በለጋ ህላዌው ባልሰላ እሳቤው ትምህርትን ዘለው የሚያልፉት ታግለው የሚጥሉት ግዑዝ ነገር አድርጎ ቆጥሮት “እነገሌ በትምህርት ወደቁ” ሲባል ሲሰማ “እንዴት ያሸንፋቸዋል? የፍየል ወተት አይጠጡም እንዴ?” ይላል ገብረየሱስ በቀና ልብ፤ ይህ የአስተሳሰብ ደረጃው ግን በሕልሙ በተገለጠለት ርዕይ ሳቢያ የትምህርት ጽንሰ ሃሳብ ነፍስ ዘርቶ ሥጋ ሠርቶ ዛሬ ለደረሰበት እሱነቱ መሻገሪያ ድልድይ ሆኖታል።
ጀሃን፣ ፋጫ፣ አከባኬ፣ አድገርማ እያለ በእረኝነት ሕይወት ቆጥቆጤ መንደር የደረሰው ገብረየሱስ በአንደኛው ቀን ምሽት ላይ ከታዛ በጀርባው ተንጋሎ ከተንጣለለው አድማስ ዓይኑን ተክሎ ሃሳብ ሲጎነጉን በፀደይ ብርሃን ያሸበረቀው የሰማዩ ደረት ያሳለፈውን ሕይወት ያነበው ዘንድ ትዝታውን ያሰፈረበትን የብራና ጥቅል ተርትሮ አቀረበለትና እያንዳንዱን መስመሮች ከራስጌ ወደግርጌ በሰርሳሪ አይኖቹ መነሻቸው።
በወርሐ ሐምሌ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት ከአባቱ አቶ ግርማይ አረጋዊና ከእናቱ ከወይዘሮ የሺ መሰለ አላማጣ የተወለደው ገብረየሱስ የውሃ ማዕበል መንጭቶ መሬት ተንሸራቶ የእርሻ ማሳቸው እንዳልነበር ሲሆን የረዘመ ጥፍሩን አስቀድሞ ከማጀታቸው ያዘለቀው ድህነት ካከናነባቸው የመከራ እከክ ሽሽት በስምንት ዓመቱ ከቀዬው ርቆ በወር የአስራ አምስት ብር ደሞዝ በእረኝነት ተቀጠረና ብርቅ የሆነበትን ኩርማን እንጀራ ፍለጋ ሳይወድ በግዱ የሰው ቤት ወዝ አነሳ።
“ይገፋል በግዱ ይስባል በግዱ፣
ያገሩ ገመገም ሲጠፋው መንገዱ።”
እንዲል አዝማሪ እንዲሁም “ከሰርክሉ እንገናኝ” በሚለው መጽሐፋቸው “የሰው ልጅ የሚፈልገውን ለመሆን የማይፈልገውን ይሆናል” እንዲሉ መራራ ጉዲና (ዶ/ር) ጭቃ አቡክቶ ውሃ ተራጭቶ እየቦረቀ በሚያድግበት በልጅነት እድሜው የቤተሰቡን ጉሮሮ ለመድፈን ወጣት ገብረየሱስ መስዋዕት ሆነ።
ከሌለው ላይ ማካፈልን በላቡ መክበርን የሕይወት መርሑ ያደረገው ብርቱና ታታሪው ሰው ይህ የዛሬ እንግዳዬ ወጣት ገብረየሱስ በኳሽራ ሜዳና በግራካሶ ተረተሮች የከብት ጭራ እየተከተለ ኑሮን ሲገፋ ብሎም ረሃብና ጥሙ ሲፈራረቅበት ቅንጣት የተስፋ መቁረጥ ምልክት አይታይበትም ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ግን የሕይወት ገጹ የከተበውን የታሪኩን ሰበዝ ይዤ የወጋችንን ሰፌድ ስሰፋ ከሁኔታው ሆድ እንደባሰው አንጀት እንደራቀው ተገነዘብኩና ከማበጃጀው የሃሳብ አክርማ አንድ ጥያቄ መዝዤ አቀበልኩት። “አሠሪዎቼ ያለጥፋቴ ሲገርፉኝና እንደሰው አልቆጥር ሲሉኝ ዋጋ እንደሌለኝ ተሰማኝና ከባይተዋርነት ባሕር ሰጥሜ ከፈጣሪም ጭምር ተገለልኩ፤ ምንም እንኳን እሱ እየሱስ ክርስቶስ ባይተወኝም” የሚል መልስ ሰጠኝ ምን ቢገጥምህ ነው በሕይወት መጽሐፍህ ውስጥ አያሌ ምዕራፎችን በኃዘን ቀለም የነከርካቸው? ስል ላነሳሁለት ጥያቄ።
“በወንፊት ውሃ ቀድተህ አምጣ ትለኛለች፤ ከሙቀጫ ጋር ታታግለኛለች፤ በእፍኝህ እሳት ጭረህ አምጣ ትለኛለች፤ ከውሻ ጋር ታቀርበኛለች” የሚለው የእንጀራ እናት ተረት እሱም ላይ ደርሶ ሀብት ንብረታቸው ይቅርና ራሳቸው እንኳን የራሳቸው ያልሆኑ ቀጣሪዎቹ ሁሉ የሞተ እህል ሲነፍጉት ስንዝር መደብ ሲከለክሉት እንባውን ከማፍሰስ በቀር ብሶቱን ለማንም አልተነፈሰም፤ ይልቁንም ከጥጆች ማደሪያ ተኝቶ የዛሬ ሕልሙን ፍቺ አገኘበት እንጂ።
በእንቅልፍ ገንዞ በቅዠት ከፍኖ ግለኝነት ከበዛበት ዓለም የነጠለው ሕልሙ እንደበጋ ሰማይ እየጠራ ሲመጣ ከሰማይ ወደምድር የተዘረጋ የብርሃን ገመድ አየ፤ በገመዱ ላይም ከበረዶ የነጣ ልብስ የለበሰ መልከመልካም ሰውዬ እየተሳበ ወረደና የሚጋባ ፈገግታ እየዘራ ገብረየሱስን ተጠግቶ “ገሬ ትምህርት ቤት ግባ” አለና እግሩን በግሩ ሲነካው ገብረየሱስ በድንጋጤ ባኖ አካባቢውን በጩኸት አናጋው። “በቁሙ ጅብ በላው፤ ምስኪን የጨው እቃ” በማለት እየተሳለቀ የቀዬው ሰው ከቦታው ሲደርስ ገብረየሱስ የሕልሙን ፍቺ አስተውሎት ኖሯል በሕልሙ ያየውን የነገውን ሕይወት በርዕይ የተነገረውን እውነት አስረድቶ ወደትውልድ መንደሩ እንዲሸኙት ለመናቸው፤ ቢያባብሉት እንኳን እሺ እንደማይላቸው ልብ ያሉት የአካባቢው ሰዎች ደመወዙን አንቀባቅበው ከሰጡት በኋላ በውድቅት ሌሊት ግማሽ መንገድ ገፈተሩት።
ከሱ እድሜ በብዙ የሚያንሱ ልጆች ከጉያቸው ፊደል ሸጉጠው ሲመለከት አንጀቱ በቅናት ደብኖ ቢከስልም መሻቱን ሳይፈጽም ወደኋላ ላያፈገፍግ ለራሱ ቃል በመግባት እያንዳንዱን ፈተና በጽናት ይጋፈጥ ዘንድ መንፈሱን አበረታ። የማለዳዋን ፀሐይ ተከትሎ እንጀራ ቢነጠፍበት እንኳን የማያስጠይፍ በአስፓልት የነደደ የከተማውን ጎዳና ጫማው ሲስም በስምንት ዓመቱ ትቶት የወጣው የትውልድ መንደሩ እንደነበረ አልቆየውምና የእንግዳነት ስሜት ገጹን ሸበበው። ያሪቲው፣ ያስጎሪው፣ የጠጀ ሳሩና የአደስ ቁኒው ሽታ በጌምፓሪስና ቫኔል ፋይቭ ሽቶ ተለውጦ አንበረጭቃውም ተዘንግቶ በፈረንጅ ቅባት ወዝቶ ሲታዘብ ካለማወቅ ወፍጮ ተሰንቅረው የላሙት አስር ዓመታት በቁጭት ቆሽቱን አሳረሩት፤ ይሁን እንጂ ለመብሰክሰክ ዕድል ሳይሰጣቸው እንደእንቁራሪቱ ጆሮውንም በመድፈን የለውጡን ባቡር ሙጥኝ አለ።
የእንቁራሪቶች የሩጫ ውድድር ተዘጋጀና ፊሽካውን ተከትሎ እሽቅድድሙ ተጀመረ፤ ዳሩ ምን ይሆናል አስቀድመው በሃሳባቸው ተሸንፈዋልና የልቦና እግራቸው ዝሎ ከተራራው አናት ሳይደርሱ ቁልቁል ፈረጠጡ። ሁሉም ነገር አንድን ነገር የሚመዝነው በራሱ የእውቀት ደረጃ ልክ ነውና በእነሱ የውድቀት ዓይን የሱንም ጥረት በይነው “አውሎ ንፋሱ መጥቶብሃል፤ መሬት መንቀጥቀጡ ደርሶብሃል” እያሉ ቢያስተጋቡም ብቸኛው እንቁራሪት ግን ሞራል የሚያሰንፈውን ወደኋላ የሚጎትተውን ፍርሃት አዘል የደከመ እስትንፋሳቸውን ከመጤፍ ሳይቆጥር ከተራራው ጫፍ ጉብ አለና በኩራት እየተንጎማለለ ባንዲራውን በማውለብለብ የድል ብስራቱን ገለጠ። የስኬቱን ምንጭ በጠየቁት ጊዜ በተስፋ መቁረጥ የሰለሉ ድምፆችን ባለመስማቱ እንደሆነ ገለጠላ ቸው።
አንተስ ሥራን በሚንቅና በሚያማርጥ ማኅበረሰብ መሐል እየኖርክ እንዴት እንዲህ ያለውን ጠንካራ የሥራ ባህል ልታዳብር ቻልክ? አልኩት የምኮመኩመው የጨዋታችን ብርዝ አንጀቴን እያራሰው። “ሥራ ሲሉት ድንግጥ ጠላ ሲሉት ሽምጥጥ” በሚል ዘመኑን ባልዋጀ አባባል ያደገ ትውልድ ቢሠራ ነበር የሚደንቀኝ” አለ በለበጣ ስቆ ሥነቃሎቻችንም በራሳቸው ያለባቸውን ግድፈት ሊያሳየኝ እየሞከረ። “ያም ሆነ ይህ” ብሎ በእንጥልጥል የተወውን ሃሳቡን ቀጠለ። “የእርሻ ማሳችን ከተጎዳ በኋላ በገበያ ቀን ከመንገድ ዳር ተቀምጠው አባቴ እንጨት እናቴ ደግሞ ውሃ እየሸጡ ቤት መርተዋልና እኔም ከኑሮ ዘይቤያቸው የተማርኩት ከክብር መውረድ ሳይሆን የሚያስነውረው ፈተናን እያማረሩ ወድቆ መቅረት ነው፤ ለዚህም ነው በቀን ሥራ ሰበብ ድፍን አላማጣን ሳካልል ኩራት እንጂ ሐፍረት ያልተሰማኝ” አለ የልቡ ሙቀት ገጹን እያፈካው።
ለመሆኑ ምን ምን ሠርተሃል? በማለት ሌላ ጥያቄ አስከተልኩ ለወጣቶች የሞራል ስንቅ የሚሆን ሃሳብ እዘግን ዘንድ ጉጉቴ አይሎ። “ለትምህርት የሚረዱኝ ግብዓቶችን ለማሟላት ብዬ ከመነኻሪያ ሥራ በተጨማሪ ሰኔ ዘቅዘቅ ሲል ጉልጓሎውን፣ መስከረም ሲጠባ አረሙን፣ አጨዳ ሲደርስ አጨዳውን በቀን ክፍያ እየሠራሁ ጎን ለጎንም ዶሮ እርባታ ጀምሬ ነበር ባጭር ቀረ እንጂ” አለ በስሱ ፈገግ ብሎ። ጥሎብኝ የጥያቄ አባት ነኝና ቶሎ መልስ ካላገኘሁ ሆዴን ይቆርጠኛል፤ ምነው? አልኩት ተቁነጥንጬ። “ዶሮ ለማርባት እውቀቱ አልነበረኝምና የጎረቤት ስጦ እየመነጨሩ ሲያስቸግሩ ጊዜ መልካም ጎረቤት ድመት ያፈራል መጥፎ ጎረቤት ዶሮ ያፈራል ብለው ሲተርቱ ሰማኋቸውና ዘርፌን ወደበግ እርባታ ለውጬ ነበር፤ እሱም ቢሆን አልተሳካልኝም እንጂ” አለ በሥራ ዓለም ውስጥ የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ የነበረውን መንገዳገድ አስታውሶ እየሳቀ። ታዲያ እንዲህ ከሆነ አንተ ስም የገዛህበትንና ለብዙዎችም ምሳሌ የሆንክበትን የልብስ ስፌቱን ሥራ መቼና እንዴት ጀመርከው? ስል ሌላኛውን የሕይወቱን ገጽ ለመግለጥ የሚያስችለኝን ጥያቄ ሰነዘርኩ።
ሁነኛ ቀጠሮ ገጥሞት ልብስ ለመቀየር ሳጥኑን ሲበረብር ሁሉም ቆሽሾ ስለነበር ሳሙና ለመግዛት ወደሱቅ በመጓዝ ላይ እንዳለ አዳፋ ሻሽ የጠመጠሙ አንድ ቄስ ኮረም ለመሄድ ሽተው ነገር ግን ለትራንስፖርት አምስት ብር እንደጎደላቸው ሲያዋዩት ሳያመነታ ያለችውን ርጋፊ ፍራንክ ዘረጋላቸውና የተባለውንም ሳይገዛ ባዶውን ተመለሰ፤ የቀጠሮው ሰዓት ግን እየደጋገመ “የምትለብሰውን ሳታሰናዳ ጊዜው ደረሰልህ፤ ምን ይውጥህ?” እያለ አሁን አሁን ያንቃጭልበታል።
“እኔም አልታመም አንቺም አትሙቺና፣
ለወቀሳ ያብቃን ሁሉም ይለፍና፣
አሁን አይመችም መች ተያየንና።”
የሚለውን የስንኝ ቋጠሮ እያመነዠከ ብርበራውን ሲቀጥል ንጹሕ የሆነ ነገር ግን የተቀደደ ሱሪ አገኘ። “ይገርማል የኛ ነገር። ሃገራችንን፣ ሕዝባችንን፣ መገልገያ ቁሳቁሶቻችንን ሳይቀር ባጣ ቆይ አድርገናቸው በቸገረን እለት ጊዜ ብቻ ነው ለፍለጋ የምንኳትነው፤ ይህን ወቅት ደግሞኮ የጣልነውን አንስተው ሌሎች ሲጠቀሙበት ብናይ ያየሁት አይቅረኝ ሆዴን ቆረቆረኝ ያሰኘናል። መቼ ይሆን አንድን ነገር የት አገኘዋለሁ? ምን ያደርግልኛል? ከሚል እሳቤ ወጥተን ያስፈልገናል፤ ይጠቅመናል፤ ለማለት ወጉ የሚደርሰን?” አለ ሐፍረት ሕሊናውን እየነዘገው።
የተቀደደ ሱሪውን አስጠቅሞ ለመልበስ ተስፋዬ ከሚባል መኪነኛ ዘንድ ሲሄድ ለሻይ ወጥቶ ስለነበር “እስከዚያው” በሚል ቁጭ አለና ራሱን በራሱ ማስተማር ያዘ፤ ወዳጁን ሲሰፋ ለሁለት ቀናት እድሜ ያህል አይቶት ያውቃልና፤ ታዲያ ይህን ጊዜ በመንገዱ የሚያልፍ አንድ የሚያውቀው ሰው ከእግዜር ሰላምታ ጋር ሞራል ለግሶት ሄደ፤ “አያያዝህን ለተመለከተው ልምድ ያለህ እንጂ ለማጅ አትመስልምና ከልብህ አጥብቀህ ብትይዘው ደና ሰፊ ይወጣሃል” በማለት። ከዚህ በኋላ ገብረየሱስና የልብስ ስፌት
“ሰፍቼም ለበስኩት አይቼም ገመትኩት፣
ሰምቶ መቻልን በሆዴ መዘንኩት።”
ይሉትን ዘፈን እያቀነቀኑ ቁርኝታቸውን አጸኑ።
በዚህ መሐል በምሥራቅ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስኳላውን ያሟሸው ይህ ወጣት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ታዳጊዋ ኢትዮጵያን ቢቀላቀልም አስረኛ ክፍል ላይ የማትሪክ ውጤት አልመጣለትምና ላቅመ መሰናዶ ሳይበቃ በመቅረቱ የተነሳ ከሀገር መውጣትን አልሞ ተከታይ ወንድሞቹን የልብስ ስፌት በማሠልጠን በእግሩ ተካቸውና በሕጋዊ መንገድ ወደሱዳን ወጣ። እዚያ እንደደረሰ ለሀገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ ቢሆንም ፍትፍት የሆነ ፀባይ አለውና ያደረበት ያልጋ ቤቱ ጌታ ከልቡ አቀረበውና ገና ሲያየው ሥራ ያፈላልግለት ዘንድ ወደደ። “እኔ ሥራ እፈልጋለሁ” የሚለውን ቃል ብቻ በዓረብኛ አጥንቶ ሥራ ፍለጋ ሲኳትን የቤቱን ደጃፍ የሚያፀዳ አንድ ኤርትራዊ አገኘና “አና ዳየር ሽቁል” ሲለው በሳቅ ተቀበለውና በሄራ ሆስፒታል ለፅዳት ሠራተኝነት አበቃው። በዚህ ሙያ ውስጥ እንዳለም ከሥራው በተጓዳኝ የዶክተሮችን መኪና በነፃ በማጠብ ያካበተው ልምድ ዛሬ ለጀመረውና ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረበትን ላባጆ ለመክፈት ቻለ። ከስምንት ወራት በኋላም እጁን የፈታበትን የልብስ ስፌት ሙያ በሱዳን ምድር አስፋፍቶት ለአምስት ዓመታት ያህል ሀብትና ንብረት አፍርቶበት አቅም ሲያበጅ ሀገሩን ያገለግል ዘንድ ወደቀዬው ተመለሰ፤ ይሁን እንጂ ሁሉን ነገር አመቻችተው እንዲጠብቁት ገንዘቡን ባአደራ መልክ የሰጣቸው ወዳጆቹ ከዱትና ሕይወቱን አመሰቃቀሉበት።
ቆም ብሎ ሲያስበው ግን ከምንም ነገር ነውና መነሻው ሞራሉን በማበርታት መንገድ ዳር ተቀምጦ መልሶ የጀመረው የልብስ ጥገና ሥራ ከራሱ አልፎ ዛሬ ላይ ለብዙዎች መለወጥ ምክንያት ሆኗል። ብሩክ ካሣሁን ስለገብረየሱስ ሲናገር አንስቶ አይጠግብም። ራሱን ሊያጠፋ እንደነበርና እሱን ካገኘ ወዲህ ግን እሱም በተራው ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አጫወተኝ። ወንድሙ ዮሐንስ ግርማይም ጠንካራ የሥራ ባህልን ከሱ እንደተማሩ ገለጸልኝ። የሃምሳ አራት ዓመቷ ዓይናለም ሽፈራውም የሰው እጅ ከመጠበቅ ያዳናቸው ገብረየሱስ ባስጀመራቸው የሻይ ቡና ሥራ እንደሆነ ከምርቃት ጋር ደግነቱን አካፈሉኝ።
እኔም በሁኔታው ተደምሜ የነገ ሕልሙን በጠየኩት ጊዜ ትልቅ ጋርመንት ከፍቶ ሴቶች በነፃ የሚሠለጥኑበትን ዕድል እንደሚያመቻች አጫወተኝ። ሕልሙ ይሰምር ዘንድ በመመኘት ጽሑፌን ቋጨሁ።
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም