በዶ/ር መኰንን ዲሣሣ፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር
ከትምህርትና ባሕርይ ጥናት ኮሌጅ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
በሀገር ደረጃ፣ ትምህርት ለልማትና ለዕድገት አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው። ትምህርት፣ ግለሰብም ራሱን የሚያቋቁምበትና የሕይወት ዘመኑን የሚመራበት አንድ የሙያ ዘርፍ ነው። የስልሳ ዓመት አዛውንት ልጃቸው ከዩኒቨርሲቲ ሲመረቅ ደስ ብሎዋቸው እቤታቸው ምሳ ጋብዘውኝ፣ ‹‹ልጄ ራሱን ሊችልልኝ ነው፤ ለኔም ድጋፍ ይሆነኛል›› አሉኝ። የሥራ ባልደረባዬ የሆነች የጽዳት ሠራተኛ፣ ሁለት ልጆቹዋ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት በማግኘታቸው ከችግር ራሳቸውንና እናታቸውን ነፃ እንደሚያወጡ፣ ደስታዋንና ተስፋዋን አጫወተችኝ።
በተቃራኒ፣ በሀገራችን፣ የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር መጨመርና የከፍተኛ ትምህርት ዕድል መስፋፋት መልካም ቢመስልም፣ አብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሚመረቀው ለሥራ አጥነት እና ለስደት ነው። ይህ ደግሞ፣ በየዓመቱ ይጨምራል። ለዚህ ግዙፍ ሀገራዊ ችግር እንደ ዋና ምክንያት ሁሌ የሚወሳው፣ የሀገራችን ኢኮኖሚ ታዳጊ መሆን ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የትምህርት አሰጣጣችንም ለወጣቱ ሥራ አጥነት እና ስደት አሉታዊ አስተዋፅኦው ከፍተኛ መሆኑን ተገንዝበን፣ መፍትሔ መሻት ያስፈልጋል።
ወደ 45 የሚሆኑ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎቻችን ትኩረታቻው በንድፈ-ሐሳብ (theory) ላይ በመሆኑ፣ በጆሮ መስማትን እንጂ፣ በእጅ መሥራትን አያስተምሩም። የግሎቹም ተመሳሳይ ናቸው። የንድፈ-ሐሳብ ትምህርት ለመንደርደሪያ ወይም መነሻ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን፣ ንድፈ-ሐሳብ የከፍተኛ ትምህርት አልፋና ኦሜጋ ሊሆን አይችልም። አሁን እየሆነ ያለው ይህ መሆኑን ተማሪዎች ምስክሮች ናቸው፤ መምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ያውቁታል። ዩኒቨርሲቲዎቻችን፣ ኮሌጆቻቸውና የትምህርት ክፍሎቻቸው በስያሜ ይለያዩ እንጂ፣ ሁሉም ከመጀመሪያ ዓመት እስከ መጨረሻ፣ የሚያተኩሩት በንድፈ-ሐሳብ ላይ ነው።
የዚህ ዓይነት የትምህርት አሰጣጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉት፦
- የመማር-ማስተማር መሠረታዊ ሂደትን፣ ማሰማት/መንገር (lecture) ብቻ ያስመስላል። ሂደቱ ሙሉ የሚሆነው፣ ማሳየት (demonstration) እና ትግበራን (practice) ጨምሮ ነው።
- ትምህርት የዕውቀት (knowledge) እና ክህሎት
(skills) ቅንብር መሆኑም ተዘንግቷል። ዕውቀት ከንድፈ-ሐሳብ ሊገኝ ይችላል፤ ክህሎት ግን የሚገኘው ከእይታና ከትግበራ (practice) ነው። የዕውቀት መገለጫው ክህሎት ሆኖ ሳለ፣ ንድፈ-ሐሳብን በዋናነት ያማከለ ትምህርት፣ ተማሪዎችን በዲግሪ ከማስመረቅ ባለፈ ለሥራ ብቁ አያደርጋቸውም። ምሩቃኑም ዲግሪ አለን ከማለት ሌላ፣ በቃል ወይም በጽሑፍ የሚገልጹትም ሆነ፣ በተግባር የሚያሳዩት ነገር የላቸውም። ዲግሪ የምስክር ወረቀት እንጂ ሙያ አይደለም። ሥራ ለማግኘትም ሆነ ሥራ ለመፍጠር ሙያ የግድ ይላል።
- ንድፈ-ሐሳብን በሚገባ ለመረዳት የሚቻለው ክህሎት ሲታከልበት ነው። ቻይኖች መማር-ማስተማርን አስመልክቶ እንዲህ ይላሉ ይባላል፦ከሰማሁ እረሳለሁ።
- ካየሁ አስታውሳለሁ።
- ከሠራሁ እረዳለሁ።
እንደ ፍልስፍና እና ታሪክ ያሉ የተወሰኑ ትምህርቶች፣ ትኩረታቸው በንድፈ-ሐሳብ ላይ ቢሆንም፣ ተማሪዎች መረዳታቸውን ለማረጋገጥ በእያንዳዱ የትምህርት ክፍለ ጊዜ፣ ማጠቃለያ (summary) መስጠት፣ ተማሪዎችን በትናንሽ ቡድን በመክፈል ምን እንደተማሩ፣ ምን እንደተረዱ፣ ምን እንዳልተረዱና የራሳቸው አስተያየት ምን እንደሆነ፣ ማወያየት (tutorial) ለመስኮቹ የተለመዱ የማስተማሪያ ዘዴዎች ናቸው።
- ትምህርት ኢንቨስትመንት (investment) እና የዕድሜ ዘመን ዋስትና (life long guarantee) መሆኑም ተረስቷል። ብዙ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚመጡት የገቢ አቅማቸው ደካማና የደካማ ደካማ ከሆኑ ቤተሰቦች በመሆኑ፣ የትምህርት ዋስትናው ለምሩቁ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቡም ጭምር ነው። ዳሩ ግን፣ አብዛኛው የዛሬ ምሩቅ በሥራ እጦት ምክንያት ራሱን ማቋቋም አቅቶት የአቅመ ደካማ ቤተሰብ ጥገኝነት እየመረረው፣ መጨረሻው ለማይታወቅ ስደት እየተዳረገ ይገኛል። ትምህርት ለሀገር ልማትና ዕድገትም ዋስትና ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው የሙያ ብቃትን ያማከለ ትምህርት (Competency-Based Education) ሲኖር ነው። የሀገራችን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ንድፈ-ሐሳባዊ ሆኖ፣ ተማሪዎች የሚመረቁት በሙያ መስኮች ሳይሆን በትምህርት ዘርፎች ላይ ነጥቦችን በማጠራቀም ነው። የዚህ አይነት የትምህርት አሰጣጥ፣ አራት ወይም አምስት ዓመት ተማሪዎች ከክፍል ሳይወጡና የሥራ ዓለም ምን እንደሚመስል ሳያውቁ፣ ነጥቦችን ማጠራቀም (Credit-Based Education) መሠረት ያደረገ ነው እንጂ፣ የሙያ ብቃትን አያስገኝም። የሙያ ብቃትን የማያስገኝ ትምህርት፣ ትምህርታዊ ጽንሰ-ሐሳብ (concept) ላይ የተመሠረተ አይደለም።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል ድርጅት (UNESCO) ባደረገው ድንጋጌ (declaration) መሠረት፣ ለግለሰብ፣ ለማሕበረሰብና ሀገር ፋይዳ ያለው የትምህርት መርሐ-ግብር (program) በአራት የትምህርት ምሰሶዎች (The Four Pillars of Education) ላይ መዋቀር ይገባዋል። እነርሱም፦
- ለማወቅ መማር (Learning to know)
- ለመሥራት መማር (Learning to do)
- ለመሆን መማር (Learning to be)
- አብሮ መኖርን መማር (Learning to live together)
ንድፈ-ሐሳባዊና ነጥቦችን ማጠራቀም ያማከለ የሀገራችን ትምህርት፣ በመጀመሪያው ምሰሶ ላይ የተንጠለጠለ ነው። ሁለተኛው ምሰሶ (ለመሥራት መማር) ተረስቷል። ሙያ/ሥራ ለሰው ልጅ፣ የሕልውናው መሠረት በመሆኑ፣ ያለ ሥራ፣ ‹‹መሆን›› (to be) እና ‹‹አብሮ መኖር›› (living together) ትርጉም የላቸውም። አራቱ ምሰሶዎች የተያያዙና ተመጋጋቢ ናቸው። ይህ ትምህርታዊ ጽንሰ-ሐሳብን የማይከተል የትምህርት መርሐ-ግብር ፍሬያማነቱ ደካማ ነው። ስለዚህ የሀገራችን ከፍተኛ ትምህርት ግለሰባዊ፣ ማሕበረሳባዊና ሀገራዊ ጠቀሜታው ሳይሆን ጉዳቱ ጎልቶ እየታየ ነው። ነገር ግን፣ አሁንም በኢንተርኔት (Internet) ላይ ያሉትን የዓለም የትምህርት መርሐ-ግብሮችን መገልበጥና የዲግሪን ደረጃ ከ1ኛ እስከ 3ኛ (BA/BSC,Master’s, PhD) ከፍ ማድረግ ያለ ገደብ ቀጥሏል። ዩኒቨርሲቲዎችም በዚህ ረገድ ውድድር ላይ ያሉ ይመስላል። ይህ አካሄድ ሙያን አይፈጥርም፤ የማይፈለገውን ሥራ አጥነትን ያባብሳል። ሙያን ለመፍጠር ብቸኛው አማራጭ ሙያን ማስተማር ነው። የትምህርታችንም ዋና ዓላማ፣ በየሙያ መስኩ የተካኑ አምራች ዜጎችን ማፍራት እንደሆነ ብዙ ተፅፏል፤ ብዙም ተነግሯል። ይህ የማይተገበር ከሆነ፣ ትምህርታችን ግቡ ምንድን ነው?
- በአሁኑ ዘመን፣ ንድፈ-ሐሳብ ብቻ ለሆነ ዲግሪ የሰው ኃይል ገበያ አናሳ ነው። ገበያው በብዛት የሚፈልገው ዕውቀትንና ክህሎትን ማቀናበር የሚችል ባለሙያን ስለሆነ፣ ንድፈ-ሐሳብን ከክህሎት ጋር ማጣመር አማራጭ የለውም። የዩቨርሲቲ ተማሪዎች የዘወትር ጥያቄም ‹‹ተመርቀን ሥራ የምንሠራበት ጥራት ያለው ትምህርት ይሰጠን፤ አሁን ንድፈ-ሐሳብ (theory) ብቻ ነው የምንማረው›› የሚል ነው። ተማሪዎች የምንሰጣቸው ትምህርት ከወቅቱ ጋር እንደማይሄድ ማወቃቸውን እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል ‹‹መምህራን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ማስተማር አለባቸው።›› አሠሪዎችም፣ ምሩቃን (ሳይንስና ቴክኖሎጂ መስክን ጨምሮ) ክህሎት አልባ መሆናቸውን በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ ይናገራሉ። ተማሪዎቻችን የምንሰጣቸው ትምህርት ውጤት ስለሆኑ፣ ያላዩትን መገንዘብና ያልተለማመዱትን መሥራት አለመቻላቸው የሚጠበቅ ነው። ታዲያ እስከ መቼ?
የሀገራችን ዘመናዊ ትምህርት የተቀዳው ከምዕራቡ ዓለም ነው። እዚያ፣ ክህሎት አልባ የንድፈ-ሐሳብ ትምህርት ከ1968 እአአ አቆጣጠር ጀምሮ ከባድ ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ፣ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው የሙያ ብቃትን ያማከለ ከፍተኛ ትምህርት (Competency-Based Higher Education) መስጠት ከጀመሩ ብዙ ዓመታት አልፈዋል፤ ተፈላጊነቱም ተመስክሮለታል። እኛ ወደዚህ የምንሸጋገረው መቼ ነው? አሁን ያለው የሀገራችን ከፍተኛ ትምህርት በምን መመዘኛ ነው እንዳለ የሚቀጥለው?
የመፍትሔ ሐሳቦች
የትምህርት አሰጣጣችን ከተሻሻለ፣ አብዛኛው ምሩቅ ባለሙያ ስለሚሆን ሥራ አጥነት እና አስከፊው ስደት እያነሰ ይሄዳል። አብዛኛው ወጣት ባለሙያና አምራች ዜጋ ከሆነ፣ የሀገራችን ኢኮኖሚ ሊያድግ ይችላል፣ ያደገ ኢኮኖሚ ለብዙሃን ሥራን ይፈጥራል፣ የወጣቱ ኑሮ ይሻሻላል፤ ወንጀልም ይቀንሳል። እነዚህን ከግብ ለማድረስ፣ የትምህርት አሰጣጣችን እንደሚከተለው መደራጀት ይኖርበታል፦
- ዕውቀትና ከህሎትን፣ በማሳያ/ሠርቶ ማሳያ ቤተሙከራ (demonstration laboratory) እና በመለማመጃ ቤተሙከራ (experimental laboratory) ማጣመር፣ ቤተ ሙከራዎቹን ቋሚ የትምህርት ሂደት (መስማት፣ ማየት፣ መስራት) አካል ማድረግ እና በዩኒቨርሲቲዎቻችን ቤተሙከራዎቹ መኖራቸውን ማረጋገጥ፤
- ተማሪዎች ወደ ትምህርት ከፍል የሚመደቡት ዩኒቨርሲቲዎች በሚሰጡት የዝንባሌ ጠቋሚ ፈተና (aptitude test) መሠረት ቢሆን፣ ውጤታማነት ይጨምራል፤ከፍላጐት ማነስ የተነሳ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥራቸው ይቀንሳል።
- ለሁሉም ተማሪዎች መጀመሪያ ዓመት ላይ መሠረታዊ የኮምፒዩተር አጠቃቀም ክህሎት (basic computer skills) ቢሰጥ፣ ብቃት ላለው ትምህርት ዝግጁ ያደርጋቸዋል። በአሁኑ ዘመን፣ መሠረታዊ የኮምፒዩተር ክህሎት፣ አንዱ የመማር-ማስተማር መረጃ (teaching aid) ስለሆነ ዩኒቨርሲቲዎች የኮምፒዩተር ቤተሙከራ (computer laboratory) ያስፈልጋቸዋል።
- የሙያና የአካዳሚ ትምህርት መርሐ-ግብርን መለየት፤ ሁለቱ ሲደባለቁ ተማሪው ምን ለመሆን እንደሚማር ግልፅ ስለማይሆንለት፣ ለትምህርቱ ያለው የዓላማ ጽናት (seriousness of purpose) እና ተነሳሽነት (motivation) ዝቅተኛ ይሆናል። በተጨማሪም፣ የትምህርቶቹ ጥራትና አግባብነት ይጋረዳሉ።
- የሙያ መርሐ-ግብር፣ መግቢያው (introduction) ንድፈ-ሐሳብ ነው። ከዚህ ተነስተው፣ተማሪዎች ሙያ ላይ የሚያተኩሩ የቤት ሥራዎችንና አጫጭር ፕሮጀክቶችን ያከናውናሉ። ከዚህ በኋላ ተማሪዎች ለ3 ወር (practicum) በፋብሪካዎች፣ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ተመድበው ምልከታ (observation) እና የሥራ ሙከራ (work practice) ያደርጋሉ። ቀጥሎም ወደ ክፍል ተመልሰው፣ ከመምህራን ጋር ንድፈ-ሐሳብን ከክህሎት ጋር የማዛመድ ትምህርት ይካሄዳል። ተማሪዎች እንደገና ከ6-9 ወር (internship) ሥራ ላይ ተሰማርተው እየሠሩ፣ ለምረቃ ፅሁፋቸው መረጃና ማስረጃ (data) ይሰበስባሉ። ተማሪዎች ከክፍል ውጭ በመስክ የሚያሳልፉዋቸው ጊዜያት፣ የአጠቃላይ ትምህርታቸው ግምገማ አካል ይሆናል። በመጨረሻ፣ ተማሪዎች በሰለጠኑበት የሙያ መስክ የምረቃ ፅሁፋቸውን ያቀርባሉ።
- የአካዳሚው መርሐ-ግብር ትኩረት ጥናትና ምርምር ላይ ሆኖ፣ ጥናቱና ምርምሩ ሀገር ገንቢ መሆናቸው እጅግ አስፈላጊ ነው።
- ለሁለቱም መርሐ-ግብሮች አስፈላጊ የሆኑ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ፣ የትምህርቶቹ አካል መሆን ውጤታማነትን ይጨምራል። በአሁኑ ጊዜ፣ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ክህሎት የማይጠይቅ ሙያ ያለ አይመስለኝም።
እነዚህን የመፍትሔ ሐሳቦች አጢኖ፣ የማሻሻያ እርምጃ መውሰድ በመጀመሪያ የሚጠበቀው ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ነው። የወጣት ምሩቃን ሥራ አጥነትና ለስደት መዳረግ በአብዛኛው ሕዝባችን ቤት ያለ ስለሆነ፣ትምህርትን አስመልክቶ፣ ሕዝባዊ ውይይትም አስፈላጊ ይሆናል። በትምህርት ጉዳይ ላይ ሁሉም ዜጋ ባለድርሻ አካል ነውና። እያንዳንዱ ወላጅም፣ ልጆቹ ለሥራ አጥነት እጩ እንዳይሆኑ ቀደም ብሎ አማራጮችን መጠቆም ያለበት ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2013