ራስወርቅ ሙሉጌታ
ትዳር በምድር ላይ የተመሰረተው የመጀመሪያው ህብረትና ተቋም ነው። የቤተሰብ፣ የህዝብ፣ የማህበረሰብ፣ የአገርና የዓለም ሁሉ መነሻ መሰረትም ነው። ተፈጥሮም ሆነ ሰውን የፈጠረ አምላክ ሰው ብቻውን መኖርና መሆን እንደማይችል እውቅና በመስጠት ውስጥ አጋር ወይም ረዳት ያዘጋጀበት መንገድ ትዳር ይባላል።
ትዳር የሰው ሙሉ መሆን ማመሳከሪያ ጭምር ሲሆን ብቻ መሆን ጎደሎ እንደሆነም ያሳያል። ትዳር ሰው ከራሱ አልፎ ለሌሎች ማሰብ እችላለሁ በሚልበት የአስተሳሰብ ብስለት ላይ ሲደርስ የሚመሰርተው ህብረት ነው።
ይህም ማለት “እኔ… እኔ” ከሚል ግለኝነት በመውጣት “እኛ” ወደ ሚል ማንነታዊ ልዕልና ሲያድግ “ለእሱ ወይንም ለእሷ ይቀመጥ” ወደ ማለት ሲመጣ የሚመሰረት ጥምርታ ነው። ይህም ሆኖ ትዳር የመሰረቱ ሁሉ የትዳርን አላማ ያሟላሉ ጥንዶቹ በሰላምም እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ይዘልቃሉ ማለት አይደለም። ይልቁንም አንዳንዶች ትዳር የመሰረቱበትን አንደኛ ዓመት የልደት በአል ሳያከብሩ የሚለያዩም እንዳሉ ይታወቃል።
ለመሆኑ ውጤታማ ትዳር ለመመስረትና የተመሰረተውንም ዘላቂ ለማድረግ ጥንዶች ምን ሊያደርጉ ይገባል ምንስ ይጠበቅባቸዋል ስንል የማህበራዊ ልማትና አመራር ባለሙያ ከሆኑትና በቲቪ ዘጠኝ የክሊፍ ሞቲቬሽን ወይም አፋፍ ለመድረስ ዝግጅት አዘጋጅና አቅራቢ አቶ ዘላለም ይትባረክን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ሃይማኖት ምን ይላል?
የሃይማኖት መጽሐፍት ትዳር ኪዳን እንደሆነ የሚያስተምሩ ሲሆን የሚጸናውም በሴት ልጅ ድንግልና አማካኝነት በሚጋቡበት ቀን በሚያደርጉት ወሲባዊ ግንኙነት በሚፈሰው ደም ነው። የድንግልና ጥቅምም ኪዳንን ማጽኛ ምስክር መሆኑ ነው። የአምላክም ሆነ የሰይጣን ትልቁ ፈሰስ ትዳር የሆነበት ምክንያት ትዳር የአገር እድገት መሰረት በመሆኑ ነው።
ጋብቻ በኢስላም እይታ የነፍስ ማረፊያ፣ የቀልብ መርጊያና መርኪያ፣ የህሊና መረጋጊያ ነው። ሁለት ጾታዎች በፍቅር፣ በመተዛዘንና በመተባበር፣ በመቻቻልና በመመካከር የሚኖሩበት ተቋም ነው። እንዲያውም ጋብቻ የነብያቶችና የመልዕክተኞች ሱና ወይም ፈለግ ነው። የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል “እናንተ ወጣቶች ሆይ ከእናንተ ውስጥ የትዳርን ጣጣ የቻለ ሰው ያግባ። ትዳር የአይን መስበሪያ፣ የብልት መጠበቂያ ነው። የትዳርን ጣጣ ያልቻለ ሰው ጾም ይጹም፣ ጾም ጋሻ ነው።”
ጋብቻ በክርስትና “ሰው አባትና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ስጋ ይሆናሉ።” ይላል። አክሎም ሐዋርያ ጳውሎስ “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፤ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን” በማለት አስተምሯል። እዚህ ላይ ትዳር በስሜት መር ወይም በእውቀት መር በሚባሉ ሁለት የተለያዩ መንገዶች እንደሚመሰረት ልብ ልንል ይገባል።
ስሜት-መር ስንል በማየት በመስማት በመውደድ የሚመሰረት ጋብቻ ሲሆን፣ እንደ መስፈርትም ቁመት፣ ውበት ወይንም ያለውን ያላትን ሃብትና ንብረትን ቆጠራ በማድረግ እንዲሁም የቤተሰብ የኑሮ ደረጃና ሃብት ጥናትን መሰረት ሲያደርግ ወይም በስማ በለው ተሰማኝና በደሳለኝ የሚመሰረት የትዳር አይነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እውቀት-መር የሚባለው ጥቂት አካላዊነት ድርሻ ቢኖረውም በዋነኝነት ሃሳብን፣ ፍላጎትን፣ ባህሪን በጠቅላላው አስተሳሰብንና ማንነትን ጥናት መሰረት ያደረገና ከመጋባት በፊት በጋራ ግብና ዓላማ መግባባትን መሰረት ያደረገ የትዳር አመሰራረት መንገድ ነው። ይህም ሆኖ ሁለቱም የትዳር አይነቶች ላይ ግጭት ሲከሰት በስሜት-መር የተመሰረተው በአሸዋ ላይ እንደሰራ ቤት ሰሪ፣ ግጭት እንደጎርፍ ሲመጣበት ብትንትኑ ሲወጣ፤ በእውቀት-መር የተመሰረተው በዓለት ላይ እንደሰራ ቤት ሰሪ፣ ግጭት እንደንፋስ ቢመጣበትም ተቋቁሞ የማለፍ ድሉ የሰፋ ነው።
በአብዛኛው እንደ ሀገር የሚከሰቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ኪሳራዎቻችን ሁሉ የሚመዘዙት ከቤተሰብ የትዳር መፍረስ ወይም መበተን ሲሆን ጠንካራ ቤተሰብ ደግሞ የአገር መሰረትን ጠንካራ ያደርጋል። ማለትም ዘርፈ ብዙ አገራዊ ችግሮቻችን በሙሉ መነሻቸው የትዳር ውስጥ ችግር ነው።
ለምሳሌ Journal of Biosocial Science የሚባል ጽሁፍ እንደሚነግረን ከሆነ በኢትዮጵያ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የፍች ቁጥር የጨመረ ሲሆን አብዛኞቹ የመጀመሪያ ጋብቻ 45% በፍች መጠናቀቃቸውን ይገልፃሉ። እንዲሁም ሁለት ሶስተኛው ትዳር በተጋቡ በአምስት ዓመታት ውስጥ ለፍች ይዳረጋል ይላል።
በተጨማሪም በፌደራል ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ (መጋቢት አምስት ቀን 2019) በአዲስ አበባ በተሰራ ጥናት በ10 ወራት ውስጥ ከ13 ሺ 419 ትዳር ውስጥ 1020 አካባቢ ወይም ከመቶ ሀምሳ ፐርሰንት 96 ነጥብ 6 ፐርሰንት የሚሆኑት ትዳሮች እንደፈረሱ ነው የሚናገሩት። ስለዚህ ትዳር ለመመስረት የሚያስብ እነዚሀን ነገሮች ከግምት በማስገባት ለመጀመር መዘጋጀት የሚኖርበት ሲሆን በትዳር ዓለም ውስጥ ያሉት ደግሞ የሚከተሉትን መንገዶች ቢጠቀሙ በትዳራቸው ደስተኛ ሆነው የመቆየት እድላቸው የሰፋ ይሆናል።
ትዳር በተፈጥሯዊ ልዩነት መካከል ባሉ ሰዎች መቃረንና መሳሳብ የተሰራ እንደመሆኑ ግጭት ዋነኛ መገለጫው ነው። ማለትም ሁለቱ ሰዎች የተለያየ ተፈጥሯዊ አስተሳሰብና ማንነትን የተላበሱ በመሆናቸው የሚቃረኑ ቢሆንም ስለሚሳሳቡ ትዳርን መመስረት ይችላሉ።
እዚህ ላይ በወንድና በሴት መካከል ያለው ፍጥረታዊ ልዩነት እንደምክንያት የሚፈላለጉና የሚሳሳቡ ሲያደርጋቸው፤ በጾታ መመሳሰል መካከል ግን ተመሳሳይ ነገሮች ይገፋፋሉ በሚለው የተፈጥሮ ስርዓት ህግ መሰረት የሚቃረኑና የሚገፋፉ ናቸው። ይህም ዋነኛ ምክንያት ወንድ ለወንድ ወይም ሴት ለሴት የሚደረግ የትዳር መጣመር ፀረ-ተፈጥሮ ለመሆኑ ማስረጃ ነው። የተለያየ ጾታ ያላቸው ጥንዶች ወደ አንድነት ለመምጣት ለመዋሃድ ደግሞ በጊዜ ውስጥ እለት እለት ይጋጫሉ።
ዋናው ነጥብ ግጭታቸውን መፍታት ከቻሉ ትዳራቸው ጸንቶ አብረው የሚቀጥሉ ሲሆን መፍታት የማይችሉ ከሆነ ደግሞ ምንአልባት አሁን እንደምንሰማው በተጋቡ በደቂቃዎች ውስጥ ወይም ሰነባብተውም ብዙ ልጅና ሃብት በትነው ለመፋታት ይዳረጋሉ። በመሆኑም ዋናው ጉዳይ አለመጋጨት ወይም ግጭትን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን ግጭትን መፍታት መቻል ነው። በመሆኑም በትዳር መካከል ግጭቶች እንዳይከሰቱ ለማድረግና የተፈጠሩ ግጭቶችን እንዴት መፍታት አንደምንችል እንደሚከተለው እንመለከታለን።
ትዳርን ለማጽናት የሚረዱ ብልሃቶች
- የአጋርን ክፍተት ማወቅ፡- በትዳር የህይወት ተጓዳኛችን ያለበት ክፍተት ምንድን ነው፣ የማይችለው፣ የጎደለበት ወይም ስስ ጎኑ የሚለውን መለየት በጣም ጠቃሚ ነው። ይህም ማለት አንደኛው ለሌላው/ለሌላዋ የማትችለውን/ የማይችለውን የከበዳትን/ የከበደውን ወይም የጎደላትን/ የጎደለውን ሲሞላ ከሌላውም ይህው ሲመለስ ማለት ነው። ስለዚህ ትዳር የሚመሰረተው ለመረዳዳት፣ ለመደጋገፍ፣ በክፍተት ለመቋቋም ወዘተ በመሆኑ (ወሲብ፣ ልጅ መውለድ ወዘተ ሁሉ እሷም ብቻዋን እሱም ብቻውን ሊከውኑት ስለማይችሉ የግድ ክፍተትን መተዋወቅ ይጠበቃል። ይህንን ለማድረግ በብዙ ባለትዳሮች በኩል ያለው ችግር ደግሞ ድብቅነት፣ እፍረት፣ ጉረኝነት ወይም የክብር ጉዳይ ክፍተታቸውን እንዲሸሽጉ ስለሚያደርጋቸው እንኳን ሊደጋገፉ ቀርቶ በየቅጽበቱ የሚያነታርካቸውን ችግር ማወቅም ሆነ መፍታት እንዳይችሉ ሲያደርጋቸው ይስተዋላል።
ሁለተኛ ክፍተትን መተዋወቅ ግጭት በተደጋጋሚ የሚያስነሳውን መንስኤ ለማወቅም የሚጠቅም ስለሚሆን የግጭት ድግግሞሹን ከመቀነስ ባለፈ “…የእኔ ነው ጥፋቱ እያወኩ…” በሚል ሃላፊነትን በመውሰድ ግጭቱን በፍጥነት ለማርገብም ሆነ ለመፍታት እድል ይፈጥራል።
- ሃላፊነትን መወጣት፡- በትዳር ዓለም ወንድም ሆነ ሴት ሁለቱም የግልና የጋራ ሃላፊነት ያለባቸው ሲሆን የግጭት ደግሞ መነሻውም ሆነ መፍትሔው ሃላፊነትን በአግባቡ መወጣት መቻል አለመቻል ነው። ሃላፊነትን መወጣት አለመቻል በውስጡ ጣት መቀሰር፣ ማሳበብ፣ ማላከክ ወይም ማመካኝት (የእሱ፤ የእሷ ችግር ነው!) ስላለበት ድርሻን በመውሰድ የበኩልን ከመወጣት ይልቅ መሸሽን ያበዛል። ይህ ደግሞ ግጭቱን ከመፍታት ይልቅ እንዲውል እንዲያድር በማድረግ ለበለጠ ልዩነት መፈጠር ምክንያት ይሆናል። እዚህ ላይ ዋናው ጉዳይ «ተጋጩ» ሲባል የሁለቱም አካሎች ድርሻ እንዳለ የሚያመላክት በመሆኑ ታረቁ ወይም ግጭታቸውን ፈቱ ሲባልም እንዲሁ የየድርሻቸውን ተወጡ እንደማለት ነው። ሃላፊነትን ስንወጣ መነጋገር፣ ይቅርታ መጠያየቅና መተላለፍ የምንችልበትን ጉል በት ስለምናገኝ ግጭቱን ለማቅለል ይረዳናል።
በተጨማሪ ሃላፊነት ሲሰማን ከራሳችን አልፈን ስለየትዳር አጋራችን ወይም ልጆቻችን እጣ ፈንታ እንጨ ነቃለን። በርግጥም የአደገኛ እጽ ሱሰኝነት መስፋፋት፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች መበራ ከት ወይም የሴተኛ አዳሪ መብዛት ሁሉ ዋነኛው ምክ ንያት ይሄው የቤተሰብ ሃላፊነትን የመውሰድ አቅም ደካማ መሆን ነው። ስለዚህ ችግሩን ስለፈጠረው መንስኤ እያሰቡ ከመናደድ ይልቅ መፍትሔው ላይ ትኩረት እንድናደርግ ይረዳናል ወይም ከችግሩ ይልቅ መፍትሔውን ማስበለጥ እንደማለት ነው።
- የቤተሰብን ገደብ አልባ ጣልቃ ገብነት ማስወገድ፡- ከእናትና አባት ይለያሉ የራሳቸውን ቤተሰብንም ይመሰርታሉ የሚለውን የትዳር መመስረቻ መርህ በተጣረሰ መልኩ በትንሹም በትልቁም ቤተሰብ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ለግጭት መንስኤ መሆን ብቻ ሳይሆን ችግሮችም እንዳይፈቱ እንቅፋት ወደ መሆን ይሸጋገራል። በዚህ ረገድ በአብዛኛው እንደሚስተዋለው በወንዱ በኩል በዋነኝነት የእናቶች ጣልቃ ገብነት ልክ እትብቱን የሚመስል ያልተለያየና በራሱ ያልቆረጠ ሲያደርገው በሴቷ በኩል ደግሞ የትዳር አጋሯ ያደረገውን ሁሉ ለወላጅ ቤተሰቦቿ አሳልፎ በመናገር በተለይ ግጭት ሲፈጠር በሁሉም ረገድ ተበደልኩ በሚል መንፈስ ማውራት ነው። በውጤትም እሱ ልፍስፍስ በራሱ ያልቆመ ከሚስቱ እናቱ የምትበልጥበት ጥገኛ ሲሆን እሷ ደግሞ ተበደልኩ… ተበደልኩ በሚል እሳቤ ለቤተሰብ የተናገረችው ስምምነት እንኳን ቢፈጠር አስቀርቶት የሚያልፈው የራሱ የሆነ ቁርሾ እንዲኖረው ያደርጋል። ስለዚህ ቤተሰብ ትዳር ያደረጉ ልጆች ህይወት ውስጥ ጣልቃ ባለመግባትና ባለትዳሮች ደግሞ ቤተሰብን ጣልቃ ባለማስገባት ግጭትን በራሳችው የመፍታትን ክህሎት ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል። ይልቁንም በግልባጩ ቤተሰብን ለሁለታቸውም ገለልተኛ መካሪና ሃሳብ ሰጭ እንዲሆን ማድረግ የሚጠበቅ ይሆናል።
- ትኩረት ወይም ጊዜ ለትዳር መስጠት፡-
ጊዜ ለትዳር መስጠት የትዳር አጋሮቻችን አብረናቸው እንደሆንን እንዲሰማቸው ከማድረግ ባለፈ ከእነሱ የሚበልጥብን ምንም ነገር እንደሌለ አመሳካሪም ነው። እናም ከስራችን፣ ከጓደኞቻችን፣ ከውጭ ካለው ጫናና ውጥረት ወዘተ ሁሉ ራስን ነፃ በማድረግ ማለትም ውጭ የለበስነውን ኮት አውልቀን በማንጠልጠል የቤት ወይም የትዳር ኮታችንን ቤት ውስጥ መልበስ ግጭትን ከመፍታት ባለፈ የግጭት መከሰትንና ድግግሞሽን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው። ነገር ግን ትኩረታችን በውሎ ቦታችን ከሆነ የቤታችንን ችግር በሃላፊነት እንኳን ልንፈታ ይቅርና የችግር ቋት መሆናችን አይቀርም። በመሰረቱ አንድ ሰው ያለትኩረት እንኳን የቤተሰቡን ችግር ሊፈታ ይቅርና የግል ችግሩንም ማስወገድ አይችልም። ስለዚህ ከስራችን፣ ከገንዘባችን፣ ከአካባቢያችን ወዘተ ሁሉ በላይ ለትዳራችንና ለትዳር ፍሬዎቻችን ጊዜን በመስጠት፣ ሃሳባቸውን እያዳመጡ ወይም አብሮ በመሆን ትኩረት እየሰጡ መንከባከብ ከጥንዶች የሚጠበቅ ይሆናል።
- መቻቻል፡- መቻቻል ለትዳር አለመናጋት ለቤተሰብ አለመበተን ዋናው ቁልፍ ነው። በትዳር ውስጥ አንዱ ሲግል አንዱ ቀዝቀዝ በማለት መተላለፍ የሚጠበቅ ሲሆን እልክ፣ ድርቅናና ግትርነት ትዳር የሚበታትኑ ግጭትን የሚያባብሱ መሆናቸውን ሁሌም በአእምሮ ማስቀመጥ ይጠበቃል። ስለዚህ አንዳንድ የሀሳብ አለመስማማቶች ሲፈጠሩ ለዘብ በማለት ጊዜ እየሰጡ ጊዜን በመጠበቅ የሚደረግ የመግባቢያ ብልሃት፣ መንገድ ነው። ይህንንም ለማድረግ ስሜትን ተረጋግቶ መግለጽ፣ ሃሳብን ማስረዳትና የሌላውንም ወገን መረዳት መቻል፣ አክብሮታዊና ትህትናዊ የንግግር ዘይቤን መከተል ትዳርን የሰላምና ዘለቄታዊ ለማድረግ የሚመከሩ የግብብነት መንገዶች ናቸው።
- ትእግስት፡- ለትእግስት የመጀመሪያው ነገር ጥንዶች የገጠማቸውን ማንኛውም ሳንካና ችግር ጊዜ ቢወስድም ሊፈታ እንደሚችል የማመን ብቃት ነው። በርግጥም ለታገሰ ሁሉም ያልፋል እንደሚባለው ትዕግስት በተፈጥሮው ያልበሰለውን የማብሰል፣ ያስቸገረውን የመፍታት፣ የከበደውን ቀለል የማድረግ ልዩ ተፈጥሯዊ አቅም አለው። ብዙ ግዜ እንደሚታየውም፤ ትእግስት የሚያደርግ ትዳሩን ያድናል። ትዕግስት ለማድረግ ደግሞ ያልተሄደበትን የመፍትሔ ማግኛ መንገድ በሙሉ በተረጋጋ መንፈስ መሞከር ይጠበቃል። ከብዙ ሰዎች የትዳር ተሞክሮ እንደሚታየው ሊፈርስ ጥቂት የቀረው ትዳር እንኳ አገግሞ መጽናት የሚችለው ትግስት ማድረግን እንደብልሃት ተግባራዊ ባደረጉ ጥንዶች መካከል ነው።
- የጋራ ግብ፣ ወይንም ዓላማ መኖር፡- ጥንዶች ድህነትን፣ ልጆች ማሳደግን፣ የቤተሰብን ፍላጎት ማሟላትን፣ ወዘተ የጋራ ግብ ወይም ዓላማ በማድረግ እስኪሳካ ወይም እውን እስኪሆን ድረስ በመካከላቸው የሚከሰተውን ግጭት መፍታት ወይም በትዕግስት መቋቋም እንዲችሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። በተጨማሪ በተናጥል በግል ያላቸውን ተሰጥኦና ዝንባሌ ለማሳካት የሚደግፋቸውን ማንኛውንም የጋራ ቅድመ-ሁኔታ በማሟላት እርስ በእርስ መረዳዳትና መደጋገፍ አለባቸው። ለምሳሌ እሱ በግል ሊሆነው የሚፈልገውን እሷም በግል ልትሆነው የምትፈልገውን ለማሳካት የሁለቱም ጉዳይ በማድረግ በጋራ ለጋራ ዓላማ መቆም እንደማለት ነው።
ባጠቃላይም የማህበረሰብም ሆነ የሀገር ችግር ሊፈታ የሚችለው ከቤተሰብ ጀምሮ በሚሰሩ የረጅም ግዜ ስራዎች ይሆናል። በመሆኑም ቤቱን መምራት ወይም የጓዳውን ችግር መፍታት የማይችል የሌሎችን ወይም የአገርን ችግር መፍታትም ሆነ መምራት ስለማይችል ቅድሚያ ለቤተሰብ ችግር ትኩረት በመስጠት ደስተኛና ተስፋ የሰነቀ ቤተሰብ መመስረት ይገባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2013