ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
እስኪ ልጠይቃችሁ አገር ማለት ምን ማለት ነው? ህዝብ መንግሥት ምንድነው? ባህል፣ ወግ፣ ስርዐት ይሄስ ከየት መጣ? አገር የቤተሰብ ነጸብራቅ ናት። ቤተሰብ የሀገር መሠረት ነው። ኢትዮጵያን የሰራናት እኔና እናንተ ነን ። አገር የእኔና የእናንተ የአስተሳሰብ ውጤት ናት። የአገርና ህዝብ ጥንካሬ ከቤተሠብ ጥንካሬ የሚመጣ ነው።
ጣታችሁን ወደ ማንም አትቀስሩ አገራችን ልክ አይደለችም ካላችሁ በመጀመሪያ እናንተ ልክ አልነበራችሁም ማለት ነው። ማኅበረሰባችን ልክ አይደለም ካላችሁ ቤተሰቦቻችሁ ሲያሳድጓችሁ ልክ አልነበሩም ማለት ነው።
በሀገራችን ጉዳይ የምንመሰገነውም የምንወቀሰውም እኛ ልጆቿ ነን። የድሮዋ ኢትዮጵያ የድሮ አባቶቻችን አስተሳሰብ ነበረች። የዛሬዋ ደግሞ የእኛ ሆና እየኖረች ነው።
በእኛ አስተሳሰብም ትቀጥላለች። የሁሉም ነገር መሠረት ቤተሰብ ነው..አስተዳደግ። ልጆች የቤተሰቦቻቸው የእጅ ስራ ውጤቶች ናቸው። ወላጆች ልጆቻቸውን እንደፈለጉ አድርገው መስራት ይችላሉ አጣመው፣ አቃንተው የመስራት ስልጣኑ የእነርሱ ማለትም የእናንተ የወላጆች ነው።
በጥሩ ቤተሰብ ያደገ ልጅ ነገ ላይ ለአገር የሚበጅ ጥሩ ዜጋ ይሆናል። በተቃራኒው ኃላፊነት በጎደላቸው ወላጆች እጅ ፍቅር አጥቶ ያደገ ልጅ ነገ ላይ አገር ከሚያፈርሱት ጋር ስለማበሩ ተጠራጣሪ የለም። ወላጆች ለልጆቻቸው አስተማሪዎች ናቸው..ልጆች ከወላጆቻቸው የነገ ህይወታቸውን ብሩህ ሊያደርግ በሚችል መልካም አስተሳሰብ ውስጥ ማደግ አለባቸው።
አስተዳደግ በማናችንም ህይወት ላይ ይሄ ነው የማይባል የበረታ ተጽዕኖ አለው። የሁላችንም ተጽዕኖ ማረፊያ ደግሞ አገርና ህዝብ ነው። ለዚህም ነው አገር የቤተሰብ ውጤት ናት ስል ያወራሁት።
አገራችንን የተሻለች አገር ለማድረግ በመጀመሪያ እኛ የተሻለ አስተሳሰብ የተሻለ ስብዕናን፣ የተሻለ የሥራ ባህልን ማዳበር አለብን። እኛ ሳንስተካከል የሚስተካከል አገርና ህዝብ የለንም።
እኛ ሳንለወጥ የሚለወጥ ምንም ነገር የለም። ሁሉም ነገር በእኔና በእናንተ ለውጥ ውስጥ ያለ ነው። አገራችን አሁን ላይ የተበላሸችው እኛ ስለተበላሸን ነው። እኛ እንዳንበላሽ ደግሞ አሳዳጊዎቻችን ከፍተኛውን ኃላፊነት ይወስዳሉ። ለምንም ነገር መሠረቱ ቤተሰብ ነው። ቤተሰብ ለአገርና ህዝብ የሚጠቅሙ ወጣቶች የሚፈሩበት ተቋም እንደሆነ አስባለሁ።
ሁላችንም አሁን የቆምንበት ቦታ ላይ የተገኘነው በቤተሰቦቻችንና በእኛ በግል እሳቤ ታግዘን ነው። እዚህ ዓለም ላይ በህይወት ለመኖር ከሚደረግ ትግል ቀጥሎ ሁለተኛው ከባድ ነገር ልጅ ማሳደግ ነው እላለሁ። መውለድ ደግሞ በተቃራኒው ቀላል ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የምትሆነን ደግሞ አገራችን ኢትዮጵያ ናት።
ለልጆች የሚሆን ምንም ነገር በሌላት አገር ላይ ነን። መውለድ እንጂ ማሳደግ አንችልበትም። የወለድናቸውን በወጉ አሳድገን ለቁም ነገር ሳናበቃ በልጅ ላይ ልጅ በመጨመር ከአፍሪካ የሚወዳደረን አጥተናል። ማሳደግን ለማያውቅ ማኅበረሰብ መውለድ በህመም ላይ ህመምን ከመጨመር ባለፈ የሚፈይደው አንዳች ነገር አለ ብዬ አላስብም።
መውለድ ትርጉም የሚኖረው፣ ወላጅነት ደስ የሚለው ለወለድናቸው ልጆች ኃላፊነት ሲሰማን ብቻ ነው። በህዝብ ቁጥራችን መቶ ሚሊዮንን አልፈን ከድህነት በቀር ለአገርም ለህዝብም የጠቀምነው ነገር የለም። ዓለም ላይ በትንሽ የህዝብ ቁጥር የዓለምን ኢኮኖሚ በቀዳሚነት የሚመሩ በርካታ ሀገራትን አውቃለው።
ስልጣኔ መውለድ ሳይሆን የወለዱትን ለቁም ነገር ማብቃት ነው። የሰለጠኑት ሀገራት ለልጆች የሚሆን ብዙ ነገር አላቸው። ከእርግዝና ጀምሮ የልጆችን አስተዳደግ ስነልቦና የሚከታተል ስርዓት አላቸው።
የዛሬው የአገራችን ክስረት ከእኩይ አስተዳደግ የመነጨ ስለመሆኑ ጥርጥር የለኝም። ከመውለድ ባለፈ ጥሩ አስተዳደግን ባህል እስካላደረግን ድረስ የነገውም የሀገራችን ክስረት በወለድናቸው ልጆቻችን በኩል እንደሚመጣ ጥርጥር የለኝም።
የወለድናቸው ልጆች አገርና ህዝብ ከመጥቀም ባለፈ ስቃይ እየሆኑብን ባለበት በዚህ ዘመን አብዛኛው የሀበሻ አብራክ ከመውለድ አልነጠፈም። አብዛኞቻችን ለመውለድ የቸኮልን ለማሳደግ ግን የዘገየን ነን። በእውቀት ከመኖር ይልቅ በዘልማድ መኖርን በመረጠ ማኅበረሰብ ውስጥ ነን።
ለመውለድ ያለንን ፍላጎት ያክል ለአስተዳደግ ቢኖረን ዛሬ ላይ በሁሉ ነገሯ የከሰረችን አገር አናይም ነበር። ወላጆች ልጆቻችሁን እንዴት እያሳደጋችኋቸው እንደሆነ ቆም ብላችሁ አስቡ።
ልጆች እንዴት እያደጋችሁ እንደሆነ ለአንድ ጊዜ ራሳችሁን ጠይቁ። ወላጆች ለልጆቻችሁ መሠረት መሆን ካልቻላችሁ በመውለዳችሁ እፈሩ እንጂ እንዳትደሰቱ። ለልጆቻችሁ ጥሩ ቤተሰብ መሆን ካልቻላችሁ በህይወት ውስጥ ለማያባራ መከራና ስቃይ እንደፈጠራችኋቸው ልብ በሉ።
ለልጆቻችሁ መልካም ወላጅ ለመሆን ካልቻላችሁ ስቃይ እየሆናችሁባቸው እንደሆኑ አስቡ። በየቦታው ህጻናት ተጥለው አይተናል። ወልዶ መጣል ብርቃችን አይደለም። ጎዳና የተወለዱ ህጻናት ሞልተውናል። ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ተጥለው ህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ካለቤተሰብ ያደጉ ልጆች ሞልተውናል።
እንዲህ እየወለድን..እንዲህ ተወልደን እያደግን ለአገር ስጋት ከመሆን ሌላ ምን ጥቅም ሊኖረን ይችላል? አገራችንን እኛው ነን ያበላሸናት። በእኛው አስተሳሰብ፣ ወደ ኋላ የቀረችው በእኛው አመለካከት ነው። እኔና እናንተ ለልጆቻችን ጥሩ ወላጆች እስካልሆንን ድረስ የአገራችን ህመም አይሽርም። ልጆቻችሁ እናንተን ናቸው።
አብዛኞቹ ወላጆች ልጆቻቸው ስለሚበሉትና ስለሚጠጡት ስለሚለብሱትም ተራ ነገር የሚጨነቁ ናቸው። አስተሳሰባቸውን ገለው በሰው ፊት ጥሩ ለብሰው እንዲታዩላቸው የሚለፉ ናቸው። አብዛኛው የሀበሻ ወላጅ ልጁ ጥሩ እንዲለብስ እንጂ ጥሩ እንዲያስብ ሲጨነቅ አላየሁም።
ከሰው እንዳያንሱ በሚል አጉል አመለካከት አካላዊ በሆኑ አላቂ ነገሮች ላይ ጊዜና ገንዘባቸውን የሚያፈሱ ናቸው። ልጆች ጥሩ ሆነው እንዲያድጉ የሚያስፈልጋቸው ልብስ ሳይሆን የአዕምሮ ግንባታ ነው።
ከሰው እንዳያንሱ በሚል አመለካከት በሌለን አቅም የማንችለውን ከማድረግ ይልቅ ባላቸው ነገር እንዲኮሩ፣ የሌላውን እያሰቡ የበታችነት እንዳይሰማቸው ታላቅ አስተሳሰብን ልንሞላባቸው ነው የሚገባን።
አዕምሮው ያልተገነባ ልጅ የቻይና እቃ ነው። ወርቅ በሚመስል አርቴፊሻል ነገር ተሽሞንሙኖ ገበያ የሚወጣ። ግን አገልግሎት የሌለው..ግን ቶሎ የሚሰበር፣ ግን ጥቅም የሌለው። አዕምሮው ያልተገነባ ትውልድ የሀገር ስጋት ነው። አሁን ላይ አገር እያፈረሱ ያሉ ጥሩ የለበሱ የእንጀራ ጠርዝ ጣታቸውን የሚቆርጣቸው ባለ ጸዐዳ እጆች ናቸው። ብሩህ ነገ ይኖረን ዘንድ በአዕምሮ መሰራት አለብን።
ልብስ ለአካል ነው የተሰራው፣ ልብስ ከብርድ ነው የሚከላከለው የአዕምሮን ስብራት አይጠግንም። ልብስ የአዕምሮን ጎደሎነት አይሞላም። የአዕምሮ ጎደሎነት የሚሞላው በአስተሳሰብ ነው። የህዝቦች ጥያቄ የሚመለሰው በእውቀት ነው። ዓለም ልታልፍ ጥቂት ጊዜ ብቻ በቀራት ስልጡን ዘመን ላይ ቆመን ወደ ኋላ የምናስበው ለዛም ነው ።
ለዛም ነው አማኝ በሆነች አገር ላይ ተፈጥረን ለፈጣሪ ቦታ አጥተን በነውር የምንኖረው። ለዛም ነው ከሀሳብ የበላይነት ይልቅ በማይጠቅሙን ተራ በሆኑ ነገሮች የምንጋፋው። ለዛም ነው ፖለቲከኛና አክቲቪስት ነን በማለት ሀገር የምንረብሸው። በአዕምሮ መበልጸግ እንዲህ አይደለም።
በአዕምሮ ያደገ፣ በስነልቦና የበለጸገ ማህበረሰብ በልዩነት ውስጥ ተስማምቶ የሚኖር ነው። እነርሱ በሀሳብ የበላይነት የሚያምኑ፣ በውይይትና በመነጋገር የበለጸጉ ናቸው። ስለዚህም ለልጆቻችሁ እውነት በመሆን የወላጅነት ግዴታችሁን እንድትወጡ አደራ እላችኋለው። ልጆቻችሁ እናንተን ናቸው። በመልካቸው ላይ መልካችሁ አለ። በነፍሳቸው ላይም ነፍሳችሁ አጎንቁሏል። በሳቃቸው ላይ ሳቃችሁ ተስሏል።
በሀዘናቸው ላይም ሀዘናችሁ ተቀምጧል። ላትሞቱ በላያቸው ላይ ለሁልጊዜም አላችሁ። ከደም ከአጥንታችሁ ተቀይጠው የስጋችሁን ወዘና ለብሰው እናተን ሆነው ከእናተ ተፈጥረዋል።
ዘለዓለማዊ ሳቃችሁ ከነሱ ውስጥ ይፈልቃል። በልጆቻችሁ ዳግም እየኖራችሁ እንደሆነ አስቡ…እነርሱ አምላክ እናተን በወርቅ ቀለም የጻፈበት ቀለሙ ናቸው። ከዚህ ሁሉ በላይ ህልምና ራዕዮቻችሁ ናቸው..ነጋችሁን በነሱ በኩል ነው የምታዩት።
ልጆቻችሁ በብዙ ነገር ያስፈልጓችኋል። የእውነት ልታሳድጓቸው ይገባል። የእውነት ሰው ልታደርጓቸው ግድ ይላችኋል። የእውነት ወላጅ ልትሆኗቸው ግዴታ አለባችሁ። አብዛኞቻችን ልጆቻችንን እያሳደግን የምንገኘው ከቤተሰብ በወረስነው ዘልማዳዊ መንገድ ነው። ልጅ ማሳደግ ጥበብ ይጠይቃል። እንዳውም ልጅ ወልዶ እንደማሳደግ ጥበብ አለ ብዬ አላስብም።
ዛሬ ላይ ለአገር ሸክም ሆነን የተገኘነው ይሄ እውነት ስላልገባን ነው ። ይሄ እውነት ስላልገባን ነው በተጋባን በማግስቱ ልጆቻችንን በየቆሻሻ ገንዳው የምንጥለው። አብዛኞቹ ልጆች በምክንያት ሳይሆን ስሜት በወለደው መኝታ ወደዚህ ዓለም የመጡ ናቸው። ስንጋባ በምክንያት እንደሆነ ሁሉ ለመውለድም ምክንያት ያስፈልገናል።
ምክንያታችን ግን ዝም ብሎ መሆን የለበትም በእውቀትና በመረጃ ላይ የተገነባ ሳይንሳዊ እንዲሆን ግድ ይላችኋል። እንደዚሁም ደግሞ አብዛኛው ወላጅ ልጁን በሚሄድበት የሚመራ ነው።
ልጆች የራሳቸው መንገድ የራሳቸው እውነት አላቸው። በዛ መንገድ ላይ እንዲሄዱ አግዟቸው እንጂ በራሳችሁ እውነት ላይ እንዲቆሙ አታስገድዷቸው። አንድ ልጅ ተወልዶ ለአቅመ ማሰብ እስኪደርስ ድረስ በአካል፣ በአዕምሮ፣ በስነ ልቦና መገንባት አለበት። ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።
በዚህ ሁኔታ ያደጉ ልጆች እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ የአገር ባለውለታ ናቸው። ወላጅነት ደብተርና እስክሪፕቶ ገዝቶ ትምህርት ቤት መላክ የሚመስለን ብዙዎች ነን።
ወላጅነት የረቀቀ ምስጢር ረቀቀ ተፈጥሯዊ ሀቅ ነው። ወላጅነት ፍጹማዊ ደስታችሁን የምታገኙበት ስፍራችሁ ነው። ጥሩ ወላጅ ስትሆኑ ደግሞ የሚሆነው ደስታው እጥፍ ድርብ ነው። ለልጆቻችሁ ድከሙ። የምትመሰገኑባቸው ልጆች ፍጠሩ። የነገዋ ኢትዮጵያ በልጆቻችሁ አስተሳሰብ ልክ የምትፈጠር ናት።
ልጆቻችሁ ደግሞ በእናንተ እጅ ውስጥ ናቸው። እናተ የእናንተ የአባቶቻችሁ ውጤቶች እንደሆናችሁ ሁሉ ልጆቻችሁም የእናንተ አስተሳሰብ ናቸው። ነገ ላይ መልካምና ለአገር ጠቃሚ ዜጋ አድርጋችሁ የምትፈጥሯቸው እናንተ ናችሁ። ነገ ላይ እንኳንም የነሱ ሆንኩ ብለው በአደባባይ በኩራት የሚናገሩላችሁን ልጆች ወልዳችሁ አሳድጉ።
ደግሜ እላችኋለው ዛሬ ላይ አገራችን የተበላሸችው በወጉ ባላደጉ ልጆች ነው። መሠረቱ የተበላሸ ፍጻሜው አያምርም። ልጆቻችሁ ላይ ትጉ..ከዛም በሁሉ ነገሩ የተስተካከለ አዲስ ትውልድ ታያላችሁ።
ለራሳችሁም ለሌላውም ስትሉ ለልጆቻችሁ ጥሩ ወላጅ ሁኑ። ወላጅ ለመሆን በሚያስችል ቁመና ላይ ብቻ ስትሆኑ ውለዱ። ለመጣል አትውለዱ፣ ስለልብስና ጫማ እንድትጨነቁላቸው አትውለዱ።
ልጆቻችሁ መጠሪያዎቻችሁ ናቸው። መደነቂያ መወቀሻዎቻችሁም ናቸው። መከበሪያ መሸማቀቂያዎቻችሁም ናቸው። ክብርና ውርደታችሁ ናቸው። በሌላችሁበት በልጆቻችሁ ትመዘናላችሁ። ምን አይነት ቤተሰብ ቢያሳድገው (ቢያሳድጋት) ነው እየተባላችሁ በሌላችሁበት ትከበራላችሁ አሊያም ትናቃላችሁ።
በቤተሰብ ውስጥ ያለ ነገር ነው ወደ ውጪ የሚወጣው ቤተሰቦቻችን አጠንክረው ካበጁን ዓለም አያሸንፈንም። ከሁሉም በፊት ወላጆች የጥሩ ስብዕና ባለቤቶች መሆን አለባቸው። ልጆች የቤተሰቦቻቸው ነጸብራቆች ናቸው። የነዚህ ነጸብራቆች ስብስብ አገር ይፈጥራል። አገር ደግሞ የሁላችንም የመጨረሻ እውነት ናት።
በልጆቻችሁ ነፍስ ፤ላይ ሰውነትን ትከሉ። የተማሩ ሳይሆን፣ ዶክተርና ፕሮፌሰር እንዲሆኑ ሳይሆን መልካም ሰው ሆነው እንዲያድጉ ስሯቸው። ታዋቂ ሳይሆን አዋቂ እንዲሆኑ ፍጠሯቸው። ስለገንዘብ ሳይሆን ስለ ሥራ፣ ስለ ጉልበት ሳይሆን ስለትህትና እየነገራችሁ አበልጽጓቸው። ስለ ጥላቻ ሳይሆን ስለ ፍቅር፣ ስለመለያየት ሳይሆን ስለአንድነት አስጠኗቸው። ለሰው ልጅ ሁሉ የሚራሩ፣ ለፈጣሪ የተመቹ አድርጋችሁ አብቅሏቸው እመኑኝ ውሎ ሳያድር ፍሬውን ትበላላችሁ።
አገር እኔና እናንተ ነን። አገር የእኔና የእናንተ ትላንትና ናት። እኔና እናንተ በሆነው በምንሆነው ልክ ትወሰናለች። የእስካሁኑ አበሳዋ በእኔና በእናተ በኩል ያገኘችው ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የእያንዳንዳችን አስተዳደግ፣ የእያንዳንዳችን አስተሳሰብ አገርና ህዝባችን ላይ አሉታዊም አዎንታዊም ተጽዕኖ አለው። ነጋችንን በአዲስ አስተሳሰብ እንጀምር። ከነበርንበት ወጥተን በአዲስነት አዲሷን ኢትዮጵያ በጋራ እንገንባ ስል እያሳሰብኩ ላብቃ። ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2013