ማህሌት አብዱል
የተወለዱት ቀድሞው አጠራር ወለጋ ጠቅላይ ግዛት ጊምቢ አውራጃ አይራ ጉሊሶ ወረዳ ነው። እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ አባታቸው አቅራቢያቸው ወደነበረው ሚሲዮን ትምህርት ቤት አስገቧቸው። በስድስት ዓመታት ውስጥ ስምንተኛ ክፍል አጠናቀቁ። በአካባቢያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ነቀምቴ ወደሚገኘው የመንግሥት ትምህርት መሄድ ግድ ይላቸዋል። ነገር ግን በወቅቱ እድሜያቸው ገና ለጋ በመሆኑ ምክንያት ከቤተሠብ ርቀው መማር እንደማይችሉ ተገነዘቡ። በመሆኑም ቤተሰቦቻቸው ቢሾፍቱ በሚገኘውና በመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ስር ይተዳደር በነበረው ኢቫንጄሊካል ኮሌጅ በተባለ ተቋም ያስገቧቸዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት ካጠናቀቁ በኋላ ሐረር በሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጦር አካዳሚ ሰልጥነው ተመርቀዋል። በመቀጠልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአሜሪካም በፒስ ኤንድ ኮንፍሊክት ስተዲስ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል።
በሙያቸው ከአፄ ኃይለሥላሴ ጀምሮ ለነበሩት መንግሥታት ሲያገለግሉ የቆዩት እኚሁ ሰው በተለይም በተለያያ አጋጣሚ በቤተመንግሥት የመስራትና ከመሪዎቹ ጋር በቅርበት የመነጋገር እድሉን አግኝተው ነበር። ለማያምኑበት ነገር ያለአንዳች ፍራቻ ‹‹ለምን?›› ብለው የሚጠይቁ መሆናቸው ብዙ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲያጎለብቱት በመጡት ሞጋች ማንነታቸው ምክንያት በሦስቱም መንግሥታት ወህኒ ቤት ተልከዋል። እንግልትም ደርሶባቸዋል። የሞት ፍርድም ተወስኖባቸው ያውቃል። ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላም ለታገሉለት ዲሞክራሲና የሰው ልጆች መብት መከበር እገዛ ያደርጋል ያሉትን አሞዲያስ የተባለውን ድርጅት ከፍተዋል።
ባለፉት አምስት ምርጫዎች ላይም በታዛቢነትና የምርጫ ትምህርት በመስጠት የተሳተፈው ይኸው ድርጅታቸው በተለይም አሁን ላይ ብርቱ ፖለቲከኞችን ያፈራና የቀረፀ መሆኑ ይጠቀሳል። በአገሪቱ ሁሉም ጫፎች በመዘዋወር በዲሞክራሲ፣ በሙስና ፣ በሰብዓዊ መብትና በህገመንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት ማህበረሰቡን በማስተማር አወንታዊ ሚና ተጫውቷል። በዘንድሮ ምርጫም በታዛቢነት ለመሳተፍ ጥያቄ አቅርበው ከምርጫ ቦርድ ይሁንታን አግኝተዋል። የዛሬው የዘመን እንግዳችን አቶ ከበደ ቀጄላ ናቸው። አዲስ ዘመን በህይወት ገጠመኛቸውና በመጪው ምርጫ ዙሪያ ውይይት አድርጓል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡– የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ከትምህርት ቤት ተባረው ነበር፤ ምክንያቱ ምን እንደነበር ያስታውሱንና ውይይታችን እንጀምር?
አቶ ከበደ፡– ልክ ነሽ፤ ያ ክስተት አሁን ላሉሁበት ደረጃና ድርጅቴን ለመከፈት እርሾ ነበር ለማለት እችላለሁ። ምን መሰለሽ በወቅቱ እማርበት የነበረው ኢቫንጄሊካል ኮሌጅ ለራሱ ዓላማ ሲል ከተማሪ ተወካይ ጀምሮ በሁሉም ቦታ ላይ ሰዎችን መርጦ የሚሾምበት አሰራር አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም። እንዳልሽው የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ የራሳችንን መሪዎች ራሳችንን መምረጥ አለብን የሚል ጥያቄ አነሳሁኝ። ይህም በብዙዎቹ ተማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት አገኘ። ይህንን ተከትሎም ተቃውሞውን በግንባር ቀደም መርተሃል በሚል ከትምህርት ቤቱ የመባረር እጣ አጋጠመኝ። ከዚያ ወጥቼ ለአንድ ሴሚስተር ከግማሽ ነቀምቴ ቀሃስ በተባለ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማርኩኝ።
አዲስ ዘመን፡– ታዲያ እንዴት ተመልሰው ወደዚያ ትምህርት ቤት ሊገቡ ቻሉ?
አቶ ከበደ፡– እንደአጋጣሚ ነቀምቴ በተማርኩበት ትምህርት ቤት ያገኘኋቸው የክፍል ጓደኛቸው የራስ መስፍን ስለሺ ሚስት ወንድም ልጅ ነበር። ከዚሁ ጓደኛዬ ጋር ሆኜ ለእረፍት ወደ አዲስ አበባ ራስ መስፍን ቤት አረፍን። የራስ መስፍን ባለቤት የእኔን ቅልጥፍናና ተግባቢነት አይተው አቀረቡኝ። በእሳቸው ምክንያትም ከልጆቸቸው ጋር የመተዋወቅ እድሉ አጋጠመኝ። ከዚያም ዮሃንስ ከተባለው የራስ መስፍን ልጅና ጓደኛቸው ጋር በመሆን ለአንድ ሳምንት ቢሾፍቱ እንድንዝናና ተፈቀደልን። እዛም በሄድንበት ወቅት ከልዑል ወሰንሠገድ መኮንን ጋር ተዋወቅሁኝ። እናም ይህችን አጋጣሚ በመጠቀም ከእነዚሁ የንጉሣውያን ቤተሰቦች ጋር በመሆን ያባረረኝን ትምህርት ቤት እንድንጎበኝ ጠየኩዋቸውና አብረን ሄድን። በወቅቱ የነበረው የትምህርት ቤቱ አሜሪካዊው ኃላፊ የንጉሣውያኑን ቤተሰብ ሲመለከት በጣም ተደናገጠ፤ ጠብ እርግፍ ብሎ አስተናገደን። ተሰናብተነው ልንወጣ ስንል አስተዳዳሪው ለብቻዬ ጠርቶ ወደ ትምህርት ቤቱ መመለስ ከፈለኩኝ በሩ ክፍት እንደሆነ ነገረኝ። እኔም በሃሳቡ ተስማምቼ ወደ ተቋሙ በመመለስ 12ኛ ክፍል አጠናቀቅሁኝ።
አዲስ ዘመን፡– የጦር አካዳሚውን የተቀላቀሉበት አጋጣሚ ምን ነበር?
አቶ ከበደ፡– እንዳልኩሽ እዛ ትምህርት ቤት ከተመለስኩ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በጥሩ ውጤት በማለፍ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመድቤ ነበር። ነገር ግን አስቀድሜ ለመኮንንነት አመልክቼ ስለነበር ስሜ ተሰርዞ ሐረር በሚገኘው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጦር አካዳሚ እንድመደብ ተደረገ። በመሠረቱ በንጉሡ ዘመን መሬት ቆንጥጠው ከተሰሩት ስራዎች መካከል የጦር አካዳሚው መሆኑ እዛ መማሬ በጣም ተጠቃሚ ነኝ። ከተቋሙ እንደተመረቅሁም በምርጫዬ ክቡር ዘበኛ ተመደብኩኝ። ይህን ተከትሎም ቤተመንግሥቱን የሚጠብቀው ሦስተኛ ብርጌድ አካል ሆኜ እንድሰራ ተላኩኝ። ይህም ከጃንሆይ ጋር የመገናኘት እና በቅርበት የመተዋወቅ እድሉ እንዲኖረኝ ረዳኝ። ይህም ብቻ አይደለም፤ እዚያ አካባቢ የሚሰሩ ስራዎችን ለማስተዋልና ለመታዘብ አስቻለኝ።
በተለይም ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ጓደኞቼ አገዛዙን በመቃወም ያደርጉት በነበረው እንቅስቃሴ ትኩረቴን ይስበው ስለነበር በቤተመንግሥቱ ከማየው ነገር ጋር ተዳምሮ ተቃውሞውን ወደ መደገፍ ገባሁ። በክቡር ዘበኛ ውስጥ እያለን በድብቅ ሠራዊቱን የመለወጥ እንቅስቃሴ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እንሠራ ነበር። በዚህ ላይ እያለን በአጋጣሚ የምናደርገው እንቅስቃሴ በመንግሥት ተነቃብንና 15 የምንሆን ሰዎች ታሰርን። የወታደራዊ ፍርድቤት መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው በሚል ሁላችንም ላይ የሞት ፍርድ ተፈረደብን። ሌሎች ጓደኞቻችን ያልታሰሩ አሉ። ለአብነት ብጠቅስልሽ እነሻለቃ አጥናፉ አባተ ፤ ተፈራ ተክለአብ፤ ግርማ ፍስሃና የመሳሰሉት ሰዎች አልተነቃባቸውም ነበር። እኛም አላጋለጥናቸውም።
የሞት ፍርዱም ከወታደራዊ ፍርድ ቤቱ ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅ እንዳልካቸውም አምነውበት ለግርማዊነታቸው እንዲያጸድቁት ቀረበላቸው። ሞታችን ፈጦ መጣ ። በኋላም የተማሪዎች ኅብረት፤ የመምህራን ማህበር፤ የሠራተኛ ማህበር ቤተሰቦቻችን እኛን ከሞት ለማትረፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያደርጉ ነበር። የመጀመሪያው ጥያቄ የታሰሩ ይፈቱ የሚል ነበር። ሰኔ 21 ያንን ሞት ለማትረፍ ሲባል ደርግ ተቋቋመ። የመጀመሪያው የደርግ ጥያቄ አክቲቪስቶቹ እንዲፈቱ የሚል ነበር። እስከ 28 ድረስ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ በኋላ እንድንፈታ ተወሰነ። በነገራችን ላይ የጃንሆይ የግል ባህሪ አወዛጋቢ ነው። ማንም ያጠናውም አይመስለኝም። ያልተጠና ማንነት ነው ያላቸው። በቤተመንግሥት በነበረኝ ቆይታዬ ብዙ አወዛጋቢ ማንነት ያላቸው ሰው መሆናቸውን ነው ያስተዋልኩት።
አዲስ ዘመን፡– ከኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ጋርም ያልተግባባችሁበት አጋጣሚ እንደነበር ሰምቻለሁ። እስቲ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሱን?
አቶ ከበደ፡– እሱ ደግሞ የተፈጠረው ገና ደርግ በተመሠረተበት ወቅት ነበር። ሻለቃ አጥናፉ ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያምን፣ ዳዊት ገብሩን እና እኔን ይጠሩና ስለአገሪቱ ቀጣይ መንግስታዊ አሰራር ምን መሆን እንዳለበት ያማክሩናል።በተለይም እኔና ዳዊት ገብሩን በክብር ዘበኛው ያለንን ተቀባይነት በመጠቀም መስከረም 2 የወታደራዊ መንግስቱን ስልጣን መያዝ ከማወጃችን በፊት ሠራዊቱን እንድናሳምን ያነጋግሩናል። ያ ዳዊት የተባለው ጓደኛዬ ‹‹ለትክክለኛው የህዝብ ጥያቄ ትክክለኛው የህዝብ ምላሽ ወታደራዊ መንግስት ነው›› የሚል መልስ ሰጣቸው። እኔ ይህንን ስስማ በጣም ደነገጥኩኝ። ምክንያቱም እኔና ዳዊት የታሰርንበትም ሆነ የታገልንበትም አብይ ጉዳይ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት አንዲቋቋም ስለነበር ነው።በመሆኑም በጓደኛዬ ምላሽ በጣም አዘንኩኝ። በዚህ ድንጋጤ ውስጥ ሳለሁ ‹‹አንተስ ምን ታስባለህ?›› ሲሉኝ እኔ ወታራዊ መንግሥት በየትኛው አገር ያለደም ገዝቶ ስለማያውቅ ለዚህ ደሃ ህዝብ አልደግስለትም፤ ወታደራዊ መንግሥት አይዋጥልኝም የሚል ምላሽ ሰጠኋቸው። ከዚያ ይልቅም ህዝባዊ መንግሥት ነው መቋቋም ያለበት ብዬ ሞገትኳቸው። ያን ጊዜ ኮሎኔል መንግስቱ ቀበል አደረገና ‹‹ክቡር ጀነራል ይሄ መሃይም ወታደር አገር መምራት አይችልም ብሎ የሚያምን ስለሆነ እሱን ይተውት እኛ ወታደር እንዴት መግዛት አንደሚችል እናሳየዋለን›› ብሎ ተናገረ።
በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ደርግ ሲመሰረት የክቡር ዘበኛ ውስጥ የነበረው ንዑስ ኮሚቴ ጠራኝና በንጉሡ በታሰራችሁበት ጌዜ ተሳክቶላችሁ መንግሥት ገልብጣችሁ ቢሆን ምን እቅድ እንደነበራችሁ ግለፅልን አሉኝ። ጊዜ እንዲሰጡኝ ጠየኩኝና ከአንድ ሳምንት በኋላ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አስፈላጊነት ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጠኋቸው ፤ ውይይት ተደረገበት። ከየአካባቢ እና ከየማህበሩ ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች እንዲሁም ወታደሩን ጨምሮ ያለበት ህዝባዊ ምክር ቤት መቋቋም ቢችል የሚል ምክረሃሳብ ሰጠኋቸው። ለሁለት ዓመት ገደማ ህዘብን ካነቃን በኋላ ዲሞክራያዊ ምርጫ እናካሂዳለን የሚል ገለፃ አደረኩላቸው። የክቡር ዘበኛው ይህንን እቅድ ሲሰማ እሳት ሆኖ ቁጭ አለ፤ ከደርግ ሰዎች ጋር ትልቅ ፍትጊያ ተፈጠረ። ስለዚህ የዚህ ሃሳብ አመንጪ ቶሎ መጥፋት አለበት ብሎ በአስቸኳይ ወደጎዴ እንድዛወር አንድ አውሮፕላን ታዘዘልኝ። እኔ መቶ አለቃ ሆኜ ሳለሁ፣ አንድ ሙሉ ኮሎኔል፣ ከሙሉ አጀብ ጋር ታዘዘልኝ። ያመፀባቸውን የክቡር ዘበኛ ሠራዊት በአንድ ወር ውስጥ ከበተኑት በኋላ ከጎዴ በአውሮፕላን አዲስ አበባ አምጥተው እስር ቤት ከተቱኝ። በህግ የተቋቋመውን መንግሥት ለማፍረስ ሞክሯል በሚል ሰባት ዓመት በእስር ቤት ከረምኩኝ። በመሠረቱ ከሃሳብ የዘለለ ያደረጉት ነገር ባለመኖሩ ሊያስጠይቀኝ አይገባም ነበር። እናም ከሰባት ዓመት በኋላ በአመክሮ ተፈታሁኝ።
እንደተፈታሁም በኮሎኔል ፍስሃ ደስታ ትዕዛዝ መብራት ሃይል በሲቪልነት እንዳገለግል ተመደብኩኝ። መብራት ሃይል እንዳጋጣሚ ኮሎኔል ተሰማ የተባሉ ወታደር ነበሩ። ያም ሆኖ ጥቃት እየተሰማኝ ነበር። ያለአግባብ መታሰሬ መብቴ መረገጡ ውስጤ ያንገበግበው ነበር። በዚያ አጋጣሚ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ዲግሬዬን በታሪክ ተማርኩኝ። በነገራችን ላይ ከጓድ መንግስቱ ጋር እናሳይሃለን ብሎ ከዛተብኝ በኋላ ስመረቅ ሽልማት ሲሰጠኝ ነው የተገናኘነው።
አዲስ ዘመን፡– የኢህአዴግ መንግሥት ከመጣ በኋላም ወደ ቤተመንግሥት የተመለሱበት አጋጣሚ ምን ነበር?
አቶ ከበደ፡– ወታደራዊው መንግሥት ፈርሶ ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ከደርግ ጋር ንክኪ ያልነበራቸው ሰዎች ይፈለጉ ሲባል እኔም አንዱ ሆንኩኝ። ተጠራሁና ቤተመንግሥት ቀረብኩኝ። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታምራት ላይኔ፣ ዶክተር ካሱ ኢላላ ሆነው አናገሩኝ። ለሥራ እንፈልግሃለን እና ባለህ አቅም አግዘን አሉኝ። ግን የአንዱ ፓርቲ አባል መሆን አለብህ አሉኝ። እኔ በሙያዬ ማገልገል ነው የምፈልገው አራት ህጻናት ልጆች አሉኝ፤ ካልፈለጋችሁ ተውት አልኳቸው። እነሱም እሺ እንፈታተሻለን አሉኝ። እኔም አበጥራችሁ ፈትሹኝ አልኳቸው። ሁለት ወር ሙሉ ፈተሹኝ። የምንም ፓርቲ አባል እንዳልሆንኩኝ አጣሩ። በሦስተኛው ወር ላይ አንድ ሰርግ ላይ ሆኜ ሰርጉን እየታደምኩ ሳለሁ በአስቸኳይ ቤተመንግሥት ትፈለጋለህ ተብዬ ተጠራሁ። ቀድሞ ያጋሩኝ ሰዎች
ለሁለት ወር ፈትሸው ምንም እንዳላገኙብኝ፤ በዚሁ እንደምቀጥል ተስፋ እንደሚያደርጉና ቤተመንግሥት በአስተዳደርና ፋይናንስ አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ ሆነው ሥራ እንደምጀምር ተነገረኝ። ቤተመንግሥት አሥር ወር ያህል ሌት ተቀን ቤተሰቤን ጎድቼ ሰራሁ። በኋላ ላይ ግን ከታምራት ላይኔ ጋር መግባባት አልቻልንም።
አዲስ ዘመን፡– ምን ነበር ያላግባባችሁ?
አቶ ከበደ፡– አንድ ቀን ጠርቶኝ የተወሰኑ ሰዎችን ስም ዝርዝር ሰጠኝና ወደ ኡጋዴን አዛውራቸው ብሎ አዘዘኝ። እኔም ጥፋታቸውን ሳላውቅ ለምን አዛውራቸዋለሁ ብዬ ሞገትኩት። ሌላ ጊዜ እንዲሁ ሌሎች ሰዎችን ስም ዝርዝር ሰጥቶኝ ይታሰሩልኝ አለ። አሁንም ለምን? አልኩኝ። በዚህ ሁኔታ ከዚህ ሰውዬ ጋር ተግባብተን መስራት እንደማንችል ተረዳሁ።ምክንያቱም ሠራተኛ መብት የወጣበት አዋጅ ሳይሻር ለምን መብት ይጣሳል የሚል ጥያቄ ነበረኝ። በመሆኑም ከአቶ ታምራት ጋር ቁጭ አልኩና ለመናገር ሞከርኩኝ። ሰዎችን ያለአግባብ ማዛወር ቤተሠብ ማመሳቀል ነው። ማሰሩም ለተጀመረው የለውጥ ሂደት እንቅፋት ነው የሚሆነው ስል ምክሬን ሰጠሁት። እሱ ግን ሊሰማኝ ባለመቻሉ በአሥረኛው ወሬ የስንብት ደብዳቤ ደረሰኝ። በመሠረቱ እኔ በመሰናበቴ አላዘንኩም፣ እንዳውም ወዲያውኑ ቢሮዬ ተንበርክኬ ፈጣሬዬን ነው ያመሰገንኩት። ህዝቡ ለውጥ እየፈለገ ባለበት ወቅት የመጡበትን መሰረት በመተውና የህዝብን ጥያቄ እያዳፈኑ መሄድ አዋጭ አለመሆኑን ስላመንኩ ፈጣሪ እንዲገላግለኝ አስቀድሜ ስፀልይ ነበር።
ከቤተመንግሥት እንደወጣሁ ለአንድ ዓመት ያህል ከሙያዬ ውጭ ዳቦ ጋገራ ውስጥ ገባሁ። ከአንድ ዓመት በኋላ ግን የዳቦ ጋገራው ብዙ እንደማያስኬደኝ ተረዳሁና ለባለቤቴ አዛወርኩት። በአንድ ጓደኛዬ አማካኝነት አቦጊዳ የሚባል በዲሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ላይ በሚሰራ ድርጅት ውስጥ ተቀጠርኩኝ። ያኔ በቃ ለእኔ ትክክለኛውን ቦታ ያገኘሁ ያህል ነው ተሰማኝ። በዚያ ተቋም አንድ ዓመት ተኩል እንደሰራሁ የመጀመሪያው ምርጫ ላይ እንድሳተፍ ከነበሩት የበጎአድራጎት ድርጅት ውስጥ አንዱ ሆኜ ተመረጥኩኝ። በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ እድሉን በማግኘቴ አንዳንድ ሰዎች ለምን የራስህን ተቋም አትመሰርትም የሚል ግፊት ያደርጉብኝ ጀመር። በተለይም የሚያውቁኝ የውጭ ዜጎች ድጋፍ አደረጉልኝና አሞዲያስን መሰረትኩኝ።
በነገራችን ላይ አሁን ዋነኛ ማነቆ የሆነብን የገንዘብ ጉዳይ ያኔ ችግር አልነበረም። በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚለግሱ በርካታ ግለሰቦችም ሆነ ተቋማት ነበሩ። ለስራችን ትልቁ ክንዳችን የነበረው ወጣቱን ማሰልጠን ነበር። ወጣቶች ቶሎ ወደ ኅብረተሰቡ የመድረስ አቅም ስላላቸው በድራማ፣ በቲያትር መልክ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በሰፋት መስራት ቀጠልን። በዩኒቨርሲቲውና ቀበሌው ድረስ በመዝለቅ የነቃ ትውልድ የማፍራት ኃላፊነታችንን ለመወጣት ብዙ ሰራን። በተለይም ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ ከፍተኛ ትብብር ያደርግልን ነበር። በነገራችን ላይ ሙስና የሚለው ቃል የተዋወቀው በእኛ ተቋም ነው። የመጀመሪያዎቹ የኢህዴግ ሰዎች የገንዘብ ጥማት ያልነበረባቸው ቢሆንም በኋላ ላይ የመጡት አመራሮችና ባለሥልጣናት ግን የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ነበሩ። ከእነሱ አልፎ ለነፃነትና ለለውጥ የታገሉትንም ሰዎች በሂደት በሙስናው ልምምድ ውስጥ እንዲገቡ አስተማሯቸው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ አጋጣሚ ልንገርሽ። መንግስቱ ሃይለማርያም በአንድ ስብስባ ላይ ሁሉም ተሰብሳቢዎች ሃሳብ ለመደገፍ እጃቸውን ሲያወጡ 70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የወርቅ ቀለበት አድርገው ያይና ‹‹ይህችን ጣት እቆርጣዋለሁ ›› ብሎ ተናገረ። የደርግ ሰዎች ከድግስ ባለፈ በግላቸው የሚያካብቱት ሃብት አልነበረም። በሙስና ስማቸው አይነሳም። እንዳውም አንድ ሰው 10 ብር ጉቦ ተቀበለ ተብሎ 15 ዓመት ተፈርዶበት እንደነበር ሰምቻለሁ። በኢህአዴግ ዘመን ግን አመራሩ ሙስናን የተለማመደ ከመሆኑ የተነሳ በይፋ የሚፈፅመው የቀን ተቀን ተግባሩ ነው የሆነው። ይህንን ሃሳብ ይዘን በስፋት ማስተማር እንደጀመርን ሙስና እኔን ሁለት ዓመት እስር ቤት በላችኝ።
አዲስ ዘመን፡– እንዴት?
አቶ ከበደ፡– ሙስና የበላችኝ እንዴት መሰለሽ፤ ስለሙስና ምንነትና በአገራችን ያለውን መልክ፤ እንዲሁም ሙስናን ለመከላከል የኅብረተሰቡ ሚና ምንድነው? የሚለውን ጉዳይ በብሄራዊ ቲያትር ሁለት ሺ ሰዎችን ሰብስበን አስተማርን። በዚያ መድረክ ላይ ኢኮኖሚያዊ እውቀት ያላቸውን እነብርሃኑ ነጋን፣ ብርሃነ መዋ፣ አቶ ተሸመ ገብረማርያም እንዲሁም በድሩ አደምን ጋብዤ ንግግር አንዲያደርጉ አደረኩኝ። በዚያ ገለፃ ላይ ከእኔ ቁጥጥር ውጭ በሆነ መልኩ የባለስልጣኑን ስም እያነሱ ውንጀላ ጀመሩ። በዚያ መድረክ ላይ በተናገሩት ንግግር ከፍተኛ የህዝብ ተቀባይነት አገኙ። ይህ ስብሰባ ጥር 2 ተካሂዶ መጋቢት 14 ፍርድ ቤት ጠርተውኝ ሌላ ሰበብ ፈልገው ለሦስት ዓመት ፈረዱብኝ። የአሁኑ የሰብዓዊ መብት ኮምሽኑ ዶክተር ዳንኤል የቅርብ ወዳጄ ነበርና ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አንድ ቀጠሮ የማያቆም ክስ ነው የሚል ሃሳብ ፃፈልኝ። ዋና መነሻቸው በዚያ መድረክ ለምን ስማችን ተጠራ የሚል ነው። በነገራችን ላይ ከእኔ ጋር 24 ሰዎች እንዲከሰሱ አቶ መለስ መመሪያ ሰጥተውበት ነበር። በአሠራር ግን 19ኙን ይተውትና አምስት ሰዎች እንቀራለን። ከአምስታችንም አራቱ ነፃ ወጥተው እኔ ብቻ ተፈረደብኝ። ሁለቱን ዓመት በጥሩ ፀባይ ጨረስኩኝ። እስር ቤት ሳለሁ በ30 ብር ታሪክ፣ ጆግራፊና ሌሎች ትምህርቶችን እስረኛውን አስተምር ነበር። በዚህም በአመክሮ ተፈታሁ።
አዲስ ዘመን፡– ከእሥር በኋላ በዚያው ስራዎት ቀጠሉበት?
አቶ ከበደ፡– እንዴታ፤ በነገራችን ላይ እኔን እዚህ ያደረሰኝ እልህ ሳይሆን ከልጅነቴ ጀምሮ እያደገ የመጣው ፍትህ መሻት ነው። ኅብረተሰባችን በህገመንግሥቱ የተሰጠውን መብትና ግዴታ ያወቀ ህዝብ መፍጠር ነው። ህዝቡ መብቱን ካወቀ መንግሥትን ይጠይቃል። የሥልጣን ባለቤት ህዝቡ ነው። እኔ ከታሰርኩ በኋላ የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮምሽን ይቋቋማል። እኔ ሁለት ዓመት በእስር ቤት ቆይቼ ስወጣ ይህ ኮምሽን ስሙ እንጂ ስራው መሬት ላይ ያልወረደ መሆኑን ተመለከትኩኝ። ከአፋር ጀምሮ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተዟዙሬ ስለሙስና አሰተማርኩኝ።
መቀሌ ላይ ባካሄድነው ስብሰባ ስንጀምር የመቀሌ ህዝብ ዲሞክራሲን ያመጡልን የእናንተ ልጆች ስለሆኑ እዚህ አገር ሙስና ይኖራል ብዬ አላስብም፣ ግን ዝም ብለን እንወያይበት ብለን ነው አልኳቸው። ይህንን ጊዜ ተሰብሳቢው እየተነሳ ‹‹እንዳውም የሙስና ምንጭ ያለው እዚህ ነው›› ማለት ጀመረ። አንዱ ተነሳና ትላንት ፀጉሩን አንጨፋሮ የታገለው ሰው ዛሬ አራት ኮብራ መኪና ተመድቦለታል። አንዱን ለሚስቱ አስቤዛ መግዢያ፣ አንዱን ለልጆቹ ትምህርት ቤት ማመላለሺያ ፣ አንድ ለራሱ፣ ሌላው ደግሞ ከአዲስ አበባ መቀሌ ንግድ የሚያካሄድበት መኪና ተመድቦለት ነው የሚኖረው የሚል ነገር ተናገረ። በየፖሊስ ጣቢያውና ፍርድ ቤቱ ያለው ሙስና ደግሞ ከዚህም የከፋ መሆኑን ነው የገለፁልኝ። በመሆኑም እንዳውም ሙስና በኢትዮጵያ ደረጃ ለማከፋፈል የተቋቋመ ድርጅት ነው አሉኝ።
በተመሳሳይ ጅማ ህዝቡ አንዳለ ወጥቶ መንግሥት ሳይሆን ሽፍታ ነው የሚገዛን አለ። ይህችን ሪፖርት ግጥም አድርጌ ፅፌ ለአባዱላ ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ላኩላቸው። በነገራችን ላይ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ ሁልጊዜ በስብሰባችን መጨረሻ ሪፖርት እንዲደርሳቸው እናደርጋለን። እኛ ይህንን ሪፖርት ካደረስን በኋላ የጅማው አመራር በሙሉ እንዲነሳ ተደረገ። በተጨማሪም ድሬዳዋ ላይ ስብሰባ አዘጋጅተን ነበር። እንደሚታወቀው የድሬዳዋ ነዋሪ ከአምስት ሰዓት በኋላ ስብሰባ መቀመጥ አይፈልግም። ያን ቀን ግን አንዲት የከተማዋ እናት በሩን ዘግተው ‹‹ስብሰባው እስከሚያልቅ አንድም ሰው መውጣት አይችልም›› ብለው ዘጉት። ህዝቡ ምሬቱን ሁሉ ዘርግፎ ተናገረ። መላው ተሰብሳቢ ያለው አስተዳደር አያስፈልገንም ብሎ ደመደመ። ያን ጊዜ አንድ የመንግሥት ኮምሽነር ተነስቶ ‹‹መንግሥት ለመገልበጥ ነው የመጣኸው›› አለኝ። ህዝቡ በሙሉ ተነስቶ ‹‹ከዚህ ሰው አንዲት ፀጉሩ ትነካና ከአንተራስ አንወርድም›› አሉት። እናም ሰውየው በህዝቡ ጩኸት ደነገጠና ይቅርታ ጠየቀ። በዚያ መሰረት ለመንግሥት ሪፖርቴን ባቀረብኩኝ በሦስት ቀን ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ እንዳለ አስተዳደሩ ተባረረ። በተመሳሳይ ወላይታ ሶዶ፣ ሐዋሳ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ አደረግን። ስለዚህ ከእኛ ድርጅት ጀርባ ግዙፍ ግዙፍ የሆኑ ውጤቶች ስላሉ ከፍተኛ ኩራት ነው የሚሰማኝ።
አዲስ ዘመን፡– ሲቪክ ማህበራት ህዝቡን በማንቃት ረገድ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ማለት ይቻላል?
አቶ ከበደ፡– መልሴ ፍትሃዊ መሆን እንዳለበት አምናሁ። ትክክለኛው ነገር የህዝባችንን ሁኔታ ካየን ንጉሣዊ አገዛዝ ነበር፣ ያ የራሱ ትርጉም አለው። ከዚያ ደግሞ ወታደራዊው የደርግ አገዛዝ መጣ። ሁሉም የየራሱ መልካምና መጥፎ ገፅታ አለው። ብዙውን ጊዜ አይኖቻችን መልካም ነገር አያይም። በንጉሡ ዘመን የነበሩ ነገሮች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የማኅበረሰቡ ስነልቦና ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል። ደርግም ማኅበረሰቡን በጣም አንቅቶታል። በደርግ ዘመን ሲቪክ ማህበራት በይፋ ባይፈጠሩም እንኳን የተለያዩ ማህበራት ኅብረተሰቡን በማንቃት ረገድ ቀላል የማይባል ሚና ነበራቸው። ነገር ግን በራሱ ሳጥን ውስጥ አስቀምጦላቸው ስለነበር በሚፈለገው ልክ እንዳይሰሩ አድርጓቸው ነበር። ኢህአዴግ ሲመጣም ተመሰሳይ ነገር ነው የተከሰተው። ህገመንግሥቱ ውስጥ መልካም ነገሮች እንዲያውቅ አልተደረገም። ለመብቱ እንዳይቆም ሆነ እንዲታገል መሰራት የሚገባው ሥራ በበቂ ሆኔታ ተሰርቶለታል ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ አንፃር በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት የሲቪክ ማህበራት ምን ያህል ፍትሃዊ ነበሩ ማለት ይቻላል?
አቶ ከበደ፡– አስቀድሜ ለመግለፅ እንደሞከርኩት በቀደሙት መንግሥታት የነበረው አሰራር አሁን ድረስ በኅብረተሰቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና እንደሚያሳድረው ሁሉ እነዚህ የሲቪክ ማህበራትም የዚሁ ችግር ሰለባ መሆናቸው አይቀርም። ለህዝብ ተቆርቆርቋሪና ለአገር ግንባታ ከልባቸው የሰሩትን ያህል ግን ሁሉም ከውግንና የፀዱ ነበሩ ለማለት አልደፍርም። ሰው በመሆናቸው ከአንዱ ጎን መሰለፋቸው አይቀሬ ነው። ስለዚህ ሲቪል ማህበራቱ ኅብረተሰቡን በሚቀርፁበት ጊዜ ፍጹም የተሳካለት ሥራ ሰርተዋል ማለት አይቻልም። ይህ ደግሞ በ1997ዓ.ም በነበረው ምርጫ ላይ በግልፅ የታየ ነው። ሲዲአርኤ ቅንጅትን ተከትሎ ግልፅ አቋም ነው ይዞ የወጣው። ይህ ሲቪክ ማህበራት በራሳቸው የሚዛናዊነት ችግር እንደነበረባቸው አንዱ ማሳያ ነው። በአንዱ ወይም በሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ተፅእኖ ስር ወድቀው ነበር። በአጠቃላይ ሚዛናዊ ነበሩ ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡– ያለፉት አምስት ምርጫዎች በእርሶ እይታ እንዴት ነው የሚገለፁት?
አቶ ከበደ፡– ምን ከምን እንመርጣለን የሚለው ነገር ሌላ ጥያቄ ሆኖ ምርጫ መካሄዱ እሙንና እንደአንድ መልካም ነገር የሚቆጠር ነው። ከዚህ አኳያ ያለፈው መንግሥት ምን ያህል ትክክለኛ ምርጫ እንዲካሄድ ይፈልግ ነበር የሚለው ነገር በራሱ ሌላው አጠያያቂ ጉዳይ ነው። እንደምታስታውሽው ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች 17 ዓመታት አፈር ልሰው ሥልጣኑን መቆጣጠራቸውን በተደጋጋሚ ይገልፁልን ነበር። በእኔ እምነት የዲሞክራሲውን ካባ ከመልበስ ይልቅ ግን ወታደራዊ አገዛዝ ሊገዙ ይችሉ ነበር። ግን ከራስ በተነጠለ ሁኔታ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርዓት ቢፈጥሩ ኖሮ መቶ ዓመት ቢገዙ ብዙዎቻችን ቅር ባላለን ነበር። በኋላ በኋላ በጥሩ መልኩ የተጀመረው ለውጥ እየዋለ እያደር ወደ ግል ጥቅም ዝቅ እያለና እየወረደ መጣ። የአገራችን ፖለቲካ አቅድ የያዘ ወይም የሃሳብ ፖለቲካ አይደለም። ይልቁንም የሃይማኖት ወይም የዘር ፖለቲካ ነው። ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ራሳቸው ሲገናኙ የሚያወሩት ሌላ ዞር ሲሉ የሚያወሩት ሌላ ነው። ይቅርታ አድርጊልኝና ሁሉንም ነገር በግልፅ የምናወራ ቢሆን ኖሮ አገረ-መንግሥት መመስረት በቻልን ነበር። በእኔ እምነት የአገረ መንግሥት በስርዓት መገንባት ያለመቻሉ ነው አሁን ያለንበት ችግር ያመጣው። ሁሉም መንግሥታት ባልገነቡት አገር ላይ ሆነው ህዝብ ለመምራት ያደረጉት ጥረት ውጤታማ አላደረጋቸውም። ህዝቡ አንድ ከማድረግ ይልቅ ልዩነቱ ላይ ነው የተሰራው። ቁጭ ብለን በልዩነቶቻችን ላይ ተነጋግረን መፍታት ባለመቻላችን ነው አሁን ላይ ፍዳ እያየን ያለነው። ፖለቲካችን ድብቅ ነው። አሁን ላይ ያለው ትውልድ በግል ተነግሮ የዚህችን አገር በሽታ ፈትሾ ወደ ትክክለኛ መስመር ካልመራው በስተቀር ችግሩ መቀጠሉ አይቀርም። ሁሉንም ነገር ከባድ ነው እያልን እኛ ሳንፈታው ለልጆቻችን ከባድ ችግር ማውረስ አይገባንም።
አዲስ ዘመን፡– ባለፉት ዓመታት ሲቪክ ማህበራት በምርጫ ታዛቢነት እንዳይሳተፉ በአሠራር መከልከላቸው በአገሪቱ ዲሞክራሲ ግንባታ ላይ ምን አይነት አሉታዊ ጎን ነበረው ይላሉ?
አቶ ከበደ፡– እንዳልሽው ትልቅ ተፅዕኖ ነበረው። ለምሳሌ አሞዲያስ የሚለው የድርጅታችን ስም አፍሪካዊ ሙከራ ለዲሞክራሲያዊ የዓለም ስርዓት ነው የሚል ትርጉም ነው ያለው። አንድ ቀን ጠሩኝና የድርጅቱ ስም ውስጡ ዲሞክራሲ ያለበት በመሆኑ ቀይረው አሉኝ። ሲጀመርም ይህ ድርጅት የተቋቋመው ዲሞክራሲ ለማስተማር ሆኖ ሳለ ስለዲሞክራሲ ማስተማር አትችልም የመንግሥት ሥራ ነው ተባልኩኝ።ለሲቪክ ማህበራት ኤጀንሲ ምክትል ሥራአስኪያጅ ገብቼ ያሁንኑ ችግር አስረዳሁት። ሁኔታውን ስለተረዳኝም ትርጓሜው ቀርቶ አሞዲያስ የሚለው ስም ብቻ እንድንጠቀምበት አዘዘልኝ። ያ የድርጅቴን ስም እንድቀይር ጫና ሲፈጥርብኝ የነበረው ኦፊሰር ለካ ጉቦም ይፈልግ ነበር። እኔ ግን በወቅቱ አልገባኝም ነበር። ባውቅም ግን ፈፅሞ ልሰጠው አልችልም ነበር። የሚገርምሽ ከትንሽ ጊዜ በኋላ የኤጀንሲው ኃላፊ መነሳቱን ጠብቆ ያው ኦፊሰር ያንኑ ጥያቄ ደግሞ አነሳና ይበጠብጠኝ ጀመር። ህገመንግሥቱ ይፈቅዳል ለምን ትከለክላለህ ብለውም ሊሰማ አልቻለም። በአጠቃላይ ይህንን ያነሳሁልሽ በእኛ ድርጅት ላይ የደረሰው በደል ሌላውንም ገፅታ ነው የሚያሳየው። ቀጠሉና በአሰራር ከለጋሽ ድርጅቶች የምታገኙትን ገንዘብ 70 በመቶውን ሥራ ላይ ታውላላችሁ፤ 30 በመቶውን ደግሞ ለአስተዳደራዊ ስራዎች ማዋል ትችላላችሁ የሚል ትዕዛዝ አወጡብን። ይህም ማለት ለምሳሌ እኔ የዚህ ሥራአስኪያጅ ድሬዳዋ ላይ አንድ ስብሰባ ባዘጋጅ የትራንስፖርት አባልም ሆነ አጠቃላይ ወጪዬ የሚሸፈነው በራሴ ደመወዝ ነው። አንድ እንግዳ ብጋብዝም ሆነ ጥናት ለሚያደርገው አካል ለሚወጣው ወጪ ሁሉ ከዚሁ ከ30 በመቶ ነው እንድንወስድ የተደረገው። በዚህ ምክንያት ብዙ መስራት ስንችል ተሸብበን ለመቆየት ተገደናል። ስለዚህ በአጠቃላይ በአሰራር አስረው በዲሞክራሲ ግንባታው ላይ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እንዳንወጣ አድርገውን ነው የቆዩት።
አዲስ ዘመን፡– ታዲያ አሠራሩ በአዋጅ እንዲሻሻል መደረጉ ከጠቀሷቸው ችግሮች ባሻገር ምን ፋይዳ ይዞላችሁ መጥቷል?
አቶ ከበደ፡– የፈረሰን ነገር መልሰሽ መገንባት ስትጀምሪ ብዙ ድካም ይኖረዋል። የተጣመመ ነገርን በቶሎ ለማቃናት ይቸግራል። አሁን ላይ ነበራዊ ሁኔታም ቢሆን የሲቪክ ማህበራቱ በገለልተኝነት ከውጭ ገንዘብ ሳይፈልግ የሚሰሩት ነባሮቹ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ መካነኢየሱስ ቤተክርስቲያን፣ የካቶሊክ ካርዲናልን የመሳሳሉት የእምነት ተቋማት ስር ያሉ አንጋፋ የበጎአድራጎት ድርጅቶች ናቸው። ይህም ማለት እነዚህ ድርጅቶች አስቀድመው ተቋማትን ያደራጁና የራሳቸው የገቢ ምንጭ ያላቸው ናቸው። ሌሎች በጎአድራጎት ድርጅቶች ግን ከእለት ተእለት ወጪያቸው ባለፈ ተጨማሪ ኢኮኖሚ በአገር ውስጥ የሚያመነጩበት እድል አልነበራቸውም።
አብዛኞቻችን ከውጭ በሚመጣ ገንዘብ ላይ ነው የተመሰረትነው። የውጭ ድጋፍ ሲቆም ስራችን አብሮ ይቆማል። የማይካደው ነገር ግን አሁን ላይ የአዋጁ መሻሻል አስቻይ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ብለን ብዙ ተስፋ አድርገን ነበር። ግን ደግሞ ወዲያውኑ ኮቪድ መጣና የእኛን ብቻ ሳይሆን የረጂ አገራትን ኢኮኖሚ ጥያቄ ውስጥ ከተተው። አሁን ላይ በአብዛኞቹ የዓለም አገራት የማይሰራ ህዝብ ነው እየተቀለበ ያለው። ስለዚህ እነሱ ከዚህ ችግር ውስጥ ሳይወጡ እኛን መደገፍ የሚችሉበት ሁኔታ ባለመኖሩ ስራችን አብሮ ተቋረጠ። በአጠቃላይ ግን አዋጅና አሰራር ከማሻሻል ባሻገር በኤጀንሲው በኩል አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተሞከረ ነው። ሠራተኞቹ እንደቀድሞ ችግር ፈጣሪ ሳይሆን ችግር ፈቺ ሆነው ነው እየደገፉን ያሉት።
በሌላ በኩል ግን ወደፊት የሚሆነውን ነገር አናውቅም ወደፊት የሚሆነው ነገር ያሳስበኛል። ምክንያቱም ይህ ስርዓት ቢቀየር የእኛም አሰራር ይቀየራል የሚል ስጋት ስላለኝ ነው። ተቋም ግንባታ ላይ በትክክል ሰርተናል የሚል እምነት ስለሌለን ነው ይህንን የምልሽ። እንደአጠቃላይ የለውጡ መንግሥት ትክክለኛ ዲሞክራሲን ለማምጣት እያደረገ ያለው ጥረት መልካም ሆኖ ሳለ አንዳንድ ቦታዎች ላይ አመራሮችን ለማነጋገር ጥረት በምናደርግበት ጊዜ በሮች የሚዘጉበት ሁኔታ አለ። በእኔ እምነት ማንኛውም አመራር ህዝብን ሊያገለግል የተሰየመ እንደመሆኑ ቀለል ብሎ የህዝቡን የልብ ትርታ ማድመጥ መቻል አለበት ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡– በዘንድሮ ምርጫ በታዛቢነት ለመሳተፍ እያደረጋችሁት ያለውን ዝግጅት ያስረዱኝ?
አቶ ከበደ፡– አስቀድሜ እንዳልኩሽ ድርጅታችን በምርጫ ላይ የካበተ ልምድና ሰፊ ተሞክሮ ያለው ነው። እንዳልሽው ለመታዘብ ጠይቀን ምርጫ ቦርድ ፅፎልናል። ከእኛ ተቋም በዘለለ ግን በአጠቃላይ አንደሀገር ምርጫ እንደሚካሄድ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ ብዙ መሰራት የሚገባቸው ስራዎች ነበሩ ብዬ አምናለሁ። ይህንን ሃሳቤን ከአንድ ዓመት በፊት ምርጫ ቦርድ ጋብዞኝ ባቀረብኩት ፅሁፍ ላይም አንስቼው ነበር። ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ሲቪክ ትምህርት ከትምህርት ቤት ጀምሮ በየትኛውም ተቋም እንደባህል ህዝቡ ውስጥ ማስረፅ ይገባናል የሚል እምነት አለኝ። ህዝቡም የራሱ አካል እንዲያደርገው የግንዛቤ ማስጨበጡ ስራ በስፋት ማስኬድ ይገባን ነበር። ሁለተኛው ይሄ ምርጫ ይካሄዳል ከተባለ የምርጫ ህጉ ላይ ቢያንስ ለስድስት ወር ያህል ህዝቡን ማስተማር ይገባል የሚል አምነት አለኝ። ምክንያቱም ህዝብ ስለመብቱ መጠየቅ የሚችለው መብቱን ሲያውቅ ነው። ለምሳሌ ለሚከፍለው ግብር ተመጣጣኝ አገልግሎት ማግኘት መቻል አለበት። ከዚህ አኳያ የመራጮች ትምህርት ላይ ትኩረት ተደርጓል ብዬ አላምንም።
በዚህ መለኪያ የዘንድሮ ምርጫ ዝግጅት በእኔ እምነት በቂ ነው ብዬ አላምንም። አንዳንድ ጊዜ ብቅ ብቅ የሚሉ ነገሮች አሉ። ግን በቂ አይደለም። ከዚያ ባለፈ አውጥተሽ መነጋገር መቻል አለብሽ። አሁን ደግሞ ሰዓቱ እንደሳሙና ቁራጭ እያለቀ ነው ያለው። ምርጫውን የሚታዘቡ አካላትም ስልጠና ያስፈልጋቸዋል። የውጭ ታዛቢዎችን አስቀድሞ መጋበዝና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አንዲያጤኑ ማድረጉ ጠቃሚ ነው። ይሄ እስካሁን አልተደረገም። ድሮ ካርተር ሴንት የሚባል ነበር፤ አሁን የለም። የአፍሪካ ኅብረት አልተጋበዘም። ድሮ ዓረብ ሊግ አንኳን ይጋበዝ ነበር። ስለዚህ ለእኔ አጠቃላይ የምርጫ ዝግጅቱ አጥጋቢ ነው ብዬ አላምንም።
በነገራችን ላይ ይሄ ብቻ አይደለም ስጋቴ፤ የሰላም ጉዳይ ሌላው አንዱና ትልቁ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ህዝቡ ሙሉ አዕምሮውን ምርጫው ላይ አድርጎል ብዬ አላማንም። ይሄ ምርጫ መንግሥት ስለፈለገው ሊካሄድ የሚችል ነገር እንጂ ህዝቡ በሰላም እጦት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነው ያለው። መሬታችን በሱዳን ተደፍሯል። የህዳሴ ግድቡ ላይ በየቀኑ በግብፅና በደጋፊዎቿ የሚደረግብን ዛቻ አለ። ኦፌኮና አነግ ምርጫው ላይ የማይሳተፉበት እድል አለ። ይህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ምክንያቱም አነሰም በዛ እነዚህ ፓርቲዎች የራሳቸው ደጋፊዎች አሏቸው። የእነሱ በምርጫው ላይ አለመሳተፍ የሚያሳድረው አሉታዊ ጎን ይኖራል። ከዚህም ባለፈ የኢኮኖሚ ጉዳይ አሁን እጅግ በጣም አሳሳቢ ሆኗል። የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሁሉ የተመሰቃቀሉ ጉዳዮች ባሉበት፣ ሰላም በጠፋበት መንግሥት ስለያዘው ብቻ መደረግ አለበት ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡– ምርጫውን በራሱ መራዘሙ ሌላ የሚፈጥረው ችግር አይኖርም?
አቶ ከበደ፡– እንዳልሽው አንቺ የጠየቅሽውን ጥያቄ ሌላም ሰው ያነሳዋል።ለእኔ ግን ከምርጫ በላይ የሚያሳስበው የአገርና የሕዝብ ደህንነት ነው። ምክንያቱም አገርና ህዝብ ከፈጣሪ ቀጥለው ዘላለማዊ ናቸው። አገርና ህዝብን ለመታደግ ምርጫን አንድና ሁለት ዓመት ማራዘሙ ችግር ይኖረዋል ብዬ አላምንም። በተለይም ደግሞ ኮቪድ በኢኮኖሚያችን ላይ ያሳረፈው ተፅዕኖ እየታወቀ ምርጫ ካልተካሄደ ማለት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። አሁን ያለውን መንግሥት ወደድነውም ጠላነው አገር እያስተዳደረ ነው ያለው። በዚህ ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ እያስተዳደረ ቢቆይና ስጋቶቻችንን ከቀረፍን በኋላ ምርጫ ብናካሂድ የተሻለ ነው። በእርግጠኝነት ችግሮቻችንን ለመፍታት ተዘጋጅተን ከሆነ በልህ ሳይሆን በሆደ ሰፊነት አገር ለመገንባት ቅድሚያ መዘጋጀት አለብን። ስለዚህ ጊዜ ትልቅ መድህን ነው። ትልቅ ፈውስ ነው። በጊዜ ሂደት ችግሮቻችን እንፈታለን ብለን ነው የምናምነው። አንዳንድ ፓርቲዎች ‹‹ምርጫው ካልተደረገ፣ ይሄ መንግሥት ህጋዊ አይደለም›› የሚሉ እንዳሉ አውቃለሁ። እነዚህ ድርጅቶች ይህንን የሚሉት አወዛግበው ቶሎ ስልጣን ላይ ለመውጣት ካላቸው ፅኑ ፍላጎት የመነጨ ነው። የሚሞኝላቸው ካገኙ ከመቀማት ወደኋላ አይሉም። ዶክተር አብይ ግን እንዳሰቡት የዋህ አልሆነላቸውም።
ስለሆነም በተገኙ ውጤቶች ላይ ተደማሪ ሥራ እየሰሩ አቅማችንን አስቀድመን ማጠናከር ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ ። ከምንም በፊት እርስበርስ ብንከባበርና ብንደማመጥ ጥሩ ነው።ከእነዚህ ሁኔታዎች በመነሳት ምርጫውን የማራዘም ነገር ለእኔ ችግር አልነበረም። አሁን ላይ ያለው መንግሥት አስተዳደሩ ላይም ሆነ የውጭ ግንኙነቱ ላይ ልምድ ያለው በመሆኑ አገር እስከምትረጋጋ ድረስ ባለበት ቢቀጥል የተሻለ ነው። ለእኔ እንዳውም አዲስ መንግሥት አምጥተን ልምድ እስከሚቀስም ድረስ የሚከተለው ምስቅልቅል ነው የሚያሳስበኝ። ይህ በመሆኑ ምርጫውን በብዙ ስጋቶች የሚፈፀም በመሆኑ ጠቃሚነቱ አይታየኝም። የሚመረጠውም አካል ያሉ ችግሮችን የሚረከብ በመሆኑ ለውጥ ለማምጣት የሚቸገር ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡– ምርጫው አይቀሬ መሆኑ ከታወቀ ወዲህ የታዛቢዎች ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ? በተለይም ከሥነምግባር ደንቡ አኳያ ምንአይነት ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?
አቶ ከበደ፡– እንዳነሳሽው ማንኛውም ታዛቢ ለምርጫ ሲቀመጥ ማክበር የሚገባው የስነምግባር ደንብና የአፈፃፀም መመሪያዎች አሉ። ለምሳሌ የምርጫው ቀን የምርጫ ጣቢያ ከማለዳው 12 ሰዓት ከመከፈቱ በፊት አስፈፃሚዎቹ ቀድመው ሊገኙ ይገባል። ከምርጫው ቀን ቀደም ብሎ የየትኛውም ፓርቲ መፈክሮች እዛ አካባቢ መገኘት የለባቸውም፤ የታጠቀ ሰው መኖር የለበትም። ልክ ምርጫ ሲጀመርም ኮሮጆው ተደፍቶ ባዶ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ሁለተኛው የምርጫ ማስፈፀሚያ ግብዓቶች ዝግጁ መሆን አለባቸው። መራጮች ከማንም ተፅዕኖ ውጭ መሆናቸውን ማረጋገጥ መቻል አለብን። ውጤቱ እስከሚታወቅና ለህዝብ እስከሚገለጥ ድረስ በጥንቃቄና በኃላፊነት መስራት ከአንድ ታዛቢ የሚጠበቅ ነው። ያም ሆኖ ግን አስቀድሜ ከገለፅኩልሽ ችግር አኳያ የዘንድሮ ምርጫ ብዙም የሚያጓጓ አይደለም። የይስሙላ ምርጫ ነው ባይባልም እንኳን ከ1997 ቱ ምርጫ አኳያ የወረደ ነው። አሁን ላይ ያለው የዋጋ ንረት ራሱ ሰው የእለት እንጀራውን በስጋት ውስጥ እንዲያስብ አድርጎታል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ምርጫው ዘንድሮ መደረግ አለበት ነው ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡– በዘንድሮ ምርጫ የሃይማኖት ሰዎች ተወዳዳሪ ሆነው ቀርበዋል። ይህ በፖለቲካው ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ ይኖረዋል?
አቶ ከበደ፡– በእርግጠኝነት ተፅዕኖ ይኖረዋል። ግን ደግሞ ህገመንግሥቱ ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ፓርቲ አይቋቋምም ይላል እንጂ የፓርቲ አባል መሆን አይችልም አይልም። ስለዚህ የምርጫ ጉዳይ ነው የሚሆነው። ይህ ግን በኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጥረው የስነልቦና ጫና አለ። እኔ እገሌ የተባለውን የሃይማኖት አባት የምፈልገው በሃይማኖቱ ትምህርት እንዲያስተምረኝ እንጂ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ እንዲያገለግለኝ አይደለም። መንፈሳዊ ተልዕኮውን ትቶ ወደ ፖለቲካ ሲመጣ ለእዛ አባት ያለን ግምት ይበላሻል። ለዚያ ሰው ብቻ ሳይሆን ለፓርቲው ያለንም እምነትም ይሸረሽራል፤ ውጤቱም ይቀንሳል። ሃይማኖትን እንደፖለቲካ መሳሪያ ለመጠቀም የሚደረግ ሙከራም ሊመስል ይችላል። ስለዚህ እንዳልሽው በፖለቲካው ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል። ለእኔ በሃይማኖታዊ ስብዕናው የማውቀው ሰው መንፈሳዊ ልዕልና ያሳጣዋል። ስለዚህ እኔ የማመልክበት ቤተእምነት አገልጋይ ፖለቲካ ውስጥ ባይገባ አከብረዋለሁ። የእምነት ሰዎች ፖለቲካ ውስጥ መግባታቸው ፖለቲካውን የቀልድ ፖለቲካ ያደርገዋል። ለፖለቲካው ክብር እንዳይኖር ያደርገዋል።
አዲስ ዘመን፡– ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ አንዲጠናቀቅ ከማን ምን ይጠበቃል?
አቶ ከበደ፡– እንዳልኩሽ እኔ የታሪክ ተማሪ ነኝ። አሜሪካን አገር በፒስ ኤንድ ኮንፍሊክት ስተዲስ ማስተርሴን ሰርቻለሁ። ከዚህ ባሻገር ሩዋንዳ የነበረውን ችግር ተመልክቻለሁ፤ ደቡብ አፍሪካም ልምድ ቀስሚያለሁ። ተመሳሳይ ችግር ካጋጠማቸው አገራት ልምድ ቀስሚያለሁ። የአገርን ሰላም ማስጠበቅና ተቻችሎ የመኖር ባህልን ማስቀጠል ከምንም በላይ ቀዳሚ ነገር ሊሆን ነው የሚገባው። በተለይም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ አጠቃላይ ፖለቲካ መረጋጋት ወሳኝ አገር ናት። ብዙና ትልቅ ህዝብ ነው ያላት። የበለጠ ትልቅ መሆን እንድንችል ደግሞ ፈጣሪ ምድሪቱ ከርስ ውስጥ በቂ ሃብት አስቀምጦላታል። ይህ ሆኖ እያለ አቅማችንንና ያለንን ሃብት አለማወቃችን ያሳዝነኛል። ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረገንም ይኸው ነው። ያለንን ሰፊ የሰው ሃይል ማስተባበር ያለመቻላችን እንደብዛታችን ትልቅ እንዳንሆን ነው ያደረገን። በዓለም ላይ እንደአንበሳ ልናስፈራ የምንችለው በአንድ ላይ ሆነን ተግባብተን ስንሰራ ነው። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ምርጫውን በሰላም ከማካሄድ ባለፈ የውጭ ግንኙነታችን ዘግተንም ቢሆን በመጀመሪያ የውስጥ አቅማችንን ማሳደግ ይገባናል ባይ ነኝ። ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው የእያንዳንዱ ዜጋ መብት የሚያስጠብቅ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ስንገነባ ነው።በተጨማሪም የሰው የመኖር መብት የማይነካባትን አገር መፍጠር ይጠበቅብናል።
ባለፉት ምርጫዎች ላይ ብዙ የሚናገሩ ሰዎች ነበሩ። ብዙ ተስፋዎችም ተሰጥቶን ነበር። ነገር ግን የተነገሩን ተስፋዎች በተነገሩን ልክ ተፈፅመዋል ወይ የሚለው ነገር አጠያያቂ ነው። ብዙ ስለተናገሩ አይደለም የተግባር ሰው የሚሆኑት። ከዚያ ይልቅም ችግሮቻችንን ነቅሶ አውጥቶ በግልፅ ለመፍታት ቁርጠኝነቱ ሊኖር ይገባል። የሚመጣው ለውጥ የእያንዳንዱን ሰው ህይወት መለወጥ መቻል አለበት። ደጋግሜ እንዳልኩሽ የአሁኑ ምርጫ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ የሚካሄድ እንደመሆኑ በጣም በጥንቃቄ ማስኬድ ይጠበቅብናል። ከዝግጅት ባለፈ የህዝቡን ስነልቦና ስሜት መገንዘብ ይገባል። ህዝብን ማረጋጋት ይጠበቃል። የመሳሪያ ጋጋታ ሰላም አያመጣም፣ ትልቁ ነገር የሰውን ልቦና መግዛት ነው። የኑሮ፣ የሰላም ስጋት ሳይኖርብን ምርጫ ማካሄድ የምንችልበትን ሁኔታ ከመንግሥት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማህበራት እንዲሁም ከእናንተ ከሚዲያ አካላት ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ከበደ፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2013