ወጣትነት ለውጥ ናፋቂነት ነው። የአንድ አገር ቀጣይነት ያለው እድገት የሚለካው ባላት ሃብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን ያንን ተረክቦ በአደራ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚችል ትውልዳዊ ትስስር ሲኖር ነው። ይህንንም እንደ ድልድይ ሆኖ ከአንዱ ትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው።
በማንኛውም አገር፣ ጊዜና ዘመን እያንዳንዱ ተተኪ ትውልድ የአገሩ ወራሽ፣ ተተኪና ተረካቢ፣ ጠባቂና ለሚቀጥለውም ትውልድ የማውረስ፣ የማስተላልፍና የማስረከብ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት።
አገርን ከእነ ሙሉ ክብሯ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ከወጣቱ የዜግነት ግዴታዎች ውስጥ አንዱ ነው። አገር በአንድና በሁለት ትውልድ ብቻ የሚቆምና የሚያልፍ ሳይሆን የማያቋርጥ ቀጣይነት ያለው ትውልድ ሁሉ የሚቀባበለው፣ የሚጠብቀው ያለፈውንና የሚመጣውን ትውልድ ሁሉ የያዘና ያቀፈ የአገርና የሕዝብ የታሪክ ሂደት ነው።
ወጣት ለአንድ አገር በሦስቱም ዘርፍ ማለትም በማህበራዊ፣ በሥነ ምጣኔ ሃብታዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርጋል። ለዚህም ነው ወጣት ለአንድ አገር የጀርባ አጥንት ነው የሚባለው።
አንድ ሰው የተሳካለት ሥራ ፈጣሪ (አዲስና የተለየ የቢዝነስ ሃሳብ ወይም ዘዴ ይዞ የተነሣ) ለመሆን፣ የያዘው ሃሳብና ሃሳቡን ተግባራዊ ማድረጊያ ገንዘብ ወሳኝ መሆናቸው አይጠረጠርም። ሆኖም እነዚህ ሁለቱ ብቻ ሥራ ፈጣሪው የተሳካለት የቢዝነስ ሰው እንዲሆን አያስችሉትም።
የሥራ ፈጣሪነት ስኬትን መቀዳጀት እንዲችል ወይም ጉዞው ወደ ስኬት የሚገሰግስ እንዲሆን ዓይነተኛ የሆኑ የሰብዕና መገለጫዎች ያስፈልጉታል። እንደ ሥራ ፈጣሪ እነዚህ የሰብዕና መገለጫዎች ወይም ጠባዮች ካሉ ሊዳብሩ፣ ከሌሉን ደግሞ እንደ አዲስ በውስጣችን ኮትኩተን ልናሳድጋቸው ይገባል።
ለዛሬ የሌዘር ኤግዞቲካ መስራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሜሮን ሰይድ ከራሷ የሥራ ህይወት በመነሳት ወጣቶች ወደ ሥራ ፈጠራ ዓለም ሲገቡ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው ለፌዴራል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ያካፈለችውን ተሞክሮዋን ለዚህ አምድ እንዲስማማ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለች ነበር ወደ ንግዱ ዓለም የተቀላቀለችው። በልጅነቷ ከህፃናት ጋር ወጥቶ ከመጫወት ይልቅ ቁጭ ብሎ ማንበብም ያስደስታት ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ ለስዕል ልዩ ፍላጎት እንደነበራት ትናገራለች።
“ሰዓሊ የምሆን ይመስለኝ ነበር። በስዕል ውድድሮችም እሳተፍ ነበር። ቴሌቪዥን እና ሬድዮ ሳዳምጥ እንኳን የሆነ ጥበብ ላይ ያለ ሰው ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት ማየት የሚያስደስተኝ ነገር ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ቤት ውስጥ እንደ የቡና ማቅረቢያ እና የራስጌ መብራት ያሉ የእጅ ሥራዎችን እሰራ ነበር።”
“ከጥበብ ጋር የተያያዙ ነገሮችን እንደምወድ እና መንገዴ ወደ ጥበብ እንደሆነ የገባኝ በልጅነቴ ነው” የምትለው ሜሮን እንደማንኛውም ልጅ በትምህርቷ ጠንካራ እንድትሆን ብትሞክርም ለምትወደው ጥበብ ግን ቤተሰቦቿ በጣም ይደግፏት እና ያበረታቷት እንደነበር ታስታውሳለች።
ምንም እንኳን ፍላጎቷ ወደ ህብረተሰብ ሳይንስ ቢያጋድልም ወደ ምትፈልገው የጥበብ ዓለም ለመግባት በተፈጥሮ ሳይንስ ስር ያሉት የተሻለ አማራጭ ስላየችበት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የድራፍቲንግ ቴክኖሎጂ እና ኮምፒዩተር ሳይንስ አጠናች።
ከፍ እያለችም ስትሄድ የህንፃ ዲዛይን የመማር ፍላጎት ስላደረባት ለዚህ ትምህርት መሰረት የሚሆነውን ድራፍቲንግ ቴክኖሎጂ ተማረች። ያወቀችውን ለማካፈል ከፍተኛ ጉጉት ስለነበራት የድራፍቲንግ ቴክኖሎጂን ተምራ እንደ ጨረሰች ለአንድ አመት ያህል በግል ኮሌጅ አስተምራ ነበር። “ያንን ሥራ ግን እንደ ቅጥር ማየት አልፈልግም! ምክንያቱም ያወቅሁትን እውቀት ማካፈሌን ማህበረሰባዊ ኃላፊነቴን እንደተወጣሁ ስለምቆጥረው ነው” ትላለች።
“አንድ ዓመት ካስተማርኩ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርቴን በዲግሪ መርሀ ግብር መማር ጀመረኩ። ከትምህርቴ ጎን ለጎንም ከትምህርት ቤት ጓደኛዬ ጋር ትንሽዬ ቢሮ በመከራየት ለተለያዩ ድርጅቶች መለያ አርማዎች፣ የቢዝነስ ካርዶች፣ ብሮሸሮች እና የመሳሰሉትን የግራፊክስ ዲዛይን ሥራዎች መሥራት ጀመርን።” ስትል ወደ ግል ሥራ እንዴት እንዳመራች ገልፃለች።
ሜሮን እና ጓደኛዋ ትምህርታቸውን ሊጨርሱ አካባቢ ደግሞ ስራቸው በጣም ተጠናክሮ እንደነበርም ታስታውሳለች። ሜሮን እንደምትለው ሥራውን የምትሠራው በጣም ወድዳው በመሆኑ እንደልቧ እንድትጠበብበት ዕድል ሰጥቷታል።
የሰው ልጅ የህይወት መንገድ መቀየሪያው ምክንያት አይታወቅምና የኔክስት ዲዛይን ትምህርት ቤት ባለቤት የሆነችው ሳራ መሀመድ የሜሮንን የዲዛይን ብቃት እና ጥበበኛነት አስተዋለች።
“ተማሪዎች ሲመረቁ የግብዣ ካርዶችን እና ሌሎች የግራፊክስ ሥራዎችን በምሠራላቸው ጊዜ አቅሜን ያየችው ሳራ ምንጊዜም ጎበዝ እንደሆንኩ ከመንገር በተጨማሪ እንድማርም ትጎተጉተኝ ነበር። ከሥራው ጋር የጊዜ መጣበቡ እንዳለ ሆኖ በገንዘብም የመማር አቅሙ እንደሌለኝ ስነግራት እሷ አስተማረችኝ። እኔም አላሳፈርኳትም አንደኛ ነበር የወጣሁት።”
ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ የግራፊክስ ዲዛይን ሥራውን ሙሉ ለሙሉ ለጓደኛዋ በመተው የራሷን አነስተኛ ቦታ ተከራይታ እህቷ በገዛችላት አንድ የስፌት ማሽን የሌዘር ቦርሳ ዲዛይንና ምርት ስራዋን ተያያዘችው።
የዲዛይን ትምህርቱም ሆነ የፋሽን መስኩ ሰፊ ቢሆንም የቆዳ ምርት ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ ሊገኝ የሚችል እና ከፍተኛ ጥራት ያለው ሆኖ ስላገኘሁት ሥራዬ አድርጌ ያዝኩት ትላለች።
ሜሮን ወደ ምርት እንዴት እንደገባች ስትገልፅ መጀመሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደልብ በጥራት የሚገኘው ምንድን እንደሆነ በማጥናት ነበር። ጥናቷም የሚያሳየው ጨርቅ ቢመረትም ለአገር ከፍተኛ ጥራት ያለው ጨርቅ እንደልብ እንደማይገኝ ስለነበር ትኩረት የሚደረገው ኤክስፖርት ላይ ነው። ያለውን እንጠቀም ቢባል እንኳን የሚገኙት ወጥ ቀለም ያላቸው ጨርቆች እንጂ ለዲዛይን ሃሳብ እና ፍላጎት ነፃነት የሚሰጡ የተለያዩ አይነት ጨርቆች ማግኘት እንደማይቻል ትገልፃለች።
“የኢትዮጵያ ቆዳ፣ በተለይ ደግሞ የደጋ በግ ቆዳ ግን በከፍተኛ ጥራት ይገኛል። ይሄ ቆዳ እንደ ጣልያን ወዳሉ አገራት ተልኮ እነሱ አንዳንድ ነገር ጨማምረውበት ተመልሶ ወደ እኛ አገር ይገባል። ይህን ሳስብ “ለምን እኛ ራሳችን ጨምረንበት ለውጭ ገበያ አናቀርበውም?” በሚል ተነሳሽነት ወደ ሌዘር ሥራ አተኮርኩ።”
በሌዘር በርካታ ነገሮችን መስራት ቢቻልም፣ ሜሮን እንደ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪነቷ ውጤታማ ለመሆን በደንብ ወደምታውቀው የቦርሳ ሥራ ላይ አተኮረች። ይህን ያደረገችው ደግሞ ሁሉንም ለመሥራት ፍላጎቱ ሳይኖራት ቀርቶ ሳይሆን በነበራት ካፒታል መስራት የምችለው አንድ ነገር ብቻ ስለነበር ነው።
ለምሳሌ የሌዘር ጃኬት ብዙ ቆዳ ይፈልጋል። ጫማ ደግሞ ምርቱ መመረት ያለበት በስፋት ነው። ስለዚህ በነበረኝ አቅም መስራት የምችለውን ቦርሳ መርጬ መለያውን “ሜሮን አዲስ አበባ” ብዬ በመሰየም ምርት ማምረት ጀመርኩኝ።
“አሁን 50 ሠራተኞች በድርጅቴ ውስጥ ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 80 በመቶዎቹ ደግሞ ሴት ሠራተኞች ናቸው። ሴት በመሆኔ ብቻ የሴቶችን ችግር ለመረዳት ቅርብ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ሴቶች በኢኮኖሚ ጠንካራ እንዲሆኑ ስለምፈልግ ለእነርሱ አብዝቼ የሥራ እድሎችን እሰጣለሁ።”
እንዲህም ሆኖ ግን በዘርፉ በርካታ ፈተናዎች እንደማይጠፉ የምትገልፀው ሜሮን ለሥራቸው የሚያስፈልጉ ጌጣጌጦች እና ተጨማሪ እቃዎችን እንደልብ ማግኘት ከባድ እንደሆነባት ትገልፃለች።
ሜሮን ሥራዋን የሚያስተጓጉሉባትን ነገሮች ስታብራራ ያነሳቻቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ጥሬ እቃ በብዛት እና ሁሌም አንድ አይነት በሆነ የጥራት ደረጃ ተመርቶ ማግኘት አንችልም። የጥራት ደረጃው ከፍ እና ዝቅ የማይል ቋሚ የሆነ ቆዳ ማግኘት የማንችል ከሆነ እንደ አገር ያስወቅሰናል፤ ምክንያቱም ከተዋዋልነው ውጭ ትንሽ ነገር እንኳን ብትቀይር ደግሞ በውጭ አገር ያሉ ገዥዎቻችን የተላከውን ሙሉ በሙሉ ይመልሱብናል። ያ ደግሞ ሌላ ኪሳራ ሆነ ማለት ነው። የውጭ ገበያ ላይ ማን ነች ያመረተችው ተብሎ ሳይሆን መጀመሪያ የሚጠየቀው “የት አገር ነው የተመረተው?” ተብሎ ነው። እንደ አገር እነዚህን ነገሮች ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ ይገባል።
የገንዘብ እጥረት ሁሌም ያለ ችግር ነው። አሁን ላይ በእጅ የሚቆይ ገንዘብ ባይኖርም የአንዱን ምርት ገቢ ለቀጣዩ መሥሪያ እንዲሆን እየተደረገ እንጂ የተመጣው ቢዝነስን ይዞ የሚያበድር አንድም ባንክ አላገኘሁም።
የምናስይዘው ንብረት ከሌለን በቀር ከባንክ ብድር ማግኘት የማይታሰብ ነው። ባንኮቻችን ቢዝነስን እንደ መያዣ አድርገው ማበደር ቢጀምሩ በጣም ይጠቅመን ነበር። እንዲህ ያሉትን ፈተናዎች በአንድ ጊዜ መቅረፍ ባይቻል እንኳን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለሥራ መጓተት ዋናው ምክንያትና መፍትሄ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
የመብራት መቆራረጥ ምንም ሊያሰራን አልቻለም! ትልቅ ፈተና ነው የሆነብን። የአንድ ቀን ምርት ዋጋ ማጣት ማለት በጣም ከባድ ነው። በተዋዋልንበት ጊዜ ማድረስም ይጠበቅብናል። ባለን አቅም ደግሞ ጀኔሬተር ተገዝቶ በየጊዜው ነዳጅ እየተሞላ የሚሰራው ሥራ ትርፋማ አያደርገንም። ሌላው ቀርቶ መንግሥት ይህንን አይነት የመሠረተ ልማት ፍላጎቶችን ቢያስተካክልልን ትልቅ ሸክም ይቀንስልናል።
በንግድ ዓለም ውስጥ መክሰር ሊያጋጥም የሚችል ነገር ቢሆንም የአገር ውስጥ ገበያ ቢቀዛቀዝ በደህና ጊዜ በውጭ ንግድ ማካካስ እንደሚቻል፤ እንደ ኮሮና ቫይረስ ስርጭት አይነት አጋጣሚ ግን ሲፈጠር እጅግ ፈታኝ እና የሚያስጨንቅ እንደሆነ ሜሮን ትገልፃለች።
“በተለይ ወረርሽኙ ወደ አገራችን እንደገባ አካባቢ እጅግ በጣም የሚያስጨንቅ ጊዜ ነበር። የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ገቢያችን ሙሉ በሙሉ ቆመ። የሠራተኛ ደመወዝ እንኳን መክፈል ከብዶኝ ነበር። ማድረግ የምችለው ብቸኛው አማራጭ ሠራተኞቼን በሁለት ፈረቃ እንዲሰሩ በማድረግ ግማሽ ደመወዛቸውን መክፈል ነበር። ያንን ሳደርግ ደግሞ የትራንስፖርት ዋጋ እጥፍ ሆነ። ይህ ደግሞ ሌላ ፈተና ነበር።
በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሲኮን አንድም የችግሩ አካል አልያም የመፍትሄው አካል መሆን የራስ ምርጫ ነውና ድርጅታችን ወዲያው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሥራ ማምረት ጀመረ። ከመጣው ፈተና ለመውጣት በምንፍጨረጨርበት ወቅት የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ ደረሰልን” ስትል ታስታውሳለች። ሜሮን እንዲህ ባሉ እና ሌሎች ፈተናዎች ተስፋ መቁረጥ እንደማያስፈልግም ትናገራለች።
“ነገሮች የሚሳኩት መውደቅ የማንፈራ ከሆነ ነው። በተለይ ወጣት ተስፋ መቁረጥ የለበትም! ጤናም ጉልበትም እውቀትም የሚኖረው በወጣትነት እድሜ ስለሆነ መሮጥ ያለብን ይሄኔ ነው። ብንወድቅም ደግሞ ራሳችንን አንስተን ድጋሚ መሮጥ ነው እንጂ ተስፋ መቁረጥ በፍፁም አያስፈልግም። በቃ ህይወት ይቀጥላል!’’ ስትል ለወጣቶች መልዕክት አስተላልፋለች።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2013