የመንግሥት፤ የሰንደቅ ዓላማ ክብርም ለመንግሥት የሚገባ ግብር መስሎ የሚሰማው አንዳንዱ ብቅ ሲል ይታያል።
ከትልቁ ብሔራዊ ባንዲራና መዝሙር ይልቅ፣ ለብሔር ባንዲራ ቦታና ከፍታ የሚሰጡም ፖለቲካዊ ድሪቷቸውን አውልቀው ቅድሚያ ለሀገርና ለሰንደቋ የሚገባትን ክብር ሊሰጡ ግድ ይላቸዋል! ወደድንም ጠላንም አንዲትን ትልቅና ሉዓላዊት ሀገርን ዝቅ አድርገን ከብሔርና ጎሳ ጋር ልናነጻጽር አንችልም፤ አይቻለንም። የፈለገውን ያህል ፖለቲካዊ ልዩነቶች ሊኖሩን ይችላሉ፤ ግን ልዩነታችንን የምንገልጸው በሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር ከሆነ፣ ከወረራት ፋሽስት በምንም አንለይም። ኢትዮጵያ መታወቂያዋ ይሄው ሰንደቅ፣ ይሄው መዝሙሯ ነው። እኛ በአንድ የቀበሌ መታወቂያ ባሕር ማዶ መሻገር እንደማንችለው ሁሉ ሀገርም በክልልና ብሔር ባንዲራ የትም፣ በምንም እልፍ ልትል አትችልም።
በዓለም የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ ውስጥ ስምጥ ገብተን እምጥ ብናስስ፣ ለውጦችን ልናገኝ የምንችለው በቅኝ ግዛት ምክንያት ብቻ ነው። በቅኝ ግዛት ስር ያልወደቅን እኛ ግን ግማሽ ምዕተ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለቴ እናፈራርቃለን። አንድ ጊዜ ሕዝብ ያመነበትን ማድረግ፣ ያመንበትንም እስከወዲያኛው አምኖ መኖር ስለሚከብደን ብዙ ነገሮችን እንነካካለን። እጅ የምናበዛበት ነገር ሁሉ መጨረሻው እጅ እጅ ማለቱ አይቀርምና ካለፉት ምንና እንዴት ልንማር እንደምንችል እንወቅበት። ዛሬ ላይ በአንዲት ኢትዮጵያ ስም በሚሰበሰቡበት በፓርላማችን ሳይቀር እያሳየናቸው ያሉ አንዳንድ ነገሮች ነገ ሀገሪቱን የሚያጠፋ እንጂ የሚገነቡ አይደሉም። በእኛ ያረጃ አስተሳሰብና አመለካከት የአዲሱን ትውልድ አዕምሮ ባተሌ አድርገን ከምኑም እንዳይሆን አናድርገው። ፖለቲካ ሌላ ሰንደቅ ዓላማ ሌላ፣ ብሔር መውደድ ሌላ የሀገር ፍቅር ሌላ…”ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” አያስፈልገንም። ክብር ለኢትዮጵያዊነታችን! ክብር ለሰንደቅ ዓላማችን! ክብር ለብሔራዊ መዝሙራችን! ክብር ለጥበብ ዜማችን!
በሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም