አብርሃም ተወልደ
በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ በመመስረት በሀገራችን ዝናብን ከቁልል ደመና ለማዘነብ የተሞከረ ስለመሆኑ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትራችን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል። ይህን ተከትሎም በመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል። በርከት ባሌ ሌሎች ሀገሮች እየተሰራበት ያለውን ይሄን ቴክኖሎጂ ሀገራችን ወደመጠቀም መግባት መጀመሯም ለኢትዮጵያውያን ታላቅ የምስራች ነው።
የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ ይህ የምስራች የማህበራዊ ድረገጽ ሰራዊቱን /ፌስቡከኛውን/ ጎርብጦታል፤ መሳለቅ ውስጥ ለመግባት ብዙም ጊዜም አልወሰደበትም፤ ብቻ ሲሳሰለቅ ሰንበተ። ለነገሩ ጊዜ የሚወሰደው አላምጦ ለሚውጥ ነው፤ ግርድፉን ለሚሰለቀጥ ጊዜ አያስፈልግም። በፌስቡከኛው እየሆነ ያለውም ይሄው ነው።
ቴክኖሎጂው አዲስ የሆነው በኢትዮጵያ መተግበር መጀመሩ ላይ ነው፤ ምንነቱም ቴክኖሎጂው በሌሎች አገሮች አስቀድሞ በሚገባ ይታወቃል። እናም በሌሎች ሀገሮች የተሰራበት ይህ ቴክኖሎጂ ነው ወደ ሀገራችን እንደሚጣና ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሰራ ያለው። ንድፈ ሀሳቡም አይደለም አሁን ሀገር ውስጥ እንዲመጣ የተደረገው። ሀገራችን በቴክኖሎጂው በመጠቀም የሙከራ ስራዋ በሰሜን ሸዋና ጎጃም አካባቢ ዝናብ ለማዘነብ ሙከራ አድርጋ ተሳክቶላታል።
ቴክኖሎጂው ለእኛ ሩቅ ሆኖ ይቆይ እንጂ ከ1960ቹ ጀምሮ እንደሚታወቅ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሄ ጋዜጣ በቅርቡ በ“አዲስ ዘመን ዱሮ” አምዱ፤ አዲስ ዘመን በ1960ዎቹ እትሙ አስነብቦ ከነበራቸው ዘገባዎች አንዱ ይሄንኑ ቴክኖሎጂ የተመለከተ ነበር። ጋዜጣው በሀምሌ 16 ቀን 1962 እትሙ “ዝናብን ማዘነብ ተቻለ” በሚል ይዞት በወጣው ዘገባ በሶቪየት ህብረት በተለይ በሌንግራንድ ከተማ የሚገኘው የጂኦ ፊዚካል ላቦራቶሪ ሰው ሰራሽ ዝናብ ሊገኝ የሚችልበትን ዘዴ በምርምር ማግኘቱን ይፋ ማድረጉን ጠቁሟል።
የምርምሩ ውጤት የሆነው ሰው ሰራሽ ዝናብ በጆርጂያ በሞዲቪያና በማዕከላዊ እስያ ግዛቶች ውስጥ ተሞክሮ አጥጋቢ ውጤት ማሳየቱንም የኤንፒ ኤን የወሬ ምንጭን ዋቢ በማድረግ ተዘግቧል ። በአንዳንድ የእርሻ ስፍራዎች እና በመሳሰሉት ክፍሎች ዝናብ በተፈለገ ጊዜ እንዲጥል ለማድረግ ለዚሁ አላማ የተዘጋጀ የተቀመመ ፈንጂ ስራ ላይ ይውል እንደነበርም አስነብቧል። ፈንጂው በአየር ላይ ሲለቀቅ የእርጥበት ቅንጣቶችን እየሰበሰበ ዝናብ ወለድ ደመናዎችን በመፍጠር የተፈለገውን ዝናብ ያስገኛል።
ቴክኖሎጂው ከአመታት በፊት ቻይና የኤሮ ስፔስ እና ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽኗ በኩል ወደ አስር ቢሊዮን ቶን ዝናብ ሊያስጥል/ሊያስዘመን የሚችል 10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ስኬዌር ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ የኬሚካል ፈርነሶች አለምን ጉድ ሊያስብ በሚችል መልኩ ገንብታለች። ይህ ፕሮጀክትም የቲቤታን ፕላትዩ አካባቢዎችን በዝናብ ለማረስረስ የታለመ ነው።
ቻይና በበጂንግ ኦሎምፒክ ወቅት አስፈሪ የነበረ ደመናን በእዚህ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በትና ወደ ዝናብ በመቀየር ስጋቱን አስቀርታለች። ይህ ደግሞ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው። እስራኤልም ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በረሃማ አካባቢዎቿን ለማልማት ተንቀሳቅሳለች።
ታዲያ ይህን ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ አምጥቶ ሞክሮ ማሳየት ችግሩ ምን ላይ ነው? በእዚህ መሳለቅ ለምን አስፈለገ። ለነገሩ ቴክኖሎጂው ላይ አይደለም ጉዳያቸው። ወዲህ ነው። እሱስ ቢሆን ወተቷን እየማጉ ላሚቷ ላይ እንደመዶለት አይቆጠርምን? ፌስቡከኞቹ ጨዋታ አልቆባቸዋል መሰለኝ። ያንኑ የጥላቻ አጀንዳቸውን ያሳለጡ መስሏቸው ነው አጉል ቦታ ገብተው የቀለሉት።
አጃቢ የሚያገኙ መስሏቸውም በዚህ ዘመን በሰው ሰራሽ መንገድ ዝናብ እንዲጥል ማድረግን ፈጣሪን እንደ መፈታተን አድርገው ቆጠሩት። በርካታ ሀገሮች እየተጠቀሙበት ያለውን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም መሞከር እንዴት ወደዚህ ድምዳሜ ያደርሳል?
ዳግማዊ አጼ ምንሊክ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገሪቱ ሲያስመጡ ‹‹የሰይጣን ስራ›› እያሉ ብዙዎች ቢያቃልሉም/ ከዘመኑ ንቃተ ህሊና አኳያ እነሱ ላይ አይፈረድም/ ቴክኖሎጂዎቹ ከመተግበር አልቀሩም። እሳቸውም ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገሪቱ በማስመጣት መጠቀሳቸው ቀጥሏል።
ስንቱን አሉባልታ እየጎለጎሉ የሚያወጡት ፌስ ቡከኛቹ፣ ቴክኖሎጂ ላይ ብዙም አላሉም። ምክንያቱ ደግሞ ጉዳያቸው ቴክኖሎጂው ላይ ሳይሆን ቴክኖሎጂው እንዲተገበር ባደረገው ላይ ነው። መቼም ቢህን በአንድ ትልቅ ስራ ውስጥ የሚጠቀስ አንድ ትልቅ ሰው እንደሚኖር አጥተውት አይደለም፤ ይሄን ማየት አሟቸው እንጂ።
“ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” እንደሚባለው፣ አሁንም አላማቸው ያው ኢትዮጵያን ማዳከም ነው። አለም በዚህ ቴክኖሎጂ ታምር እየሰራ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂውን ማሰቧን ለዚያውም በዚህ ዘመን ከመንፈሳዊ ጉዳይ ጋር እያያያዙ ማብጠልጠል ተከታይ አገኛለሁ ፤በዚህ ደግሞ አንድ ሰሞን አምሳለሁ የሚል መነሻ ቢኖራቸው ነው።
እንደሚታወቀው ፌስቡከኞች ቆም ብለው አስበው አይሰሩም። የኛዎቹ ፌስቡከኞች ደግሞ ይብሳሉ ፤ የሴረኞች መሳሪያ ናቸው፤ የተጠለፉና የተተበተቡ የማጥላላት ዘመቻ ሰራዊት ናቸው። ይህ ባይሆን ለሀገር ይጠቅማል ተብሎ እየተሰራበት ያለን ተግባር ይዞ የመጣን ማጥላላት ውስጥ ባልገቡ ነበር።
አሉባልታን መጎልጎል ስራቸው የሆነው ፌስቡከኞች፣ ስንት የሚጎለጎል ጥሩ ነገር እያለ በጥቂቶች የሴራ ወጥመድ ውስጥ ገብተው እየተንደፋደፉ ናቸው። ሆኖም ክፉውንም ደጉንም መቀበልና ማቀበል ድንቁርና ሊባል እንጂ ሌላ ስም አይሰጠውም።
በደነዘዘ ትውልድ ፌስቡክ እና የዩቱዩብ ጦረተኛ በፈዘዘ ዓለም እንደ “ንቃት” ያለ የሚያስቀጣ የለም፤ በሀገራችን በሰው ሰራሽ ዘዴ ዝናብ ማዝነብ መቻል አንድ ትልቅ እርምጃ ነው። ለነገሩ በአንቀላፋ ትውልድ ውስጥ መንቃት ልክ የማይሆንበት ሁኔታ አለ ።
ወዳጄ! ሁሉንም ማወቅ አይጠበቅብህም ስለዚህም የማታውቀውን ጉዳይ ሰዎች ሲያነሱ/ በማህበራዊ ድረ ገጽም ይሁን በሌላ/ መረጃው ከሌለህ ዝም ማለት መልካም ነው። ካልገባህም ነገሮችን በአርምሞ ተመልክት ፤ ለማድመጥ የፈጠንክ ለመናገር ግን የዘገየህ መሆን ይገባሃል። ለመቀበልም ለማቀበልም እንዲሁ። ይህ ደግሞ ማትረፊያ እውነት ነው! ምክንያቱም ጉዳዩን አታውቀውማ !
በየማህበራዊ ሚዲያ የሚጮኸው ሁሉ ባለማወቅ የተነሳ የሚጮሀ ነው። አየህ ባሻዬ! “ዝምታ” ሰው በኀይል ጮኾ ከሚገልጸው የበለጠ የልብህን ሀሳብ በግልጽ የሚያሳይበት ጊዜ አለ። እየጮኸ የሚሳደብን ሰው በዝምታ ማለፍ ለተሳዳቢው ትልቅ መልዕክት ያስተላልፋል።
ስድብን ፣ትችትን፣ ነቀፌታን የሚያበዙ ሰዎችን የጀርባ ታሪክ ማጤን አይከፋም፤ከዚያ ውጪ ግን ስድብን በስድብ ከመመለስ ይልቅ ማስገንዘብ አልያም በዝምታ ማለፍ ይገባል። ይህም ለዚያ “ግልብ” ሆድ አደር “እንደ አንተ ከአፌ ክፉ ቃል አይወጣም፤በዚህ ማንነቴን አሳይሃለሁ፤ራሴንም መቆጣጠር እችላለሁ።” የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ይቻላል። ተሳዳቢ መረጃ የሌለው ዘባራቂ ነው። እኔ ይህን አስገነዝባለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና መንግስታቸውን መደገፍ አለመደገፍ ሌላ ጉዳይ ነው፤ ዓለም ከዓመታት በፊት ሞክሮ እየተጠቀመበት ያለውን ቴክኖሎጂ እየሞከርን ነው ሲሉ ግን በርቱ እንደማለት የምታጣጥል ከሆነ ሁዋላ ቀርነትህንና አሳፋሪነትህን ያመለክታል፤አሁንም ድንቁርና ላይ መሆንህን ያሳያል ። የሚጠቅምና የማይጠቅመውን ሳይለዩ የተወረወረን ሁሉ መቀበልና ማቀበል ድንቁርና ነው። ዝምታም ብልሃት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2013