ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሀገራችን የሉዓላዊነት፣ የፍትህ፣ የአንድነት ጉዳይ እና ከድህነት ያወጣናል ብለን ተስፋ የጣልንበት አሻጋሪያችን ትልቁ ፕሮጀክት ነው። የእያንዳንዳችን አሻራ ያረፈበት፣ በራሳችን ገንዘብና እውቀት የምንገነባው፣ የምንኮራበት የሀገራችን መለያ ሰንደቅ ዓላማችን ጭምር ነው።
ፕሮጀክቱ ለኢትዮጰያውያን የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የመኖርና ያለመኖር፤ ኤሌክትሪክ አግኝቶ ወደ ብርሃን የመውጣትና በጥቅጥቅ ጨለማ ውስጥ ሲዳክሩ የመኖር ያለመኖር ምርጫ ያህል ነው። በመሆኑም ነው በአንድ ልብ በአንድነት መንፈስ ወደ ስራ የተገባውና አሁን የደረሰበት ደረጃ የደረሰው።
የፕሮጀክቱ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ከመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁንም ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ከጉሮሮአቸውና ከኪሳቸው ቀንሰውና መቀነታቸውን ፈትተው ቦንድ በመግዛት እና ስጦታ በማበርከት እየደገፉ የሚገኙት።
ይሁን እንጂ ገና የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ፕሮጀክቱ እንዳይጀመር ከተጀመረም እንዳይጠናቀቅ በርካታ እንቅፋቶች ከውጭም ከውስጥም አጋጥመዋል። ፕሮጀክቱ አቅም፣ ብቃትና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ባለመያዙና ባለመመራቱ ምክንያት የግንባታ ላይ ስህተቶች ተፈጥረዋል። ነገር ግን እድሜ ለለውጡ፤ ሳይረፍድ ማስተካከል ተችሏል፡፡
የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ 10 ዓመቱን ሊደፍን በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ የቀሩት ይህ ፕሮጀክት በአምስት ዓመት በ80 ቢሊዮን ብር ወጪ ይጠናቀቃል ተብሎ ወደ ስራ ቢገባም በታሰበው ልክ መጓዘ አልቻለም። ሆኖም ይሄንን የማረምና የማስተካከሉ ስራ በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶት በመሰራቱ አሁን በትክክለኛው መንገድ ላይ ይገኛል። እነሆ ግንባታውም ከ 78.8 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡
በህዝቡ በሚደረገው ያላሰለሰ ድጋፍ ፤ በመንግስትም በሚካሄደው ቆራጥ አመራር፣ ያልተቆጠበ ክትትልና ቁጥጥር ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ያለበትን ግድፈት አርሞ ወደ ስራ በመግባቱ ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት መያዝ ተችሏል። ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትም በተያዘው ዓመት እንደሚሞላና የመጀመሪያ የሃይል ማመንጨት የሙከራ ስራ እንደሚጀመር በዕቅድ ተይዞ እየተሰራ
ይገኛል።
ሆኖም አሁንም የውስጥና የውጭ ኃይሎች በጋራ አብረው ሊያደናቅፉ ጥረት አድርገዋል። በተለይም ግብጽ ከምስረታው ጀምሮ ልዩ ልዩ የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ሰበቦችን በመደርደር አሁንም ድረስ ፕሮጀክቱ ስኬታማ እንዳይሆን አቅሟን ሁሉ አሟጣ መጠቀም ላይ ትገኛለች፡፡
በተጨማሪም የግድቡ እውን መሆን ከጫፍ ሲደርስ ሌሎች ጣልቃ ገቦችም ብቅ ብቅ ብለዋል። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በሚመለከት ከነበራት አቋም ፍንክች ሳትል የህዳሴ ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡
ወደፊትም ፍንክች እንደማይል መንግስት የያዘውን ጠንካራ አቋም ደግሞ ደጋግሞ አሳውቋል። በመሆኑም ህብረተሰቡ አሁንም ያለውን ጫና ተረድቶና የመንግስትንም አቋም አውቆ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትብብሩን እና አንድነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት። ስንተባበር አንድ ስንሆን እንደምንሰራ ፤ ጠላትን እንዴት ድል እንደምናደርግ ከአድዋ ተምረናል። የዚህ ትውልድ አድዋ የዚህ ትውልድ ጀግንነት የሚረጋገጠው ደግሞ የህዳሴ ግድቡን ፍጻሜ በማብሰር መሆን አለበት።
ፕሮጀክቱ እስካሁን ከተያዘለት በጀት በእጥፍ ወጪ ሆኖበታል። ሆኖም አሁንም ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ህዝቡ ቦንድ በመግዛት ፣ በጉልበቱ እና በእውቀቱ ባለቤትነቱን ማስመስከር ይጠበቅበታል።
በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ብዙና የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ቢያጋጥሙም መንግስት ግን ለህዝቡ ‹‹እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን›› ሲል የገባውን ቃል በድጋሚ አረጋግጧል። አሁንም የህዳሴ ግድቡን በተያዘለት እቅድ መሰረት ለማጠናቀቅ የተገባው ቃል የማይታጠፍ መሆኑን ‹‹ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት በጣም እየተፈተነችባቸው ያሉ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ ግድቡን ለኢትዮጵያ ህዝብ ቃል በገባነው መሠረት እናሳካዋለን፡፡
ይሄ የሚታጠፍ ሃሳብ አይደለም›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በስድስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ 11ኛ እንደራሴዎች መደበኛ ስብሰባ ላይ አስረግጠው ገልጸዋል።
ይሄ ለህዝቡ የተገባው ቃል ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠናክር፣ ሞራልን ይበልጥ የሚያነሳሳ እና በመንግስት ላይም መተማመንን የሚያሳድር ነው። መንግስት ህዝብን፤ ህዝብም መንግስትን ሲያምንና አንድነት ሲኖር ጠላት ከየትኛውም ጎራ ቢነሳና ቢያብር አፍሮ ይመለስ ይሆናል እንጂ የጀመርነውን የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ከማጠናቀቅ አያግድም።
ኢትዮጵያ አሁንም የትኛውንም የጎረቤት ሀገራት በማይጎዳና ፣ ተጠቃሚነቷንም በማይሸረሽር፣ በፍትሀዊ ተጠቃሚነት መርህ እየሰራች ነው። ይሄንንም አቋሟን የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ጊዜ አረጋግጧል። አሁንም ወደፊትም የተገባው ቃል በተግባር ይገለጣል እንጂ ወደኋላ የሚመለስና የሚታጠፍ አይሆንም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2013