በግለሰብ ፣ በማህበረሰብም ሆነ በሀገር ደረጃ የሚፈጠሩ ችግሮቹ በቂ ምክንያት አላቸው። ምክንያቶቻቸው የችግሮቹን ግዝፈት የሚወስኑ ሲሆን፤ መፍትሔዎቻቸውም ችግሮቹን በማወቅ ልክ የሚወሰኑ እንደሆኑ ይታመናል።
ከችግሮች በዘላቂነት ወጥቶ የተሻለ ሕይወት ለመምራት ከያንዳንዱ ችግር በስተጀርባ ያለውን መሰረታዊ ምክንያት በአግባቡና በተረጋጋ አዕምሮና መንፈስ መመርመር ያስፈልጋል። በዚህ መልኩ ያልተገኘ መፍትሐ ውሎ ይደር እንጂ ለተጨማሪ ችግር ምንጭ ከመሆን ያለፈ አይሆንም። ችግሩን ማወቅ የመፍትሔው ግማሽ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው።
ሀገራችን እንደ ሀገር የረጅም ዘመናት ታሪክ ፣ እንደ ሀገርም ከብዙዎች የቀደመ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ያላት ቢሆንም ታሪኮቿ የስኬት ብቻ ሳይሆኑ የግጭቶችም እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
ቀደም ሲል ከነበርንበት የስልጣኔ ማማ ወርደን አሁን ላይ ከዓለም በድህነታቸው ከሚጠቀሱ ሀገራት ተርታ ተመድበን የመጠቀሳችን እውነታም የግጭት ታሪኮቻችን ድምር ውጤት እንደሆነም ለመናገር አይከብድም።
ከዚህ በላይ ደግሞ በአንድ ወቅት ደርሰንበት የነበረው የስልጣኔ ማማ ላይ ተመልሰን ለመውጣት አለመቻላችን፣ ለዚህ የሚሆን መነሳሳትና መነቃቃት ማጣታችን ከላይ ያሳነውን እውነታ የበለጠ ተጨባጭ ያደርገዋል።
የውድቀታችንን ምክንያት አለማወቃችን ፣የችግሮቻችንን ምክንያቶች በአግባቡ ሳናውቅ በየዘመኑ መፍትሔ አድርገን የሄድንባቸው መንገዶችም ሆኑ ፣መንገዶች ያስከፈሉንን ከፍ ያለ ዋጋ በአግባቡ መመርመር አለመቻላችን በእንቅርት ላይ ጆር ደግፍ ሆነውብን ቆይተዋል።
ከቅርቡ ዘመን ብንነሳ እንኳን በ1950ዎቹ መጨረሻ ላይ ተነስቶ የነበረው ተራማጅ ትውልድ ከፍ ያሉ ሀገር አሻጋሪ ሃሳቦችን አንስቶ በታላቅ ቁርጠኝነት ሕይወቱን እስከ መስጠት ቢደርስም በመጨረሻ የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነው።
ያ ትውልድ የቱንም ያህል ተራማጅ አስተሳሰብ ቢይዝ፣ የቱንም ያህል ለመስዋዕትነት የተዘጋጀ ማንነት የነበረው ቢሆንም ሀገራዊ ችግሩን በሰከነ አዕምሮና መንፈስ በአግባቡ ለመረዳት ከመሞከር ይልቅ የኔ ሃሳብና የችግር ትንተና አልፋና ኦሜጋ ነው በሚል በብዙ የስሜት ሞቅታዎች ታጅቦ ያሰበውንና የተመኘውን ማድረግ አቅቶት አልፏል።
ከዚያ ወዲያ ያለው ሀገራዊ እውነታም ቢሆን ሀገርን እንደ ሀገር ከማሻገር ይልቅ የአሸናፊነት መንፈስ በፈጠረው ሞቅታ ላይ የተመሰረተ ስለነበር ፣ የሚጨበጥ ፍሬ ማፍራት እቅቶት ሀገርን ወደከፋ ችግር እንዳስገባትና ችግሩም ዛሬም ድረስ ሀገርና ህዝብን ዋጋ እያስከፈለ እንደሚገኝ ግልጽ ነው።
ለውጡ ሀገራዊ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ሀገራዊ ችግሮቻችንን በተሻለና መንገድ በሰከነ መልኩ ቁጭብለን እንድንመለከት ዕድል የሰጠ ቢሆንም አሁንም ችግሮቻችን በአግባቡ ለማወቅ ከመጣር ይልቅ የችግሮቹ ጥላ ላይ ቆመን ከፍ ባለ ስሜት እየተነዳን እንገኛለን።
በአንድ በኩል ስለ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሲያዜም የነበረውን የቀደመውን ትውልድ የመከነ ዜማ እያዜምን ፣ በሌላ በኩል ያ ትውልድ ተስፋውና ርእዩ የመከነበትን ምክንያት ለመስማት ፈቃደኝነት እያጣን ለራሳችን እየጮህን የዛሬ ተስፋችን ላይ ግርዶሽ እያበጀን እንገኛለን።
ለባልና ሚስት ጉዳይ እንኳን ትልቅ ስፍራ በሚሰጠው ማህበረሰብ ውስጥ ተወልደን አድገን ከፍ ላለው ሀገራዊ ጉዳይ ለባልና ሚስት የምንሰጠውን ያህል ትኩረት እያጣን መጥተናል። ቤተሰብን ከመፍረስ ለመታደግ የሰጠነውን ያህል ትኩረት ለሀገር መፍረስ መስጠት እየተሳነን መጥቷል።
የዚህ ዓይነት ለባህላችንና ከዚሁ ከሚመነጨው ማንነታችን ጋር በተቃርኖ በሚቆም የአስተሳሰብ መሰረት ላይ ቆመን እንደሀገርም ሆነ እንደ ህዝብ መድረስ የምንፈልግበት ቦታ መድረስ እንችላለን ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ከዚያም በላይ በተሰጡን የተስፋ ቀኖቻችን ላይ የማፌዝ ያህል ይቆጠራል።
ከሁሉም በላይ በተለይ አሁን በብዙ ተግዳሮቶች ተከበን ባለበት ወቅት ችግሮቻችንና ችግሮቻችን በተስፋ ቀኖቻችን ላይ የፈጠሩትን ጥላ አምነን ከፍ ባለ ስሜት ከመነዳት ራሳችንን መጠበቅና ሰከን ማለት ይኖርብናል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሰሞኑ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ሰከን እንበል ሲሉ ያስተላለፉት መልዕክትም በዚህ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ትልቅ መልዕክት ነው። ችግሮቻችን ከኛ በላይ የሆኑት ባለመስከናችን እንጂ ከኛ በላይ ስለሆኑ አይደለምና ከችግሮቻችን በላይ መስከን ይጠበቅብናል።
በሰከነ ስሜትና መንፈስ ትናንቶቻችንን መርምረን ዛሬዎቻችንን ከሚገድሉ የትናንት ችግሮቻችን መውጣት ይኖርብናል። ወደ ብልጽግና የጀመርነው መንገድ ፍጻሜው የሚያምረውና ለትውልዶች ተስፋ የሚሆነውም ቀድመን በመስከን፣ በሰከነ መንፈስ ማሰብ እና ማድረግ ስንችል ብቻ ነው!
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2013