የኤርትራ ህዝብ ለበርካታ ዘመናት ለነፃነት ባደረገው ትግል ነፃነቱን ተቀዳጅቶ እንደ አገር ራሱን በራሱ ማስተዳደር ከጀመረ እነሆ ሶስት አስርት አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከነዚህ ጊዜያት ውስጥ ግን ሁለት ሶስተኛው ጊዜ ያለፈው የሁለቱ አገራት ህዝቦች እንዳይገናኙ ተደርጎና የቅርብ ሩቅ እንዲሆኑ መንገዶች ተዘግቶ ነው፡፡
ከደርግ ውድቀት ማግስት በሁለቱ አገራት የተሻለ ልማትና ዴሞክራሲ ይመጣል የሚል ትልቅ ተስፋ ነበር፡፡ በተለይ ሁለቱ አገራት በባህል፣ በቋንቋ፣ በስነልቦና እና ህዝብ ለህዝብ በነበራቸው ጥብቅ ቁርኝት የተነሳ ከሌሎች የጎረቤት አገራት በተሻለ ሁኔታ ቀጣዩ አብሮነታቸው ከፍ ያለ ተስፋ ጭሮ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የታሰበው ሳይሆን ቀርቶ የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጭምር የለያየ ክስተት እንዲፈጠር ተደረገ፡፡ በዚህም እናትና ልጅ፤ አባትና ልጅ፣ እህትና ወንድም፣ ወዘተ ሁሉ እስከመለያየት የደረሱበትና ከዚያም በላይ ትርጉም በሌለው ጦርነት አንዱ ሌላው ላይ እንዲተኩስ የተደረገበት ሁኔታ መፈጠሩ ከአብዛኛው የሁለቱ አገራት ህዝቦች እዝነ ህሊና የማይወጣ መጥፎ ጠባሳ ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ እነዚህ ከማንም በላይ ቅርበት የነበራቸው የሁለቱ አገራት ህዝቦች እንዳይገናኙ የተደረገበት መንገድ በፖሊሲዎች ጭምር እንዲደገፍ የተደረገበት ነባራዊ ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡ በህወሓት ጁንታ ይመራ የነበረው የቀደመው ስርዓት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ላይ ጭምር የሁለቱ አገራት ህዝቦችን በጠላትነት እንዲተያዩ በስም ለይቶ ያስቀመጠበት እና ግንኙነቱን በፖሊሲ ለመዝጋት የሄደበት መንገድ ምን ያህል የነዚህን ሁለት ወዳጅ አገራት ህዝቦች ስነልቦና የጎዳ እንደነበር በቅርቡ ከለውጡ ወዲህ ከፈጠረው አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ወዲህ ተመልክተናል፡፡
በዚህ መሰረት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደስልጣን በመጡ እለት በውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ዘርፈብዙ ችግር ከመፍታት በዘለለ ከጎረቤት አገራት ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባ በአፅንኦት ገልፀዋል፡ ፡ በተለይ ለ20 አመታት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የቆየው ሞትአልባ ጦርነት እንዲያበቃ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ በገቡት ቃል መሰረት እቅዳቸው እውን ሊሆን ችሏል፡፡
የሁለቱ አገራት ህዝቦች ከማንም በላይ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውና በመካከላቸው የተቀመጠው አጥር ይህንን ግንኙነት የማይፈልጉ ሃይሎች ሴራ እንደነበርም በቅርቡ ግንኙነቱ በታደሰበት ወቅት የታየ ጉዳይ ነው፡፡ የኤርትራ ህዝብ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለመጀመሪያ ጊዜ አስመራ ሲገቡ የነበረው የህዝብ ስሜትና አቀባበል ለዚህ ማስረጃ ነው፡፡ በወቅቱ የኤርትራ እናቶች እና አባቶች እንዲሁም ወጣቶች ደስታና ፈንጠዚያ ህዝቡ ምን ያህል ለጋራ እድገትና አብሮነት ትልቅ ፍላጎት እንደነበረው ያሳየ ነበር ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ ሲመጡና ከዚያ በኋላም በሀዋሳና በባህር ዳር የነበረው የህዝብ አቀባበልና ደስታ ህዝቡ ምን ያህል እርስ በርሱ በተዳፈነ ፍቅር ውስጥ እንደቆየ በተጨባጭ ያመለከተ ነው፡፡
ከዚያ በኋላም ቢሆን የህዝቡን ስሜት በተመለከተ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርበው የተናገሩ የሁለቱ አገራት ዜጎች ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት ምን ያህል የሁለቱን አገራት ዜጎች ስነልቦና የጎዳ እንደነበር ማየት ያስችላል፡ ፡ በዚህ የተነሳም ግንኙነቱን ተከትሎ የተራራቁት የሁለቱ አገራት ህዝቦች ለመጠያየቅና አንዱ ወደሌላው እየሄደ ናፍቆቱን ለመወጣት ያደረጉት እንቅስቃሴ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ግንኙነቱን ተከትሎ በርካታ ኤርትራዊያን ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል፤ በዚያው ልክ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ኤርትራ ተጉዘዋል፤ ለዘመናት ተነፋፍቀው የነበሩ ቤተዘመዳማቾችም ናፍቆታቸውን ተወጥተዋል፡፡
እንግዲህ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ግንኙነት ለ20 አመታት በመቋረጡ የጥቂት ሴረኞች የተንኮል ስራ ቢሆንም የሁለቱ አገራት ሀዝቦች ከጊዜ በኋላ መገናኘታቸውና አንድነታቸውን ማስቀጠላቸው አልቀረም፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች እና መንግስታት እንደቅርብ ጉርብትና ብቻ ሳይሆን ለዘመናት አብሮ እንደኖረ፣ እንደተዋለደና የአንድነት ስነልቦናው እንደተቆራኘ ህዝብ መደጋገፋቸውንና አንድነታቸውን ማጠናከራቸውን ይበልጥ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
በቅርቡም ለ20 አመታት የሁለቱን አገራት ህዝቦች ግንኙነት አቋርጦና ህዝብን ከህዝብ አራርቆ የቆየው የህወሓት ጁንታ ዳግም ኢትዮጵያን ለመበተን አቅዶ ሲንቀሳቀስ የኤርትራ ህዝብ እና መንግስት ከዚህ በኋላ ሁለቱን አገራት ህዝብ መነጣጠል እንደማይቻል በተግባር አሳይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በከፍተኛ ፈተና ውስጥ በገባችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የኤርትራ ህዝብና መንግስት ያለምንም ማወላወል ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ኢትዮጵያን ከብተና ታድጓል፡፡ ይህ ደግሞ ከአንድ በመተማመን ላይ ከተመሰረተና አንድ የጋራ ስነልቦና ካለው የጎረቤት አገር የሚጠበቅ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ አመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት የኤርትራ ህዝብና መንግስት የዋለልን ውለታ መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት ግንኙነቶች አገርን ከመፍረስ እና ከብተና ከማዳናቸውም በላይ በጋራ ለማደግ ወሳኝ ናቸውና ለወደፊቱም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም