በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
ደብዳቤው የተጻፈው በእንግሊዝኛ ነው፤ ልቅም ባለ እንግሊዝኛ። ደብዳቤው የተጻፈበት መንፈስ አንድ ቀን በወደኩበት መንገድ ላይ አምላክ ያስበኛል በሚል ልብ ነው። ደብዳቤው የተጻፈው ይህን ማህበረሰብ በተቀየመ በቅይማት ውስጥ ዓመታትን ባስቆጠረ ሰው ነው። ደብዳቤው የተጻፈው ከብዙ አስርት ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና ክፍል ተማሪ በነበረ ሰው ነው። ደብዳቤው የተጻፈው በጎዳና ላይ ቤቱን ያደረገ በጎዳና ላስቲክን ወጥሮ በላስቲክ ውስጥ ኑሮውን ባደረገ በጉልምስና እና በሽምግልና ድንበር ላይ በሚገኝ ሰው ነው። በመንገዱ ላይ የወጡትን ኃይሎች መቋቋም ሳይችል ቀርቶ የተደበቀ ሰው ደብዳቤ። በግለሰቡ ቦታ ሆነው ሲያስቡት ያማል።
በጎዳናዎቻችን ላይ የሚኖሩ ሰዎች ብዙ ታሪክ ይዘዋል። የዛሬ ጽሑፋችን መነሻ ያደረግነው ታሪክ እውነተኛ ታሪክ ነው። በሕይወት ጉዞ ውስጥ ልቡ እጅጉኑ አዝኖበት ካለበት ሀገር ሸሽቶ ወደ አዲስ አበባ የመጣ፤ ከአዲስ አበባም ወደ ዱከም አቅንቶ በአንድ ወቅት ኑሮውን ጎዳና ያደረገ ሰው ታሪክ ነው። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለወንጌል አገልግሎት መንገድ ላይ በወጡበት ጊዜ ያገኙት፤ ከጎዳናም እንዲነሳ አድርገው አቅማቸው በፈቀደ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀል የረዱት ሰው ታሪክ። ጎዳናዎቻችን ላይ በዝምታ ማህበረሰቡን የሚታዘቡ ባለታሪኮች አሉ። ለዛሬ በሕይወት ጉዞ መስመራችን ላይ ኃይል ኖሯቸው ስለሚገፉን እናነሳለን። ዓላማችን ኃይሎቹን ተቋቋሞ የሕይወት ጉዟችንን በድል መጨረስ መቻል ነው።
እውቁ የስትራቴጂ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ማይክል ፖርተር የተባሉ በንግድ አሠራር ስልት ላይ የሚጽፉና የሚያስተምሩ ሰው አምስቱ ኃይሎች የሚሏቸው ኃይሎች አሉ። በንግዱ ዘርፍ ላይ የሚታዩት አምስቱን ኃይሎች ለእያንዳንዳችን በቀን ተቀን ኑሮ ውስጥ እንዴት እንደሚታይ እናያለን። በመንገዳችን ላይ የሚታዩት ኃይሎች በህይወታችን ላይ የሚያመጡትን ተጽእኖ ለመቋቋም እንዲረዳን በሚችል ሁኔታ እንመለከታለን። በሌላ ገጽታው ደግሞ እኛም እራሳችንን በሌላው ላይ ከምንፈጥረው ተገቢነት የሌለው ተጽእኖ አንጻርም እንድንመረምር እንጋብዛለን። በዛሬው ጽሑፍ ሦስቱን ኃይሎች እንመለከታለን፤ በቀጣይ ሳምንት ደግሞ ቀሪዎቹን።
1. ተፎካካሪዎቻችን፣
በልጆች መንደር ተገኝተን የሚያደርጉትን ዓይተን ከምንገረምባቸው ነገሮች መካከል አንዱ እርስ በእርስ የሚያደርጉት ፉክክር ነው። ወንድማማች የሆኑ ልጆች ላይ ፉክክሩ በደንብም ይታያል። ሲታጠቡ ፉክክር፣ ሲበሉ ፉክክር፤ ሲጫወቱ ፉክክር፣ ሲተኙ ፉክክር፣ ሲያለቅሱ ፉክክር ወዘተ። አብረው እየበሉ ትኩረታቸው የራሳቸው የምግብ ሳህን መሆኑ ቀርቶ የወንድማቸው ወይንም የእህታቻው ሳህን ላይ ሆነው እንዳይቀደሙ ራሳቸውን ይጠብቃሉ። በሕፃናት ልጆች ላይ በግልጽነት የሚታየው ፉክክር የሚታይበት መልኩ ይለያይ እንጂ በሌሎች የቤተሰብ አባላትም ላይ ይታያል። በአንድ ቤት ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ዘንድ ፉክክር ስላለ ሀገራዊ ብሂላችን “የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል” የሚለን።
ከቤተሰብ አውጥተን ወደ ጉርብትና ብንወስደውም ፉክክርን እናያለን። ፉክክርን በጉርብትና ውስጥ ባለው ማህበራዊ ካፒታል አንጻር ስንመለከተው አንዳችን ቤት ውስጥ ያለው ሶፋ አገልግሎት መስጠት አለመስጠት ሳይሆን በጎረቤታችን ውስጥ ካለው ሶፋ አንጻር እየተመለከትን ዳኛ በሌለው ፉክክር ውስጥ እንኖራለን። በልብስ፣ በሞባይል፣ በመኪና፣ በቤት ውስጥ ቁሳቁስ፣ ወዘተ ሁሉ ፉክክር ውስጥ አስበውበትም ይሁን ሳያስቡበት የሚገኙ ጥቂት አይደሉም።
ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ጀርባ ያለው የምዕራባውያን ተጽእኖን ምክንያት በጥሞና ስንመረምር ጉዳዩን ፉክክር ሆኖ እናገኘዋለን። ኢትዮጵያን አስታኮ በአካባቢው ላይ ያለውን የቻይናን የበላይነት ለመግታት በማሰብ የተሄደባቸው መንገዶች መኖራቸውን ምልክት እያየን ነው። ግብፅ በቀጣናው ላይ ያላትን የበላይነት በኢትዮጵያ ላለመነጠቅ ጭምር እንጂ የህዳሴው ግድብ የሚፈጥርባት ተጽእኖ ብቻም አይደለም ሲባልም ይደመጣል።
በቤተእምነቶች መካከል ስላለው ፉክክር ለአንባቢው ማንሳት ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል። ከሕፃናት እስከ አዋቂዎች፣ ከቤተሰብ እስከ ማህበረሰብ፣ የተማረውም ይሁን ያልተማረው፣ ሃይማኖተኛ ይሁን እምነት የለሽ በፉክክር መርከብ ላይ የተሳፈርን መሆኑ እርግጥ ነው።
በሕይወት መንገዳችን ላይ ፉክክር ያለው ተጽእኖን ገምግመን እናውቃለን? በግምገማችን በፉክክር ሕይወት ውስጥ የሄድንበት እርቀት የፈጠረልን አዎንታዊ ጥቅም ወይንስ አሉታዊነት ምን ይመስላል?
ሕይወት ከፉክክር ነፃ ማድረግ ባይቻል እንኳን በፉክክር አማካኝነት መስመር ላለመሳት መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ሀገራዊ ፖለቲካችን ውስጥ ያለው ፉክክር መለኪያው የሬሳ ቁጥር ሆኖ ስናይ ልባችን ይደማል። ፉክክሩ በመግደልም ሆነ በመጨፍጨፍ ሲሆን የፈጣሪ ያለህ እንላለን።
የእውቅ ሰዎች ፉክክር ደግሞ ከተቀናቃኞቻቸው ጋር ሆኖ በሚዲያ ሽፋን ተሰጥቶትም እንከታተላለን። አንድ ታዋቂ ሰው እርሱ እውቅናን ባተረፈበት ዘርፍ ውስጥ ካለ ከሌላ ታወቂ ሰው ጋር ይፎካከራል። በፉክክርም የተቀናቃኙን ውድቀት የእርሱ ድል አድርጎም ይነሳል።
በአጭሩ በሁሉም ስፍራ የሚገኝ ምናልባትም ምድራችን አሁን ያላትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ገጽታ እንድትላበስ ካደረጓት ምክንያቶች መካከል አንዱ ፉክክር ነው። በፉክክር ውስጥ አንዱ ተፎካካሪ ለሌላኛው በጥንቃቄ የሚታይ ኃይል ነው። በንግድ የሚፎካከሩ ድርጅቶች አንዳቸው የሌላኛውን ስልትና አካሄድ እያጠኑ የራሳቸውን ይቀይሳሉ።
ወደ ግል ሕይወት ስንመጣ፤ በሕይወታችን ውስጥ ፉክክር የፈጠረው አዎንታዊ እና አሉታዊ ነገሮችን መመልከት አስፈላጊ ነው። ጤናማ ያልሆነ ፉክክርን ከሕይወታችን ውስጥ ለማስወገድ አሁን የተሻለው ጊዜ ነው። በባልና ሚስት መካከል የሚኖር አላስፈላጊ ፉክክር መዳረሻው ቤተሰብን መበተን ሆኖ ይገኛል። ከጎረቤት ጋር የሚኖረው ፉክክር የጉርብትናን ማህበራዊ እሴት የሚጎዳ ሆኖ ዓመታትን በሚዘልቅ ቂም ውስጥ እንዲኖር ምክንያት ይሆናል። በሥራ ቦታችንም ሆነ በቤተ-አምልኳችን ወዘተ የሚገጥመን ፉክክር የሕይወታችንን ውድ የሆኑ ቀኖችን መልስ ይወስናል።
ተፎካካሪዎቻችን እንደሆኑ የምናስባቸው ወይንም የገባንበት ፉክክር በሕይወታችን ውስጥ ያለውን መስመር የመወሰን አቅሙን መግራት እንድንችል እንደ አንድ ኃይል እንድናያቸው አስቀድመን ተመለከትን።
በዱከም መንገድ ላይ ጎጆውን ቀይሶ የነበረው ሰው ወደ ጎዳና ከመውጣቱ በፊት የገጠመው ችግር ምን ነበር? ጤናማ ያልሆነ ፉክክር ምን ያህልስ ድርሻ ነበረው? በግል ሕይወታችን የምናየው የፉክክር ጉዞስ ምን ዓይነት እንድምታ እንዳለው መርምረን እናውቃለን? በሰላም መኖር የሚገባንን ህይወታችንን ከመረብሽ አንጻርስ የፉክክር ድርሻውን እንዴት እንመዝናለን?
2. አቅራቢዎቻችን
ዛሬያችንን ለመወሰን ከሚታትሩት ኃይሎች መካከል ሌላኛው አቅራቢዎቻችን ናቸው። አቅርቦትን በማምጣት ረገድ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች በሕይወታችን ውስጥ አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ተጽእኖን ፈጣሪ ሆነው በመንገዳችን ላይ አሉ። ልጆች ከአባትና እናት አቅርቦትን ይቀበላሉ። እናትና አባት በልጆች መንገድ ላይ የሚኖራቸው ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑ ለውይይት የሚቀርብ አይደለም።
ተፈጥሯዊ ኃላፊነት ካላቸው እናትና አባት ባሻገር በሥራ ግንኙነት፣ በጉርብትና እና በሌሎችም መንገዶች የሚገጥሙን አቅራቢዎች አሉ። መታየት ያለበት ነገር አቅራቢዎቻችን በምን ልብ የሚያስፈልጉንን እያቀረቡልን መሆኑ ላይ ነው። በፈረንጆቹ ዘንድ ነፃ የሚባል ነገር የለም። ሁሉም አቅራቢ ስለሆነ ጥቅሙ ነው የሚል እሳቤ አላቸው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ማህበራዊ ወረት ብዙ ምስቅልቅልን እየሸፈነ በሚያልፍበት ሁኔታ ውስጥ ነፃ የሚባል ነገር የለም ብለን ብንነሳ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ልንደርስ እንችላለን። እኛ ኢትዮጵያውያን እየኖርን ያለነው በማህበራዊ ወረት ውስጥ ባለ የአምላክ ጸጋ መሆኑን የሚያወሱት ተጨባጭ እውነታዎች ስላሉን።
ከመወለድ ቀጥሎ የአቅራቢነት ግንኙነት የሚገኘው በትዳር ግንኙነት ውስጥ ነው። ጾታዊ ግንኙነትን መነሻ የሚያደርጉ ሁሉም ዓይነት ማለትም የእጮኝነትም ሆነ የትዳር ግንኙነቶች ውስጥ ከሚ ፈጠሩ ቀውሶች በስተጀርባ የአቅ ራቢውና የአቅራቢው ተቀባይ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚገኝ ልብ ይገኝበታል። አንዱ ወገን ለጊዜያዊ ጥቅም ብሎ ሲቀርብ ሌላኛው ረጅምን ጉዞ የሚያስብ ይሆንና ወደ መለያየት ሲመጣ ሕይወትን የሚያሳጣም ሆኖ ይስተዋላል። ሕይወትን ከማሳጣትም ባሻገር ለመናገር በሚሰቀጥጥ ሁኔታ አካላዊ ጥቃት ሲደርስ ይሰማል። በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ካሉት ጾታዊ ጥቃት ባሻገር በአሰቃቂ ሁኔታ እጮኛን ሆነ የትዳር አጋርን የመግደል ወንጀልን በጥሞና መመርመር ቢቻል ብዙ ትምህርት የሚሆኑ ነገሮች እንደሚገኝባቸው ይታመናል።
አቅራቢዎች ያላቸውን ኃይል መሆን ባለበት መጠን እንዲሆን በማድረግ የሕይወት ጉዟችንን በፍሬ ለማስኬድ ማሰብ ያስፈልጋል። ዛሬ በሕይወታችን ውስጥ የሚያስፈልገንን የሚያቀርቡልን ሰዎች ጋር የልብ አንድነታችን ምን ያህል ነው? ልባችን በአንድ ላይ ሳይሆን ስለምንቀበለው አቅርቦት ብቻ ብለን ወደፊት እያስኬድነው ያለነው ህይወት እንዴት እንደሚቆም አስበንስ እናውቃለን? በአንድ አቅራቢ ላይ የተንጠለጠለው ሕይወታችን ከአቅራቢው ጋር ያለው ግንኙነት መስመር ቢስት ሕይወትን እንዴት ለመምራት እናስባለን? ሌሎች የበረከቱ ጥያቄዎችን እያነሳን ራሳችንን መፈተሽ እንችላለን። መዘንጋት የሌለበት እውነት ግን አቅራቢዎች በህይወታችን ውስጥ ያላቸውን ኃይል ነው። የኃይል አጠቃቀማቸው በአውንታዊነት ሚዛን የሚደፋ እንዲሆን ማድረግ ግን ይገባል።
በመሆኑም አቅራቢዎቻችን በሕይወት መንገዳችን ላይ ያለውን ተጽእኗቸውን መመርመር በዙሪያችን ያሉትን ኃይሎች በሚገባ ተረድተን ሚዛኑን እንድንጠብቅ በብርቱ ያግዘናል። የፕሮፌሰር ማይክል ፖርተር የአቅራቢዎች እይታ በቀጥታ ለሚሠራው ሥራ ግብአትን የሚያቀርቡት የሚኖራቸውን ተጽእኖ የተመለከተ ቢሆንም ለእኛ እንዲመቸን አድርገን ቃኝተነዋል።
አባታችን፣ እናታቻን፣ ወንድማችን፣ እህታችን፣ አጎታችን፣ አክስታቻን፣ ጎደኛችን፣ ጎረቤታችን፣ አሠሪያችን፣ ወዘተ እነርሱ ለእኛ እኛም ለእነርሱ የምናደርገው ነገር አለ። በሕይወታችን ያላቸው አስተዋፅ ከፍተኛ ቢሆንም ሕይወትን በአቅራቢዎቻችን ላይ ሙሉ ለሙሉ ተደግፎ መምራት ግን ዘለቄታዊ መፍትሔ አይደለም። በተቻለው መንገድ ራስን እየቻሉ መሄድ አስፋላጊ ነው። ራስንን መቻል በገንዘብ ብቻ አይደለም። ራስን መቻል ራስን መምራት በመቻልም ነው። ራስን መቻል በፈተና ውስጥ ተቋቁሞ መውጣት አቅምን በመገንባትም ነው። ራስን መቻል ጥራት ያላቸውን ውሳኔዎች በራስ ወደ መወሰን አቅም በመምጣትም ነው።
አቅራቢዎቻችን በህይወታችን ውስጥ ያላቸው ተጽእኖ ሁልጊዜ እነርሱ የሚወስኑልን፣ ሁልጊዜ እነርሱ የእኛን ሥራ የሚሠሩልን፣ ሁልጊዜ እነርሱ የእኛ ወኪል ሆነው የሚገኙበት ወዘተ ሲሆን፤ በራሳችን መቆም የማንችል እንሆንና እነርሱን ባጣን ጊዜ ሕይወት ቀለሟ ተቀይሮ ለዓይናችን የማይስማማ ለልባችንም የማይሆን ይሆናል።
በመንገዳችን ላይ ካሉት ኃይሎች መካከል አንዱ አቅራቢዎች ናቸውና እንዴት በሕይወታችን ውስጥ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው የታሰበበት መስመር ያስፈልጋቸዋል።
በዩኒቨርሲቲ መገኘት ከባድ በሚባልበት ወቅት ላይ ለዩኒቨርሲቲ የበቃው የምህንድስና ሰው የጉልምስና ወራቱን እያገባደደ ባለበት ዕድሜው ላይ እንዴት ለጎዳና ሊበቃ ቻለ? የአቅራቢዎች ተጽእኖስ ምን ያህል ይሆን? ዛሬ አቅራቢያችን የሆኑ ነገ የሕይወታችን መመሰቃቀል ምክንያት እንዳይሆኑ ምን ያህል በውስጣችን አድገናል?
3. ደንበኛችን
“ደንበኛ ንጉሥ ነው” የሚለው ቃልን ከለመድነው ሰነበትን። ደንበኛ የገቢ ምንጭ ስለሆነ አባባሉ ደንበኛ ሁሉም ነገር ነው ለማለትም የዳዳው ይመስላል። በእኛ አውድ ንጉሥ ማለት ሁሉም ነገር ነው የሚለው እንድምታ ከፍ ያለ ስለሆነ።
በሕይወት ጉዟችን ውስጥ የእኛን አገልግሎት ወይንም የእኛን ሥራ የሚፈልጉ አሉ። እነርሱ ሌላኛው በሕይወታችን ላይ ተጽእኖን የሚፈጥሩ ኃይሎች ናቸው።
ከእውቅና በፊት ፍሬያማ የሆነ ኑሮን መኖር የሚችሉ ነገር ግን በእውቅና ምክንያት የሚጠፉ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ምን እንማራለን? በሥራችን ወደ እኛ የተሳቡ አድናቂዎቻችን የሆኑ ወደ ኋላ እንዲመልሱን ምክንያት መሆን እንዴት እንፈቅዳለን?
ደንበኞችን እንደ ንግዱ በቀጥታ ትርጉሙ ባንወስድም የእኛን ሃሳብ፣ እይታ፣ አገልግሎት ወዘተ የሚፈልጉ ሰዎች የሕይወት ጉዞ ላይ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መንገድ ተጽእኖቸውን ማሳረፍ የሚችሉ መሆናቸውን መረዳት ተገቢ ነው።
አድናቂዎቻችን ቁጥራቸው ይቀንሳል ብለው እሴትን መጣል አለ። የምንመራቸው ሰዎች አግባብነት የሌለው ጩኸት የተነሳንበትን እንዲያስጥለን መፍቀድም የተገባ አይደለም። ይህን ማድረግ በጀመርን ጊዜ ጣዖት ወደ መሥራት እንገባለን። በዙሪያችን ያሉትን ወደ መሥራት፤ እኛ ልንሠራው የተገባውን ሳይሆን።
በሕይወት ጉዞህ ውስጥ እንደ ግለሰብ የምትኖርለት ጥሪ ያስፈልጋል። ጥሪህን ለመኖር ስትነሳ የሚገጥሙህን ፈተናዎች እየተከላከልክ ለመጓዝ ዝግጁ መሆን አለብህ። ከዚህም መካከል አንዱ በዙሪያችን ያሉ የሚከተሉን፣ የሚያደንቁን በአጭሩ የእኛን አገልግሎት ውይንም ምርት የሚጠቀሙ ናቸው። እነርሱ ከእኛ እንዳይሄዱ እንደ ንግድ የምንሠራ ከሆነ ኃይላቸው በቀጥታ የሕይወታችንን ጉዞ ይነካዋል።
ሙሴን ባጡት ጊዜ አሮንን ጣዖት ያሠሩት እስራኤላውያን የደረሰባቸው ኪሳራ በተለያየ መልኩ ዛሬም ያጋጥማል። በብዙ የሚመነዘር አቅም ያላቸው ሰዎች በትንሹ ተቀጭተው እንዲቀሩ ሆነዋል። ልንኖርለት በሚገባው መንገድ ላይ እየተራመድን ያገኘናቸው ወደ ራሳቸው መንገድ አስገብተው ከመስመር አስወጥተውን ራሳችንን ማየት እጅግ መክሰር ነው።
ዛሬ በዙሪያችን ያሉትን ኃይሎች እየመረመርን ነገሮችን በሚዛኑ እንድናደርግ እያየን። ተፎካካሪዎች፣ አቅራቢዎቻችን እና ደንበኞቻችን ቀዳሚዎቹ ሆኑ። በሚቀጥለው ሣምንት ቀሪ ሁለቶችን እንመለከታለን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2013