ፍሬህይወት አወቀ
የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባውን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት መካሄዱ ይታወሳል። በዕለቱ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚው ዘርፍ ከለውጡ ወዲህ ባሉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ተስፋ ሰጪ እድገቶች የታዩበት መሆኑን አንስተዋል። የተመዘገበውን ለውጥ በተመለከተ እንዴት ተረዳችሁት? ምን ተስፋና ስጋቶች አሉ? ስንል ላነሳነው ጥያቄ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ምላሽ ሰጥተውናል።
በሀገሪቱ የተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪና ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ ያነሱት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡት ዝርዝር ሃሳቦች ለታቀደው ሀገራዊ ዕቅድና የታለመውን ግብ ለመምታት ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸውን ይናገራሉ። ነገር ግን በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ባሉ ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት በእያንዳንዱ ማህበረሰብ ላይ በተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የቻለ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ።
የማክሮ እና ማይክሮ ኢኮኖሚ ዘርፎች ባስመዘገቡት ውጤት በተያዘው ዓመት ስድስት ወራት ብቻ ባንኮች አንድ ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ብር መሰብሰብ ችለዋል። ይህ ከፍተኛ ቁጥር ነው ነገር ግን በዚሁ ልክ የማህበረሰቡ ኑሮ አልተለወጠም፤ አልተሻሻለም። ይህም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ የመጣ ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ ‹‹በንግድ ሥራ ላይ ያለው ሃይል ማን እንደሆነ ይታወቃል›› በማለት የጠቀሱ መሆኑን ዶክተር ወንዳፈራሁ አስታውሰዋል። ስለዚህ የተገኘው ውጤቱ ማህበረሰቡ ላይ በአንድ ጊዜ የሚታይ አይደለም። ነገር ግን በጊዜ ሂደት እየተመዘገበ ያለው ውጤት በማህበረሰቡ ህይወት ላይ የመታየት ዕድል አለው። በተለይም ደሃው ህብረተሰብ ሀብት እንዲያፈራና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር በብዙ ርቀት መስራት ይጠይቃል።
የተጀመረውን ልማት አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ በቀጣይ አሥር ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የልማት ተምሳሌት ማድረግ ይቻላል። ለዚህም በተጣለው ጠንካራ መሰረት ተስፋ እንድንሰንቅ ሆኗል። በተለይም በ10 ዓመት ፍኖተ ካርታው ላይ የፖሊሲ አቅጣጫ ለውጥ እንዳለ በግልጽ የሚታይ ነው።
ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው ሀገሪቷ ለውጭ ገበያ በምትልከው ምርት እንኳን እራሷን ችላ ተጨማሪ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ አልቻለችም። በአሁኑ ወቅት ግን በአብዛኛው ምርት ጨምሯል። ለአብነትም ሶስት መቶ ሺ ኩንታል ስንዴ ለማምረት ታቅዶ 180 ሺ ተግባራዊ ማድረግ መቻሉና ዘይት ላይ የተጀማመሩት በሙሉ ከውጭ የሚገባውን ምርት መቀነስ የሚችሉ በመሆናቸው ጥሩ ተስፋ ይታያል።
በተለይም ሰላምና መረጋጋቱን በማምጣት የፖለቲካው ምህዳር ሰፍቶ ከውጭ ያለውን ጠላትና የተለያዩ ጫናዎችን መቋቋም እንዲሁም ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ከተቻለ አሁን በተያዘው አቅጣጫ የአፍሪካ ተምሳሌት ለመሆን ጊዜው ሩቅ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ። ለዚህም እርሾ መኖሩንና መሰረቱ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር አጥላው ዓለሙ በበኩላቸው፤ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ መሻሻል የሚታወቀው በሚነገረን ቁጥር ሳይሆን ፊት ለፊት በሚታዩ ትላልቅ ጉዳዮች መሆኑን ይጠቅሳሉ። ለአብነትም ማህበረሰቡ ያለበት የኑሮ ሁኔታ፣ የዋጋ ንረት መቀነስ አለመቀነስ እና የሥራ አጥ ቁጥሩን ማየት ይቻላል።
በአሁኑ ወቅት በስራ ሰዓት በመንገድ ላይ ብዛት ያለው ወጣት ሲንቀሳቀስ የሚስተዋልበት ሁኔታ አለ። ይሄ የስራ አጥ ቁጥሩን የሚያሳይ እንደሆነ ይናገራሉ። ስለዚህ ምንም እንኳን ኢኮኖሚው በከፍተኛ መጠን የተሻሻለ ከሆነ ውጤቶቹ በተጨባጭ ፊት ለፊት ማህበረሰቡ ላይ መታየት እንደሚኖርባቸው ያነሳሉ።
ለአብነትም የውጭ ምንዛሪ ችግር ማቃለል ከተቻለ ዜጎች አሁን ላይ ምንዛሬ ለማግኘት መቸገር እንደሌለባቸውና ከውጭ በሚገቡ ቁሳቁሶች ላይም አሁን እየታየ ያለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት መታየት አልነበረበትም። ስለዚህ የኢኮኖሚ መሻሻሎች መገለጽ ያለባቸው በተግባር መሆኑን ዶክተር አጥላው ይናገራሉ።
ሆኖም ግን በዋናነት የዋጋ ግሽበቱ መቀነስ እንዳለበት ያነሳሉ። ለዚህም በተደጋጋሚ እንደሚባለው ገንዘብን ሰብስቦ ወደ ገበያ ማስገባትና ከገበያው መሰብሰብን መሰረት ያደረገውን የሞኒተሪ ፖሊሲን መጠቀም። ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር መስራት ያስፈልጋል። ምርት ካልጨመረ እጥረት ይፈጠራል። ሁሉም ነገር ላይ እጥረት ካለ የዋጋ ንረት ይከሰታል። ነገር ግን እጥረቱ በአንዳንድ ነገሮች ላይ ብቻ ከሆነ የዋጋ ንረት የማይከሰት መሆኑን አስረድተዋል።
ስለዚህ የሞኒተሪ ፖሊሲውን ማስተካከልና ሰዎች ሥራ እንዲሰሩ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ይመክራሉ። አሁን ላይ በሀገሪቱ ዕለት ዕለት እየጨመረ የመጣው የሚሰራ ሰው ሳይሆን ተፈናቃይ ነው። ይህ ትልቅ ችግር መሆኑን አመልክተው ሰላምና ጸጥታው ላይ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት አበክረው ሊሰሩበት ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ኢኮኖሚው የቱንም ያህል ቢሻሻል በማህበረሰቡ ላይ ለውጥ ማምጣት የማይችል ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው።
ኢኮኖሚ ከፖለቲካው ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው በመሆኑ ሰላም ከሌለ ሥራ አይኖርም፤ ሥራ ከሌለ ደግሞ እጥረት ይኖራል፤ መለወጥ ይቸግራል ። እነዚህ ችግሮች ተደማምረው በቀጣይ የመንግስትን ጉሮሮ የሚያንቁ ትላልቅ ችግሮች ይሆናሉ። ስለዚህ ከሁሉ አስቀድሞ በሰላምና በጸጥታው ላይ መንግስት ሰፊ ሥራ መስራት ቀዳሚ ስራው ሊሆን ይገባል።
ከዚህም ባለፈ ሀገራዊ በሆነው የልማት ዕቅድ ገዠው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ካልቻሉ አንዱ የገነባውን ሌላው እያፈረሰ ዘላቂ ልማት ሊመጣ አይችልም በማለት የጋራ መግባባቱ ወሳኝ መሆኑን በመግለፅ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
ባለፉት ሦስት የለውጥ ዓመታት የገንዘብ ስርጭት 15 በመቶ፤ ቁጠባ 25 በመቶ፤ የብድር አቅርቦት 38 ነጥብ አራት በመቶ ዕድገት መመዝገቡ፤ አገሪቱ ያለባትን የውጭ እዳ ጫና ባለፉት ሶስት ዓመታት ከነበረበት 37 ነጥብ ስድስት በመቶ ወደ 26 ነጥብ ስምንት በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉ፤ የብር ኖት በመቀየሩ ብቻ ስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች አካውንት በመክፈት 98 ቢሊዮን ብር መቆጠብ መቻሉ እንዲሁም በ2010 ዓ.ም አጠቃላይ 730 ቢሊዮን ብር የሰበሰቡት ባንኮች በዘንድሮ ዓመት ስድስት ወር ብቻ አንድ ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ብር መሰብሰብ መቻላቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሀገሪቱ በኢኮኖሚው ዘርፍ ወደፊት እየተራመደች ስለመሆኗ መግለጻቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2013