በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
ህይወት ምርጫ እንደሆነች ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? አሁን ያላችሁበት ሁኔታ ሀብታችሁ፣ ዝናችሁ ድህነትና ማጣታችሁ፣ ሰላምና መከራችሁ ሁሉ በምርጫችሁ ያገኛችሁት እንደሆነስ ስንቶቻችሁ ገብቷችኋል? አንዳንዶቻችን በጸጸት አንዳንዶቻችን በኩራት እንኖራለን።ሁሉ ያለን እንዳለን ሁሉ ምንም የሌለንም ሞልተናል…ሚስጢሩ ግን እኛ ለመሆን የመረጥንውን ነን የሚለው ነው›።አትጠራጠሩ ይህ አለም በምርጫ የተሞላ ነው፣ የፈለጋችሁትን ነገር በፈለጋችሁት ጊዜና ቦታ ማግኘት ይቻላችኋል።ይህ እንዲሆን በሰዎች የአስተሳሰብ ልክ አስገዳጅ በሆነ ስርዐት ውስጥ አለም ተሰርታለች።የምንፈልገው ነገር በዝቶና ተትረፍርፎ የትም አለ እርምጃችን ግን ወደማይጠቅመን ቦታ ነው።የሚያስፈልገን እያለ ሩጫችን ሁሉ ወደማይጠቅመን ስፍራ ነው ለዚህም ነው ከሀሳባችን ከህልማችን ጎለን የምንኖረው።ለዚህም ነው ሁሉን ማግኘት እየቻልን በማጣት የምንሰቃየው።ለዚህም ነው ለሙላት ተፈጥረን በጉድለት የምንኖረው።
ህይወትን በብዙ ነገር ላይ አልተረዳናትም እላለው።ህይወትን የተረዳናት ቢሆን ኖሮ አሁን ባለንበት ስፍራ ላይ አንገኝም ነበር።ብዙዎቻችን ህልምና ራዕያችን ላይ እቃቃ የምንጫወት ነን።ብዙዎቻችን በህይወት ላይ የምንቀልድ ነን።ትርፍ ነፍስ ያለን ይመስል ለሰውነታችን ክብርና ልዕልና አንሰጥም።ህይወትን የተረዷት አስማት በሚመስል ሁኔታ እየኖሩ ነው።ለዛውም ከኋላችን ተነስተው፣ ለዛውም ከኋላችን ተወልደው።ከሁሉ አስቀድማችሁ ህይወትን ማሰብና…ማሰላሰል ነው።ህይወት ውድ ዋጋ ያላት የአንድ ጊዜ ስጦታ ናት።እኛ ግን በዚህ ውድና ድንቅ ተፈጥሯችን ህይወት ምን ማለት እንደሆነች አልተረዳንም።ህይወት ምን ማለት እንደሆነች የተረዳ ግለሰብ በራሱ ላይም ሆነ በሌሎች ላይ ጥፋት አያደርስም።
የሚያስፈልጋችሁ ነገር የት ቦታ እንዳለ ለይታችሁ እወቁ።ብዙ ነገር እየፈለጋችሁ እንደሆነ አውቃለው…ትላንትም ዛሬም ፍለጋ ላይ እንደሆናችሁ ይሄንንም አውቃለው።ግን የምትፈልጉትን አግኝታችሁ አታውቁም..ሁሌም ፍለጋ ላይ ናችሁ.።ፍለጋ ከመውጣታችሁ በፊት የምትፈልጉት ነገር የት እንዳለ እወቁ፣ ያ የምትፈልጉት ነገር የት ቦታ እንደሚገኝ ካላወቃችሁ ትርፉ ድካም ነው።የሚያስፈልገንን ለይተን ስናውቅ አንድ ሱቅ ገብተን እቃ ለመግዛት እንደመጠየቅ ያክል ሁሉም ነገር ቀላል ሆኖ በየቦታው እናገኘዋለን።ከሁሉም በፊት ግን ህይወትን ተረዷት..መኖርን መርምሩት..ከዛም የምትፈልጉት ነገር..ራዕያችሁ፣ ህልማችሁ የት ቦታ እንዳለ ለማወቅ ሞክሩ።ያኔ ስትፈልጉት የነበረውን አጠገባችሁ ታገኙታላችሁ።
ብዙ ሰዎች ህልማቸው የት ጋ እንዳለ የማያውቁ ጭራሽ ለምን እንደተፈጠሩ የማያውቁ ናቸው።አንዳንዶች ደግሞ ለምን እንደተፈጠሩ የሚያውቁ ግን የተፈጠሩበትን አላማ ለማሳካት የማይደክሙ አይነት ናቸው።የመፈጠራቸውን ምክንያት ተረድተው ህልማቸውን ለማሳካት የሚጥሩት ጥቂቶች ናቸው ።አገር የነዚህ ሁሉ አስተሳሰቦች ጥርቅም ናት።አንድ ሀገርና ህዝብ አደገ የሚባለው በውስጡ የሚያስቡ..የሚያገናዝቡ ማህበረሰቦች ሲኖሩበት ነው።ድህነት መነሻውም መድረሻውም አስተሳሰብ ነው።በአስተሳሰባችን ከንቱዎች ከሆንን በኑሯችንም ከንቱዎች ነን።የምፈልገውን አጣሁ አትበሉ አይደለም ለእናተ ይቅርና ለፍጡር ሁሉ የሚበቃ ሀብት አለም አላት።የምትፈልጉትን ካጣችሁም የሚያስፈልጋችሁን ስላላወቃችሁ ነው እላችኋለው።
ቡቲክ ገብተህ ያማረህን ሱፍ ለመግዛት የሚያስፈልግህ ምንድነው? ገንዘብ አይደል..ገንዘብ ከሌለህ ሱፉ የአንተ አይሆንም፤ ሌላ ገንዘብ ያለው ሰው መጥቶ ይገዛዋል..አንተም እንዳማረክ ይቀራል።በህይወት ውስጥም እንደዚህ ነው የምትፈልጉትን ለማግኘት ምርጫችሁን ለይታችሁ ማወቅ ይኖርባችኋል።ከዛም ሱፉን ለመግዛት ገንዘብ እንዳስፈለገህ ሁሉ ምርጫህንም የአንተ ለማድረግ ጥረት ያስፈልግሀል።የምትፈልጉትን ነገር ለማግኘት ህልምና ራዕይ ከሌላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሌላ ሰው ሲወስደው ቆማችሁ ነው የምታዩት ለምትወዱት ነገር ካለፋችሁ የበይ ተመልካች ሆናችሁ ትኖራላችሁ።ምን እንደምትፈልጉ ካወቃችሁ፣ ምርጫችሁ የት እንደሚገኝ ከተረዳችሁ ቀጣዩ ስራችሁ የሚሆነው ከህልማችሁ ጋር የምትፈልጉት ነገር ወደሚገኝበት ቦታ መሄድ ነው።ልብ በሉ የምትፈልጉት ነገር ዝም ብሎ አይገኝም።ጥሩ ነገር ሁሉ ልፋት ይፈልጋል..ህልማችሁን እውን ለማድረግ መልፋት ግድ ይላችኋል።
መልካም ህይወት ከመከራ ኋላ የተደበቀ ነው።ለመምረጥ መዘጋጀትና እንድንመርጥ የሚያስችለንን ሀይል መላበስ ግድ ይለናል።ካለ ፍለጋ ካለ መልካም ሀሳብ፣ ካለ ትጋት ማንም ከመሬት ተነስቶ የሚፈልገውን ነገር የራሱ ማድረግ አይችልም።ይህን እውነት ወደ ህይወት ስናመጣው እንዲህ ይሆናል..ህይወት ጥሩ ለሚመርጡና ጥሩ ለሚያስቡ ሁልጊዜም ጥሩ ናት።የትም መቼም ይሁን ወደ ፊት ለመሄድ ስትነሱ ሩቅ የሚያደርስ ሀሳብ ይኑራችሁ።መቼም የትም ይሁን ምንም ነገር ለማድረግ ስትነሱ ቀና ልብን በጎ ማንነትን የእናንተ አድርጉ።መከራን አትሽሹ..ችግርን አትጸየፉ…ስኬት ያለው መከራ ውስጥ ነው።ስቃያችሁን ውደዱት..ወርቅ የአሁኑን ውድነቱን ያገኘው በእሳት ተፈትኖ እንደሆነ አትርሱ።እጆቻችሁን ስራ አስለምዷቸው።ልቦቻችሁን ቅንነት አስተምሯቸው።ነፍሶቻችሁ ፈጣሪን እንዲያውቁ፣ ነውርና ግፍን እንዲሸሹ አድርጋችሁ አብጇቸው፡፡
አለም ለሁሉም እኩል ናት ለአንዱ እናት ለአንዱ እንጀራ እናት አይደለችም።ሆናም አታውቅም።አንድ እውነት ግን እነግራችኋለው አለም የባለ ራዕዮች ናት።የህልመኞች..የአስተዋዮች ናት።ከሌሎች በልጣችሁና ተሽላችሁ ካልተገኛችሁ የምትኖሩት ርካሽ ነገሮችን ስትሰበስቡ ነው።ለማሸነፍ ተጫወቱ፣ ሁሌጊዜም የተሻለውን ነገር ተመልከቱ።የምትፈልጓቸው ነገሮች ሁሉ መንገዳችሁ ላይ ናቸው።በትክክለኛው መንገድ ላይ እንደሆናችሁ ልብ በሉ።አሁን ላይ እየኖርን ያለነው ህይወት የምርጫችንን ነው። እየሆን ያለው ሁሉ በእኛ ፍላጎት ነው።የምትኖሩትን ህይወት የማትወዱት ከሆነ ምርጫችሁን ማስተካከል አለባችሁ።የትላንት ምርጫችን የዛሬውን እኛን ፈጥሮናል..የዛሬ ምርጫችን ለነገ ማንነታችን ወሳኝነት አለውና ከወዲሁ ምርጫችሁን ማስተካከል አለባችሁ።
ብዙ ሰዎች በተሳሳተ ምርጫ የተሳሳተ ህይወትን የሚገፉ ናቸው።ጥቂቶች ብቻ ናቸው ልክ በሆነ አስተሳሰብ ልክ የሆነ ህይወትን እየኖሩ ያሉት።ሁሉ ነገራችን ያለው በምናስበው ነገር ውስጥ ነው።የምናስበው ነገር ደግሞ የእኛ እንዲሆን የምንመኘው ነገር ነው ።እርሱም ምርጫ ይባላል..እርሱም ውሎ አድሮ የእኛ ማንነት ሆኖ አንድ ቀን ወደ ህይወታችን ይመጣል።እየሄዳችሁበት ያለው ጎዳና ልክ ነው? አሁን ላይ እያሰባችሁት ያለው ሀሳብ የሚያዋጣችሁ ነው? ራሳችሁን መርምሩ..አስተሳሰባችሁን ፈትሹ።እያሰባችሁ ኑሩ..ህይወት ማሰብ ናት..ማቀድና ማለም ናት።ህይወት ራስን መምራት መቆጣጠርም ናት።ህይወት በማሰብ ውስጥ ያለች ድርጊት ናት።ሳታስቡ የምትኖሩት ቅንጣት ህይወት አይኑራችሁ።ብዙዎቻችን ተስፋ ቆርጠን በከንቱነት የምንኖር ነን።ምርጫችንን ስለማናውቀው ወዴት እንደምንሄድ እንኳን ሳናውቅ መንገድ ጠፍቶብን ግራ ተጋብተን የምንኖር ብዙዎች ነን።ተመርቀን ስራ ለመያዝ መንግስትን የምንጠብቅ፣ ለምንም ነገር መንግስት ላይ ጣታችንን የምንቀስር፣ የቤታችንን ችግር ሁሉ ሳይቀር መንግስት እንዲፈታልን የምንፈልግ ብዙዎች ነን።
መንግስት ማለት እኔና እናንተ ነን…ያለእኔና እናንተ ህብረት መንግስት ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ የለውም።መንግስት ማለት የእኔና የእናንተ አስተሳሰብ፣ የእኔና የእናንተ ውህደት ነው።የሰፈራችሁን ቆሻሻ መንግስት መጥቶ እንዲያነሳላችሁ አትጠብቁ፣ የከተማችሁን ጽዳት ማዘጋጃ ቤት ሰራተኛ ቀጥሮ እንዲያጸዳላችሁ አትጠብቁ።የመንደራችሁን ጸጥታ ፖሊስና የጸጥታ ሀይል ቆሞ እንዲከላከል አታስቡ..ለሀገራችን እኛም ያገባናል።ለሰፈራችን፣ ለከተማችን ባጠቃላይ ለሀገራችን መንግስት ሆነን እያንዳንዳችን ሀላፊነታችንን መወጣት አለብን።አንዳንድ ሰዎች ይገርሙኛል ለምንም ነገር መንግስትን የሚጠብቁ ናቸው።ተምረው መንግስት ስራ እንዲያስቀጥረን የምንጠብቅ ብዙዎች ነን..ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት አለብን።በላቀ ሀሳብ ወደፊት መራመድ ይኖርብናል።ከቻላችሁ በበለጸገ አስተሳሰብ ለመንግስት ጉልበት በመሆን የሀገራቸውን ትንሳኤ ከሚያስቀጥሉት ውስጥ ስማችሁን ጻፉ።ካልቻላችሁ ደግሞ ከወቀሳና ከትችት ወጥታችሁ ሀገራችሁን ሳትጎዱ በታማኝነት ኑሩ።የእናንተ በጎ አመለካከት ከእናንተ አልፎ ለሌሎች የሚበጅ ታላቅ ሀይል ነው።
ህይወትን አሸንፈው በደስታ የሚኖሩ ሰዎች እኛ ለመሆን የመረጥንውን ነን ይላሉ።ማንም የመረጠውን ይሆናል።ማንም ለመኖር የመረጠውን ህይወት መኖር ይቻለዋል።ማንም እንዲኖረው የሚፈልገውን የራሱ የማድረግ አቅም አለው።ለመሆን የምንፈልገው ሁሉ እጃችን ውስጥ ነው።ወድቀን ከሆነ ማንም አልጣለንም፣ አልተሳካልን ከሆነ ማንም መንገዱን አልዘጋብንም፣ ድሀ ሆነን ከሆነ ማንም ብልጽግናን አልከለከለንም ሁሉም በእኛ አስተሳሰብና ምርጫ በኩል የሆነ ነው።እኔም እኮ የምነግራችሁ ከዚህ እንድትወጡ ነው ።የማወራችሁ አስተሳሰባችሁን እንድታርቁ ነው ።በሚገርም ሁኔታ ያሰባችሁት ሁሉ ገና ከአእምሯችሁ ሳይወጣ ነው ሁለንተናዊው አለም ይሄ ሰው ይሄን ነገር ይፈልጋልና ይሰጠው ሲል ትዕዛዝ የሚያስተላልፈው።መቼም ይሁን ጥሩ ነገር አስቡ።ለሀገር ለወገን የሚጠቅም አዎንታዊ ሀሳብን የራሳችሁ አድርጉ።ሀሳብ የጥቅሙን ያህል ጉዳት አለው።
በመልካም ሀሳባቸው የተጠቀሙ እንዳሉ ሁሉ ብዙዎችም በእኩይ ሀሳባቸው ጠፍተዋል።ሀሳባችሁን ምረጡ…ሀሳባችሁ እኔ የማልረባ ሰው ነኝ የሚል ከሆነ ውሎ ሳያድር የማትረቡ ሰው ሆናችሁ ራሳችሁን ታገኙታላችሁ።ሀሳባችሁ እኔ ምንም የማልጠቅም ሰው ነኝ ከሆነም በማግስቱ ጥቅም አልባ ሆናችሁ ትገኛላችሁ።ሁሌም ብሩህ ነገን ተመልከቱ አስተሳሰባችሁ ነጋችሁን እንዳይገልባችሁ ተጠንቀቁ።ምርጫችሁ ለሌሎች የሚጠቅም ገናና ይሁን።በሀሳባችን የቃረምንውን ጋፍ እንቶፈንቶ መሸከም አቅቶን የምንንገዳገድ ብዙዎች ነን።የኑሮ ሸክም በግለሰቦች የሚፈጠር የምርጫ ችግር ነው።ዛሬ ላይ በራሳችን ላይ የፈጠርነው ማንኛውም ህመምና ስቃይ ሁሉ በምርጫችን በኩል የእኛ የሆነ ነው።መቆም አቅቶን የምንንገዳገደው፣ ህይወት ትርጉም የለሽ ሆና የምትታየን ፍላጎታችን ባመጣብን ጣጣ ነው።አለምም ፍጥረቷም በእናንተ የምርጫ ግዛት ስር ነው።ሌላ የምትፈጥሩት አዲስ ሰማይና ምድር የለም ሁሉም ነገር ያለው እናንተ ጋር ነው ።
የህይወታችሁ ፈጣሪ እናንተ ናችሁ..የሀገራችሁ መጻኢ እድል በእናንተ አሁናዊ አስተሳሰብ የተቃኘ ነው።ለምኞታችሁ እጅ አትስጡ..ከአለም በልጣችሁ እንጂ አንሳችሁ እንዳትገኙ።በእናንተ እና በሌሎች መካከል የተፈጠረው የህይወት ልዩነት በአስተሳሰብ የተፈጠረ እንጂ አንዱ ብርቱ አንዱ ደካማ ሆኖ እንዳይመስላችሁ።የተፈጠርነው ሁሉን አግኝተን በደስታ እንድንኖር ነው።ወደዚህ አለም የመጣነው ሁሉን እንድንችል ሁሉን እንድናገኝ በታላቅ ተፈጥሮ ነው።አስተሳሰባችን ግን እዛና እዚህ አድርጎናል።ተለያይተን የምንኖረው በአስተሳሰባችን ነው።ጥሩ የሚያስቡ፣ ጥሩ የሚመርጡ ሁሌም ከላይ ናቸው።
የምትፈልጉትን ለማግኘት፣ የህልማችሁን ፍሬ እንድትበሉ በአስተሳሰባችሁ መላቅ አለባችሁ።ተቀምጣችሁ የምታዩ፣ ተኝታችሁ የምትመኙ፣ ሳትሰሩ ታላቅ ነገርን የምትናፍቁ ከሆናችሁ እናንተ ከንቱ ናችሁ..አሁኑኑ ከእንቅልፋችሁ ንቁ..ከጨለምተኝነት ውጡ።የተፈጠራችሁበትን ምክንያት እወቁ..ድከሙ ልፉ።አላማችሁ የቱ ጋ እንዳለ ፈልጉ።ዝም ብላችሁ አትኑሩ..ምርጫችሁን ለሌሎች አሳልፋችሁ አትስጡ።ወደ ፊት ተመልከቱ…ብዙዎች ከስኬታቸው ጫፍ ሲደርሱ ታክተው የሚመለሱ ናቸው።ብዙዎች ከሀሳባቸው ጥግ ሲደርሱ ወደ ኋላ የሚያማትሩ ናቸው።ከሄዳችሁ ወደ ፊት ሂዱ..ምንም ቢሆን ወደ ኋላ አትመለሱ።ከኋላ ምንም የለም ።ታላቅነታችሁ ያለው ከፊት ነው ።በመሄድ ውስጥ ራሳችሁን አግኙት..ከህልማችሁ ሳትደርሱ መቼም ቢሆን እንዳትቀመጡ።ሞክራችሁ አልሆን ሲላችሁ፣ ፈልጋችሁ ስታጡ፣ ሮጣችሁ ሲደክማችሁ ተስፋ አትቁረጡ…ከስኬታቸው ሊደርሱ ትንሽ ሲቀራቸው በልፋታቸው ማብቂያ ሠአት ሁሉንም ትተው በሽንፈት ወደነበሩበት የተመለሱ ብዙዎችን አውቃለው።እናተ ግን ትንሳኤያችሁን እስክታዩ ድረስ ከማሰብ፣ ከመምረጥ፣ ከመጣር እንዳትቦዝኑ አደራ እላችኋለው።ዛሬ ነገ ሳትሉ አሁኑኑ ከነበራችሁበት አፍራሽ አመለካከት ውጡና ወደሚደነቅ ታላቅ እውነት ተጓዙ ስል በማሳሰብ ጽሁፌን ላብቃ።ቸር ሰንብቱ፡፡
ብዙ ነገር እየፈለጋችሁ እንደሆነ አውቃለው…ትላንትም ዛሬም ፍለጋ ላይ እንደሆናችሁ ይሄንንም አውቃለው።ግን የምትፈልጉትን አግኝታችሁ አታውቁም..ሁሌም ፍለጋ ላይ ናችሁ.።ፍለጋ ከመውጣታችሁ በፊት የምትፈልጉት ነገር የት እንዳለ እወቁ፣ ያ የምትፈልጉት ነገር የት ቦታ እንደሚገኝ ካላወቃችሁ ትርፉ ድካም ነው
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም