አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
‹‹ሰከን ማለት ያስፈልጋል›› የሚለውን ንግግር ከሰማሁበት ሰዓት ጀምሮ ‹ሰከን› በአእምሮዬ ደግሞ ደጋግሞ ተመላለሰ ፤ እውነት እኮ ነው። ምን እየሰራን ነው ብሎ ሰከን ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ማንን በማን ላይ እያነሳሳን ነው? ሀገራችን ወደየት እንድትሄድ? ህዝባችን በምን አይነት ቂም በቀል ላይ እንዲወድቅ እየፈለግን ነው? ብዬ ሳስብ ብዙ ነገሮች ይገርሙኛል።
ጎሳን ጠቅሶ ዋይታ እናትና አባትን አለያይቶ ልጆችን ለጎዳና ፣ ለስደትና ለችግር መዳረግ እንደሆነ የሚጠፋው አለ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም እኛ እኮ ከአንድ ዘር ከአንድ ብሄር ብቻ የተፈጠርን ህዝቦች አይደለንም። አባት ከወዲያ እናት ከወዲህ ሆነን የተጋመድን ነው። ትስስራችን እስከ አያት ቅድመ አያት ሲጎተት ደግሞ ብዙ ነን። የማንለያይ እንዳንፋታ ሆነን የተሳሰርን ገመድ።
እና ይሄን ህዝብ እንዴት እናለያየው ብሎ ነገር አርቆ አለማሰብ ይሆንብኛል። አሁን እኮ አንዳንዶች ጉዳዮቻችን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ብቻ ተብለው የሚታሰቡ ሆነው ይታያሉ ።
እከሌ እከሊት እንዲህ አለች ተቆረቆረች… አይነት ተራ ዝና ለማግኘት ይመስላል። ፖለቲከኞቻችን ስለሚያልቀው ህዝብ አንድም ቀን ጮኸው አያውቁም፤ ከጮሁና ከተናገሩም ስለ መንደራቸው ነው። ተወካዮቻችን ያልናቸውም ይሄንኑ ሲያራምዱ አይተን ታዝበናቸዋል።
እዚህ ላይ ግን መዳፈር አይሁንብኝ እና ተወካዮቻችን የእውቀት ልካቸው የማስተዋል ጥበባቸው እዚህ ደረጃ ላይ ነው እንዴ ብዬ ራሴን ደጋግሜ እንድጠይቅ አድርጎኛል። ቆይታም እኮ ትምህርት ቤት ነው። በቆየን ቁጥር መብሰል የለብንም እንዴ? አሁን ይህን ክፉ ጊዜ አቻችሎ ህዝብን መክሮና አስተምሮ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ በምን እናባብሰው አይነት አስተያየት ሲሰጡ እንደመመልከት ያለ አሳዛኝ ነገር የለም። በስሜት መገንፈል እንደ ቡና ጀበና አካል ማቆሸሽ ነው ትርፉ ፤እናም ሰከን ያለ ያተርፋል ብል ያጠፋሁ አይመስለኝም ።
አንድ ነገር ግን አከብራለሁ። ማንም ሰው የመሰለውን የመናገር መብት አለው ። የመረጠውን ህዝብ ድምጽ መስማትና ማሰማት አለበት። ሲበደል በደሉ ሲጨቆን ሲገፋ ድምጽ መሆን አደባባይ ብቅ ብሎ መፍትሄ ማፈላለግ ይገባል። ይሄ ደንብም ነው። የሞራል ግዴታም ጭምር። ነገር ግን አንድ ደግሞ ትልቅ ጉዳይ መኖሩን መዘንጋት አይገባም። ‹‹ሀገር›› የሚባል ነገር አለ።
በሀገር ውስጥ የቆምንለት የምንለው ህዝብ ጭምር አለ። ይሄን አቻችሎ ሁሉንም ነገር በልኩ ማየት ያስፈልጋል። ሀገር ከሌለ የእኔ ጎሳ የመንደሬ ወሬ ሁሉ አይነሳም። እንኳን ስለመንደር እልል ማለት መኖርም አጠያያቂ ይሆናል። ስለዚህ ከሚሰጡ አስተያየቶች ጀርባ ህዝብና ሀገርን ማሰብ ይቅደም ። ለሁሉም ነገር ሰከን ማለት ያስፈልጋል።
በሀገራችን ‹‹ሰከን ያለ ቡና›› የሚባለው እኮ ዝም ብሎ አይደለም። ቀላልም አይደለም። ምላስ የማይጎረብጥ፣ ጉሮሮ የማይከረክር የጠራ ቡና እንጠጣ፤ ምቾት እየተሰማን የዶሮ አይን የመሰለ ውብ ቡና በአይናችንም በምላሳችንም እያጣጣምን እንጠጣ ማለት ነው። የሰከነ ቡና ሱስን ይገፋል፤ እርካታን ያመጣል። እናም ጉዳዮቻችን አስተያየቶቻችን፣ አመለካከቶቻችን ሁሉ ሌላውንም አሻግሮ የሚያዩ ሰከን ያሉ መሆን አለባቸው። የሰከነ ያሰበውን ውጤት ያያል።
እኛ እኮ ያልተጋባነው፣ ያልተዋለድነውና ያልተዛመድነው ብሄር ብሄረሰብና ሃይማኖት የለም። አንዱ ሲመዘዘ የማይጎዳ የማያለቅስ አይኖርም። ይሄ በዝምድናችን ብቻ ሳይሆን ወገኔ ብለን አብሮ በመኖራችን ጭምር ያገኘው ጸጋችን ነው። የአሁን ሩጫው ይሄንን ጸጋችንን ለመግፈፍ ነው።
ሀገር ለማሳጣት ወገን በወገን ላይ ለማነሳሳትና ለማጫረስ ነው። ይሄ ደግሞ አይጠቅምም። ይሄን ያስተናገዱ የዓለም ሀገራት የገጠማቸውንም ከቅርቡ እስከ ሩቁ አይተናል። ከዚህ መማር ብልህነት ነው።
የእከሌና የእገሌት ብሄር ሃይማኖት ሳይል አብሮ የኖረው፤ ኀዘን ደስታውን አብሮ ያጣጣመ ፣ ችግሩን አብሮ የተቋደሰን ይሄን ህዝብ ዛሬ ሊያለያዩት የወሰኑት ፖለቲከኞቻችን ናቸው።
የቆሰቆሱት እሳት ሲነድ ደግሞ ዳር ሆነው የሚያራግቡት እነሱና ተላላኪዎቻቸው ናቸው። በውጭ ያሉት ተላላኪዎቻችን በሞቀ ቦታ ተቀምጠው በል በለው እያሉ እነሱ በርገር ሲገምጡ እኛን በድንጋይና በጥይት ያጋድላሉ።
የሚለኩሱት እሳት ሲነድ የሚበላው ዳር ሆኖ አዋጊውን አይደለም ፣ እኛኑ ወንድም እህትማማቾችን ነው። እናም አሁንም ደግመን ደጋግመን ለስልጣን ለጥቅም ብለን የምንሰራው ፖለቲካዊ ሴራ ዋጋ እያስከፈለን ነው።
ሁሉንም ነገር በስሜት ሳይሆን በስሌት ፤ በጭፍን ሳይሆን በእውቀት አውጥቶና አውርዶ ሰከን ብሎ በማሰብ ይሁን። ሰከን ትርጉሙ ብዙ ነው፤ አሁንም እንላለን፤ ወንድምን ከወንድሙ አታጫርሱ! ሀገር አታፍርሱ! ህዝብን አታምሱ! አታሰቃዩ! ሰከን ብላችሁ አስቡ።
ሌላው እዚህ ማዶ ያኛው እዛ ማዶ ሆኖ መወራወሩ አሁንም አይጠቅምም። ወደፊትም ሊጠቅመን አይችልም። እኛን የሚያዋጣን አንድነታችን ብቻ ነው። በአብሮነታችን ተፈላልገን ማንም ጣልቃ ሳይገባብን፤ ማንም አውቅልሀለሁ ብሎ ሳያባላን በራሳችን የምንኖረው አብሮነት ነው የሚጠቅመን ፤እሱን እንቀጥል፤ ተውን ተውን ከራሳችን ላይ ውረዱ በሰው ህይወት አትቀልዱ ልንላቸው ይገባል።
ዛሬ ሀገራችን ከውጭም ከውስጥም ያንዣበበባት አደጋ አስፈሪ ነው። የእኛን መከፋፈል የእኛን ልዩነት የሚፈልጉ ብዙ ናቸው። ይሄ ለማንም ግልጽ ነው። አንዳንድ ፖለቲከኞቻችንም ይሄንን ፍላጎት ለማስፈጸም እየዳከሩ ሊሆን እንደሚችል መገመት ክፉ አይደለም።
አንዳንድ ነገሮች ይሄንን የሚያሳዩ ናቸው። እናም አሁንም ሆነ ወደፊት ስለኢትዮጵያ ሀገራችን ስለመላው ህዝባችን እያሰብን ከመንደርተኝነት እንውጣ። ከስሜት ርቀን በሰከነ አእም ሮ እንመራ፣ እንምራ !።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2013