ግርማ መንግሥቴ
ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ሳይቋረጥ እየተነገረና እየተደረገ ያለው ሁለት ነገር ነው። “እባካችሁ ጥንቃቄ እናድርግ” እና “ክትባቱ በየደጁ እየተቃረበ ነው” የሚል። እኛም ሁለተኛውን ትተን የመጀመሪያው ላይ አተኩረን እንነጋገራለን። ምንም እንኳን ጉዳዩ “የሰለቸ” ቢመስልም ወደ ተግባር ተለውጦ እስካልታየ ድረስ ይህን ማድረጉ፤ “እባካችሁ ጥንቃቄ እናድርግ” ወዘተ ማለቱ መቀጠሉ የማይቀር ይሆናል። በተለይ ይህን መዘናጋት በአይን በብረቱ እየተመለከቱ እንዳላዩ ማለፍ የሙያ ግዴታን አለመወጣት ብቻ ሳይሆን ከራስ ጋር መጣላትም ጭምር ነው።
በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ያለው ኮቪድን የተመለከተ ተጨባጭ እውነታ የመከላከሉን ተግባር፤ ማለትም የሚመለከተው አካል “ኮቪድ ፕሮቶኮል” በሚል አጠቃላይ መመሪያ ስር ያስቀመጣቸውን የመከላከል ተግባራት እርግፍ አድርገን መተዋችን ነው። በቃ ትተነዋል። በተለይ ድሬዳዋን በመሳሰሉ ትላልቅ ከተሞች ይህ በይፋ የሚታይ ተግባርና ስጋትን የደቀነ አደጋ ነው።
ኮቪድና ያለበት ይዞታ
የኮቪድን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መንግስት በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት ፈጣን መረጃዎችን በየወቅቱ እየወሰደ፤ መረጃዎችንም እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን መረጃዎቹ ከሚሰጡባቸው ማሰራጫዎች መካከልም ማህበራዊ ድረ-ገፅ የሆነው ፌስ ቡክ ይገኝበታል። ከዚህ አንፃር የመመሪያዎችና ማስጠንቀቂያ ደውሎች ጥሪ በቀላሉ ተደራሽ ናቸው ማለት ነው። ችግሩ ያለው ትኩረት መነፈጋቸው ላይ ነው።
ኮቪድን በተመለከተ ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው ስርጭቱ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ሲሆን በአገራችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ፤ የተያዦችም ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ፤ ሰዎችም በየእለቱ ህይወታቸው እያለፈ ይገኛል።
ይህ ሁሉ ሲሆን በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ የመጠንቀቁና እራስንም ሆነ ቤተሰብን ከቫይረሱ የመከላከል ሁኔታ አይታይም። እየታየ ያለው ነገር ምንም የሌለ በማስመሰል ከኮቪድ በፊት በነበረው የአኗኗር ዘይቤ የመቀጠሉ ጉዳይ ነው። ችግሩ ይሄ ነው።
ኮቪድን ስለመከላከልና መፍትሄው
ወረርሽኙ ከቪድ በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አማካኝነት በይፋ ከተገለፀ አንድ አመትን ዘሎ ሁለተኛውን ተያይዞታል። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የሆነውን እጅግ ዘግናኝና ሁሉንም ሰው አንገት ያስደፋ፣ የመኖር ህልውናውን ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲከት ያስገደደ፣ ነገ ተራው የኔ ቢሆንስ በሚል ሲያስጨንቅ የነበረውን ያን ሁሉ ያልታሰበ ሰብአዊ ቀውስ እዚሁ መድገም አያስፈልግም።
በዚህ አንድ ዓመት ከምናምን ሂደት ውስጥ አዋጪ ሆኖ የተገኘውና በባለሙያዎች ሲመከር የቆየው መፍትሄ እራስንና ሌላውንም ከቫይረሱ መከላከል ሲሆን፤ የመከላከያ መንገዱም ከእጅ ስልካችን ላይ ጀምሮ በሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ጉሮሮ ሲተላለፍ፤ በሁላችንም ጆሮ ሲንቆረቆር የሚውለው መመሪያ ነው።
መመሪያው በውስጡ ያካተታቸው በርካታ መርሆዎች ቢኖሩም ዋና ዋናዎቹም ርቀትን መጠበቅ፣ ማስክ ካለማድረግ መቆጠብ፣ እጅን በውሃና ሳሙና ሙልጭ አድርጎ መታጠብ፣ አንዳንድ ነገሮችን በነኩ ወይም ባደረጉ ቁጥር ወዲያውኑ እጅን በሳኒታይዘር ማፅዳት ናቸው። አሁን ችግሩ አብዛኞቻችን ከእነዚህ ጋር ተለያይተናል። በመሆኑም አደጋ አለ ማለት ነው።
የት ድረስ ተዘናግተናል?
መዘናጋታችን ከአድማስ ባሻገርን ሁሉ ያለፈ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም። እየኖርን ያለነው በእውነተኛው ዓለም (በኮቪድ የተወረረ) ውስጥ ሳይሆን እራሳችን በፈጠርነውና ከኮቪድ ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ ነው። እየኖርን ያለነው መኖር ያለብንን ሳይሆን ተቃራኒውን ነው። እያደረግን ያለነውም እንደዛው።
ሰሞኑን ለስራ ጉዳይ ወደ ድሬ ዳዋና አካባቢው ለስራ ተዘዋውረን እንደተመለከትነው በአካባቢው ያለው ፀረ-ኮቪድ እንቅስቃሴ ይህ ከላይ ቁጭ ያደረግነው አንቀፅ በትክክል የሚገልፀው ነው የሚሆነው።
ለጊዜው ስለ ድሬዳዋና አካባቢው ስላጋጠመን እናውራ እንጂ ይህ በእነዚህ አካባቢዎች የተመለከትነው ጉዳይ በሌሎች የለም ማለት አይደለም። እስከዛሬ ስንለው እንደ ነበር እና ወደ ፊትም እንደምንለው ችግሩ ሁሉም ጋር ነው ያለው። ልዩነቱ ዛሬ ስለ ድሬዳዋና አካባቢው ማውራታችን ብቻ ነው።
በድሬ ምንም የጎደለ ነገር የለም። ከፍቅር ጀምሮ ሁሉ በእጅ ሁሉ በደጅ ነው። ከተማዋ እራሷ ለዚህ ነው መሰል የተፈጠረችው። መስተንግዶዋ ሁሉንም በእኩል ደረጃ በማየት ላይ የተመሰረተ ነው። ማንም ከማንም አይበልጥም፤ አያንስምም።
ድሬ በዘመኑ የፖለቲካ ወረርሽኝ ካልተጠቁት ከተሞች አንዷ ስትሆን “እኛ” እና “እነሱ” የሚሉ አግላይና ነጣይ አስተሳሰቦች በድሬ ምንም አይነት ስፍራ የላቸውም። እነዚህን ለማራገብ አልፎ አልፎ ሙከራ ቢኖርም እንኳ ነዋሪው ምንም አይነት ጆሮ ባለመስጠቱ መርዙ ወደ ከተማዋ ሊሰርፅ አልቻለም፤ ወይም ሁሌም ይዘራል ሁሌም ይመክናል። (ይህ እራሱን ችሎ ሌላ ጊዜ የምናየው ይሆናልና እንለፈው።)
የአሁኑ ትልቁ፣ አሳሳቢና አስጊው ችግር ኮቪድን በተመለከተ የሚታየው መዘናጋትና አጠቃላይ ነዋሪው የ “ኮቪድ ፕሮቶኮል” ን ተግባራዊ ያለማድረጉ ጉዳይ ነው። በከተማዋ ምንም አይነት ጥንቃቄ አይታይም።
ድሬ በከፍተኛ ደረጃ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ጎልቶ የሚታይባት ከተማ ነች። ባብዛኛው የእንቅስቃሴው አስኳል ቢዝነስ ሲሆን በከፍተኛ ደረጃ የህዝብ እንቅስቃሴ የሚታይበትና የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚስተዋልበት ነው። ከአሸዋ ሜዳ ጀምሮ እስከ እላይኛው የገበያ ማእከል ድረስ ያለውን ብቻ እንኳ ለተመለከተ ያለ “ኮቪድ ፕሮቶኮል” የሚታሰብ አይደለም። እውነታው ግን እሱ ሳይሆን ያለ “ኮቪድ ፕሮቶኮል” ህይወት ሲንቀሳቀስ መታየቱ ነው።
ምን ይበጃል?
ለሁላችንም የሚበጀው አንድ ነገር ብቻ ነው። እሱም የሚነገረው ሁሉ እውነት መሆኑን አምኖ መቀበል። ኮቪድ የዓለም ስጋት መሆኑን፤ የሰውን ልጅ እንደ ቅጠል እያረገፈ መሆኑን፤ ከተያዙ መዳን ከባድ መሆኑን፣ ማስክ ማድረግ ከራስ ባለፈም ማህበራዊ ሃላፊነት መወጣት መሆኑን፤ ለ”ኮቪድ ፕሮቶኮል” መገዛት ማለት ከግል ህይወትም ባለፈ ለአገርና ወገን የሚያስገኘው ትርፍ ቀላል አለመሆኑን መረዳት ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2013