ለችግር ያልተበገረ ማንነት

ገብረእየሱስ ድህነት በፈጠረበት ጫና ትምህ ርት ቤት ገብቶ የመማር ሃሳብ አልነበረውም። የእሱ ዋነኛ የዕለት ተዕለት ተግባር ከብቶችን በእረኝነት ማሰማራት እና ከመስክ አውሎ አጥግቦ ወደ ቤት ማስገባት ነበር። ሆኖም እረኝነት ሥራ በጣም ከባድ ስለነበር በርካታ ችግሮችን መጋፈጥ የግድ ይለው ነበር።

በአንድ ወቅት በእረኝነት ተቀጥሮ ሲሠራ በድንገት ትንሿ ጣቱን እንጨት ይወገዋል። እንጨቱም ዘለቅ ብሎ ስለገባ ቁስሉ ይጠናበታል፤ እንደልቡም ለመላወስ ይቸግረዋል። እንደልቡም ተንቀሳቅሶ ከብቶቹን ለመጠበቅ ይቸገራል። ከብቶች ደግሞ በአግባቡ በእረኛ ካልተጠበቁ ወደ ሰው እርሻ ገብተው ማበላሸታቸው አይቀርም።

በእግሩ ቁስል የተነሳ እንደልቡ መንቀሳቀስ ያልቻለው ገብረእየሱስ እንደፈራው ከብቶቹ በሰው ማሳ ውስጥ ገብተው በርካታ ጥፋት ፈጸሙ፤ በእዚህ የተነሳ የገብረየሱስ እጣ ፋንታ ከቁጣ አልፎ በሳማ እስከመገረፍ ደረሰ።

ገብረእየሱስ እረኛ ሆኖ ሲያገለግል በርካታ ሰዎች ገጥመውታል፤ ከስድብ እና ግልምጫ አልፎ በሳማ እስከ መገረፍ የደረሰ ቅጣት ቢደርስበትም በእዚያው ልክ ደግሞ አንጀታቸው እንስፍስፍ የሆኑ ሰው በልቶ የሚጠግብ የማይመስላቸው ገራገር ሰዎችም ገጥመውታል።

በወርሀ ሐምሌ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ዘጠኝ አመተ ምህረት ከአባቱ አቶ ግርማይ አረጋዊና ከእናቱ ከወይዘሮ የሺ መሰለ አላማጣ የተወለደው ገብረየሱስ የውሃ ማእበል መንጭቶ መሬት ተንሸራቶ የእርሻ ማሳቸው እንዳልነበር ሲሆን ከድህነት ለመሸሽ በስምንት ዓመቱ ከቀዬው ርቆ በወር የአስራ አምስት ብር ደመወዝ በረኝነት ተቀጠረና ብርቅ የሆነበትን ኩርማን እንጀራ ፍለጋ ሳይወድ በግዱ የሰው ቤት ወዝ አነሳ።

“ይገፋል በግዱ ይስባል በግዱ፣

ያገሩ ገመገም ሲጠፋው መንገዱ።”

እንዲል አዝማሪ እንዲሁም “ከሰርክሉ እንገናኝ” በሚለው መጽሐፋቸው “የሰው ልጅ የሚፈልገውን ለመሆን የማይፈልገውን ይሆናል” እንዲሉ ዶክተር መራራ ጉዲና፤ ጭቃ አቡክቶ ውሃ ተራጭቶ እየቦረቀ በሚያድግበት በልጅነት እድሜው የቤተሰቡን ጉሮሮ ለመድፈን ወጣት ገብረየሱስ መስዋእት ሆነ።

ከሌለው ላይ ማካፈልን በላቡ መክበርን የሕይወት መርሁ ያደረገው ብርቱና ታታሪው ሰው፤ ይህ የዛሬ እንግዳዬ ወጣት ገብረየሱስ በኳሽራ ሜዳና በግራካሱ ተረተሮች የከብት ጭራ እየተከተለ ኑሮን ሲገፋ ብሎም ርሃብና ጥሙ ሲፈራረቅበት ቅንጣት የተስፋ መቁረጥ ምልክት አይታይበትም ነበር።

ያሪቲው፣ ያስጎሪው፣ የጠጀሳሩና የአደስ ቁኒው ሽታ በጌምፓሪስና ቫኔል ፋይቭ ሽቶ ተለውጦ አንበረጭቃውም ተዘንግቶ በፈረንጅ ቅባት ወዝቶ ሲታዘብ ካለማወቅ ወፍጮ ተሰንቅረው የላሙት አስር ዓመታት በቁጭት ቆሽቱን አሳረሩት፤ ይሁን እንጂ ለመብሰክሰክ እድል ሳይሰጣቸው የለውጡን ባቡር ሙጥኝ አለ።

አንተስ ሥራን በሚንቅና በሚያማርጥ ማህበረሰብ መሃል እየኖርክ እንዴት እንዲህ ያለውን ጠንካራ የሥራ ባህል ልታዳብር ቻልክ? አልኩት የምኮመኩመው የጨዋታችን ብርዝ አንጀቴን እያራሰው። “ሥራ ሲሉት ድንግጥ ጠላ ሲሉት ሽምጥጥ” በሚል ዘመኑን ባልዋጀ አባባል ያደገ ትውልድ ቢሠራ ነበር የሚደንቀኝ” አለ በለበጣ ስቆ ሥነቃሎቻችንም በራሳቸው ያለባቸውን ግድፈት ሊያሳየኝ እየሞከረ።

“ያም ሆነ ይህ” ብሎ በእንጥልጥል የተወውን ሃሳቡን ቀጠለ። “የእርሻ ማሳችን ከተጎዳ በኋላ በገበያ ቀን ከመንገድ ዳር ተቀምጠው አባቴ እንጨት እናቴ ደግሞ ውሃ እየሸጡ ቤት መርተዋልና እኔም ከኑሮ ዘይቤያቸው የተማርኩት ከክብር መውረድ ሳይሆን የሚያስነውረው ፈተናን እያማረሩ ወድቆ መቅረት ነው፤ ለእዚህም ነው በቀን ሥራ ሰበብ ድፍን አላማጣን ሳካልል ኩራት እንጂ ሃፍረት ያልተሰማኝ” አለ የልቡ ሙቀት ገጹን እያፈካው።

ለመሆኑ ምን ምን ሠርተሃል? በማለት ሌላ ጥያቄ አስከተልኩ ለወጣቶች የሞራል ስንቅ የሚሆን ሃሳብ እዘግን ዘንድ ጉጉቴ አይሎ። “ለትምህርት የሚረዱኝ ግብአቶችን ለማሟላት ብዬ ከመኪና እጥበት በተጨማሪ ሰኔ ዘቅዘቅ ሲል ጉልጓሎውን፣ መስከረም ሲጠባ አረሙን፣ አጨዳ ሲደርስ አጨዳውን በቀን ክፍያ እየሠራሁ ጎን ለጎንም ዶሮ እርባታ ጀምሬ ነበር ባጭር ቀረ እንጂ” አለ በስሱ ፈገግ ብሎ።

ጥሎብኝ የጥያቄ አባት ነኝና ቶሎ መልስ ካላገኘሁ ሆዴን ይቆርጠኛል፤ ምነው? አልኩት ተቁነጥንጬ። “ዶሮ ለማርባት እውቀቱ አልነበረኝምና የጎረቤት ስጥ እየመነጨሩ ሲያስቸግሩ ጊዜ መልካም ጎረቤት ድመት ያፈራል መጥፎ ጎረቤት ዶሮ ያፈራል ብለው ሲተርቱ ሰማኋቸውና ዘርፌን ወደ በግ እርባታ ለውጬ ነበር፤ እሱም ቢሆን አልተሳካልኝም እንጂ” አለ በሥራ ዓለም ውስጥ የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ የነበረውን መንገዳገድ አስታውሶ እየሳቀ።

ታዲያ እንዲህ ከሆነ አንተ ስም የገዛህበትንና ለብዙዎችም ምሳሌ የሆንክበትን የልብስ ስፌቱን ሥራ መቼና እንዴት ጀመርከው? ስል ሌላኛውን የሕይወቱን ገጽ ለመግለጥ የሚያስችለኝን ጥያቄ ሰነዘርኩ።

ሁነኛ ቀጠሮ ገጥሞት ልብስ ለመቀየር ሳጥኑን ሲበረብር ሁሉም ቆሽሾ ስለነበር ሳሙና ለመግዛት ወደሱቅ በመጓዝ ላይ እንዳለ አዳፋ ሻሽ የጠመጠሙ አንድ ቄስ ኮረም ለመሄድ ሽተው ነገር ግን ለትራንስፖርት አምስት ብር እንደጎደላቸው ሲያዋዩት ሳያመነታ ያለችውን ርጋፊ ፍራንክ ዘረጋላቸውና የተባለውንም ሳይገዛ ባዶውን ተመለሰ፤ የቀጠሮው ሰዓት ግን እየደጋገመ “የምትለብሰውን ሳታሰናዳ ጊዜው ደረሰልህ፤ ምን ይውጥህ?” እያለ አሁን አሁን ያንቃጭልበታል።

“እኔም አልታመም አንቺም አትሙቺና፣

ለወቀሳ ያብቃን ሁሉም ይለፍና፣

አሁን አይመችም መች ተያየንና።”

የሚለውን የስንኝ ቋጠሮ እያመነዠከ ብርበራ ውን ሲቀጥል ንጹህ የሆነ ነገር ግን የተቀደደ ሱሪ አገኘ። “ይገርማል የእኛ ነገር። ሀገራችንን፣ ሕዝባችንን፣ መገልገያ ቁሳቁሶቻችንን ሳይቀር ባጣ ቆይ አድርገናቸው በቸገረን እለት ጊዜ ብቻ ነው ለፍለጋ የምንኳትነው፤ ይህ ወቅት ደግሞ ኮ የጣልነውን አንስተው ሌሎች ሲጠቀሙበት ብናይ ያየሁት አይቅረኝ ሆዴን ቆረቆረኝ ያሰኘናል። መቼ ይሆን አንድን ነገር የት አገኘዋለሁ? ምን ያደርግልኛል? ከሚል እሳቤ ወጥተን ያስፈልገናል፣ ይጠቅመናል ለማለት ወጉ የሚደርሰን?” አለ ሃፍረት ህሊናውን እየነዘገው።

የተቀደደ ሱሪውን አስጠቅሞ ለመልበስ ተስፋዬ ከሚባል መኪነኛ ዘንድ ሲሄድ ለሻይ ወጥቶ ስለነበር “እስከዚያው” በሚል ቁጭ አለና ራሱን በራሱ ማስተማር ያዘ፤ ወዳጁን ሲሰፋ ለሁለት ቀናት እድሜ ያህል አይቶት ያውቃልና፤ ታዲያ ይህን ጊዜ በመንገዱ የሚያልፍ አንድ የሚያውቀው ሰው ከግዜር ሰላምታ ጋር ሞራል ለግሶት ሄደ፤ “አያያዝህን ለተመለከተው ልምድ ያለህ እንጂ ለማጅ አትመስልምና ከልብህ አጥብቀህ ብትይዘው ደና ሰፊ ይወጣሃል” በማለት አበረታታው። ከእዚህ በኋላ ገብረየሱስ የልብስ ስፌት

“ሰፍቼም ለበስኩት አይቼም ገመትኩት፣

ሰምቶ መቻልን በሆዴ መዘንኩት።”

ይሉትን ዘፈን እያቀነቀኑ ቁርኝታቸውን አጸኑ።

በእዚህ መሃል በምብራቅ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስኳላውን ያሟሸው ይህ ወጣት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ታዳጊዋ ኢትዮጵያን ቢቀላቀልም አስረኛ ክፍል ላይ የማትሪክ ውጤት አልመጣለትምና ላቅመ መሰናዶ ሳይበቃ በመቅረቱ የተነሳ ከሀገር መውጣትን አልሞ ተከታይ ወንድሞቹን የልብስ ስፌት በማሰልጠን በእግሩ ተካቸውና በሕጋዊ መንገድ ወደሱዳን ወጣ።

እዚያ እንደ ደረሰ ለሀገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ ቢሆንም ፍትፍት የሆነ ጸባይ አለውና ያደረበት የአልጋ ቤቱ ጌታ ከልቡ አቀረበውና ገና ሲያየው ሥራ ያፈላልግለት ዘንድ ወደደ። “እኔ ሥራ እፈልጋለሁ” የሚለውን ቃል ብቻ በአረብኛ አጥንቶ ሥራ ፍለጋ ሲኳትን የቤቱን ደጃፍ የሚያጸዳ አንድ ኤርትራዊ አገኘና “አና ዳየር ሽቁል” ሲለው በሳቅ ተቀበለውና በሄራ ሆስፒታል ለጽዳት ሠራተኝነት አበቃው።

በእዚህ ሙያ ውስጥ እንዳለም ከሥራው በተጓዳኝ የዶክተሮችን መኪና በነጻ በማጠብ ያካበተው ልምድ ዛሬ ለጀመረውና ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል የፈጠረበትን ላባጆ ለመክፈት ቻለ። ከስምንት ወራት በኋላም እጁን የፈታበትን የልብስ ስፌት ሙያ በሱዳን ምድር ለአምስት ዓመታት ያህል ሀብትና ንብረት አፍርቶበት አቅም ሲያበጅ ሀገሩን ያገለግል ዘንድ ወደቀዬው ተመለሰ፤ ይሁን እንጂ ሁሉን ነገር አመቻችተው እንዲጠብቁት ገንዘቡን በአደራ መልክ የሰጣቸው ወዳጆቹ ከዱትና ሕይወቱን አመሰቃቀሉበት።

ቆም ብሎ ሲያስበው ግን ከምንም ነገር ነውና መነሻው ሞራሉን በማበርታት መንገድ ዳር ተቀምጦ መልሶ የጀመረው የልብስ ጥገና ሥራ ከራሱ አልፎ ዛሬ ላይ ለብዙዎች መለወጥ ምክንያት ሆኗል። ብሩክ ካሳሁን ስለገብረየሱስ ሲናገር አንስቶ አይጠግብም። ራሱን ሊያጠፋ እንደነበርና እሱን ካገኘ ወዲህ ግን እሱም በተራው ለሌሎች የሥራ እድል መፍጠሩን አጫወተኝ።

ወንድሙ ዮሐንስ ግርማይም ጠንካራ የሥራ ባህልን ከሱ እንደተማሩ ገለጸልኝ። የሃምሳ አራት ዓመቷ አይናለም ሽፈራውም የሰው እጅ ከመጠበቅ ያዳናቸው ገብረየሱስ ባስጀመራቸው የሻይ ቡና ሥራ እንደሆነ ከምርቃት ጋር ደግነቱን አካፈሉኝ።

ገብረየሱስ በሀገር ሠርቶ የመለወጥ ተምሳሌት ነው። በሕገወጥ መንገድ ተሰዶ በሰው ሀገር ከመሰቃየት ይልቅ በሀገር ውስጥ ከትንሽ ነገር ተነስቶ ትልቅ ቦታ መድረስ እንደሚቻል ምሳሌ የሚሆን ወጣት ነው። የእረኝነትን ውጣ ውረድ አልፎ፤ የተለያዩ የጉልበት ሥራዎችን ሠርቶ፤ ልብስ ሰፍቶ እና መኪና አጥቦ ሕይወቱን ለማቃናት በብዙ ለፍቷል። ከእዚያም አልፎ በሰው ሀገር ያፈራው ገንዘብ በቅርብ ሰዎቹ ቢካድም ተስፋ ሳይቆርጥ ነገን አሻግሮ በማየት የድል አክሊል ተጎናጽፏል። ዛሬ ከራሱም አልፎ ለበርካታ ወጣቶች ተስፋ ሆኗል።

እኔም በሁኔታው ተደምሜ የነገ ሕልሙን በጠየኩት ጊዜ ትልቅ ጋርመንት ከፍቶ ሴቶች በነጻ የሚሠለጥኑበትን እድል እንደሚያመቻች አጫወተኝ። ሕልሙ ይሰምር ዘንድ በመመኘት ጽሑፌን ቋጨሁ።

በሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You