“ፍሬሹ” ተቀጣሪ

ቡርቃ መንደርን የከበቧት የወ ግሎ፣ መነጎበናና የቡላ ተራ ሮች አቀማመጧን ጉልቻ ላይ የተንጠለጠለች ድስት አስመስለውታል። ለጀልኮ ቡርቃ መንደር እትብቱን የቀበረባት ብቻ ሳትሆን ከልጅነት ትዝታው ባሻገር ልቡንም የተነጠቀባት ጭምር ናት። እድሜ ለያለም ጌጥ ይግባና የተፈጥሮን ጠባይ የለየባት አዳምና ሄዋንን ያወቀባት የቤተመቅደስ መቅረዙ የሕይወት ጓዙ አድርጎ በልቡ ጽላት ከከተባት ዘመኑ ቢሰላ የወተት ጥርሱን መንቀል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ የቀዬው ነዋሪ ይናገራል።

መውጫ መውረጃዋ አውራ ጎዳና ከቤታቸው በራፍ ስለሆነ ጀልኮና ያለም ጌጥ ካይን ጥቅሻ አልፈው ላቅመሃሳብ ልውውጥ በቁና እንደንጋት ጀንበር የፈካው የፍቅራቸው ጮራ ሙቀቱን ለግሷቸው ግንኙነታቸው ፋፋ። በወጋቸው መሃል እንዴት ልቧ እንደገባ ስትነግረው እንዲህ ትላለች ሳቅ እየቀደማት። የያለም ጌጥን ታላቅ እህት ለመውሰድ በሚዜነት ሙሽራውን አጅቦ ሲደርስ

“አናስገባም ሰርገኛ፣

ከደጅ ይተኛ።”

የሚለው ባህላዊ ክዋኔ ጠብቀውና “እንገባለን አትገቡም” ግብግቡ ሲታክተው “ተዉታ እኛም ቤት አለን” ብሎ ለመመለስ ፊቱን ሲያዞር ይህን የሰሙ ደጋሾች የፈረስ መላክተኛ ልከው ሰርጉን ከመስተጓጎል አተረፉት። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሰርግ በመጣ ቁጥር “ተዉታ አለ ጀልኮ” እየተባለ ተረት ወጣለት።

የተፈጥሮን ግምጃ ለብሰው የማሽላ ውል ብኝ እየተገባበዙ ከንፈር የተቃመሱበትን ወዝ የተነሳሱበትን አያሌ ትዝታዎች በምናቧ ሰሌዳ ሰድራ “ይብላኝ ለኔ እንጂ አንተስ ለፈረንጅ ትምህርት ከተማ ገብተህ በሰው ጫካ ስትዋጥ ትዘነጋኛለህ” አለችው እንባ ያረገዙ አይኖቿን ባይበሉባዋ እንደዕንጩጭ በቆሎ እያርመጠመጠች። እሱም ቢሆን ይህ ነው ባይላትም ለወላጆቹ ማሳወቅ እንዳለበት አምኖ በድንግዝግዝ ተስፋ ተለያት።

“ማሽላ ጠባቂ ላያድር ያመሻል፣

ፈርቼ ነው እንጂ ልቤስ ከጅሏታል።”

እንዳለው አዝማሪ የያዘውን የፍቅር ግለት ላያቱ ሙሉ ጎጃም አበበ ሊያሳያት በወደደ፤ እሷ ግን ፍጥምጥሙ ቀድሞ ደርሷት ኖሮ እግሩ ጉበኑን እንዳለፈ በነገር ልምጭ ተቀበለችው። “በትምህርት ሰአት ገበያ በወጣችበት አጋጣሚ ጊዜ ድራሽ ሲሆን እየጠበቀችህ አብራችሁ እንደምትመለሱ ድፍን ቡርቃ የቡና ቁርስ አድርጓችኋል። በወሬ ወፍጮ ሰልቋችኋል፤ እንደፍቅሬና አስናቀ ውጭ ሀገር ሄደህ መማር ነው ወይስ እንደታመነና አባተ ወድቀህ ያገር መሳቂያ መሆን?” ስትል ከሃሞት የመረረ ቁጣዋን ግታ ፍቅርን እንደእሳት ኩሽ እያለች አሳድጋው ለሴቶች ዓለም ባዳ አደረገችውና ዛሬ ላይ ባልደረባው ቻይና ልትቀርበው ብትሻ የተዘጋ በር ሆነባት።

ጀልኮ ባለበት ክፍል ለምልክት ያለው ወንድ እሱ ብቻ ነውና ወደ ቢሯቸው የመጣ ሁሉ “ፍካሬ ኢየሱስ የተናገረው ደረሰ እንዴ?” ሳይላቸው አይቀርም። ከዝምታው የተነሳ ሠራተኛው ስሙን አያውቀውምና ከጁ በማይጠፋው “ዘ ቫሊውስ ኦፍ ሰልፍ ኤክስፕሬሽንስ” ደራሲ በፕሮፌሰር ፒተር አዳምስ ነው የሚጠሩት። ቻይና ልቡን የቆለፈበትን ቁልፍ አርቆ ቀብሮታልና ልታገኘው ባለመቻሏ እልህ ተናንቋት ተቅበጠበጠች። “ትውልዱ እንደሆነ ሞቷል ለማን ብለህ ነው የምታነበው?” በማለት ጠየቀችው መግቢያ እንዲሆናት ፈልጋ።

“አሟሟቱንም ቢሆን ለማወቅ ንባብ ጥቅም አለው” ብሎ ቃሉን ከረቸመ። ቁጥብ አንደበቱ ሆዷን የባሰውን ቆረጣትና የጸነሰችውን ፍቅር ለመገላገል ከዝምታው ወደብ መልህቋን ጣለች። ጀልኮም በተራው አያቱ የሳለችበት ጦር እየተደነቀረ ባያስደነብረው ኖሮ መውደዱን ሊገልጥላት በቻለ። ዳሩ ምን ይሆናል እሱና ፍቅር “የሰው ሆዱን የወፍ ወንዱን” የማወቅ ያህል ናቸው። “ለማይከፈልበት የግዜር ሰላምታ ምን ያስነፍግሃል?” አለችው አስከትላ በነገር ልትበረብረው እየጣረች።

“ከይስሙላ ሰላምታ ካንጀት የመነጨ የፍቅር ኩርፊያ አይሻልም ብለሽ ነው?” አላት በድቅድቁ የሃምሌ ጉም ብቅ እንደምትለው የክረምት ጸሃይ የክት ፈገግታውን እያሳያት። ቻይና “የፍቅር ኩርፊያ” ያለውን ቋጠሮ ፈትታ አንዳች ሚስጥር ለመቃረም ስትዳክር የምታልጎመጉማቸው ቃሎች ከጆሮው ተዘርተው እንዲህ ሲል አሳፈራት። “እርግጠኛ ነኝ ቆንጆ ነሽ ያለሽ ወንድ ውበት አይቶ አያውቅም ማለት ነው?” አለ አይኖቹን ከሷ ላይ ነቅሎ ወደመጽሃፉ እየመለሳቸው። ክንፏ ተቆርጦ መሬት ለመሬት እንደምትልሞሰሞሰው ቢራቢሮ ቻይና አንገቷን ደፍታ ወደወንበሯ ስታዘግም “እንኳን አንተ ሶምሶንም ከደሊላ አላመለጠ” ስትል ጥርሷን ነክሳ ዛተች ንቀቱ አብግኗት።

የሥራ መውጫ ሰአት ደርሶ ከተሰፋበት ወንበር ተላቆ ወደበሩ ሲያቀና “ፒተር ጠብቀኝ” የሚል ድምጽ ሰምቶ ዞር ቢል ቻይና ናት። ከግር ጥፍሯ እስከራስ ጠጉሯ ባንክሮት ቢመለከታት የተፈጥሮ ለዛ አጣባትና በቡቲክ አሻንጉሊት መሰላት። የመዘነጥ ሃሳቧን አጉድሎ እቃ ለማውረድ የተንጠለጠለች ያስመሰላት ሂል ጫማ ከለበሰችው ግማሽ ጨርቅ ጋር ተዳምሮ ውበቷን መቀመቅ አውርዶታል። አቅፎ አስቀራት እንጂ እንደገደል ዛፍ ስትወዛወዝ ደረጃው ከድቷት ጥርሷን ለቅማ ነበር።

ወገቡን ጨምድዳ ይዛ “ጀግና ሚስት ብትኖርህ ነው እንደዚህ አሽሞንሙና የምትልክህ፤ ደግሞም የተቀባኸው ሽቶ እንደቅዳሴ እጣን ነፍስን በሃሴት ይሞላል” አለችው አይኖቹን ባይኖቿ አንጋጣ እየተመለከተችው። “አንተ ግን እኔ የምልህ?” አለች ቀጠለችና። “የመሥሪያ ቤቱን የሻይ ክበብ አትጠቀምም ሰርቪስም አትገለገልም ኩራት ነው ወይስ?” ብላ የጎሪጥ አስተዋለችው።

“በኔ ፍሬሽነት የናንተን ሲኔርነት ላድምቀው ብዬኮ ነው” አለ ለስንብት እጁን እየዘረጋላት። “እስኪ አሁን እንኳን ተሸነፍ” አለችው የድንቢጥ መኪናዋን የጋቢና በር ከፍታ እንዲገባ እየጋበዘችው። “ያድዋ ሞራል አይፈቅድልኝማ” አለ ተንሸራሽቶ ቀበቶውን አጠለቀና።

ሰፈሩን ነግሮ አቅጣጫውን ሲጠቁማት ቻይና ግን “ለንቁ ፈረስ ያለንጋ ጥላ በቂው ነው” ብላ ተረተችና ወደራሷ ቤት መሪውን ስትጠመዝዝ “አልገባሽኝም?” አላት ግራ በተጋባ አስተያየት እንደመርፌ ወግቶ ይዞ።

ሀብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You