በእምነት
“አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ” ይላል የአገሬ ሰው።አዎ! ሰው አውቆ ከተኛም ብቻ ሳይሆን ልቦናው እውነቱን እየተገነዘበ በራሱ ላለመቀበል ጥረት ካደረገ ማንም ምንም ቢለው መስማት አይፈልግም።ግን አንዳንድ ጊዜ አይንን ገለጥ አድርጎ በማየት ክፉን ከደጉ፤ ጠቃሚውን ከጎጂው በመለየት ድጋፍና ተቃውሞን ማሰማት ይገባል። ግን እንዲሁ ሁሉን ጥላሸት መቀባት ማሽሟጠጥና ማንጓጠጥ እንደ ሰውም እንደ አገርም ይዞ ሟች መሆን ነው።
አገር የሁላችንም ናት፤ መልማቷ ማማሯ ለኑሮ ምቹ መሆኗ የሚጠቅመው ሁላችንንም ነው።በዚሁ ልክ ደግሞ መጎሳቆሏ ከአገር በታች ሆና ለዜጋዋም መሰደድ ምክንያት መሆኗ ደግሞ አንገታችንን የሚያስደፋው እንደ አገርና ህዝብ አንድ ላይ ነው። ታዲያ እንኳን የሞከርነውን የጀመርነውን ውጤት ልናይበት ዳር የደረስነውን ሥራ ቀርቶ ያላሰብነውንም ነገር ጥሩ ከሆነ ብናሞግስ ድጋፋችንን ብንሰጠው ክፋቱ ምንድ ነው? እንደ እኔ ግን የተጠናወተን በሽታ የበታችነትን የሚያሰማ ክፋትና ተንኮልን ብቻ የሚያመላክት በመሆኑ አውቆ የተኛ የሆንን ይመስለኛል። ግን ደግሞ ለራሳችን ለአገራችን ለምን ክፉ እንሆናለን?
እንግዲህ ጽሁፌን በወቀሳ የጀመርኩት ሰሞኑን እየታዘብኩ ያለሁት ነገር እንደ ዜጋ ስላስቆጨኝ፤ ብሎም ለራሳችን ምቀኛ የምንሆነው በምን ምክንያት ነው ? የሚል ስሜትን ስለፈጠረብኝ ነው ።ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ መዋላቸው ይታወሳል።በዚህን ወቅት ካነሷቸውና እኔን በግሌ እንደ ኢትዮጵያዊ ልቤን ሞቅ ካደረጉ ሀሳቦች ብሎም የነገ የልጆቼ ተስፋ ሲለመልም ካሳየኝ ሥራ መካከል በቴክኖሎጂ የታገዘ ሰው ሰራሽ (አርተፊሻል ) ዝናብን ማዝነብ መጀመራችን ነው።
ይህ እንደ ኢትዮጵያ ላለች ድሃ አገር የመኖር ዋስትናውን በዝናብ ላይ ብቻ ላንጠለጠ ህዝብ ትልቅ የምስራች አይደለምን? ለእኔ ከየምስራችም በላይ ነው።እንደውም ሥራው ውጤታማ ሆኖ የሚታይበትን ቀን ያስናፈቀኝ ጀምሯል። ነገር ግን በማህበራዊ ሚዲያም በሌላም ላይ የምሰማውና የምመለከተው ሽሙጥና ከይሆናል ወደ አይሞከረም የሚመስሉ ሀሳቦች አሳፍረውኛል።ሰው እንዴት ለራሱና ለአገሩ ይህንን ያህል ምቀኛ ይሆናል? እንድልም ያስገደደኝ ሆኗል።
ጎረቤታችን ኬንያ “አርቴፊሻል ዝናብ” መጠቀም ከጀመረች ዋል አደር; ኸረ እንደውም ዓመታትን አስቆጥራለች። ኢትዮጵያ ገና ሙከራ ላይ መሆኗ ግርምትና ትንግርት ማስከተሉ በጣም ያስገርማል ። በቅንነት ካሰብነው ነገሩ ቀላል ከመሆኑም በላይ እጅግ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን በዚህ ምቀኝነታችን እኛ ካልቻልን ያው ሁሉን አሳልፈን መስጠት እንደለመድነው አንድ የእስራኤል ወይንም የቻይና ካምፓኒ በተመጣጣኝ ወጪ ሥራውን ሊሰራው ይችላል። ምንም ትንግርት የለውም።
ኢትዮጵያ ዘመናዊ ድሮኖች ከገዛች ዓመታትን አስቆጥራለች። ድሮኖች ጥቅም ላይ የሚውሉት ቦንብ ለመጣል ብቻ አለመሆኑ ደግሞ መታወቅ አለበት ። በዚህ መልኩ ኬሚካል ረጭተው ዝናብም ያመጣሉ። በቅርቡ በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ እንኳን ድሮኖቹ ቦንቡ ሲያዘንቡ አጨብጭበን ነበር፤ ታዲያ ዝናብ ሊያዘንቡ ነው መባሉ ምኑ ነው ግራ ያጋባን ።
ቴክኖሎጂው ከዚህ ቀደም በእኛ አገር ያልተሞከረ ነው ።ነገር ግን እነ እስራኤልና ሌሎች አገራት አረብ ኤሚሬትን ጨምሮ በአግባቡ እንደሚጠቀሙበት የሃብታቸው ምንጭ አድርገውት ከእነሱ አልፎ እኛን የሚረዱበት መሆኑን መቼም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ያውቃል ብዬ አስባለሁ ።ታዲያ እኛም ወግ ደርሶን ራዕይ ያላቸው አመራሮች ገጥመውን የረጂ አገራትን ቴክኖሎጂ ባለን አቅም አመጥተን ተግባራዊ እናድረግ እነሱ የደረሱበት እንድረስ ማለት ምኑ ነው ክፋቱ? እንደው ሁሉን የማንጓጠጥ ባህርያችን ካልሆነ በቀር።
እንግዲህ እኛም ወግ ደርሶን እንደ ሌሎቹ አገሮች ደመናን አከማችተንና ወደ ሰማይ ልከን ዝናብ አዝንበን ዓመቱን ሙሉ ዘርተን ልንቅም ዳር የደረስን ይመስለኛል። አምላክ የምቀኛን ጆሮ ይድፈንልን አይናቸውን ገልጠው ማየት የተሳነቸውን ሰዎች አይናቸውን ብቻ ሳይሆን ልቦናቸውንም ያብራልን እንጂ።
ምናልባት እነዚህ ሰዎች ቴክኖሎጂው አያስፈልገንም ባይ አይመስሉኝም፤ ግን ደግሞ እንደ መከራከሪያ የሚያነሱት አገሪቱ ሳትረጋጋ እዚህም እዚያም ያለው የጸጥታ መደፍረስ መልክ ሳይዝ ስለ አርቴፊሻል ዝናብ ማሰብ ቅንጦት ሆኖባቸው ይመስለኛል።ግን ደግሞ ይህ ቅንጦት አይደለም፤ ምናልባትም አገርን ከማረጋጋቱ ሥራ ጎን ለጎን የሚሰራ እንጂ ።
እንደ እኔ ለዚህ ሁሉ መባላታችን አንዱና ዋናው ምክንያት የሚመስለኝ ድህነታችን ነው፤ ይህንን ተጠቅመው ደግሞ የራሳቸውን ኪስ መሙላት የሚፈልጉ ኃይሎች ትርፍራፊያቸውን እየወረወሩልን እንዳንረጋጋ ሥራችንን እንዳንሰራ እግር ከወርች አስረው ያባሉናል ።ሁሉም ነገር የእነሱ ውጤት ነው ታዲያ የአገሬ ሰው አይንህን ገለጥ አድግረህ ክፉን ከደጉ አትለይም፤ ጥቅምና ጉዳትህን አታውቅምን ?
በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዳሉት መንግሥትን መጥላት አለመፈለግ ይቻላል፤ ግን በተመሳሳይ መልኩ አገርን መጥላት መካድ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው ፤ ይህ ቴክኖሎጂም ሆነ ሌላው ሥራ ለአገር የሚጠቅም አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ የሚያደርግ ከመሆኑ አንጻር፤ ጥላቻችንን በጭፍን ተቃውሞ የተሰራን እንዳልተሰራ ማድረግ ‹‹ምን ይጠቅመናል?›› ብሎ በመናቅ መግለጽ ኢትዮጵያዊነትም አይደለም፤ ወደፊት ሊያራምደን አይችልም።
ኸረ ጎበዝ ድህነት በቃን ! ማለት መቻል እኮ አለብን።የሰው ልጆች መገኛ፣ቀደምት የታሪክ ባለቤት፣ የውብ የተፈጥሮ ባለጸጋ ፣ የስልጣኔ ምንጭ ነበርን ብሎ ማውራት ብቻውን ዳቦ አልሆነልንም። አዎ ቀደምት ነበርን ነገር ግን ለዛ ቀደምትነታችን ያበቃን መንገድ ምንድነው? ብለንስ አይናችንን ከፍተን አይተናል? ታሪክ አገላብጠናል? አይመስለኝም ።እኛ ዛሬ ቀደምት ነበርን ብለን እንድናወራ ያስቻለንን ታሪክ የሰሩት አባት እናቶቻችን እኮ ተስማምተው፣አንድ ሆነው፣ተደጋግፈው፣በጨዋነት ስለኖሩ ነው።
እኛስ? “ኤጭ፣አይሆንም ፣አንችልም፣አይሞከርም ” የሚለውን ነው ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን ማውረስ የምንፈልገው? ወይስ አሁን በጀመርነው መንገድ ታሪካችንን የተፈጥሮ ሀብታችንን ከቴክኖሎጂ ጋር እያስተሳሰርን ተጠቅመን አዲሲቷን ኢትዮጵያ መስራት፤ እንግዲህ የሚሻለንን የምናውቀው እኛ ነን፤ እኔ ግን አሁንም አይናችንን እንክፈት፣ከጭፍን ጥላቻና ነቀፌታ አይሆንም አያስፈልገንም ከሚል አስተሳሰብ ለመውጣት እንሞክር ወደ ከፍታ ለመውጣትም መንገዳችንን እንጀምር ባይ ነኝ።
ይህ ቴክኖሎጂ በተለይም ለእንደኛ በተፈጥሮ ሀብት ለታደለች አገር ብዙ ሳያደክም ግን ደግሞ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል እንደሚሆን በግሌ ባልጠራጠርም መንግሥት ሥራውን መጀመሩ ሙከራም ማድረጉን እያበረታታሁ ለወዳጅም ለጠላትም ለቀናም ለጠማማም ሲባል ግን ሥራው ከግቡ ይደረስ ዘንድ ትኩረት ያግኝ የሚለው ደግሞ ምኞቴም ማሳሰቢያዬም ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም