በፍትህ ሥርዓት ውስጥ ፍትሃዊ ውሳኔ ለመስጠት እና ፍትህ ለማስፈን ምስክሮች የማይተካ ሚና አላቸው። ምስክሮች በወንጀል ፍትህ ሥርዓት ውስጥ የወንጀል ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ በምርመራ ሂደት መሳተፍ እና በችሎት ክርክር ምስክርነት በመስጠት የፍትህ ሥርዓቱን ያግዛሉ።
ምስክሮች የሚሰጡት ምስክርነት በተቃራኒው በተከራካሪ ወገን ወይም በተከሳሽ ላይ ፍርድ የሚያስከትል በመሆኑ ተከሳሾች በወንጀል ምርመራ እና በክስ ሂደት በምስክሮች ወይም በቤተሰቦቻቸው ላይ ጫና በማሳደር እና በማስፈራራት የፍትህ አስተዳደርን ለማደናቀፍ ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ።
ስለሆነም ለወንጀል ምስክሮች ጥበቃ በማድረግ ከጥቃት እና ከአደጋ ስጋት ነፃ የሆነ ምስክርነት እንዲሰጡ ማስቻል አስፈላጊ ነው። በዚህ ምክንያት በዓለም ላይ የተለያዩ አገራት የምስክሮች ጥበቃ ህግን በማውጣት በስራ ላይ ያዋሉ ሲሆን ህጎቹ በአብዛኛው ጥበቃ የሚያደርጉት ለከባባድ እና የቅጣት መጠናቸው ከፍተኛ ለሆኑ ወንጀሎች ነው።
ኢትዮጵያም የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 በማውጣት በስራ ላይ አውላለች። በአዋጁ ለወንጀል ምስክሮች ከሚደረጉ የጥበቃ እርምጃዎች ውስጥ ምስክርነትን ከመጋረጃ ጀርባ መስጠት ይገኝበታል። ውድ አንባቢዎቻችን የዝግጅት ክፍላችንም በኢትዮጵያ ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት ስለሚሰጥበት ሁኔታና አግባብ እንዲሁም ከተከሳሽ መብት አንፃር የህግ መሰረቱን እንደሚከተለው ይዳስሳል።
የምስክሮች ጥበቃ ህግ በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ የተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ህግ አዋጅ ቁጥር 434/1997፤ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012፤ በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/2012፤ በ2003 የወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ እና የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 ለምስክሮች ጥበቃ ስለማድረግ ሰፊ ሽፋን ሰጥተዋል።
አዋጅ ቁጥር 699/2003 ተፈፃሚ የሚሆነው በሕግ የተደነገገው የፅኑ እስራት መነሻ ከግምት ሳይገባ አስር ዓመትና ከዚያ በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ሊያስቀጣ በሚችል የወንጀል ድርጊት ተጠርጣሪ ላይ የሚሰጥ ምስክርነትን ወይም ጥቆማን ወይም የሚካሄድ ምርመራን በሚመለከት ሆኖ የወንጀል ድርጊቱ ያለምስክሩ ወይም ያለጠቋሚው ምስክርነት ወይም ጥቆማ በሌላ ማናቸውም መንገድ ሊረጋገጥ ወይም ሊደረስበት የማይችል ሲሆን፤ እና በምስክሩ፣ በጠቋሚው ወይም በቤተሰብ ህይወት፣ አካላዊ ደህንነት፣ ነጻነት ወይም ንብረት ላይ ከባድ አደጋ ይደርሳል ተብሎ ሲታመን ነው።
በአዋጁ አንቀጽ 4 ስር የጥበቃ እርምጃ አይነቶች በዝርዝር የተቀመጡ ሲሆን እርምጃዎቹ በተናጠል ወይም በጣምራ ለጥበቃ ተጠቃሚ ተፈጻሚ ሊደረጉ ይችላሉ። በአዋጁ ከተዘረዘሩት የጥበቃ እርምጃዎች ውስጥ የአካልና ንብረት ደህንነት ጥበቃ፣ የመኖሪያ ስፍራ መቀየርን ጨምሮ ደህንነቱ የተጠበቀ የመኖሪያ ቦታ መስጠት፣ ማንነትንና ባለንብረትነትን መደበቅ፣ ማንነትን መቀየር፣ ለራስ መጠበቂያ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ መስጠት፣ የፍርድ ሂደት ተጀምሮ ምስክርነት እስከሚሰጥ ድረስ የምስክር ማንነት እንዳይገለጽ ማድረግ፣ ምስክርነት በዝግ ችሎት እንዲሰጥ ማድረግ፣ ምስክርነት በአካል ሳይታይ ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆኖ ወይም ማንነትን በመሸፈን እንዲሰጥ ማድረግ፣ ማስረጃ በኤሌክትሮኒክስ ወይም በሌላ የተለየ ዘዴ እንዲቀርብ ማድረግ ይገኙበታል።
ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት ስለመስጠት የህግ መሰረቱ እና ህገ-መንግስታዊነቱ
በወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች አዋጅ 699/2003 አንቀፅ 4/1/በ የተገለጸው የምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት መስጠት የሚያስፈልገው ከተከሳሽ ጋር የዐይን ግንኙነት ስለማይኖራቸው ያለፍርሃት የሚያውቁትን ሐቅ ለማስረዳት ስለሚያስችላቸው እና ተከሳሽ የምስክሩን ማንነት መለየት ስለማይችል በምስክሮች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ዛቻ እና ማስፈራራት እንዲሁም በህይወት እና በንብረት ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋን ማስቀረት ስለሚያስችል ነው።
ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት እንዲሰጡ ሲደረግ ሁለት ተቀናቃኝ ፍላጎቶች ይንፀባረቃሉ። እነዚህም በአንድ በኩል ፍትህ ለማገዝ ሲሉ ህይወታቸው እና ንብረታቸው በተከሳሻ ሊደርስ ከሚችል የአደጋ ስጋት ውስጥ ለገባ ምስክሮች መደረግ ስላለበት ጥበቃ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የተከሳሾች መብት ነው።
በዚህም በሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (ICCPR) አንቀፅ 14 እንደተደነገገው የተከሰሱ ሰዎች የቀረበባቸውን ማስረጃ የመከላከል እና ምስክሮችን መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብት አላቸው። በተመሳሳይ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 20(1) እና (4) ለእነዚህ የተከሳሽ መብቶች እውቅና ተሰጥቷቸው ይገኛሉ። ከዚህ አንጻር የምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት መስጠት ህገ-መንግስታዊ አይደለም የሚሉ ሰዎች አሉ።
ይሁን እንጂ ማንነት ሳይገለፅ ምስክርነት ከመስጠት ጋር በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ የወንጀል ችሎት ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ተነስቶ የነበረ ሲሆን፤ ጉባዔው ፍርድ ቤቱ የላከውን የትርጉም ጥያቄ በመ/ቁ 2356/2009 መመርመሩን በመጥቀስ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) ድንጋጌን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥቷል።
በሰጠው ማብራሪያ በአንቀጽ 20(4) ምስክሮችን በሚመለከት የተደነገገው የተከሰሱ ሰዎች የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ መብት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ እንጂ፣ የምስክሮችን ስም ዝርዝርና አድራሻ እንዲደርሳቸው ግዴታ የሚጥል አለመሆኑን ገልጿል።
በሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 20(4) ላይ ለተከሳሾች መብት የሰጠበት ምክንያት፣ ፍትሐዊ የሙግት አካሄድ እንዲኖር መሆኑን አክሏል። ተከሳሽ የምስክሮችን ስምና አድራሻ ማወቁ ፍትሐዊ የሙግት አካሄድን ከማሳካት ይልቅ፣ ምስክሮችን ለአደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች እንዳይፈጸሙ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠርና በሕጎች አግባብ እንዲወሰን ለማድረግ መሆኑን ጉባዔው አስረድቷል።
በመሆኑም ተከሳሾች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) መሠረት የምስክሮችን ስም ዝርዝር እንዳይደርስ ማድረግ፣ ከተገለጸው መብት ጋር የማይጋጭና የሕገ መንግሥቱን መርህ የተከተለ መሆኑን በመግለጽ፣ የቀረበለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።
ይህ የህገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ውሳኔ የሚያመለክተው ለምስክሮች ጥበቃ ሲባል ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት እንዲሰጡ ወይም የምስክሮች ማንነት እንዳይገለፅ ማድረግ በህገ-መንግስቱ ላይ ከተቀመጠው የተከሰሱ ሰዎች መብት ጋር የማይቃረን እና ህገ-መንግስቱን የተከተለ ህግ መሆኑን ነው።
ምስክሮች ማንነታቸውን ሳይገልጹ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ምስክርነት እንዲሰጡ ቢደረግም ተከሳሾች የቀረቡባቸውን ምስክሮች በችሎት መስቀለኛ ጥያቄ ከመጠየቅ የሚያግዳቸው ባለመሆኑ የተከሰሱ ሰዎች የመከላከል መብት ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ አለ ማለት አይቻልም።
ስለሆነም ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት እንዲሰጥ ማድረግ ፍትህ ለማገዝ ሲሉ ህይወታቸውን ለአደጋ መጋለጥ አሳልፈው ለሰጡ ምስክሮች ጥበቃ ሲባል መከናወን ያለበት የፍትህ ሥነ -ሥርዓት ህገ-መንግስታዊ ነው።
በአጠቃላይ ፍትህ በማገዝ ሂደት ህይወታቸው የአደጋ ስጋት ውስጥ ለሚገኝ የወንጀል ምስክሮች የሚወሰዱ የጥበቃ እርምጃዎች ወንጀል ፈፃሚዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እና የህብረተሰቡ ሰላማዊ ኑሮ እንዲረጋገጥ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
ምንጭ:- ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2013