ተገኝ ብሩ
አካባቢው ሰው የማይላወስበት ምድረ በዳ ይመስል ጭር ብሏል። የፀሐዩ ንዳድ ሁሉንም ሰው በየቤቱ በየስርቻው ከቶታል። ንፋሱም እንደ እሳት ወላፈን ይጋረፋል።
አንድ ጎልማሳ እንደ ነገሩ ከላዩ ላይ የጣለው ስስ ነጠላ ከሰውነቱ ቅጥነት ጋር ተዳምሮ በንፋስ እየተውለበለበ ሲታይ ከርቀት የሆነ እንጨት ላይ የተሰቀለ ጨርቅ አስመስሎታል። ሰውዬው ንፋሱ እየገፋው በባዶ እግሩ በፀሐይ በተጠበሰው አሻዋማ አፈር ላይ በፍጥነት ይራመዳል። ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ ወደፈለገው ከተማ ተቃርቧል። የድካም ስሜት ፊቱ ላይ በጉልህ ይነበባል። ከሚኖርበት ገጠርና ሩቅ አካባቢ ተነስቶ በደንብ ከማያውቃት ሰፊና ስልጡን ከተማ መግቢያ ላይ ተቃርቧል።
ፊቱ ገርጥቷል። ውስጡ እጅግ ንጹህ የሆነ ልብሱ ግን የወየበ የገጠር ሰው። ይህ ሰው ወዳጁን እጅግ ናፍቋል። አግኝቶ ሊያወራው ፣የናፈቀውን አይኑን ሊያይ፣ ተቀምጦ ሊያዋየው ቸኩሏል። ስለዚህ ሰው ሰዎች ሲያወሩም ስለሰማ መውደዱ ጨምሯል። አቻ የማይገኝለት የሰዎች ወዳጅ መሆኑ ገብቶት እሱም ከልቡ ወዶት ሊያገኘው መጥቷል።
የገጠሩ ሰው ከጓሮው የወይን ዘለላ ቀጥፎ ቀጥፎ ይዞ ነው ወድ ወዳጁን መጠየቅ የፈለገው። ወዳጁ ይህን ወይን ሲበላ ማየት በዚያም መደሰት እና መወያየት ፈልጓል። ወዳጁ ወዳለበት ከተማ ሲመጣም ለሁለተኛ ጊዜ ነው። የወዳጁ ፍቅር ጥልቅና የእውነት ነውና
በባዶ እግሩ ድካሙን ችሉ እሾሁን ተቋቁሞ፤ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ እንዲመጣ አንዳች ብርታት ሆኖታል።
ይህ ንጹህ ባላገር ከተማው መግቢያ ላይ ሲደርስ ግን ጉልበቱ ዛለ። የበረታ ድካም ተሰማው። ወዳጁን በዚህ ድካም ውስጥ ሆኖ ማግኘት አልፈለገም፤ ትንሽ ለማረፍና ብርታት ለማግኘት አሰበና ከጀርባው ያንጠለጠለውን ወይን ያለበት ከረጢት አውርዶ ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ አረፍ አለ፤ በዚያውም የአካባቢውን ሁኔታ መቃኘት ጀመረ። ከረጅም ዓመት በፊት የሚያውቀው አካባቢ ተለዋውጧል። የሰዎቹ ሁኔታ ልዩ ሆነበት። ከእሱ ገጠራማ መንደር ጋር ማወዳደር ጀመረ። የአለባበስ ስርዓቱ፣ የመንገዱና የመንደሩ አወቃቀር ወዘተ እያነጻጸረ ሲያስብ ቆየ።
በገጠር ቤቶች እንደ ከተማው የተቀራረቡ አይደሉም። በሰፊው ታርሶ የለማ አዝመራ እንጂ ጥቅጥቅ ያለ መንደር የለም። ከጓሮ ተቀጥፎ ይበላል እንጂ ተሸምቶ አይበላም፤ እዚህ ከተማ ላይ የሚሸጠው እሱ የሚኖርበት አካባቢ የድካም ፍሬ መሆኑን ያውቃልና ሳያስበው “አይ አንቺ ከተማ እኛ ገጠሮቹ ባንኖር እንዴት ትሆኚ ነበር?” ብሎ ጥያቄ አቀረበላት። ከሀሳቡ ሲነቃ ድካሙ ወጣለትና ተነስቶ ወዳጁ ከሚገኝበት ከተማ መሀል ገባ።
ከወዳጁ ከሚኖርበት መንደር ደረሰ። ከወዳጁ ግቢ ሲገባ ሊያገኘው የፈለገውን ወዳጁን ከርቀት ተመለከተው። በፍጥነት ሄዶም “ወዳጄ እንዴት ነህልኝ” ብሎ፤ ተጠመጠመበት። ወዳጁም ሰው አክባሪ ለሰዎች አዛኝና አፍቃሪ ነበረና አፃፋውን መለሰለት።
ወዳጁም ምን እግር ጣለህ ሲል ባላገሩን ጠየቀው።
ባላገሩም በፈገግታ ተሞልቶ እጅግ እንደናፈቀውና ከሩቅ አካባቢም ሊጠይቀው እንደመጣ ነገረው። ያ መልካም የተባለው ሰው በባላገሩ ሁኔታ ተገርሞ በፍቅር በጥሞና ሲመለከተው ከቆየ በኋላ ወደ ማረፊያው ይዞት ሄዶ ማውጋት ጀመሩ።
ከዚያም ሰዎች የተሰበሰቡበት ሰፊው አዳራሽ ውስጥ ገቡ፣ሰዎቹም በክብር ተቀበሉዋቸው። ይህ ለሰዎች አዛኝና ከራሱ ይልቅ ለሰዎች ይኖራል የተባለ ሰው ቤት ሁሌም በእንግዳ ይሞላል። የዚያም ቀንም ከሩቅ አካባቢ እሱን ለመጠየቅ ብዙ ሰው ተሰባስቦ ባለበት ወቅት ነው ባለጋሩን ይዞት የገባው።
ባላገሩና ወዳጁ ለብቻቸው እያወሩ ናቸው። ባላገሩ ያመጣውን የወይን ፍሬ ለወዳጁ ሰጠው። መልካሙ ሰው ወይኑን አንድ ባንድ እያነሳ መመገብ ጀመረ። ይህን የተመለከቱ ማረፊያ ውስጥ የተሰባሰቡ ወዳጆቹ መልካሙ ሰው ከወትሮ የተለየ ባህሪ ማሳየቱ በጣም ገረማቸው።
ያ ከራሱ አስቀድሞ ሌሎችን ማብላት ከሌሎች ጋር ተካፍሎ መጉረስ የለመደው ሰው የቀረበለትን ወይን ብቻውን መብላቱን ቀጠለ። ወዳጆቹም እየሆነ ባለው በጣም ተደመሙ ። ያለወትሮው ብቻውን መብላቱ ገረማቸው። እርስ በርስ እየተያዩ ይነጋገሩ ጀመር። “እንዴ ዛሬ ምንድንው የተፈጠረው?እንዴት እኛን ወዳጆቹን ጥሎ ብቻውን ይበላል?” አለ አንደኛው። ሌላኛው ደግሞ “እኔም ገርሞኛል፤በፍፁም እንዲህ ያደርጋል ብዬ አልገምትም። ብቻውን መብላት የማይወደው ሰው ፀባዩ በአንዴ ይቀየራል ብዬ አላስብም ነበር ፤ይገርማል” ሲል አከለ።
ሁሉም ሁኔታውን እስከመጨረሻ መከታተላቸውን
ቀጠሉ።” ወይ የሰው ነገር አጃይብ ነው።” ተባባሉ። እነሱ ይህን እያሉ ባለበት ወቅትም መልካሙ ሰው ወይኑን ብቻውን መብላቱን ቀጥሏል። ሰዎቹም በሁኔታው ከማስገረም አልፈው ሰውዬውን ማማት ጀመሩ ፤የወረፉትም ነበሩ።
የገጠሩ ሰው ግን ከወዳጁ ጋር ያረገውን ቆይታ ወዶታል፤የወይን ፍሬውን አጣጥሞ ሲበላ በማየቱ ተደስቷል። ወደ አመሻሹ ላይ ያ ወደ ቤቱ ሊሄድ ተነሳ፤ መልካሙም ሰው ሊሸኘው ብድግ አለ። ተያይዘው ሲወጡም አንድ ሁኔታቸውን ሲከታተልና መልካሙን ሰው ሲያማ የቆየ ሰው ተከተላቸውና ባላገሩን አብረው ሸኙት። ሸኝተው ሲመለሱም ተከትሏቸው የወጣው ሰው መልካም የተባለውን ሰው ጥያቄ አቀረበለት። “እርሶ ከሰው ጋር መበላት የሚወዱ ፣ከራስዎ በፊት ሰውን የሚያስቀድሙ ነበሩ፣ ዛሬ ግን ያን አላደረጉም። ለምን? ብዙ ሰው ደሞ በትዝብት ሲመለከቶ ነበር” አለው ።
ያ መልካም ሰውም “ሰውየው ከሩቅ አገር እኔን ለማስደሰት ወይን ተሸክሞ መጥቶ እንድበላ ጋበዘኝ፤ እኔም ሁላችንም አብረን እንድንበላ ነበር ፍላጎቴ፤ አንዱን የወይን ዘለላ ስቀምሰው ግን በጣም ጎመዘዘኝ። ይሄ ወይን ለሁሉም ሰው ቢከፋፈል ከሰዎቹ መካከል አንድ ሰው እንኳን የሰውየውን ልፋት ሳይረዳ ወይኑ ጎምዛዛ ነው ብሎ ቢናገር የገጠሩ ሰው ይከፋል ብዬ አሰብኩ። እናም ሰውየው ደስ ብሎትና በስጦታውም ተደስቶ እንዲሄድ ለማድረግ ብዬ ነው ወይኑን ብቻዬን የበላሁት ሲል መለሰለት። ጠያቂው በሰማው ነገር ተገርሞ መልካሙን ሰው ይበልጥ አከበረው፤ ወደደውም። ተፈፀመ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2013