መላኩ ኤሮሴ
የእንሰት ተክል በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በደቡባዊ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚኖሩ የሀዲያ፣ የጉራጌ፣ የስልጤ፣ የከምባታና ጠምባሮ፣ የሲዳማ፣ የወላይታ፣ የአላባ፣የጌዴኦ፣ የዳውሮ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የከፋ፣ የሸኮና የሌሎች ብሔረሰቦች ዘንድ ዋነኛ ምግብ ነው።
በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ብሄር ብሄረሰቦች ምግቦቻቸውን የሚያዘጋጁት ከዚሁ ከእንሰት ነው። እንሰት በነዚህ አካባቢዎች ከምግብነት ባሻገር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው። አንዳንድ የእንሰት ዝርያዎች ለመድሃኒትነት የሚያገለግሉ ሲሆን በተለይም ሰው እና እንስሳት ስብራት በሚያጋጥማቸው ወቅት የእንሰት አይነቶችን በመመገብ ከስብራቱ እንዲጠገኑ ይረዳል። ለቤት መስሪያ በተለይም የቤት ጣሪያ እና ግድግዳ በሚሰራበት ወቅት ከእንሰት የሚገኘውን ገመድ መሰል ማሰሪያ ይጠቀማሉ። ለመቀመጫና ለመተኛነት (ጅባ) ይሰራበታል። ሌላም ሌላም ።
የእንሰት ጠቃሜታ ለሰው ልጅ ብቻ አይደለም፤ ለእንስሳትም ጭምር እንጂ። እንሰት በሁለት መንገድ ለከብቶች በምግብነት ያገለግላል። አንድም እንሰት ተነቅሎ ለእንስሳት በማቅረብ፤ ሁለተኛ እንሰት በሚፋቅበት ወቅት ለቆጮነት የማይሆኑ የእንሰት ክፍሎች ለከብቶች ምግብነት ይውላል።
እንሰት በትንሽ መሬት ላይ ብዙ ምርት ያስገኛል፤ በቀላሉ ይበዛል፣ ይራባል፤ መሬት ከያዘ ከሁለት ዓመት ጀምሮ ቅጠሉ እና ዘንጉ እየተቆረጠ ጥቅም መስጠቱ፣ ቅጠሉ ዳቦ እና ሙልሙል ለመጋገር ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑ በምግብነት በተወሰነ መንገድ ፕሮቲን ካላነሰው በስተቀር በውስጡ ሁሉንም የንጥረ ምግቦችን የያዘ ተክል መሆኑን መረጃዎች ይገልጻሉ ።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮቴክኖሎጂ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አዲሱ ፍቃዱ እንደገለፁት እንሰትን 20 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በመደበኛነት በቀን ሦስት ጊዜ ይመገበዋል። ነገር ግን በግብርናው ዘርፍ የሚሠሩ አካላት ትኩረት ባለመስጠታቸው ከእንሰት የሚገኘውን ጥቅም ማግኘት አልተቻለም። እንሰት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኝ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ዓመት ሙሉ አረንጓዴ ሆኖ የሚዘልቅ ተክል ነው።
በኢትዮጵያ እንሰትን አዘውትሮ የሚመገበው የህዝብ ብዛት እነ ቤልጀም ካላቸው ህዝብ በላይ ነው። ነገር ግን በትክክል ጥቅም ላይ እንዲውል ትኩረት አልተሰጠውም ይላሉ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ እና የባዮ ቴክኖሎጂ መምህር የሆኑት ዶክተር አዲሱ ።
በተለይም ከፍተኛ የመሬት ጥበት በሚስተዋልባቸው በእነዚህ አካባቢዎች ከብቶች ከአካባቢያቸው ርቀው እንዳይሄዱ እንዲሁም ቤት ውስጥ ከማደሪያቸው እንዳይወጡ የሚታሰሩበት ገመድ የሚዘጋጀው እንሰት ተፍቆ በሚገኘው ቃጫ ነው። በአጠቃላይ እንሰት በነዚህ አካባቢዎች ለሚኖሩ ህዝቦች ሁሉ ነገራቸው ነው። ከዚህም ተነስተው ነው አንዳንድ ፀሐፍት አረንጓዴ ወርቅ እስከማለት የደረሱት።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፋብሪካዎች ለሚመረቱ ምርቶችም እንደ ግብዓት እያገለገለ ይገኛል። ዘመናዊ የመድሃኒት ፋብሪካዎች የእንሰት ምርትን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። የእንሰት ንጥረ ነገር የሆነውን ቡዕላ የተሰኘ ምርት ማጣበቂያዎችን ለመስሪያነት እየተገለገሉበት ነው።
እንሰት እድገቱን ለመጨረስ በአማካይ ከአምስት እስከ ስድስት ዓመታት የሚጠይቅ ሲሆን ተክሉ ምንም አይነት ዘመናዊ ማዳበሪያዎችን ሳይፈልግ በተፈጥሯዊ ብስባሾች ብቻ የሚያድግ በመሆኑ አዋጭነቱን የላቀ ያደርገዋል።
ከአካባቢው ህዝቦች ከፍተኛ የሆነ ቁርኝት ያለው ይህ ሰብል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከባድ አደጋ ተጋርጦበታል። በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው የእንሰት አጠውልግ በሽታ በሰብሉ ላይ ከባድ አደጋ እያደረሰ ነው። በዚህም ምክንያት የሰብሉ ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ይገኛል።
በእንሰት ምርትና ምርታማነት ከሚታወቁት ዞኖች አንዱ በሆነው በሀዲያ እንሰት ከምግብነት ባሻገር የአካባቢው ህዝቦች የኑሮ ደረጃ አመላካችም ተደርጎ ይቆጠራል። ብዙ እንሰት ያለው ሰው እንደ ሀብታም ይቆጠራል። ብዙ እንሰት በማልማት የሚታወቅ አባወራ ሲሞት በባህላዊ የለቅሶ ስነ ስርዓት (አረጃ) ላይ ስንኝ ይቋጠርለታል።
የእንሰት አጠውልግ በሽታ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ ይከው ሀዲያ ዞን ነው። በዞኑ በሌሞ ወረዳ ቦቢቾ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሽራሜ ጋዶሬ፤ የሰባት ልጆች እናት ሲሆኑ ባለቤታቸው ስራ ፍለጋ ወደ ደቡብ አፍሪካ ቢሰደድም በደቡብ አፍሪካ እንዳሰበው ሰርቶ ስኬታማ ሊሆን ባለመቻሉ ሰባቱንም ልጆቻቸውን ብቻቸውን ያሳድጋሉ፤ ያስተምራሉ።
ከስምንት ዓመት በፊት ኑሯቸው ሙሉ በሙሉ በግማሽ ሄክታር ላይ ባለሙት እንሰት ላይ የተመሰረተ ነበር። ለምግብነት የሚጠቀሙት እንሰት ነው። በወይዘሮ ሽራሜ ቤት አሰራሩን እና መበያውን እንደ ሁኔታው እና እንደ ጊዜው እየቀያየሩ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት የእንሰት ውጤቶችን መመገብ የተለመደ ነበር።
ለወይዘሮ ሽራሜ እንሰት ምግብ ብቻ አልነበረም። ከብቶቻቸውን የሚያስሩበት ገመድ የሚያዘጋጁበት፤ በቤት የሚተኙበት “ጅባ” የተሰኘ ምንጣፍ የሚሠሩበት፣ ልጆቻቸው እና ከብቶቻቸው ስብራት ሲያጋጥማቸው የሚያክሙበት እንዲሁም የማገዶ እንጨት እጦት በሚያጋጥምበት ወቅት እንደ ማገዶ የሚጠቀሙትም ምርት ነው። የገቢ ምንጫቸውም ነው። ለምግብነት ከመጠቀም ባሻገር ለገበያ በማቅረብ ሌሎች ለቤታቸው አስፈላጊ የሆኑትን መሠረታዊ ፍላጎቶች የሚሸምቱት ቆጮ በመሸጥ በሚያገኙት ገንዘብ ነው።
ከስምንት ዓመታት ወዲህ ግን እንሰት አጠውልግ በሽታ የእንሰት ማሳቸውን በማጥቃቱ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደወደቁ ይናገራሉ። ግማሽ ሄክታር ላይ ያለሙት እንሰት በአጠውልግ በሽታ ስለወደመባቸው የወይዘሮ ሽራሜ ቤተሰብ ከእንሰት ጋር ለዘመናት የነበረው ቁርኝት ተበጥሷል። እንሰትን ለማልማት ይጠቀሙበት የነበረውን መሬትም ሌሎች ሰብሎችን ለማልማት እየተጠቀሙበት ነው።
እንደ ወይዘሮ ሽራሜ ማብራሪያ በእንሰት አጠውልግ በሽታ በወደመው የእንሰት መሬት ላይ ሌሎች ሰብሎችን በተለይም በቆሎ እና ስንዴ እያለሙ ቢሆንም እንደ እንሰት ሊሆንላቸው አልቻለም። ከቀለብ ፍጆታቸው አንፃርም ከእንሰት ጋር ሊወዳደር የሚችል ሊሆንላቸው አልቻለም። አሁን የሚያመርቷቸው ሰብሎች እንደ እንሰት ምርት ብርካቴ እንደሌላቸው ያነሳሉ። በዚህም ምክንያት ኑሯቸው እንደከበዳቸው ጠቅሰዋል።
ሌላኛው የቀበሌው ተወላጅ አርሶ አደር አቶ አለሙ ተስፋዬ እንደሚሉት፤ እንሰትን ማልማት በአካባቢው ከአያቶቻቸው ዘመን ጀምሮ የተለመደ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በእንሰት አጠውልግ ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች እንሰት ከማልማት ይልቅ ሌሎች ሰብሎችን ለማልማት እየተገደዱ ነው።
ሁለት ጥማድ ማሳ ላይ አልምተውት የነበረው የእንሰት ሰብል የዛሬ አምሥት ዓመት አካባቢ በእንሰት አጠውልግ በሽታ እንደወደመባቸው የሚናገሩት አቶ ዓለሙ፤ ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ እንሰት ልማት ቢመለሱም በሽታው ከአፈር ውስጥ ጨርሶ ባለመጥፋቱ የተከሉት የእንሰት ሰብል ዳግም በበሽታው እንደተጠቃባቸው ይናገራሉ።
የእንሰት አጠውልግ በሽታን ለመቆጣጠር የተለያዩ አካላት ወደ አካባቢው በመሄድ ጥናቶችን እና ምርምሮችን ያደረጉ ቢሆንም እስካሁን ድረስ አንዳች መፍትሄ ማግኘት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።
በቅርቡ ክልል አቀፍ የእንሰት አጠውልግ በሽታ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል። በዚህ መድረክ ላይ የእንሰት አጠውልግ በሽታን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል ውይይት ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የተለያዩ አካላትም የተለያዩ የመፍትሄ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አግደው በቀለ የበሽታውን መንስኤዎች እና መፍትሄዎችን አሳይተዋል። እንሰት አጠውልግ በሽታ በባክቴሪያ ምክንያት የሚፈጠር መሆኑን ጠቁመዋል። በሽታው ባክቴሪያ በመሆኑ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አዳጋች እንዳደረገውም ተናግረዋል።
የደቡብ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በሽታውን ለማጥፋት የሚደረጉ ጥረቶች ውጤት እስኪያስገኙ ድረስ ማሳን በማጠር ከሰውና ከእንሰሳት ንክኪ ነፃ ማድረግ እንዲሁም ማሳን ከአረምና በሽታውን ሊሸከሙ ከሚችሉ ተዋህስያን ነፃ ማድረግ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
ኢንስትቲዩቱ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አግደው፤ በሽታውን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን፣ ከእንሰት ጤነኛ ተክልን በመውሰድ በላብራቶሪ የማባዛት እንዲሁም በሽታ አምጪ ተዋህስያንን የመለየት ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግሥት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ስራዎች ክላስተር አስተባባሪና የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንደተናገሩት እንሰት ከምግብነት ባሻገር ከደቡብ ብሄሮች እና ብሄረሰቦች ባህልና ታሪክ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ሰብል ነው።
ሰብሉ የህዝቡ የገቢ ምንጭም መሆኑን ያነሱት አቶ አንተነህ እንሰት አጠውልግ በሽታ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ባለው የእንሰት ሰብል ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ጠቁመው፤ በሽታውን ለመቆጣጠር የተለያየ ጥረቶች እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል። የእንሰት አጠውልግ በሽታን ለመከላከል ሁሉ በተደራጀ ንቅናቄ ሊመራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
እንሰት አጠውልግ በሽታ መከላከል ግብረ ሀይል መቋቋሙን የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልል አቀፍ ደረጃ የእንሰት አጠውልግ በሽታ ግብረ ሃይል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ስራዎች ክላስተር አስተባባሪና የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ሰብሳቢ፣ በዞኖች የየዞኖቹ ዋና አስተዳዳሪዎች እንዲሁም በልዩ ወረዳዎችም የየወረዳዎቹ ዋና አስተዳዳሪ የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢዎች ይሆናሉ።
አንዳንድ የሀገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች በሽታን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን፣ ከእንሰት ጤነኛ ተክልን በመውሰድ በላብራቶሪ የማባዛት እንዲሁም በሽታ አምጪ ተዋህስያንን የመለየት ስራ እየሰሩ እንደሆነ በተደጋጋሚ የገለጹ ቢሆንም ዛሬም ችግሩን ከምንጩ መቅረፍ አልተቻለም። በዚህም ምክንያት የአርሶ አደሮቹ የችግር ዘመን እየተራዘመ ይገኛል።
በተበታተነ መልኩ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አሁንም ችግሩን ሊቀርፍ አይችልም። በመሆኑም በዋናነት የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግሥት ከምርምር ተቋማትና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመሆኑ በሰብሉ ላይ የተጋረጠበትን ችግር ለመቀልበስ በተደራጀ መልኩ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2013