የአርሶ አደሩን ምርት ወደ ጎተራ

በሀገራችን ያለው የእርሻ ሥራ ሺዎች ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ያለበት የእድገት ደረጃ ግን ገና በመዳህ ላይ ነው፡፡ ለማለት ያስደፍራል። ከሺህ ዓመት በፊት በሬ ይጎትቱ የነበሩ አርሶ አደሮች ከሃያ እና ከዛም በላይ በሆነ ትውልዳቸውም የተፈጠረ አዲስ ነገር የለም። የገበሬው ልጅ ጠንካራ በሬ ጠምዶ ለማረስ ጥጆቹም ጠንካራ በሬ ሆነው ተጠምደው ለመታረስ ቃል የተገባቡ ይ መስላል።

በትንሹ ባለፈው አንድ መቶ ዓመት የሚደርስ ጊዜ ግብርናው መዘመን እንዳለበት በየወቅቱ ዘመንን ካሉ ሰዎች በተደጋጋሚ ሲነገር ሰምተናል። በተለይ ከ1950ቹ በኋላ የተማረው ኃይል ሁሉ ትኩረቱ ወደ አርሶ አደሩ ሆኖ ነበር። ነገር ግን ዛሬም ድረስ አብዛኛው አርሶ አደር በአዲስ በሬ በአዲስ ሞፈር መሬቱን ከመንካት የዘለለ ለውጥ አልገጠመውም።

አንድ አርሶ አደር ከተማ ደርሶ እንደ ቀልድ ወደ አፋችን የምናደርገውን እህል ለማድረስ ብዙ ጊዜ አይደለም ብዙ ድካምም ያሳልፍበታል። ድካሙ ደግሞ እንዲህ በቀላሉ በጉልበት ብቻ የሚገመት አይደለም። የጉልበት ድካም ማታ ቤት ያፈራውን እህል ቀማምሰው ጋደም ሲሉበት የደከመው ጉልበት፤ መበርታቱ የዛለው ጡንቻ መጠንከሩ አይቀሬ ነው።

አርሶ አደር ግን ከዚህም ባለፈ ብዙ እረፍት የሚነሳ የአዕምሮ ሀሳብም አለበት። ከጅምሩ እህል ሳይዘራ የበሬና ሞፈር ቀንበር አንግቶ ወደማሳው ለእርሻ ሲወርድ ውሎው በአንድ ወገን በሬና አፈር በመግፋት ጉልበቱን የሚፈተንበት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የማዳበሪያ መምጣት አለመምጣት የዋጋው ነገርና ሌሎችንም በማሰላሰል አዕምሮውን እያደከመ የሚውልበት ነው።

ዘሩ መሬት ከነካ በኋላም ሥራውም ሀሳቡም ተጠናክሮ ይቀጥላል። በአንድ ወገን በደቦ የአረምና የኩትኳቶ ሥራው እንዲከናወን ከጎረቤትና ከአካባቢ ነዋሪ መምከር። ከዘር በኋላ የሚደረግ ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲደርስ ከቀበሌና ወረዳ ሹማምንት ጋር መነጋገር የየእለት ተግባሩ ሆኖ ይሰነብታል።

ብሎም ከአንበጣው መንጋ እና የተለያዩ ሰብል አጥፊ ተሕዋስያንን ለመከላከል በፀረ ተባይ መድኃኒት ፍለጋ ይቀጥላል። በዚህ ውስጥ አልፎ ሁኔታዎች ተሰካክተው ዘሩ ለፍሬ የደረሰለት ገበሬ ሀሳቡም ተግባሩም ከጎረቤትም ከነጋዴም ከሹመኛም ይፋታና ወደፈጣሪው ማዘንበል ይጀምራል።

ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ እንዲጥል የዘወትር ምኞት ብቻ ሳይሆን የየእለትም ጸሎቱ ሆኖ እንደሰነበተው ሁሉ፤ አሁን ደግሞ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የደረሰ እህሉን እንዳያጠፋበት ዝናቡን አውርድልኝ ባለው አፍ ፈጣሪውን ዝናቡን ያዝ አድርግልኝ ወደማለት ይሸጋገራል።

አሁን ያለንበት ወቅት ይህ ነው።

ከብዙ ፈተናዎች በኋላ የአርሶ አደሩ ሰብል ደርሶ የሚሰበሰብበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህም ማለት አርሶ አደሩ የዓመት ልፋቱን ውጤት የሚያይበት ወቅት ማለት ነው። በመንግሥትም በኩል በተደጋጋሚ እንደተነገረን በዚህ ዓመት ብዙ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ለዚህ የሚያበቃም ከማዳበሪያ ጀምሮ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጩ ተደርጓል። እነዚህን ጅማሮዎች ለፍሬ ለማብቃት ከአጨዳ እስከ ጎተራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁላችንም በትብብር መሥራት አለብን። ከቅርብ ግዜ ወዲህ የአርሶ አደሩ ሌላ ዕዳ ሌላ መሰናክል እየሆኑ ከመጡት ጉዳዮች መካከል ከተፈጥሮ ችግር ባለፈ በተወሰኑ አካባቢዎች ብልጭ ድርግም የሚሉ ግጭቶች ናቸው።

አንድ ገበሬ የደረሰ ሰብሉን በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግር የሚያጣበት ሁኔታ ቢፈጠር ኀዘኑና ሰቀቀኑ ለፍተው ያሳደጉትን ልጅ የማጣት ያህል ነው። እዚህ ላይ እንግዲህ የሚነሳው ጥያቄ ከእኛ ምን ይጠበቃል የሚል ይሆናል። በእርግጥ በአብዛኛው አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ለቀናት ተፋተው አርሶ አደሩን በመደገፍ ላይ መሆናቸውን እናውቃለን።

በተመሳሳይ ለቁጥር የሚታክቱ የመከላከያና ሌሎች የሕግ አስከባሪ አካላት በዚሁ ሠናይ ተግባር ላይ ተሠማርተው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም ሰምተናል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ጉዳዩ እስኪጠናቀቅ ድረስ የተሰጠው ትኩረት የሚደረገውም ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚል እምነት አለኝ።

በዚህ ረገድ በተለይም አንዳንድ አለመረጋጋት ባለባቸው አካባቢዎችና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ይከሰታል ተብሎ በሚሰጋባቸው ቦታዎች ፈጣን የኅብረት ምላሽ የሚጠበቅ ይሆናል። በሀገራችን «አንድ ሰኔ ያጠፋውን አስር ሰኔ አይመልሰውም » የሚባል ነገር አለ። ይህ ትልቅ እውነትም ትልቅ መልእክትም ያለው ነገር ነው።

ዛሬ አርሶ አደሩ ሰብሉን እንዲሰበስብ ምቹ ሁኔታ ካልፈጠርንለት እሱንም ቤተሰቡንም የማይወጡት ችግር ውስጥ መዝፈቅ እንደሆነ መገንዘብ ያሻል። ገበሬ በማሳው ያዘመረውን ሰብል አጣ ማለት ባዶ የሚሆነው ጎተራው ብቻ ሳይሆን በረቱም ነው። ለአርሶ አደር ሰብሉ ለእሱ ብቻ ሳይሆን እንደራሱ ለሚንከባከባቸው ከብቶቹም የቀለቡ መሠረት ነው። እህሉንም ከብቱንም አጣ ማለት ደግሞ ያለ ቅድመ ሁኔታ ቀዬውን ለመልቀቅ የሚገደድ ይሆናል።

በመሠረቱ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ሊደረግ የሚገባው ድጋፍ በጊዜና በሁኔታ መወሰን አለበት ብዬ አላምንም። ምክንያቱም አሁን ያለንበት ወቅት አርሶ አደሩን በዓመት አንድ ግዜ እሱንም ወቅት ጠብቆ ከማምረት ለማላቀቅ የተጀመሩ ሥራዎች በመኖራቸው ነው። እነዚህ ሥራዎች ደግሞ እንደሚጠበቀው ለውጤት ከበቁ እንደ ግለሰብም እንደ ሀገርም ለስንዴ ልመና የሚዘረጉ እጆችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሰብሰብ የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። የግብርናው መስክ ደግሞ ጠቀሜታው ለአርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ለመላው ሕዝብና ለመንግሥትም ጭምር መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።

በሌላ በኩል ግብርናውን ደግፈንና ትኩረት ሰጥተን ባቃናነው ቁጥር የከተሜው ሕዝብ ኑሮ ቀለል ማለቱ አይቀሬ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ መንግሥትም የጀመራቸው ሰፋፊና ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ፋታ አግኝቶ እንዲከውን አብዛኛውን የሀገሪቱ ሕዝብ የሚይዘው የአርሶና አርብቶ አደሩ ክፍል ጤናማ ሊሆን እንደሚገባ ይታወቃል። ይህ ማለት ከአርሶና አርብቶ አደሩ ምርት ከሚገኘው የውጪ ምንዛሪ ተጠቃሚነት ባለፈ እንደ ማለት ነው።

በመሆኑም በያለንበት በሁለት ወገን ለአርሶ አደሩ ትኩረት ልንሰጥ ይገባል። ይህም ማለት አንደኛው አውቀንም ሆነ ባለማወቅ በተለያዩ ምክንያቶች አርሶ አደሩ የእርሻ ሥራውን በሚያከናውን ቦታ በግጭት ውስጥ ያለን ለሕዝባችን ስንል እጃችንን መሰብሰብ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሌሎቻችን በያለንበት ከአርሶ አደሩ ጎን አብረን በመሰለፍ ዓመት የለፋበትን ምርት ለጎተራው እንዲያበቃ መርዳት ነው ።

ራስወርቅ ሙሉጌታ ,

 አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You