
ፎርነሪያ ምሽት ቤት በሰው አይነት ተሞልቶ ለተመለከተው ጠጠር መጣያም ያለ አይመስልም። ትግስት ከሁለት ሴት ጓደኞቿ ጋር በመዝናናት ላይ ሳለች ነበር ተከስተ ጎቢጤው ወደመዝናኛ ሥፍራው የዘለቀው። እነትግስት በሩ ስር ነበር የተቀመጡት፣ ጎብጤው ወንበራቸውን ታኮ ሲያልፍ ብቅል አውራጅ ቁመቱ አይኗን ወስዶት ስትተክልበት “ምነው የኔ እህት? እኔ የረሳሁት አንቺ ያልዘነጋሽው ብድር አለብኝ እንዴ?” አላት ከጨረቃ የደመቀ ፈገግታውን እየለገሳት።
“ከሰው ጋር ተመሳስለህብኝ ነው ይቅርታ” አለችው ፊቷ ጥርስ ብቻ ሆኖ። “አምቻሽ ጋር ነው?” አለ እንኳን ምክንያት አግኝተው እንዲሁ የማይከደኑ ከናፍሮቹ ተፈልቅቀው ጥርሱን አስጥተው እያሳዩ። ኧረ ነገር ብርበራ! ዳርዳርታው እንዴት ነው እባክህ?” አለች የኮረኮሯት ያህል ካንጀቷ እየሳቀች።
“ምነው አሳላፊ መሰልክ? ና እንጂ?” ሲሉት ተከስተ ጎቢጤው በእጁ የይቅርታ ምልክት አሳይቷት ወደሚጠብቁት ጓደኞቹ ፈጠን ፈጠን ብሎ እየተራመደ ሄደ። ትግስት በዓይኗ ብትሸኘውም ምስሉን ከልቧ ጽላት አስቀረችውና የተለዋወጡትን ተረብ በምልሰት እያመነዠከች ቆዘመችበት።
ሁኔታዋን ልብ ያለችው ትርሲት “ሽልንግ ሲሆንብሽ አትባንኚም እንዴ? ሌባኮ ነው” አለቻት ቁጣ ባዘለ አስተያየት እየተመለከተቻት። ሽልንግ ያለችው ፈገግታውን መሆኑ ነው። ሃመረ ቀጠለችና “በሌብነት ዝናን ከማትረፉም በላይ የልደታ ሰፈር ሁለተኛ ስሙ ተከስተ ጎቢጤው ሆኗል” ስትል ሌላ ማብራሪያ አከለችላት። “የልብ ወይስ የገንዘብ?” አለች ትግስት ቀልቧን የሰረቀው ቁመናው ሃሳቧን ሰቅዞ ይዞት።
ትግስት በጀርመን ኦስሎ ዩኒቨርሲቲ ሳለች የትምህርት ጊዜዋን እንዳይሻማባት በመስጋት ወጣትነት የወለደውን ስሜት ስትሸሽ ቆይታለች፤ አሁን ግን የሃሳቧን መንገድ የልቧን መውደድ ተከትላ ደስ በሚል ስቃይ ራሷን ልትፈትን ወስና መልህቋን ተከስተ ላይ ጥላለች።
ከሰየሙት ወይን ተጎንጭታ “ተጫወቱ” አለቻቸው ለስሙ ሃሳብ እንዳረገዘች። ትርሲት ብርጭቆዋን አንስታ አፏ ዘንድ አድርሳ እየመለሰችው “የሌለሽን ሲሰጥሽ ያለሽን እየወሰደብሽ ነው” አለቻት የተክለጻዲቅ መኩሪያን “ህይወቴ” መጽሃፍ በምናቧ እየገለጠች፤ ይህን ስትላት ትግስት ወደጀርመን ለማቅናት አዛውንት አባቷ ኤርፖርት እየሸኟት ሳለ ያጫወቷት ወግ ታወሳትና ደጋግማ አንቀራጨችው።
የሚዋኘውን ትንሽ ልጅ ያልታሰበ ደራሽ ውሃ መጥቶ ሲወስደው የድረሱልኝ ጥሪ ያሰማና ጩኸቱን የሰማ አንድ መንገደኛ ሕይወቱን ይታደገዋል። በሌላኛው ቀን ጎዳና ሲያገጣጥማቸው ትንሹ ልጅ ለምስጋና ከባለውለታው እግር ስር ሲወድቅ “እንኳንም በሕይወት ተረፍኩ የሚያስብልህ አጋጣሚ ለመሆኑ እርግጠኛ ሁን” አለ ሰውዬው ፊቱን ቅጭም አድርጎ። ትግስት “እኔም በተሰማኝ ስሜት እርግጠኛ መሆን ይኖርብኛል” አለች በረጅሙ ተንፍሳ።
ጭፈራው ደርቶ ሙዚቃው አልቆ በጀመረ ቁጥር የሚወላከሱ ሰካራሞች የምሽት ቤቱን መድረክ አጣበው ሲደንሱ ምስቅልቅልነታቸው ሚዶ ያልጎበኘው ጸጉር ይመስላሉ። የስሊንዶን “አይካን ተች ዘ ስካይ” ዘፈን ከስፒከሩ ሲንቆረቆር ተከስተ ብቻውን እየደነሰ ስትመለከት አንዳች መግነጢሳዊ ሃይል ስቧት ነፍሷ ሳታውቀው መድረኩ ላይ ተገኘችና ትግስት የጎቢጤን ወገብ ይዛ እንደዕንዝርት ትሾር ጀመር። ስሊንዶን ጨርሳ ክሩ ሲቀየር የስልክ ቁጥራቸውን ተለዋወጡና ወደቦታዋ ስትመለስ እነትርሲት ባግራሞት እየተመለከቷት ነበር።
ትርሲት “ወደው የዋጡት ቅልጥም እንደፍሪንባ አይጥምም” ስትል ተረተችና የሳህሉን ታሪክ አጫወተቻት ድንገት ብትማር ብላ። “በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት አቶ ሳህሉ የሚባሉ ዘናጭ ሌባ ነበሩ አሉ። ታዲያ አንድ ቀን የገበያ እለት ስለነበር ወጪ ወራጁንና የያዙትን እቃ በዓናቸው ሲመዝኑ አንዲት ባልቴት ዋጋ ያረገችውን ሂሳብ ከደንበኛዋ ሳትቀበል መጥታ ኖሯል፣ ለመመለስ ስታስብ በቅርጫት የያዘችውን ጓዟን በአደራ ለማስቀመጥ ሰው ስትፈልግ አቶ ሳህሉ ከመንገዱ ዳር ተቀምጠው አየችና ቀርባ ያቆይዋት እንደሆነ ስትጠይቃቸው “ወይ አለመተዋወቅ?” አሉና ፈቃዳቸውን ሰጧት። አለባበሳቸውን አይታ ነውና ምግባራቸውንም የለካችው የእጅ አመላቸውን ሞራላቸው ታግሎ አሸነፈና ሴትዮዋ ስትመለስ ባደራ መልክ የተቀበሉትን ንብረት አስረከቧት” ብላ ሃሳቧን ሳትቋጭ ትግስት በነገሯ ጣልቃ ገባች። “የምትይው ገባኝ ጓደኛዬ! አንቺም ቅጽበታዊ ስሜትሽ የወለደውን መውደድና ፍቅርሽን በምነት ብትሰጭው ለግብሩ ሳይሆን ለቃሉ ታምኖ ሙሉ ሰው ይሆንና የግልሽ ታደርጊዋለሽ ነው አይደል?” አለች ከአፏ የነጠቀችውን ሃሳብ በራሷ ልክ ሰፍታ።
“እሳት ከነደደ አመድ መቼ ይገዳል፣
ሰው ሁሉ እንደዚህ ነው አጥፊውን ይወዳል።”
እንዲል ዘፋኙ የሰው ልጅ ልቡ ስለሻተው ቀልቡን ስለገዛው ነገር መስማት ይፈልጋል እንጂ ተፈጥሯዊ ጠባዩ ሆኖ ሥራው ሁሉ እንደጓያ ነቃይ የፊት የፊቱን ነው፤ ለዚህም ይመስላል ትርሲት የምትላት ነገር ብታጣ ዝምታን መምረጧ።
ትግስት ከቤት ደርሳ ልብሷን ስታወልቅ ባልማዝ ያጌጠው ያንገት ሃብሏ ከቦታው የለም፤ ስልኳን አንስታ የመታችው ቁጥር የተከስተን ድምጽ አመጣላት። “የሰማሁት ነገር እውነት ሆነ ማለት ነው?” አለች እልህ እየተናነቃት። “እንኳን ሃብልሽ ልብሽም አልቀረኝ፤ ይልቁንስ ድፍረት አይሁንብኝና በአቦሉ የተውነውን ፌሽታ ብናበርከውስ?” አለ ተከስተ ጎቢጤው ፍጹም ትህትናን ተላብሶ።
እሽታዋን እንዳገኘ በኮንትራት ታክሲ ብርችምችም ሆቴል ይዟት ተፈተለከ። ጥግ ላይ ተቀምጠው ገበታ ቀርቦ እየተጎራረሱ ከተመገቡ በኋላ ጣታቸውን አስወርደው ከጽዋቸው ጋር ወግ መዘዙ። “ለምን ጎቢጤው እንደተባልክ አንስተህ ምንም ሳታስቀር ስለራስህ አጫውተኝ” አለችው ዓይኗን ካይኑ ሳትነቅል እያስተዋለችው።
“ደርግ ወንጀለኞችን አስሮ ከመቀለብ ይልቅ ወደሻኪሶ አዶላ ለወርቅ ቁፋሮ ይወስደን ነበር፤ እኛም “ግፋ ቢል አዶላ አንሳ ቢል አካፋ” በማለት ዘፈንን። ሁልጊዜ አንጎብሼ ስለምውል በዚያው ጎብጬ ቀረሁና “ጎቢጤው” የሚል መጠሪያ አስለጠፈብኝ፤ እድሜ ለሶቤት ህብረት ማሽን! “በባህላዊ መንገድ የምታወጡት ወርቅ ቢዘምን ጥሩ ነው” ብላ ማሽን ስትሰጠው ደርግም “እዳ ቀለለ” ብሎ ሲበትነን ክፍያችን መቋረጡ ብቻ ሳይሆን ሥራ አጥም ሆንኩና መላ ባጣ የኖርኩበትን ሌብነት አጧጥፌ ካንቺ ሃብልና ልብ ለመገናኘት በቃሁ” አለ እንደማለዳ ጮራ የሞቀ ፈገግታ እየዘየራት።
ትግስት እንደወርቅ አንጥራ አዲስ ማንነት በማልበስ የግሏ ልታደርገው ሞራሏን አበርትታ “ሥራ ብታገኝ ስርቆቱን ትተዋለህ?” ስትል ጠየቀችው ተስፋ ሰንቃ። ቃሉን በከንፈር ማህተም አረጋገጠላት። ፍቅራቸው እንደጸደይ መስክ ፈክቶ ህልማቸው እንደምንጭ ውሃ ጠርቶ “ጎቢጤው ስጋ ቤት” ተከፈተ። አንድ ቀን ከሥራ ቦታው አዝማሪ መጥቶ ሲጫወት ግጥም አቀበለው።
“ጎቢጤው አልነበረም ወይ የሌቦች አለቃ፣
ዛሬ ታማኝ ሆኖ ላደራ ሲበቃ።”
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም