(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
በቅርቡ በአብሮ አደግ እህቴ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝቼ ነበር። ይህቺን በእጅጉ የምወዳትና የማከብራትን ጓደኛዬን የሞት መልአክ የላከባት ይህ ኮቪድ 19 ይሉት ክፉ ወረርሽኝ ነው። የሳቂታዋና የፍልቅልቋ እህታችን ድንገተኛ ህልፈተ ሕይወት እኔን ራሴን ጨምሮ በርካታ ቤተሰቦቿንና ወዳጆቿን ድንጋጤ ላይ ጥሎ እህህ ያሰኘን ለወራት ያህል ነበር። አሁንም ቢሆን በድንገተኛ አሟሟቷ ግርታ ላይ የወደቀው ቤተሰቧ ገና ወደ ሙሉ መጽናናት ደረጃ ላይ አልደረሰም።
ይህ ክፉ ወረርሽኝ የብዙ ኢትዮጵያዊያንን ቤትና ኑሮ አንኳኩቶ በመግባት ምን ያህሉን ወገን የኀዘን ማቅ እንዳለበሰ፣ በርካቶችንም የኀዘን ፍራሽ ላይ እንዳስቀመጠ የገፍ መርዶውን እየሰማንና እያስተዋልን ስለሆነ ለብዙዎቻችን እንግዳ ክስተት እንዳይደለ ይገባኛል። በሐኪሞቻችን ያላሰለሰ ርብርብና በፈጣሪ ተራዳኢነት በሽታው አማቋቸውና አሰቃይቷቸው “በሽልም የወጡ” ዕድለኞች ፈቃደኞች ቢሆኑና “የሞት ደርሶ መልስ” ተሞክሯቸውን በይፋ በሚዲያ ቀርበው ቢያካፍሉን ምንኛ በባነንን ነበር ብዬ ማሰቤ አልቀረም።
ብዙዎቻችን ከጥንቃቄ እየተዘናጋን በምናሳየው ቸልተኝነትና ዳተኝነት ውጤቱ ገና የሚጠበቀውን ያህል እየተገለጠ አይደልም። ዳፋው በምልዓት ይፋ በሚሆንበት ወቅት ምን ሊከሰት እንደሚችል የእንቆቅልሹ ውስብስብነት በግሌ “ድፍን ዕንቁላል” እንደሆነብኝ አለ። ወረርሽኙ ከትናንት ይልቅ ዛሬ እየተስፋፋ በመሄድ ላይ መሆኑ እየታወቀ ዜጎች ግን በድንዛዜ ውስጥ ወድቀንና ችላ ብለን ስንዘናጋ ማስተዋሉ በራሱ የመርግ ያህል ይከብዳል። ይህንን መሰሉን አሳራችንን “ምከረው ምከረው፤ እምቢ ያለ እንደሆነ መከራ ይምከረው” እየተባለ ብቻ በቸልታ የሚታለፍ ጉዳይ ሳይሆን ርብርቡ በንቃትና በትጋት መከወን እንዳለበት ደግሞ ደጋግሞ ያለማሰለስ ማሳሰቡና ማስተማሩ አግባብም ተገቢም ይመስለኛል። “አይበቃም ወይ መፋዘዙ” ብላ ያንጎራጎረችው የሀገራችን ድምፃዊት ለካንስ ቢቸግራት ነው ያሰኛል።
ከላይ በጠቀስኩት የውድ ጓደኛዬ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ለቀብር የተሰባሰበውን ሕዝብ ያጽናኑት መንፈሳዊ አባት ያስተማሩት ትምህርትና የከወኑት አንድ ሃይማኖታዊ ልምምድ ይህንን ጽሑፍ እንድጽፍ በእጅጉ ምክንያት ሆኖኛል። የአስከሬኗ ግባተ መሬት በሃይማኖታዊ ወግና ሥርዓት ያስፈጸሙት እኒያ አገልጋይ አባት ለሦስት ያህል ጊዜያት እፍኝ አፈር እየዘገኑ “አፈር ነሽና ወደ አፈር ትመለሻለሽ!” በማለት ካሳረጉ በኋላ፤ በማስከተልም ኀዘንተኛውን ያጽናኑትና ያስተማሩት እጅግ ልብ ውስጥ ጠልቆ የሚገባ ትምህርት በመስጠት ነበር። መልዕክታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ ከተለመደው አካሄድ ወጣ ያለ ጥያቄ እንዲህ ሲሉ ጠየቁ፤ “የተከበራችሁ ኀዘንተኞች ለአንድ አፍታ ያህል በዙሪያችሁ ያሉትን የሙታን ሐውልቶች ዞር ዞር እያላችሁ እንድትመለከቱ ጥቂት ጊዜ እሰጣችኋለሁ።”
የተሰበሰበው ሕዝብ በግርታ ውስጥ እንዳለ የመምህሩን ትዕዛዝ ለመፈጸም ግራና ቀኝ፣ ፊትና ኋላ እየተዟዟረ ሐውልቶቹን እየተመለካከት ሳለ አጨብጭበው ቀልባችንን እንድንሰበስብ ካደረጉ በኋላ የሚከተለውን ንግግር ማድረግ ጀመሩ። “ዙሪያችንን በከበቡን ሐውልቶች ስር በድናቸው ያረፈው ሙታን በአንድ ወቅት አንቱ፣ የተከበሩ፣ እመቤቴ፣ ወይዘሮ፣ አቶ፣ ዶ/ር፣ ሳይንቲስት፣ መምህር፣ ደራሲ፣ ነጋዴ ወዘተ. እየተባሉ የክብር ቦታና አክብሮት ይሰጣቸው የነበሩ ታላላቅ የሀገር ጌጦች፣ የወገን አለኝታዎች ነበሩ። አንዳንዶችም በለጋ ዕድሜያቸው የተቀጩ ሕፃናት ነበሩ። አረጋዊያንና ዕድሜ ጠገቦችም አሉበት። መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ሃይማኖተኞች፣ ፈላስፋዎች፣ አዋቂዎች፣ ደጋጎች፣ ጨካኞች፣ ሩህሩሆች ስንቱ ተቆጥሮ ይዘለቃል። መገለጫቸው ዝንጉርጉር፣ ዓይነታቸውም ይህ ቀረሽ የማይባል ነው። ዛሬ ሁሉም በድን ሆነው ከመቃብር በታች በመዋል አስከሬን ተብለዋል። አንቱነት ወደ አንተነት፣ እርስዎነት ወደ ሟችነት ተለውጦ ሁሉም አፈር ተጭኗቸው ድንጋይ ተንተርሰዋል። ስለምን ቢባል ከአፈር ተፈጥረው ወደ አፈር መመለስ የማይጋፉት የፈጣሪ ትዕዛዝ ስለሆነ ብቻ ነው።”
“በዚህች አጭር ሕይወታችን በሰላም ኖረን በሰላም ብናልፍ ምን ነበረበት? በመልካም ተግባራችን ታውቀን ብንኖርስ ምን ክፋት አለው? ብንስማማ፣ ብንከባበር፣ ለወገንና ለሀገር በጎ ሠርተን ብናልፍ ምን ነበረበት? ባንጨካከን፣ ባንገዳደል፣ ባንቋሰል፣ በቋንቋ፣ በብሔርና በኃላፊው ማንነታችን ባንጨራረስ ምን አለበት?”
“ወገኖቼ ስሙኝ!? እያንዳንዳችን የክብደታችን ልክ ስንት ኪሎ እንደሆነ የምናውቅ ይመስለኛል። የአንዳንዶቻችን የኪሎ ክብደት ሃምሳ፣ ስልሳ፣ ሰማንያ፣ ዘጠና ወይም ከዚያ በላይ ወይም በታች ሊሆን ይችላል። የኪሏችን መጠን ምንም ይሁን ምን የተሸከምነው ሃምሳ፣ ስድሳ፣ ሰማንያና ዘጠና ኪሎ አፈር መሆኑን አንርሳ። ለዚህም ነው እንዲህ እንደ እህታችን በዕለተ ሞታችን ስንብታችን ሲፈጸም ‘አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ’ እያልን የምንሸኘው።” የካህኑ ምክርና ትምህርት በርግጠኝነት አንድ ዳጎስ ያለ የመጽሐፍ ጥራዝ ሊወጣው የሚችል ይዘት ያለው ነበር። እኒህን መሰል መምህራንና ካህናትን ያብዛልን።
ምሥጢረ አፈርና እኛ ቋሚዎች፤
“አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” የሚለው የካህኑ ትምህርትና “ሁላችንም በኪሏችን ልክ ተሸክመን የምንዞረው የአፈር ክምር ነው” የሚለው ፍልስፍናቸውን ከሰማሁበት ዕለት ጀምሮ ዕረፍት ላገኝ ስላልቻልኩ አዕምሮዬ የስንግ ተይዞ መፈናፈኛ ማጣቴን አልሸሽግም። ምነው ይህ እውነት ለሁሉም ሰው በተገለጠ በማለትም መመኘቴ አልቀረም።
እጅግም ጊዜ ሳልወስድ በነፍሴ ውስጥ የሚያቃጭለው የካህኑ ፍልስፍና ጠርቶ እንዲገለጽልኝ በማሰብ ወደ አንድ ወዳጄ ዘንድ ስልክ በመደውል ቀጠሮ ያዝኩኝ። ይህ ወዳጄ በአፈር ምርምር ዘርፍ ሀገሪቱ ካፈራቻቸው ጥቂት ልጆቿ መካከል አንዱና አንቱታ ያተረፈ የዘርፉ ፕሮፌሰር ነው። ለእኔው የእንቆቅልሽ ጥያቄና ግርታ መልስ ለመስጠት እርሱ ራሱ ምሳ ጋብዞ “እህ ለምን የሞት ቀጠሮ ነው ብለህ ፈለግኸኝ?” በሚል የመንደርደሪያ ጥያቄ ፈጥነን ወደ ውይይታችን እንድንገባ በሩን ወለል አድርጎ ከፈተልኝ። ወይይት ከማለት ይልቅ ጥያቄና መልስ ነበር ማለቱ ይቀላል። እኔ እጠይቃለሁ፤ እርሱ ይመልሳል።
“በሀገራችን ያሉት የአፈር ዓይነቶች ስንት ናቸው?” የመጀመሪያው ጥያቄዬ ነበር። “አሥራ ስምንት ወይንም አሥራ ዘጠኝ ቢሆኑ ነው” ከብዛቱ ቁጥር ጋር ቀለል ያለ ማብራሪያ በማከል ለጥያቄዬ መልስ ሰጠኝ። “የአፈር ዓይነቶቹ ይዘትና ባህርያትስ ምን ይመስላል?” ሁለተኛውን ጥያቄዬን አስከተልኩ። ጥሩ ተመራማሪ ብቻም ሳይሆን ጥሩ መምህርም ስለሆነ በቀላሉ ሊገባኝ በሚችል አቀራረብ እየተነተነ አስረዳኝ።
“ሳይንሳዊው ገለጻ ለጊዜው ስለማያስፈልግህ በቀላሉ እንዲገባህ በተራ ቋንቋ ላስረዳህ። አንዳንዱ አፈር የዳበረ፣ አንዳንዱም ጭንጫ፣ አንዳንዱ የደለል አፈር፣ አንዳንዱ አሲዳማ (Acidic soil የሚባለው ይሆን ይሆን ብዬ ፈገግ አስደረግኹት።) አለማወቄን አላዳነቀም። ይህን ገለጻ በሚገባህ ዘዴ ላስረዳህ ሞከርኩ እንጂ ዝርዝሩና ትንታኔው እጅግ የረቀቀ ነው። አሁን ለምሳሌ፤ sandy soil, clay soil, silt soil, peat soil, chalk soil, loam soil ወዘተ. እያልኩ ዓይነቱንና ባህርያቱን ብዘረዝርልህ ምን ይጠቅምሃል?” ከዚህ በላይ መሄድ ስላላስፈለገኝ ወዳጄን አመስግኜ ከተለያየሁ በኋላ ፈጥኜ ወደ ቤቴ በመመለስ የማጥኛ ክፍሌን ዘግቼ በግል ፍልስፍናዬ መወዛወዝ ጀመርሁ።
የኪሎው ምጣኔ ምንም ይሁን ምን ተሸክመን የምንንቀሳቀሰው ሥጋ ለካንስ የአፈር ቁልል ኩይሳ ነው። ለዚህም ነው እንደ መጽሐፉ ቃልና እንደ ካህኑ ትምህርት ይህንን ዓለም ስንሰናበት እንደየእምነታችን “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” በሚል መሰናበቻ ወደተፈጠርንበት አፈር የምንቀላቀለው። እርግጥ ነው አንዳንዱ የተሸከመው የአፈር ቁልል “ሰብዕናው” ለም አፈር ሆኖ ብዙ አዝመራ አዝምሮበት ሊሆን ይችላል። የአንዳንዱም አፈር “አሲዳማ” ይሉት ዓይነት ሆኖ ሁሌም የሚኖረው ለራሱ ብቻ፣ ለነፍሱ እርካታ ብቻ መሆኑ ምክንያቱ ይሄው ነው።
በልጅነት ዕድሜያችን “በቃኝ” ማለት ተስኖን “ደግመን ደጋግመን አልጠገብኩም!” እያልን ወላጆቻችንን ስናስጨንቅ “የምን አሲዳማነት ነው?” እያሉ የሚገስጹን ለካንስ “አሲዳም” ማለት አልጠግብ ባይነትን የሚወክል ኖሯል። ይህን መሰሉ ልምምድ የአሲዳማነት መገለጫና የተሸከምነው አፈራችን ውጤት ነው። በሀገርና በሕዝብ ላይ “አሲዳምነት” የተገለጠባቸውን በርካታ የቅርብና የሩቅ ታሪኮቻችንን ብንዘረዝር ብዙ የሞራል ትምህርቶችን መሰነቅ ይቻላል። የዘርፉ ባለሙያዎች አንዳንድ የአፈር ዓይነት ቢታከም የተሻለ ፍሬ ሊያፈራ ይችላል ማለታቸውም ትዝ ሲለኝ መገረሜ አልቀረም። ለካንስ አሲዳማ አፈር ቢታከም ይፈወሳል። ለማዳበሪያ የሚውል አፈር ከውጭ ሀገራት እየተገዛ መምጣቱም አጃኢብ ያሰኛል። ለካንስ “አፈርን የሚያዳብር አፈርም” አለ? የእኛም ሰብእና እንደዚያው ነው።
አንዳንዱ የተሸከመው የአፈር ቁልል ጎርፍ እንዳመጣው የደለል አፈር (silt soil) የተካበ እንጂ በተፈጥሮ የረጋ አፈር አይደለም። ይህን መሰሉን አፈር የተሸከሙ ስግብግቦች የሚያካብቱት ሀብትና ንብረት ወዛቸውን ጠብ አድርገው የሰበሰቡት ሳይሆን “የአጋጣሚ ጎርፍ ባመጣው ዘረፋ ደልበው” ያከማቹት ሊሆን ይቻላል።
አንዳንዱ የተሸከመው የአፈር ዓይነት በጠመኔ መስሪያ “chalk soil” ቢመሰል መራቀቅ አይሆንም። ጠመኔ የመምህር ዋነኛ መሳሪያ ነው። “ጠመኔ ትጥቁ!” በሚል ርዕስ የተጻፈ አንድ ግጥም ትዝ ይለኛል። ከዓመታት በኋላ ከደራሲው መምህር ከመስቀሉ ባልቻ ጋር ተዋውቀን ዛሬ ጥሩ ወዳጆች ለመሆን ችለናል። አንዳንዱ የተሠራበት አፈር ተራ አፈር ሳይሆን መልካም ታሪክ ተጽፎ በሚያልፍበት በጠመኔ በሚመሰል “የአፈር ስሪት” የተፈጠረ ሊሆን ይችላል። ፍልስፍናውን አራቀን እንተንትነው ብንል ስለዚሁ የአፈር ማንነታችን ብዙ ማለት ይቻላል።
ይሄንን ሃሳብ የሚያጎለብትልንን የቅዱስ መጽሐፍ አንድ ምሳሌ ማስታወሱ መልካም ይሆናል። ምሳሌው ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማረው የትምህርት ክፍል ነው። ታሪኩ በአጭሩ እንዲህ ይላል። “እነሆ ዘሬ ሊዘራ ወጣ። እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፣ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ አፈር በሌለበት ጭንጫ ላይ ወደቀ፤ መሬቱም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያውኑ በቀለ። ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥርም አልነበረውምና ደረቀ። በእሾህ መካከል ባለ አፈር ላይ የወደቀ ዘርም ነበር። በበቀለም ጊዜ እሾሁ አነቀው፤ በመልካም አፈር ላይ የወደቀው ዘርም ብዙ ፍሬ ሰጠ። አንዳንዱ መቶ፣ አንዳንዱ ስድሳ፣ አንዳንዱም ሠላሳ ፍሬ አፈራ። ጆሮ ያለው ይስማ!” (የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 13)።
እርግጥ ነው፤ ጆሮ ኖሮን ብንሰማ፣ ልቦና ኖሮን ብናስተውል ከተፈጥሯችንም ሆነ ከፍጥረታት ብዙ መማር እንችላለን። የተሸከምነው “አፈር” እያሳሳን ምን ያህል ጊዜ ሌሎችን በድለን በራሳችንም ላይ እንደፈረድን በጥሞና ብናሰላስል ኅሊናችን እውነቱን ሊያጫውተን ይችላል። ነፍሰ ሄር ብዙነሽ በቀለ ስለዚሁ ረጋፊ የሥጋ ማንነታችን ከግማሽ ክፈለ ዘመን በፊት ያንጎራጎረችውን አንድ የዜማ ግጥም ብናስታውስ ነገራችንን ያጎለብት ይመስለኛል።
አሸብርቆ ደምቆ እንደ ፀሐይ፣
ተውቦና አጊጦ የምናይ፤
የዛሬው ውብ ገላ [መልካችን]፣
ነገ የአፈር ቀለብ ነው ሥጋችን፣
ምንም ብንሳሳለት ብንንገበገብለት
ይፈርሳል በጊዜያቱ ሥጋ ነውና ከንቱ።
ትውልድና ዜጎችን በመልካም ባህርይ አቅንቶ የሚያርቀው ይህንን መሰሉ የግብረገብ ትምህርት መሆኑ ይታወቃል። ባለፉት ዓመታት ለዚህ መሠረታዊ ጉዳይ ትኩረት በመንፈግ ልጆቻችንን መረን ለቀን የማይመጥናቸውን “ነፃነት” እንዲያጣጥሙ በመፍቀዳችን ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለን እንዳለ ውጤቱን እያየን ነው። “ለዴሞክራሲ መብታቸው” ቅድሚያ እንዲሰጥ፤ “ለግለሰባዊና ቡድናዊ ግዴታቸው ይደርሱበታል” በሚል ቅኝት በተዘጋጁት የሥነ ዜጋና የሥነ ምግባር መማሪያ መጻሕፍት ልጆቻችንን ከአላባው ምርት ይልቅ ገለባውን ስለመገብናቸው ውጤቱ ከፍቶብን ቤተሰባችንና ማሕበረሰባችን በምን ያህል ቁዘማ ላይ እንዳለ የአደባባይ ምሥጠራችን ነው። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከላይ በጠቀስኩት የመማሪያ መጻሕፍት ዝግጅት ውስጥ ድርሻ ስለነበረው ችግሩን በሚገባ ያውቀዋል። ለተፈጸመው ሀገራዊ ስህተትም ሁሌም እንደተጸጸተ አለ።
የሆነው ሆኖ ዛሬም አልመሸም። ዛሬም ጊዜ አለ። በኪሏችንና በይዘቱ (nutrients) ልክ የተሸከምነው ፈራሽ አፈር ወደ መቃብር ከመሸኘቱ በፊት ቁምነገር ዘርተን ብናመርትበት በእጅጉ ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም። በሀገርና በሕዝብ ላይ ሴራ መሸረብ ዞሮ ዞሮ ጉሹን በጋራ ከመጎንጨት ነፃ ሊያወጣን አይችልም። የሚያምርብን በሰብእና ማሳችን ላይ የተንዠረገገና ሕዝብን የሚጠቅም ፍሬ አፍርቶ ለሌሎች መድኅን መሆን እንጂ “የሞት ድግስ” እየደገሱ በእኩይ ተግባር መታወቅ ከራስም፣ ከኅሊናም ሆነ ከፍትሕ ጋር ግጥሚያ ከመግጠም አይተናነስም። “ጆሮ ያለው ይስማ! ኅሊና ያለውም ያስተውል” ማለት ይሄኔ ነው። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2013